ኢትዮጵያ በማዕድን ሀብት የታደለች ሀገር ናት። ቀደም ባሉት ጊዜያት ይህንን የማዕድን ሀብት አልምቶ ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ እምብዛም አልተሰራም፤ ማዕድናት በጥናት ለመለየት በተከናወነ ተግባር እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በጥናት የተለዩት ማዕድናት 30 በመቶ ብቻ መሆናቸው፣ በሀገሪቱ የማዕድን ጥሬ እቃዎች እያሉ ከውጭ እየገቡ ያሉበት ሁኔታም ይህንኑ ያመለክታሉ። በወርቅ በኩል ከሚታዩ ውስን የማልማት ሥራዎች ውጭ ብዙ ርቀት የተሄደበት ሁኔታ የለም። እሱም ብዙም ባልዘመነ መልኩ ሲካሄድ ነው የቆየው።
መንግሥት በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለማዕድን ዘርፉ የሰጠውን ትኩረት ተከትሎ ግን በዘርፉ ለውጦች እየታዩ ናቸው። ከእነዚህ ለውጦች መካከልም በድንጋይ ከሰል ማዕድን ላይ እየተካሄደ ያለው ልማት ይጠቀሳል። በእዚህ ልማት ሀገሪቱ ባለፈው ዓመት ከውጭ ማስመጣት የነበረባትን የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ መሸፈን ችላለች።
በድንጋይ ከሰል ልማቱ በርካታ ዜጎች በማህበራት ተደራጅተው እየሰሩ ሲሆን፣ የድንጋይ ከሰል ልማቱን በኩባንያ ደረጃ ለማካሄድ ወደ ስድስት የሚደርሱ ኩባንያዎች ፈቃድ ወስደው እየሰሩ ስለመሆናቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ከእነዚህ ኩባንያዎች ውስጥ አንዱ ‹‹ዮ ሆልዲንግ ንግድ እና ማኑፋክቸሪንግ›› የተሰኘው ሀገር በቀል ድርጅት ነው። ድርጅቱ ዮ ሆልዲንግ በተሰኘው ድርጅቱ በማዕድኑ ዘርፍ በመሰማራት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማውጣት ከውጭ የምታስገባውን የታጠበ የድንጋይ ከሰል የሚተካ ምርት ፋብሪካ አቋቁሞ የድንጋይ ከሰል እያመረተ ይገኛል።
የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ያነጋገራቸው የድርጅቱ የአቅርቦት ሰንሰለት ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ፍቅሬ እንዳሉት፤ ‹‹ዮ ሆልዲንግ››፤ የታጠበ የድንጋይ ከሰል ማምረት የሚያስችለውን ፋብሪካ የገነባው በ2014 ዓ.ም ነው፤ ይህ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በከማሼ ዞን በወሪንቃሃ ቀበሌ የተገነባ ፋብሪካ፣ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የድንጋይ ከሰል እጥበት ማከናወኛ ፋብሪካ ነው።
ፋብሪካው የደንበኞችን ፍላጎት መሠረት ባደረገ መልኩ የታጠበ የድንጋይ ከሰል ለሚፈለገው ዓላማ እንዲሆን አድርጎ አምርቶ ማቅረብ የሚችልበት አቅም አለው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ለሲሚንቶ፣ ለብረት፣ ለወረቀት፣ ለሴራሚክ፣ ለጂፕሰም እና ለሌሎች ፋብሪካዎች ግብዓትነት የሚውል የታጠበ የድንጋይ ከሰል በማምረት ለተለያዩ ፋብሪካዎች እያቀረበ ይገኛል ብለዋል።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ የድንጋይ ከሰል የማምረት ሥራውን በቀን ለ16 ሰዓታት እያካሄደ ሲሆን፣ በሰዓት 150 ቶን የድንጋይ ከሰል እያጠበም ይገኛል። ይህ ምርት ካለው ፍላጎት አኳያ በቂ ስላልሆነ የሚያመርተውን የታጠበ የድንጋይ ከሰል መጠን በእጥፍ የሚያሳድጉ ሥራዎችን እየሰራ ነው። ለእዚህ የሚያስፈልጉ እቃዎች ከውጭ እንዲገቡ እየተደረገ ነው።
