የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ያዘጋጀው የክለቦች ሻምፒዮና ትናንት ተጠናቋል። በውድድሩ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ አጠቃላይ አሸናፊ መሆን ችለዋል። ስምንት ክለቦች በአዋቂና ታዳጊ ስፖርተኞች መሳተፋቸውም ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ በ2017 ዓ.ም ለምታዘጋጀው የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና ብሔራዊ ቡድኑን የሚወክሉ ተወዳዳሪዎች በሻምፒዮናው እንደተመረጡም የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። ውድድሩ ከኅዳር 23/2016 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ላለፉት አምስት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የነበረ። በዚህም በአዋቂዎች ምድብ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲሁም በታዳጊዎች ምድብ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የውድድሩ አጠቃላይ አሸናፊ እና የዋንጫ ተሸላሚ መሆን ችለዋል።
በሻምፒዮናው በሁለቱም ፆታዎች፣ በታዳጊዎችና አዋቂዎች ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታችና ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ ተወዳዳሪዎች የተካፈሉ ሲሆን 82 ወንድና 74 ሴት በድምሩ 156 ስፖርተኞች መሳተፋቸው ተጠቅሷል፡፡
በነጠላ በተደረገው ፉክክር ከ18 ዓመት በላይ ወንዶች ኢዮብ ሲሳይ፣ ደራራ መኮንንና መላኩ በላይ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ1ኛ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ሲፈጽሙ፤ ከ18 ዓመት በላይ ሴቶች እንዲሁ ሜሮን ከንግድ ባንክ 1ኛ፣ ከና ረዘመ ከኦሮሚያ ፖሊስ 2ኛ እና ዮርዳኖስ ንግዴ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ 3ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድራቸውን ፈጽመዋል። ከ18 ዓመት በታች ወንዶች ነጠላ ውድድር ቶማስ አስማማው እና ተመስገን ታከለ ከኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ 1ኛ እና 2ኛ ሆነው ሲያጠናቅቁ፣ ዳንኤል ፀጋዬ 3ኛ ደረጃን በመያዝ ጨርሷል። በተመሳሳይ ነጠላ የሴቶች ከ18 ዓመት በታች ውድድር አርሴማ ለማ፣ ታሪኳ አገኘሁ እና ወርቃለም በየነ ከኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ አጠናቀዋል።
በአፍሪካ ሻምፒዮና ማሰለፍ የሚፈቀደው አምስት ተጨዋች ቢሆንም ኢትዮጵያ አዘጋጅ ሀገር በመሆኗ 7 በነጠላ ወንድ እና 7 በነጠላ ሴት፣ በጥቅሉ 14 ስፖርተኞችን እንደምታሰልፍ ተገልፃል። ለዚህም በውድድሩ የሚሳተፈውን ብሔራዊ ቡድን የሚወክሉ ስፖርተኞች በዚህ ሻምፒዮና እንደተመረጡ ለማወቅ ተችሏል። ለተመረጠው ቡድን ዝግጅት እና መስተንግዶ ኮሚቴ እንደተዋቀረ የተገለጸ ሲሆን ለብሔራዊ ቡድኑ ድጋፎችን በማፈላለግ ጥሩ የሆነ ዝግጅት እንደሚደረግም ታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ አዘጋጅ ሀገር እንደመሆኗ የተሻለ ዝግጅትን አድርጋ ለዓለም ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና የሚያበቃትን ውጤት ለማስመዝገብ ከወዲሁ እየተሠራ እንደሆነም ተጠቁሟል። ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ደረጃ ጥሩ ብትሆንም እንደ አፍሪካ ተፎካካሪ ለመሆን ብዙ ሥራዎች መሠራት እንዳለበትም ተጠቅሷል። በመሆኑም የተሻለ ውጤትን ለማስመዝገብና ቀድሞ ለመዘጋጀት ታስቦ የብሔራዊ ቡድኑ ምርጫው ቀደም ብሎ ሊደረግ ችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ተስፋዬ ብዛ፣ የብሔራዊ ቡድኑን ምርጫ አስመልክቶ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፣ ኢትዮጵያ በመጪው ዓመት የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮናን እና የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤን ታስተናግዳለች። ውድድሩ ሀገር ውስጥ ከመካሄዱ አንጻር ለዓለም ሻምፒዮና ማጣሪያ የሚያበቃ ውጤት ለማምጣት ታቅዶ እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ ተፎካካሪ ለመሆን ብዙ መሠራት የሚያስፈልግ በመሆኑ ሰፊ ዝግጅት ለማድረግ ታስቦ ብሔራዊ ቡዱን መምረጫ ውድድሩ ቀደም ብሎ ሊከወን መቻሉንም ገልጸዋል። ከዚህ በፊት ብሔራዊ ቡድን የሚመረጠው ፌዴሬሽኑ በሚያዘጋጀው አራት ዓይነት ውድድሮች ከ1-5 የሚወጡትን ተወዳዳሪዎች ሰብስቦ እርስ በርስ በማፎካከር እንደነበረ አስታውሰው፣ አሁን ግን ከበጀት እጥረት ምክንያት እነዚህን ውድድሮች በማካሄድ ብሔራዊ ቡድንኑን የመምረጥ እድሉ ጠባብ በመሆኑ በአንድ ውድድር ብሔራዊ ቡድን የሚወክሉ ስፖርተኞችን መምረጥ ግድ እንደሆነ ተናግረዋል። በዚህም መሠረት ጊዜያዊ ብሔራዊ ቡድን በመምረጥ አቅም የሚፈቅድ ከሆነ ቀሪ ውድድሮችን በማካሄድ ብሔራዊ ቡድኑን የሚቀላቀሉ ስፖርተኞች ሊኖሩ እንደሚችሉም ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ስር በየዓመቱ የሚደረጉ የተለያዩ ውድድሮች የሚገኙ ሲሆን ከነዚህም መካከል ፌዴሬሽኑ በጀት ይዞ የሚያወዳድራቸው እና የቴክኒክ ድጋፍ የሚያደርግላቸው ውድድሮች ናቸው። በፌዴሬሽኑ በጀት የሚካሄዱ ውድድሮች አንደኛና ሁለተኛ ዙር የክለቦች ሻምፒዮና፣ የኢትዮጵያ ሻምፒዮና እና ለሁሉም ክፍት የሆነ የግል የበላይነት የማስጠበቅ ውድድሮች ዋንኞቹ ናቸው፡፡
በውድድሩ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ኦሮሚያ ፖሊስ፣ ኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ፣ ፒንግ ፖንግ፣ የኔነህ አዲስ፣ ኦሜድላ እና ወወክማ ተሳታፊ እንደ ነበሩ ተጠቁሟል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ኅዳር 28 ቀን 2016 ዓ.ም