13ኛው የአዲስ አበባ ከተማ አቀፍ የአካል ጉዳተኞችና መስማት የተሳናቸው ስፖርታዊ ውድድርና ፌስቲቫል ከህዳር 24 ጀምሮ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚና በአራት ኪ.ሎ ወወክማ እየተካሄደ ነው፡፡ በውድድሩ ከ11ዱም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ መስማት የተሳናቸውና አካል ጉዳተኞች በተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
ውድድሩ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ሕጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ትብብር እንደተዘጋጀ ታውቋል፡፡ የውድድሩ አስተናጋጅ የካ ክፍለ ከተማ ሲሆን ውድድሩ ‹‹መስማት የተሳናቸውና የአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለዘላቂ ልማት ግቦች ስኬት ትርጉም ያለው ትሰስር›› በሚል መሪ ሃሳብ ነው እየተካሄደ የሚገኘው፡፡
ውድድሩ በየዓመቱ የሚካሄድ እና ሁሉም አካል ጉዳተኛና መስማት የተሳናቸው ስፖርተኞች የሚሳተፉበት ትልቅ መድረክ መሆኑም የአዲስ አበባ መስማት የተሳናቸው ስፖርቶች ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡ በዚህም አካል ጉዳተኞች በውድድሩ በመሳተፍ በውጤትና በተለያዩ ሽልማቶች የሚነቃቁበት መሆኑን ተጠቅሷል፡፡ በተጨማሪም ለኢትዮጵያ ቻምፒዮና እና ለሌሎች ሀገር አቀፍ ውድድሮች ከተማውን በመወከል የሚሳተፉ ስፖርተኞች የሚመረጡበ ነው፡፡
በውድድሩ ከ11ዱም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ከ200 በላይ አካል ጉዳተኞችና ከ200 በላይ መስማት የተሳናቸውና ሌሎችም ስፖርተኞች እየተሳተፉ ሲሆን ታህሳስ 6/2016 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡ ውድድሩ 7 የጉዳት ዓይነቶችን ያካተተ ሲሆን የእግር ጉዳት፣ የእጅ ጉዳት፣ በአይነ ስውራን ሙሉ ለሙሉና በጭላንጭል፣ ዊልቼር የሚጠቀሙ ስፖርተኞች ተፎካካሪ ናቸው፡፡ ከ13 በላይ የስፖርት ዓይነቶች በፉክክሩ የተካተቱ ሲሆን በአትሌቲክስ (ሩጫ፣ ውርወራና ዝላይ)፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ዳርት፣ ገመድ ጉተታ፣ ክብደት ማንሳት እና ሌሎች የስፖርት ዓይነቶች ተካተዋል፡፡
የአካል ጉዳተኞችና መስማት የተሳናቸው ስፖርታዊ ውድድርና ፌስቲቫል ሁለንተናዊ ጥቅምን ከሚያረጋግጡ መድረኮች መካከል አንዱ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፣ በከተማው ለሚገኙ አካል ጉዳተኞች እውቅና ከመስጠቱ ባሻገር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነ ልቦናዊ እንዲሁም ጥቅማቸውን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ተገልጿል፡፡ በዚህም መስማት የተሳናቸውና አካል ጉዳተኞች በስፖርት የመሳተፍ አቅምም ብቃትም በመያዛቸው እንደዚህ አይነት ውድድሮች መዘጋጀታቸው ከተማ አስተዳደሩን ብሎም ሀገርን የሚወክሉ ስፖርተኞችን ለማፍራት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሏል።
የአዲስ አበባ ከተማ መስማት የተሳናቸው ስፖርቶች ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ እሌኒ ጌትዬ፣ የውድድሩ ዓላማ አካል ጉዳተኞችን በስፖርቱ ማሳተፍና ተጠቃሚ ማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በውድድሩ ማንኛውም አካል ጉዳተኛ የመሳተፍ መብትና ዕድል እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡ የስፖርት ፖሊሲው አካል ጉዳተኞች በሚማሩበት፣ በሚሠሩበትና በሚኖሩበት አካባቢ መሳተፍ እንደሚችሉ የሚያስቀምጥ በመሆኑም በዚህ ውድድር የሚሳተፉ ስፖርተኞች በነዚህ ስፍራዎች ተሳትፎን በማድረግ እንደመጡም ገልፀዋል፡፡
የዘንደሮ ውድድር ከሌላው ጊዜ ትንሽ ቀዝቀዝ ያለ እንደሆነ የጠቀሱት ወይዘሮ እሌኒ፣ ብዙ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መሠራታቸውን አስረድተዋል፡፡ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የበጀት ውስንነቶች የነበሩ ቢሆንም የውስጥ ውድድሮችና ቅስቀሳዎች በስፋት ተካሂዷል፡፡
የአዲስ አበባ መስማት ተሳናቸውና አካል ጉዳተኞች ስፖርቶች ፌዴሬሽን በትብብር የስፖርተኞቹን ተሳትፎና ጥቅም ለመጨመር በቀጣይ በከተማው ያሉትን ሁሉንም አካል ጉዳተኞች በስፖርቱ ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ እንደሚሠራም ገልፀዋል፡፡ ለአካል ጉዳተኞች የሚሆን ምቹ ሁኔታ ባለመኖሩ በቀላሉ ተሳትፎ ባለማድረጋቸው ቅሬታ የሚሰማቸው ቢሆንም በውድድሩ በመሳተፋቸው ጥሩ የሆነ መነቃቃት እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡
እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች በስፖርቱ ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግና ስፖርቱ እንዲስፋፋና በሁሉም ክፍለ ከተሞች ደረጃውን የጠበቀ ኮሚቴ የማደራጀት ሥራ እየተሠራም ነው፡፡ ለዚህም ከሁሉም መስማት ከተሳናቸውና አካል ጉዳተኞች የተውጣጣ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡ በዚህ ዓመት የፌዴሬሽኑን አዲስ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የማዋቀር ሥራ እንደተሠራም አክለዋል፡፡
በተጨማሪም ከድርጅቶች ጋር በመነጋገር አካል ጉዳተኞችን በክለብ እና በቡድኖች ደረጃ እንዲይዙ እና የማሳተፍ ሥራዎችም እንዲሰሩ የማድረግ ሥራዎችም እንደሚሠራም ተጠቁሟል፡፡ ከዚህ ቀደም አምስት ክለቦች የተመሠረቱ ሲሆን ይህንን ባለሀብቱንና ሌሎች አካላትን በማስተባበር ተጨማሪ ክለቦችን ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡
በመሆኑም ፌዴሬሽኑ በታዳጊ ስፖርተኞችና ክለቦች ላይ በመሥራትና ኤሊት ስፖርተኞችን በማፍራት ተጠቃሚና ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ አካል ጉዳተኞች እድሉ ቢመቻችላቸው ምንም ነገር ማድረግ የሚችሉ በመሆኑ ማህበረሰቡ አካል ጉዳተኞች ላይ ያለውን አመለካከት በመቀየር እገዛ በማድረግ እንደሚገባም ተጠቁሟል፡፡
ዓለማሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ኅዳር 29 ቀን 2016 ዓ.ም