በፈተናዎች ያልተሰበረ መንፈስ …

ልጅነት …

ባሌ ጎባ ተወልዶ ከመንደር ቀዬው ላይ አድጓል። ልጅነቱ መልካም ነበር። እንደ እኩዮቹ ሮጦ፣ ተጫውቶ ለመዋል ወላጆቹ ነጻነት ሰጥተውታል። ረጅምና ለግላጋ ነው። ገና በልጅነቱ መመዘዝ የጀመረው ቁመቱ ከባልንጀሮቹ ነጥሎ፣ ለይቶ ያሳየዋል።

ጥላሁን ዓለሙ ወላጅ አባቱን በሞት ያጣው ገና የስድስት ዓመት ሕፃን ሳለ ነበር። ይህ ዕድሜ የተወለት ቢኖር የአባቱን ንጹህ ፍቅርና ትዝታ ብቻ ነው። ለወላጅ እናቱ ከአባቱ ሞት በኋላ ሕይወት ቀላል አልሆነም። እሱን ጨምሮ ለሚያኖሩት ቤተሰብ ኃላፊነቱ ከበዳቸው።

የጥላሁን አባት ጠንካራ ገበሬ ነበሩ። የእሳቸው ብርታት ቤታቸውን በጥጋብ ተድላ አኑሯል። ከዓመት ዓመት የሚያፍሱት ምርት ለሚስት ልጆቻቸው በረከት ሆኖ ለሌሎች ተርፏል። እማወራዋ ድንገት አጋር ትዳራቸውን ቢያጡ ቀን ጨለመባቸው። ውሏቸው በሀዘን ትካዜ ተያዘ።

አባወራው ከጥላሁን በፊት ያፈሯቸው ልጆች አሉ። ከሚስታቸው ጋር የያዙት ሀብት ንብረት እስከዛሬ ለሁሉም ጸጋ ሆኖ ቆይቷል። ከእሳቸው ሞት በኋላ ግን ይህ የርስት ጉዳይ ጥያቄ አስነሳ። ሀብቱ ‹‹ይገባናል›› ያሉ ባለመብቶች ክርክር ያዙበት። ጉዳዩ በሕግ እንዲፈታ ፍርድ ቤት መመላለስ ግድ ሆነ። የጥላሁን እናት ተሟጋቾችን ለመርታት ከዳኛ ፊት ቀረቡ። ውዝግብ፣ ክርክሩ ቀጠለ።

ጥላሁን ለእናቱ የተለየ ፍቅር አለው። ከአባቱ ሞት በኋላ ‹‹አለኝ›› የሚለው ብቸኛ ሰው እሳቸውን ነበርና ሕይወቱ ከማንነታቸው አልተነጠለም። ሕጻን ቢሆንም ፍርድ ቤት አብሯቸው ቆሟል። ውዝግብ፣ ክርክሩን በእኩል ተካፍሏል። ዘመኑ ሰዎች በመሬት ርስት ጉልት የሚካሰሱበት፣ ጊዜ ነበር። ይህ ሁሉ ለትንሹ ጥላሁን ትዝታ ነበር። ዛሬም ድረስ ውል ይለዋል።

ድንገቴው ለውጥ…

የጥላሁን እናትና ተከራካሪዎቹ ክስ ላይ ሳሉ በሀገሪቱ ታላቅ ለውጥ ተከሰተ። ንጉሱ ከሥልጣን መውረዳቸውን ተከትሎ አብዮቱ ፈነዳ። ይሄኔ መሬትና ርስት ይሉት ጉዳይ ታሪክ ሆነ። አጋጣሚው የነጥላሁንን ቤተሰብ ሕይወት ለመቀየር አፍታ አልፈጀም።

የለውጡ ነገር ክርክር ሲካሄድበት የቆየውን የውርስ ጉዳይ መና አስቀረው። ርስት ጉልት ‹‹ይገባናል›› ያሉ ሁሉ በመሬት ለአዋጁ መመሪያ ታገዱ። ይህን ተከትሎ የተነሳው ብጥብጥ አካባቢውን ሰላም ነሳው። ግጭትና አለመረጋጋቱ ስጋት ቢሆን እነ ጥላሁን ስፍራውን ለቀው ሊወጡ ግድ ሆነ።

