ስድስቱ የአመለካከት ለውጦች

አሁን ላይ የምናገኘው ገቢ፣ በሕይወታችን ውስጥ ያለን ደስታና ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት በሙሉ የአመለካከታችን /mind set/ ውጤት ነው። አንዳንዴ እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች በውስጣችን ይፈጠራል። ‹‹ከእኔ በእውቀት፣ በልምድ፣ በእድሜ የማይሻልና የማይበልጥ ሰው እንዴት በኑሮ ሁኔታና በገቢው ሊበልጠኝ ቻለ?›› ልንል እንችላለን። ምን አልባት የጥያቄው መልስ ልዩነቱን የፈጠረው አመለካከት /mind set/ ሊሆን ይችላል። ማይንድ ሴት ደግሞ አእምሯችን የተቀረፀበት መንገድ፣ አመለካከትና አስተሳሰብ ነው። ወይም በእንግሊዘኛው mental attitude or inclina­tion ተብሎ የሚጠራው ነው።

ለምሳሌ ስልካችሁ ሳምሰንግ፣ አይፎን ወይም ሌላም ዓይነት ሊሆን ይችላል። ከስልኮቹ በላይ በጣም ወሳኝ ነገሮች ግን በስልኮቹ ውስጥ ያሉት መተግበሪያዎች /applications/ ናቸው። እነዚህ መተግበሪያዎች እንድንደዋወል፣ መልዕክት እንድንላላክ፣ ፎቶና ቪዲዮዎችን እንድናይ፣ ፎቶ እንድናነሳ፣ ቪዲዮ እንድንቀርፅ፣ መጽሐሃፍ እንድናነብ ያስችላሉ። ያለመተግበሪያዎቹ ስልኮቹ ባዶ ቀፎ ናቸው።

አእምሯችንም እንደስልኮቹ ነው። ሕይወታችንን የሚወስነው በአእምሯችን ውስጥ የሚመላለሰው አመለካከትና አስተሳሰብ ነው። ስለማንኛውም ነገር ያለን አመለካከት ሕይወታችንን ይወስነዋል። ያለመተግበሪያው ስልኮ ባዶ እንደሆነ ሁሉ ያለ አመለካከት /mind set/ ለውጥ ሕይወትን መቀየር የማይታሰብ ነው። በዙሪያችን ዝግ የሆነ አመለካከት ያላቸው ሰዎች አሉ። ‹‹እኔ እድለኛ አይደለሁም፣ ይህን ነገር ለማሳካት አልተፈጠርኩም፣ በፍቅር ግንኙነት ወይም በትዳሬ እንድደሰት አልታደልኩም፣ እውቀት ስለሌለኝ ትምህርት አይሳካልኝም፣ የገንዘብና የሥራ እድል የለኝም፣ ሕይወት ለኔ ከባድ ናት›› የሚሉ ብዙ ዓይነት ዝግ የሆኑ አመለካከቶች አሉ። በሕይወታችን በራሳችን የምንሰጠው ድምዳሜ ወይም ብያኔ አለ። ይህ ዝግ የሆነ አመለካከት/close mind set/ ይሰኛል።

እነዚህ ሰዎች በአስተሳሰባቸውና በአመለካከታቸው ምክንያት ከሚፈልጉበት ይቀራሉ። በሌሎች ሰዎች ለውጥ ይቀናሉ። ነገር ግን እንዲህ የሚሆኑት ምንም ጎድሏቸው አይደለም። ከሙያ ሙያ፣ ከእውቀት እውቀት ይኖራቸዋል። ሆኖም አመለካከትና ድፍረቱ ስለሌላቸው ወደኋላ ይቀራሉ። ከነሱ ብዙም የማይሻሉ ሰዎች ጥለዋቸው ይሄዳሉ። ታዲያ ምንድን ነው ማድረግ ያለብን? ስድስቱ በሕይወታችን ውስጥ መቀየር ያሉብን የአመለካከት ለውጦች ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣሉ።

