እንኳን ለኢትዮጵያውያን ቀን አደረሰን፤ አደረሳችሁ!

 ኢትዮጵያ መልከ ብዙ ናት፤ ይሄ መልከ ብዙነቷ ደግሞ ከፍ ያለ ድል እና ገድል ባለቤት በሆኑ ሕዝቦቿ አማካኝነት የሚገለጽ ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ያለ ኢትዮጵያውያን መገለጫ እንደሌላት ሁሉ፤ ኢትዮጵያውያንም ያለ ብዝሃነታቸው ማንነት አልቦ መሆናቸውን መረዳት ይገባል።

ይሄ ብዝሃነት ደግሞ ለኢትዮጵያውያን ውበትና ኃይል፤ ለኢትዮጵያም ጌጥ እና ብርታት ነው። በውበት ያጌጠ ማንነት፤ በተሰባሰበ ኃይል የበረታ ሀገር ደግሞ መገለጫውም መከሰቻውም ብዙ ነው። ምክንያቱም ውበቱ ያደምቀዋል፤ ብርታቱ ያገዝፈዋል። እየደመቀ የገዘፈ ሕዝብና ሀገር ደግሞ ሀገራዊ ብልጽግናውም፤ ዓለምአቀፋዊ ተጽዕኖውም እውን መሆኑ አይቀሬ ነው።

ይህ እንዲሆን ታዲያ ኢትዮጵያውያን ዘመናትን ዋጋ ከፍለዋል። ምክንያቱም በአንድ በኩል አሃዳዊ እሳቤ፤ በሌላ በኩል ጽንፍ የወጣ የማንነት ትርክት ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን ጠርዝ አስይዞ ሲያጓትት፤ ሲያታኩስና ሲያጋድልም ኖሯል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያዊነት በብርቱ ድር የተሸመነ ማንነት ነውና መጓተትና መታኮሱ ሊበጥሰው፤ ኢትዮጵያዊነትን በኅብር ከደመቀው መገለጫው ሊያወርደው አልተቻለውም።

ዛሬ ላይ ለ18ኛ ጊዜ የሚከበረው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ደግሞ የዚህ አንዱ ምስክር ነው። ኢትዮጵያ የመልከ ብዙነቷ፤ ኢትዮጵያውያንም በሕዝብ የደመቀው የማንነት ትስስራቸው አውድ ሆኖ፤ የትናንቱ ችግር እንዳይደገም የሚማማሩበት፤ የነገ አብሮነታቸው በኅብር ከፍ ብሎ እያበበ ለፍሬ የሚበቃበትን አካሄድ የሚመክሩበት መድረክ ነው።

“ብዝኃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት” የሚለው የበዓሉ መሪ ሃሳብ የሚያመለክተውም፤ ኢትዮጵያ የብዝሃነት ሀገር መሆኗ ብቻ ሳይሆን፣ ብዝሃነቷን በእኩልነት አውድ ላይ አኑራ ማስቀጠል መቻሏ ለሀገራዊ አንድነት በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን ነው። ምክንያቱም ብዝሃነት የሃሳብም፣ የባህልና እሴትም፣ የቋንቋና አመለካከትም፣ የብሔርና ሃይማኖትም፣… መልክ አለው። ይሄ የበዛ መልክ ደግሞ በእኩል ሊታይ፤ በእኩል ሊገለጥ፤ በእኩል ሊስተናገድ ይኖርበታል። ይሄ ሲሆን የሕዝቦች አብሮነትና አንድነት ይጠነክራል፤ ሀገርም በተባበረ የሕዝቦቿ አቅም ትጸናለች።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዓሉን አስመልክተው “እንኳን ለኢትዮጵያዊነት በዓል አደረሳችሁ” ሲሉ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስገነዘቡትም ይሄንኑ ነው። እርሳቸው እንዳሉት፤ ይህ በዓል የኢትዮጵያዊነት በዓል ነው። ኢትዮጵያዊነት ማለት ደግሞ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ማዕከል ያደረገ ሀገራዊ ማንነት ነው። ምክንያቱም፣ ኢትዮጵያዊነት በአንድ በኩል የብሔር ብሔረሰቦችን ብዝኃነት የሚቀበል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ይሄንን ብዝኃነት አስተሳስሮ የያዘና ለዘመናት የተሻገረ ጠንካራ አንድነት አለ ብሎ የሚያምን ነው።