በወቅቱ ጥላሁን ቄስ ትምህርት ቤት ገብቶ ነበር። የፊደል ቆይታውን እንዳጠናቀቀ መደበኛ ትምህርቱን ለመቀጠል አንደኛ ክፍልን ጀመረ። ይህ ወቅት ከሚወዳቸው እናቱ የነጠለው ጊዜ ነበር። ቤተሰቡ አካባቢውን ርቆ በሄደ ጊዜ የእሱ ዕጣ ፈንታ በአክስቱ ቤት፣ እንዲሆን ተወሰነ። የእሳቸው እግር ‹‹ዶሎመና.. ከተባለ ስፍራ ሲያቀና ጥላሁን ከአክስቱ ቤት ተቀምጦ መማር ነበረበት። ይህ ጊዜ የልጅነት ዓይኑ በእናት ናፍቆት የተንከራተተበት እንደነበር ያስታውሳል። እንዲያም ሆኖ ትምህርቱን አልተወም። በጥንካሬ ተምሮ ሰባተኛ ክፍል ደረሰ።

የዛኔ ጥላሁን በሚኖርበት አካባቢ የእግር ኳስ ቡድን ነበር። በቡድኑ እሱን መሰል ታዳጊዎች ታቅፈው መጫወትን ለምደዋል። አንድ ቀን ጥላሁን ከጓደኞቹ ጋር ሲጫወት እግሩን ስቶት ወደቀ። አወዳደቁ ከበድ ቢል እጁ ላይ ጉዳት ገጠመው። ዕለቱን ህመሙ ቢሰማውም ማንም ትኩረት አላለውም ።

ውሎ አድሮ የጥላሁን ህመም መባባስ ያዘ። ከአሳዳጊ አክስቱ በቀር የቅርብ ቤተሰብ የሌለው ልጅ የእጁን ችግር በቤቱ ይዞ ቀናትን ቆጠረ። ታዳጊው በወቅቱ ትምህርቱን ከማቆም በቀር ምርጫ አላገኘም። ቀስ እያለ ህመሙ መዳን ሲጀምር ወደ ትምህርት ገበታው የመለሰው አላገኘም። ጥቂት ጊዚያትን ሸንኮራ እየሸጠ ሊኖር ተገደደ።

ከቀናት በኋላ ከዓመታት በፊት የተለየችው አንዲት እህቱ ወደመንደራቸው ዘለቀች። አባቱ ከሞቱ በኋላ በማደጎ ወደ ሌላ ስፍራ ሄዳ ነበር። እህቱ የጥላሁንን አለመማር ባየች ጊዜ ውስጧ አዘነ። ከዚህ በኋላ ያለ ትምህርት መቆየት እንደሌለበት ወሰነች።

ጥላሁን ከሰባተኛ ክፍል ያቋረጠውን ትምህርት ሊቀጥል ደብተሩን አነሳ። በጊዜው ሥርዓተ ትምህርቱ በመቀየሩ ወደ ስድስተኛ ክፍል ሊከለስ ግድ አለው። ትምህርቱን መከለሱ ክፉ አልሆነም። የስምንተኛ ክፍልን ብሔራዊ ፈተና ከመቶ ዘጠና ዘጠኝ በማምጣት አለፈ።

ወጣትነትን በአዲስ አበባ ..

አሁን ጥላሁን ልጅነቱን አልፎ ጉርምስናውን ጀምሯል። ይህ ዕድሜ ክፉና ደጉን፣ የሚለይበት ማንነቱን የሚያውቅበት ነው። ዛሬ ራሱን ችሎ መንቀሳቀስ አያቅተውም። ከወላጅ እገዛ፣ ከዘመድ ክትትል ወጥቷል። ድንገቴ አጋጣሚ አዲስ አበባ ‹‹ቄስ ሰፈር›› ላይ ያደረሰው ጥላሁን ከአካባቢው መላመድ አላቃተውም።

ጥላሁን በትልቅ እህቱ ቤት ተቀምጦ ትምህርቱን መማር ቀጠለ። በእንጦጦ አጠቃላይ የዘጠነኛ ክፍልን ሲቀጥል በውጤቱ ተመስጋኝና ተወዳዳሪ ሆነ። ዓላማ ነበረውና መዘናጋት አልፈለገም። ሁሉን በጊዜው አቻችሎ ለቁም ነገር ጊዜ ሰጠ።

አሁን አስረኛ ክፍልን ተሻግሮ አስራ አንደኛን ጀምሯል። ይህ ጊዜ ከርሞ ለሚወሰደው የማትሪክ ፈተና የሚዘጋጅበት፣ በርትቶ የሚተጋበት ነው። እናም ጠዋት ማታ ደብተሩን ይዞ ከቀለም ጋር ያወራል። ያለ አባት ያደገው፣ በእናት ናፍቆት የኖረው ጥላሁን ራሱን ችሎ ‹‹ሰው›› ለመባል ብዙ ሞክሯል። ከልጅነቱ ለትምህርት የነበረው ትኩረት ዛሬ ከጫፍ ሊያደረሰው መንገድ ላይ ነው።