1ኛ. ‹‹ይሄንን ማግኘት እፈልጋለሁ›› የሚለውን አመለካከት ‹‹ይሄን ለማግኘት ይሄን አደርጋለሁ በሚለው አመለካከት መቀየር

ምኞትህንና ፍላጎቶችህን ሁሉ እውን የምታደርገው በተግባር ብቻ ነው። የተግባር ሰው መሆን አለብህ። ታዋቂው የሥነ ልቦና ባለሙያ ጄምስ አለን ‹‹you will not get what you want, you will get what you are›› ይላል። የምትፈልገውን ነገር አታገኝም፤ የሆንከውን ነው እንደማለት ነው። አንተ ማለት በየቀኑ እየደጋገምክ የምታደርገው ነህ። የምታስበውን ብቻ አይደለህም። ስለዚህ ማሰብ ብቻ በቂ አይደለም። መመኘትንና መሻትንማ ሁሉም ሰው ይፈልጋል። ግን አያገኝም።

ለምሳሌ ውጭ ሀገር ሄደህ መማር መፈለግህ ይሆናል። ነገር ግን ውጭ ሀገር ሄደህ ለመማር ካንተ የሚጠበቀውን ነገር እያደረክ ነው ወይ? የውጭ ቋንቋ እየተማርክ ነው ወይ? የውጭ ቋንቋዎችን ለመፈተን እየተዘጋጀህ ነው ወይ? በስኮላርሺፕ የትምህርት እድል አግኝተው ውጭ ሀገር የሄዱ ሰዎች ምን እንዳደረጉ ታውቃለህ? እነሱ የሰሯቸውን ወይም የተጠቀሙባቸውን ቪዲዮዎችና የተጠቀሙባቸውን ቴክኒኮች አንተ እያደረካቸው ነው ? በቃ! ተግባር ማለት ይህ ነው።

ለምሳሌ ሕይወትህን መቀየር ትፈልጋለህ። ደመወዝህን እጥፍ ማድረግ ትችላለህ። አሁን ባለኸው አንተና እጥፍ በሆነው ደመወዝህ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ሙያ ነው?፣ እውቀት ነው?፣ የትምህርት ዝግጅት ነው? ወይስ ልምድ ነው? ይህን ለይተህ ማወቅ አለብህ። ከዛ እፈልጋለሁ ከሚል አመለካከት ወጥተህ የምፈልገውን ለማግኘት እንዲህ አደርጋለሁ ማለት አለብህ። መንሳፈፍ ማቆም አለብህ።

በሌላውም ነገር የተረጋጋ ሕይወት፣ ትዳርና የፍቅር ግንኙነት መመስረት ልትፈልግ ትችላለህ። ነገር ግን የቤት ሥራህን እየሰራህ ነው ወይ? አንተ ማድረግ እየቻልክ በስንፍናህ ምክንያት ያልፈፀምካቸው ብዙ ተግባሮች አሉ። እነርሱን ተመልከታቸው። ‹‹ትልቁ የተሰጥኦ ክምችት ያለው መቃብር ስፍራ ነው። ሁሉም ሰው ያልተዘፈነ ዘፈን አለው። ያልተፃፈ መጽሐፍ አለው። ሁሉም ተሰጥኦውን፣ ችሎታውንና ብቃቱን ይዞት አልፏል›› ይላል ዶክተር ማይለስ ሞርኖ። እኛም ይዘነው የምንፈልገውን ነገር በአእምሯችን እያሰላሰልነው ማለፍ የለብንም። ስለዚህ ማግኘት እፈልጋለሁ ከሚል አስተሳሰብ ወጥተን ይህንን ለማግኘት ይህንን አደርጋለሁ ወደሚል አስተሳሰብ መቀየር አለብን።