ከዚህ አኳያ ሲታይ በዓሉ ይሄንን ብዝኃነት አስተሳስሮ የያዘና ለዘመናት የተሻገረ ጠንካራ አንድነትን ማጽናት የሚቻልበትን እድል የሚሰጥ መሆኑ እሙን ነው። ምክንያቱም በዓሉ ኢትዮጵያውያን ብሔር ብሔረሰቦች ባህልና እሴቶቻቸውን ዓደባባይ ላይ ከማሳየትና ከማሳወቅ በተጓዳኝ፤ ይሄንን ባህልና ወጋቸውን ሊማማሩበና የጋራ ሀብታቸው ሊያደርጉበት የሚችሉበት ነው።

ከዚህም በላይ ደግሞ፣ በኅብረ ብሔራዊ አንድነት ላይ የተመሠረተውን የብሔራዊነት ትርክት የሚገነባበት በዓል ነው። ምክንያቱም የኅብረብሔራዊ አንድነት ትርክት ጫፍ እና ጫፍ ከቆሙ (የአሃዳዊነትም ሆነ ጽንፍ የወጣ የብሔርተኝነት) አፍራሽ ትርክቶች የሚያላቅቅ፤ ኢትዮጵያውያን ዘመናትን በዘለቀው የአብሮነትና እኩልነት መሠረት ላይ እንዲጸኑ መደላድል የሚፈጥር እሳቤ ነው።

“ኅብረ ብሔራዊነት ሀገርን ለመከፋፈልና ለማዳከም ከተገነባው ነጠላና ጽንፈኛ ትርክት የምንወጣበት መንገድ ነው” በሚል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹትም ይሄንኑ ነው። ምክንያቱም የኅብረ-ብሔራዊነት ትርክት ከፖለቲካዊ ታሪካችን ይልቅ ማኅበራዊ ታሪካችንን በማጉላት፣ ከትናንትና ይልቅ በዛሬና በነገ ዕድሎቻችንና ሥራዎቻችን ላይ በመመሥረት፣ በሕገመንግሥታዊ ሥርዓት ላይ የቆመ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመመሥረት የሚያስችል ገዥ ትርክት ነው።

ይሄን ትርክት የማስረጽና የማጽናት ተግባር ደግሞ የአንድ ወገን ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያውያን የቤት ሥራ ነው። ትናንት ኢትዮጵያን ለማጽናት ያለ ልዩነት የተሳተፈ ኢትዮጵያዊ፣ ዛሬ ይሄንን በሕብር የደመቀ አንድነቱን ለማዝለቅ ወደኋላ ሊል የሚገባው አይኖርም። ምክንያቱም የኅብረ-ብሔራዊነት ትርክት መነሻዎችም ባለቤቶችም ብሔር ብሔረሰቦች ናቸው።

ሃሳቡም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች መከራና ፈተና ሳይነጣጥላቸው፣ ለጋራ ዕጣ ፈንታቸው ሲሉ በአንድነት የከፈሉትን መሥዋዕትነት ከማጽናት የሚነሣ ነው። “ኢትዮጵያን ያልገነባ፣ ለኢትዮጵያ ዋጋ ያልከፈለ፣ ማንም ሕዝብ የለም። ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በገነቧትና ዋጋ በከፈሉባት ኢትዮጵያ በፍትሐዊነት፣ በእኩልነትና በነጻነት የመኖር መብትም አላቸው። ኢትዮጵያን ከልመና የማላቀቅና የብልጽግናን መሠረት የመጣል ግዴታም አለባቸው፤” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሳሰቡትም ለዚሁ ነው።

የኅብረ-ብሔራዊነት ትርክት ይሄን ብዝኃነትና አንድነት ማዕከል ያደረገ አሰባሳቢ ትርክት ነው። በመሆኑም በዓሉ ሲከበር ከበዓሉ ማድመቂያ ተግባራት በተጓዳኝ፤ አሰባሳቢ ትርክትን ማስረጽ ላይ ትኩረት በማድረግ ሊሆን ይገባል። እናም የአኩሪ ባህሎችና ማንነቶች መገለጫ በሆነው እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን የምናጸናበት ትርክት ላይ ለምንመክርበት ዛሬ ለምናከብረው ለ18ኛ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓል እንኳን አደረሰን፤ አደረሳችሁ!

አዲስ ዘመን   ኅዳር 29  ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You