ጥላሁን የአስራ አንደኛ ክፍልን ማገባደድ እንደያዘ ህመም ቢጤ ተሰማው። ህመሙ እግሩን ይዞት ነበርና እንዳሻው ሰውነቱን አላዘዘም። ጉዳዩ አሳሳቢ ቢሆን ህክምናውን ሊያይ ግድ ሆነ። በታከመባቸው ሆስፒታሎች ያገኘው ውጤት ተመሳሳይ ነበር። ከቅዝቃዜ ተያይዞ የመጣ ችግር መሆኑ ተነግሮታል። ጥላሁን እያመመው ነው። እንዲያም ሆኖ ትምህርቱን ትቶ ቤት አልዋለም። ጥርሱን ነክሶ ህመሙን ቻለ። እስከዛሬ የለፋበትን፣ አርቆ ያለመለትን ትምህርት ማጠናቀቅ ዓላማው ነው።

ትምህርቱን ሲጨርስ ለዩኒቨርስቲ ይዘጋጃል። ይህ እንዲሆን ከመንገዱ መደናቀፍ ከሃሳቡ መዘናጋት የለበትም። ህልመኛው ወጣት ያሰበው አልቀረም። ከእግሩ ህመም እየታገለ የማትሪክ ፈተናን አጠናቀቀ።

አሁን ጥላሁን ውጤቱን መጠበቅ ይዟል። ባለው ጊዜ ወደራሱ ተመልሶ ውስጡን እያዳመጠ ነው። የተለየ ህመም አይሰማውም። ማትሪክ ተፈትኖ በቆየባቸው ጥቂት ወራት ለራሱ ጊዜ ሰጥቷል። ኑሮው በእህቱ ቤት ነውና ሕይወት አልከበደውም። እንደታናሽነቱ እየታዘዘ፣ እንደትናንቱ መሆኑን ቀጥሏል።

አሁን የክረምት ጊዜ ነው። ሰኔና ሐምሌ በዝናብ ታልፈዋል። ጭቃ ጎርፉ ዳመና ብርዱ የወቅቱ መገለጫ ነው። ክረምት ሲሆን በትምህርት የቆዩ ተማሪዎች መጻሕፍትን ያነባሉ። ለወላጆቻቸው ይሰራሉ፣ ለራሳቸው ይተጋሉ። በነሐሴ ክረምቱ ያበቃል። አዲሱ ዓመት ይሞሸራል። ጥላሁን እንደእኩዮቹ ሁሉ በክረምቱ መጻሕፍት ሲያነብ ተማሪዎችን ሲያስጠና ቆይቷል።

የጨለማው መንገድ …

ጥላሁን ከቀናት በአንዱ ከእህቱ ጋር ዘመድ ጥየቃ ከቤት ራቁ። የደረሱበትን አካባቢ ከዚህ ቀድሞ አያውቀውም። ጉዳያቸውን ፈጽመው ከሰፈሩ ሲወጡ ሰዓቱ ገፍቶ ምሽቱ አይሎ ነበር። በእግራቸው መንገድ የያዙት እህት ወንድም ጉዟቸውን ቀጥለዋል። የጨለማ መንገድ አይመችም። ከጉድጓድ ከጉድባው ይከታል። በተለይ የማያወቁት አካባቢ ሲሆን ችግሩ ይብሳል።

ዘመድ ጠያቂዎቹ መንገዳቸው ቀጥሏል። ጥላሁን እርጥቡ የክረምት መሬት የተመቸው አይመስልም። ከአንድ ሰፍራ ደርሶ ሸርተት አደረገው። ጨለማ ነውና ራሱን መጠበቅ አልቻለም። ቦታው ላይ ያገኘው ብረት ክፉኛ ጎድቶታል። እንደምንም ተነስቶ ለመሄድ ሞከረ። እንዳሰበው አልተራመደም።

ከነህመሙ ቤት የገባው ጥላሁን ለመንቀሳቀስ ሞከረ። ጉዳዩ ከባድ ሆነበት። ማግስቱን ሆስፒታል ደርሶ ለቀናት ሐኪም ዘንድ ተመላለሰ። ችግሩ በመርፌና መድኃኒት አልዳነም። አልጋ አስይዞ ያስተኛው ጉዳት ያለአንዳች መፍትሔ አቆየው። ከሆስፒታል የተሰጠው ውጤት ተስፋ የሚያጭር አይደለም። ሐኪሞች ጉዳቱን አይተው በቀላሉ እንደማይድን ነግረውታል።