2ኛ. ‹‹ሕይወት ከባድ ነው›› የሚለውን አመለካከት ‹‹ሕይወት ቀላል መሆን ይችላል›› በሚል መቀየር

ይህ የብዙ ሰዎችን አእምሮ የተቆጣጠረ አስተሳሰብ ነው። በተለይ ወላጆቻችን፣ በዙሪያችን ያሉ ሰዎች፣ የምናከብራቸው ሰዎች ሕይወትን አክብደን እንድናይ አድርገው ነው ያሳደጉን። ‹‹አንተ! ሕይወት ቀላል መስሎሃል፣ ገንዘብ እንደቀልድ የሚገኝ መስሎሃል፣ ጠንክረህ ካልተማርክ ሕይወት እኮ ከባድ ነው፣ ትዳርም ቀላል ነገር አይደለም›› ይሉናል። በንግግራቸው ነገሮች ካላቸው ሸክም ክብደት በላይ ይበልጥ እንዲሰማን ያደርጉናል። ሌሎችንም አስተያየቶች በዙሪያችን እንሰማለን። ሥራ የለም፣ ትምህርት ሥርዓቱ ወድቋ፣ መንግሥት እኮ ወድቋል፣ ሌባ የሚከበርባት ሀገር ናት፣ ፍትህ እኮ የለም፣ በዚህ ሰዓት ምን ልሁን ብለህ ነው ቢዝነስ የምትጀምረው የሚሉ ብዙ ዓይነት አስተሳሰቦችንና ሕይወት አክባጅ ንግግሮችን እንሰማለን።

ሰዎች የሚነግሩን ነገሮች ሁሉም ውሸት አይደሉም። አብዛኛዎቹ እውነት ናቸው። ችግሩ ግን ድምዳሜው ላይ ነው። ሕይወት ከባድ ናት ብለን ከደመደምን የእውነትም መለወጥ ይከብደናል። ሕይወት ከባድ ልትሆን ትችላለች። አዎ! ከባድ ናት። ግን ቀላል መሆን አትችልም እንዴ? ትችላለች። ቀላል የሆነላቸው ሰዎች እኮ አሉ። ከእነሱ መካከል እኔ ልሆን እችላለሁ ማለት አለብን። ምን አልባት ሕይወትህን ያከበደው አመለካከትህ ሊሆን ይችላል። የመረጥከው ሥራ ሊሆን ይችላል። የማትወደውን ነገር እየተማርክ ሊሆን ይችላል። በዙሪያህ ያላየሃቸው ዓይንህን ገልጠህ ያልተመለከትካቸው ብዙ እድሎች ይኖራሉ። አንተ ሕይወት ከባድ ናት ብለህ ስለደመደምክ ቀላል ነገሮች አይታዩህም። እነዛን እድሎች ለማየት ግን ግርዶሹን መግፈፍ አለብህ።

3ኛ. ‹‹ለእኔ አይሆንም›› የሚለውን አመለካከት ‹‹እንዴት ለእኔ ይሁን›› በሚለው መቀየር

አንዳንዴ ከመሬት ተነስተን ወይም ሞክረን ሊሆን ይችላል ራሳችን ላይ የምንደመድማቸው ሃሳቦች አሉ። ‹‹መቼም ሊኖረኝ አይችልም፣ መቼም ላሳካው አልችልም፣ ይህ ለእኔ የማይታሰብ ነው›› የምንላቸው ነገሮች አሉ። ስኬት፣ ገንዘብ፣ ትዳር፣ የፍቅር ግንኙነትና ሌላም ሊሆን ይችላል። ብቻ ይሄ ለእኔ አይሆንም፣ ለእኔ አልተፈጠረም የምንላቸው ነገሮች አሉ።

አንተም እንደዚህ ብለህ ካመንክ እውነት ነው አታገኘውም፤ አይሳካልህም። አየህ ብዙ ሰዎች የሚሸነፉት ሞክረው ወይም ብርቱ ጥረት አድርገው አይደለም። ገና ምንም ሳይሞክሩ በሃሳብ ነው የሚሸነፉት። ቁጭ ብለው ያስቡትና አይታያቸውም። ወዲያው እጅ ይሰጣሉ። ‹‹አይ ለእኔ አይሆንም›› ይላሉ። ሁሉም ሰው እንደማይሆንልህ ሊነግርህ ይችላል። አንተም ለራስህ እንደማይሆን ሊሰማህ ይችላል። ‹‹አሁን እኔ ተምሬ የት እደርሳለሁ፣ ተቀጥሬ ስንት ብር ላገኝ ነው፣ ገንዘብ ቆጥቤ ስንት ሊሞላልኝ ነው፣ እንደው በዚህ ሰዓት ቢዝነስ ብጀምር ያዋጣኛል›› ልትል ትችላለህ።

በተለይ ካንተ ብዙ የማይሻል ሰው አሉታዊ ነገር ሲነግርህ አትስማው። ለምን መሰለህ? የራሱን ሕይወት በትንሽ መልኩ እንኳን ያለቀየረ ያንተን ሕይወት እንዴት አድርጎ ነው የሚቀይረው። ነገር ግን ደግሞ ብዙ ነገር ይነግርሃል። ‹‹እኔ የከሰሩ ብዙ ሰዎች አውቃለሁ ተው ይቅርብህ፣ አርፈህ ተቀመጥ፣ ይቅርብህ፣ ጐመን በጤና፣ እጅህ ላይ ያለውን እያብቃቃህ ዝም ብለህ ባለህ አትኖርም…..ወዘተ›› ይልሃል።

ድሬቶውን እያመጣ አእምሮህ ላይ ይጭንብሃል። እንደማይቻልና አንተ መሞከር እንደሌለብህ ይነግርሃል። እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ሕይወታቸውን መከላከል ብቻ እንጂ ማጥቃት አያውቁም። ስለዚህ አንተ አንዳንድ ጊዜ ደፈር ብለህ ካልሞከርክ እንዴት ነው ሕይወትህ ሊቀየር የሚችለው? ቁጭ ብለህ ተአምር ሊፈጠር አይችልም። አንተ የምትወደውን ሥራ እቤትህ የተኛህበት ድረስ መጥቶ ማንም ሊሰጥህ አይችልም። ራስህ ተነስተህ መሞከር አለብህ። የተሻለ ነገር በጥረትህና በልፋትህ አግኝተኸው እስኪመጣ ድረስ መሮጥና መታገል አለብህ።

4ኛ. ‹‹ነገሮች ሲስተካከሉ እጀምራለሁ›› የሚለውን አመለካከት ‹‹አሁን እጀምርና በሂደት ነገሮች ይስተካከላሉ›› በሚለው መቀየር

በርካታ ሰዎች የሆነ ነገር ለመጀመር ትክክለኛውን ጊዜ እየጠበቁ ነው። የሚገርመው ነገር ግን ትክክለኛው ጊዜ የሚባል ነገር የለም። ነገር ግን ‹‹ትክክለኛው ሰዓት ላይ ቢዝነሱን እጀምራለሁ፣ ትክክለኛው ሰዓት ላይ ትዳር እይዛለሁ፣ በትክክለኛው ሰዓት እንዲህ… አደርጋለሁ›› ብለው ያቅዳሉ። ‹‹የትራፊክ መብራት ሁሉ አረንጓዴ ካልሆነ፣ መንገዱ ሁሉ ክፍትፍት ካላለ ከቤት አልወጣም›› ካልክ መቼም አትወጣም። ምክንያቱም መብራት ሁሉ አረንጓዴ ሊበራ አይችልም፤ መንገዱም ሙሉ በሙሉ ክፍት ሊሆን አይችልም።

ስለዚህ ትክክለኛው ጊዜ ይምጣ ብለህ ቀጠሮ አትያዝ። ምክንያቱም ትክክለኛው ጊዜ አይመጣም። ትክክለኛ ጊዜ የሚባልም የለም። በሕይወትህ ውስጥ ለምትፈልጋቸው ነገሮች ቀጠሮ መስጠት የለብህም። ቋንቋ መልመድ ከፈለክ መሳሳትን መፍራት የለብህም። መራመድ የሚፈልግ ሰው ብዙ ጊዜ እንደሚወድቅ ማወቅ አለበት። ሕፃናት ቆመው ለመራመድ ጥረት ሲያደርጉ ብዙ ጊዜ ይወድቃሉ። ግን የትኛው ልጅ ነው ‹‹እኔ አሁንስ መውደቁ ደከመኝ›› የሚለው? ሁሉም ልጅ መጀመሪያ ላይ ይጋጫል፤ ይወድቃል መጨረሻ ላይ ግን መራመድ ይችላል።