ጥላሁን ከልጅነት ዕድሜው አንስቶ የደጋገመው የእጅና እግሩ ጉዳት ጊዜ ጠብቆ በርትቶበታል። ያለ አንዳች ተስፋ ከአልጋ የቀረው ወጣት አሁንም የማትሪክ ውጤቱን እየጠበቀ ነው። ብዙ የለፋለት ትምህርት ለፍሬ እንደሚያበቃው ያምናል። ድኖ ሲነሳ ከዩኒቨርሲቲ እንደሚገኝ ያስባል። ይህን ሲያስብ ነገው ብሩህ ሆኖ ይታየዋል።

ጥላሁን አሁንም አልጋ ላይ ነው። ተስፋ የጣለበት ድኖ መነሳት ዕውን አልሆነም። ሲቆም ሲቀመጥ የሚደነዝዘው አካሉ እንዳሻው አልታዘዘም። ዛሬም በዓይኑ ውል የሚልበት ትምህርቱ ከአእምሮው ውሎ ያድራል። ከቀናት በአንዱ ድንገት የተሰማው የማትሪክ ተፈታኞች ውጤት ለጥላሁን ጆሮ ደረሰ። ሁሉም ውጤቱን ለማወቅ ከያለበት ተጠራራ። የዛኔ ታማሚው ጥላሁን ካልጋው አልተነሳም ። እንደ ሌሎች የድካሙን ፍሬ ማየት አልታደለም። ካለበት ሆኖ ውጤቱን አስጠየቀ። ብርቱው ወጣት ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባውን አመርቂ ውጤት አስመዝግቧል።

እነሆ! ጊዜው ደረሰ። ማትሪክን ያለፉ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ሊያቀኑ ሻንጣዎችን አነሱ። ጎበዙ ጥላሁን ከነእሱ መሀል አንዱ ነው። እንደሌሎች ግን የመማር ዕድል አልቀናውም። ያደረበት ህመም እጅና እግሩን ይዞ ከቤት እንዳዋለው ወራት ተቆጥረዋል። ባልንጀሮቹ ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲያቀኑ እሱ ከአልጋው እንደተኛ ሸኛቸው።

በፀበል በሕክምናው መፍትሔ የጠፋለት ህመም የመዳን ተስፋ አላሳየም። ተኝቶ የሚውለው ጥላሁን አሁን አማራጭ እያጣ ነው። ይህ ስሜት በውስጡ ባደረ ጊዜ አዲስ አበባን ትቶ ወደ ትውልድ ሀገሩ ሊሄድ ወሰነ።

ባሌ ጎባ…

ጎባ በደረሰ ጊዜ ለውስጡ ብሩህ ተስፋን አቀበለው። የቀሰመው ትምህርት እንዳይጠፋበት ውሎው ከመጻሕፍት ጋር ሆነ። ዘንድሮ ያመለጠውን ትምህርት ለከርሞ በስኬት እንደሚገባበት ተማመነ። የአካባቢው ልጆች ከእሱ ዕውቀት ሊጋሩ ከጎኑ ተገኙ። የያዘውን አልሰሰተም። የጠየቁትን እያስረዳ፣ የከበዳቸውን ማስጠናት ቀጠለ።

ዓመት አልፎ ዓመት ተተካ። ጥላሁን ስለትምህርቱ ተስፋ አልቆረጠም። ዩኒቨርሲቲ የመግባት ህልሙ ከእሱ ነበርና ዕድሉን ሊሞክር መረጃ ጠየቀ። ያሰበው አልተሳካም። ቀድሞ ያልጀመረውን ትምህርት መቀጠል እንደማይችል ተነገረው። ውስጡ ቢያዝንም ተስፋ አልቆረጠም። እውነታውን በይሁንታ ተቀበለ።

ከእናቱ ጋር ኑሮ ከጀመረ ወዲህ በረዳቶቹ አጋዥነት ጥቂት ይንቀሳቀሳል። አሁን ዶሮዎች ማርባት፣ የጓሮ አትክልት ማልማት ጀምሯል። ይህ ሁሉ ሲሆን ጤናው ላይ ለውጥ አልታየም።

ከ1990 ዓ.ም ወዲህ ጥላሁን ችግሩ እየባሰበት ሄደ። በሰዎች ድጋፍ የቆየው አካሉ መልሶ ከአልጋ ዋለ። አልላወስ ያለው እጅ እግሩ ሙሉ ለሙሉ ከሰው ርዳታ ጣለው። አንዳንዴ እጆቹ ሲዘረጉ መታጠፍ ያቅታቸዋል። እንደምንም ሲታጠፉ ደግሞ መዘርጋት ይሳናቸዋል። የእግሩም ላይ ህመም የተሻለ አይደለም። ችግሩ ከፋ፣ ህመሙ ባሰ።

ጥላሁን ረጅሙን ጊዜ ያሳለፈው ከእናቱ ጋር በመኖር ነው። እሳቸው የልጃቸውን ችግር ለመሸከም ትከሻቸው ሰፊ ነው። እሱም ቢሆን በእሳቸው ተስፋውን ጥሏል። ታሞ ቢሰቃይም በእናቱ እስትንፋስ ውስጡ ይታከማል። ብሶቱ ይጠፋል።

ይህ ሁሉ እውነታ ግን በአንድ ቀን ክፉ አጋጣሚ ታሪኩን ቀየረ። አሉኝ የሚላቸው አንድ እናቱ በሞት ተለዩት። አሁንም ጥላሁን ወስጡን አሳምኖ እውነታውን ተቀበለ። እናቱ ለእሱ የግል ስጦታው፣ የማንነቱ ዋልታ ናቸው። ያለ አባት፣ ያለ ረዳት በችግር አሳድገውታል። ከእሳቸው ጋር ክፉ ደግን አልፏል። ዛሬ ትልቅ ሰው ቢሆንም ለእሳቸው ሁሌም ልጅ ነበር።

ጥላሁን ከሕፃንነቷ ጀምሮ እንደ ልጅ ያሳደጋት ዘመዱ በቅርቡ አለች። ውሎ አድሮ ግን ቤቶቿ ባል ታግባ፣ ትዳር ትያዝ ብለው ከእሱ ዘንድ አራቋት። ከዚህ በኋላ ከብርታቱ በቀር አጋር ይሉት አጣ።

ሀዘንና ህመም ከብቸኝነት ተዳምሮ ያለ ረዳት የቀረው ጥላሁን ከተኛበት አልጋ ሆኖ ብዙ ያስብ ጀመር። በአንድ አጋጣሚ ሰዎችን በበጎነት ስለሚያግዙ ሰዎች ታሪክ መስማቱን ያስታውሳል። የመቄዶንያውን መስራች ቢኒያምን ጨምሮ ስለ ሌሎች ልበ መልካሞቸ ደጋግሞ አዳምጧል።

ውሳኔው…

2007 ዓ.ም ለጥላሁን የውሳኔ ጊዜ ሆነ። ባሌ ጎባ ለቆ ለመውጣትና አዲስ አበባ ለመመለስ ቆረጠ። ምክንያቱ እነዚህን በጎ ሰዎች በአካል ለማግኘት ነበር። በአውቶቡስ ተሳፍሮ ካሰበው ሲደርስ የተቀበሉት ታላቅ እህቱ ነበሩ። በወቅቱ እሱን ለማገዝና ለማኖር የሚያስችል አቅም እንደሌላቸው ተረድቷል።

ጥላሁን የሰውነቱ መግዘፍ ለእንክብካቤ አያመችም። ህመሙን ይዞ እህቱንና ቤተሰባቸውን ማስቸገር ማስጨነቅ መሰለው። በእሱ ጉዳይ የመከሩ ወገኖች ለዘለቄታው የሚኖርበትን ማረፊያ አፈላለጉለት። ከጊዚያት በኋላ ጥላሁን ‹‹የወደቁትን አንሱ የነዳያን በጎ አድራጎት›› ውስጥ ራሱን አገኘው።

በዚህ ስፍራ ሰፊ እጆች፣ መልካም ፊቶች በቅንነት ተቀበሉት። ከሐምሌ 2008 ዓ.ም ጀምሮ ለቤቱ ቤተሰብ የሆነው ጥላሁን እንደልማዱ ነገሮችን በበጎ ተቀብሎ መኖር ይዟል።

ዛሬም ከአልጋ በማይነሳው አካሉ፣ በማይንቀሳቀሱት እጅና እግሮቹ ተማሮ አያውቅም። ፈጣሪውን በሙሉ አፉ ያመሰግናል። ያለፈበት መንገድ እሾሀማ ቢሆንም ስለምን ብሎ ከራሱ አይጣላም። ሁሌም በምስጋና ፈጣሪውን ያወድሳል፣ ከአልጋ የዋለው፣ ማንነቱ ዓለም ከንቱ መሆኑን ባስታውሰው ጊዜ ውስጡ ይበረታል። ውስጡ እንደ አካሉ አይደለም። ሁሌም በጽናት ይቆማል። ጠንካራው፣ አይሰበሬው፣ ብርቱ ጥላሁን ዓለሙ።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 29  ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You