አንተም ለሚመጣው አደጋ ኃላፊነት ለመውሰድ ዝግጁ መሆን አለብህ። እንደሚሳካለህ እያመንክ ጀምረህ ላይሳካልህ እንደሚችልም ማወቅ አለብህ። ማሸነፍን የመፈለግህን ያህል መሸነፍም እንዳለ ማወቅ አለብህ። ግን ሳላሸነፍ አላቆምም ማለት አለብህ። ለራስህ ቃል መግባት አለብህ። ሜዳው ለጥ ካላለ ጉዞ አልጀምርም አትበል። ሜዳው አቀበትና ቁልቁለት ይኖረዋል። ከፍታና ዝቅታ ይኖረዋል። ሕይወትም እንደዛ ነው። የምፈልገው ነገር ካልተስተካከለና ካልተሟላ አልጀምርም አትበል። ‹‹እጀምራለሁ ያውም አሁኑኑ፤ ከዛ ግን ነገሮች በሂደት ይስተካከላሉ›› በል።

5ኛ. ‹‹ጥሩ እድል የለኝም›› የሚለውን አመለካከት ‹‹ብዙ ስሞክር እድለኛ እሆናለሁ›› በሚለው መቀየር

በእድል ብታምንም በጣም ወሳኙ ነገር ያንተ ልፋትና ጥረት በሕይወትህ ውስጥ ከምታገኛቸው እድሎች ጋር ሲጋጭ ወይ ሲገናኝ የሆነ ተአምር ይፈጥራል። ሳትሞክር ግን እድል የሚባል ነገር የለም። በተኛህበት የሚደርስህ እድል የለም። ሎተሪ እንዲደርስህ እንኳን ሎተሪ መቁረጥ አለብህ። አየህ! ካንተ የሚጠበቀውን አንድ ርምጃ ሳትወስድ የሚቀየር ነገር መጠበቅ የለብህም። አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ ስታደርግ ነው እድል ወደ ሕይወትህ የሚመጣው። ስለዚህ ይህን አመለካከት ከአእምሮህ አውጣው። ጥሩ እድል የለኝም አትበል። ብዙ ስሞክር እድለኛ እሆናለሁ በል።

6ኛ. ‹‹ብዙ ዋጋ ከፍዬበታለሁ፤ መቆም አልችልም›› የሚለውን አመለካከት ‹‹ሁሉንም እንደ አዲስ እጀምራለሁ›› በሚለው መተካት

አንዳንድ ጊዜ በሕይወታችን ውስጥ መሳሳታችንን እያወቅን ‹‹ብዙ ገንዘብ አባክኛለሁ፣ ብዙ ዋጋ ከፍያለሁ፣ ረጅም ዓመት አጥፍቻለሁ፣ ስለዚህ ይህን ነገር አላቆምም›› እንላለን። አንዳንድ ተማሪዎች ሕክምና፣ ሕግ፣ ወይም ምህንድስና ለመማር ዩኒቨርሲቲ ይገባሉ። ከዛ ሁለትና ሶስት ዓመት ይቆዩና በተማሩበት ትምህርት ተመርቀው ሥራ እንደማይሰሩ ይገባቸዋል። እንደማይፈልጉት ይገለጥላቸዋል። ነገር ግን ‹‹እንዴ! ልመረቅ ሁለትና ሶስት ዓመት እየቀረኝ ምን ብዬ ነው የማቆመው፤ ቤተሰብስ ምን ይለኛል›› ይላሉ። ‹‹የምወደውን ልማር ብል እኮ ከዜሮ ልጀምር ነው፤ አይ እንደዛ አላደርግም›› ይላሉ። ስለዚህ እየበሰበሱ፤ ጭቃው ውስጥ እንደገቡ እያወቁት ጉዟቸውን ይቀጥላሉ።

አንዳንድ ጊዜ ‹‹የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም›› የሚለውን አባባል ሕይወታችን ላይ እንተገብረዋለን። ረጅም ጉዞ ስለተጓዝክ ብቻ ወደ ግብህ አትደርስም። ያንተ መድረሻ ወደ ምሥራቅ ሆኖ ወደ ምዕራብ በተቃራኒ አቅጣጫ አስር ዓመት ስለተጓዝክ የምትፈልገበት ቦታ አትደርስም። አየህ! ስህተት በስህተት ሊታረም አይችልም። ግን ደግሞ ረጅም ዓመት የሰራህበትን ሥራ ብታቆም ልትከስር ትችላለህ። ማድረግ ያለብህ ሥራውን ሳታቆም ጎን ለጎን ያን የምትወደውን ነገር ማስኬድ ነው። አዲሱን መንገድ ለመጀመር ቢያንስ ማሰብ መሞከር አለብህ።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 29  ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You