ፋብሪካው ወደ ሥራ የገባው ከሁለት ዓመት በፊት መሆኑን አቶ ቴዎድሮስ ጠቅሰው፣ በአካባቢው በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በሚፈለገው ፍጥነት ወደ ሥራ ለመግባት እንዳልቻለ አሁን ግን ወደ ማምረት ሥራው መግባቱን ይናገራሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ ድርጅቱ ፋብሪካ ያቋቋመበት አንዱ ዋና ዓላማ በሥሩ ላሉት ብዙ ፋብሪካዎች ለግብዓትነት የሚያስፈልገውን የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ ለማምረት ነው። ካሉት ፋብሪካዎች ውስጥ አንዱ ‹‹ኢሲኤንድ ኢ›› የተሰኘው የብረት ማምረቻ ፋብሪካ ሲሆን፤ ለፋብሪካው የሚሆነው ጥሬ እቃ ግብዓት ከውጭ በማስመጣት እና በማቅለጥ የተለያዩ ፌሮዎችን ሲያመርት ቆይቷል።
የታጠበ ድንጋይ ከሰል የማምረቱ ሥራ የድንጋይ ከሰሉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ውጪን ስለሚጠይቅ በዚህ ዙሪያ የሚያጋጥመውን ተግዳሮት ለመፍታት ግብዓቱን ሀገር ውስጥ በማምረት ብረት ከውጭ ማስገባት ለማቆም በማሰብ የተገባበት ነው።
በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በብረት ማዕድን ፍለጋ ላይ በሰፊው ተሰርቶ እንደነበር ጠቅሰው፣ ይህም የፍለጋ ሂደት ብረት ከብረት ማዕድን አፈር ለማምረት ያለመ ነበር ይላሉ። ማዕድን ለማምረት ደግሞ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ያስፈልጋል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ብረቱን ከአፈር ለመለየት በሚደረገው የማቅለጥ ሂደት ከፍተኛ መጠን ያለው ኃይል ስለሚያስፈልግ አሁን ባለው የመብራት ኃይል ይህን ማዕድን ለማቅለጥ የሚታሰብ አይሆንም ሲሉ ይገልጻሉ። ስለዚህ ይህንን ኢነርጂ ሊተካ የሚችለው ብቸኛው ኃይል የድንጋይ ከሰል ነው። ብረትን እያቀለጡ ወደሚፈለገው ምርት ለመቀየር የሚቻለው በድንጋይ ከሰል ኃይል አማካኝነት ነው ሲሉ ያብራራሉ።
ድርጅቱ ወደ ድንጋይ ከሰል ማጠብ ሥራ የተሰማራበት ሌላው ዋንኛ ምክንያት ወደፊት እንደ አፍሪካም ሆነ እንደ ሀገር ትልቅ ኩራት የሆነ ከብረት ማዕድን የተለያዩ ብረቶችን ማምረት ላይ ለመስማራት በመፈለጉ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለዚህ ወሳኝ የሆነው ድንጋይ ከሰል ስለሆነና ያለሱ ምንም መሥራት ስለማይቻል ነው ብለዋል።
በሀገራችን ያለው የድንጋይ ከሰል መረጃ በቅርቡ ያለውን የሚያሳይ እንደሆነ የሚጠቁሙት አቶ ቴዎድሮስ፤ የድንጋይ ከሰል ባሕርያት ጥልቅ መሆናቸውን ይናገራሉ። ለዚህም ድርጅቱ ከህንድ፣ ከደቡብ አፍሪካና ከተለያዩ ሀገራት ባለሙያዎችን በማስመጣት በድንጋይ ከሰል ክምችት ዙሪያ ጥናት ማካሄዱንም ይገልጻሉ። በተደረገው ጥናት መሠረትም በኢትዮጵያ ያለው የድንጋይ ከሰል የማቃጠል አቅም ብረትን ለማቅለጥ ከፍተኛ አቅም ያለው መሆኑ መታወቁንም ተናግረዋል።
ይህ የድንጋይ ከሰል ከተመረተ በኋላ እላይ ያሉትን የተለያዩ ኬሚካሎች በመቀነስ ኃይል መጨመር እንደሚቻል አስታውቀዋል፤ የድንጋይ ከሰል ከተመረተ በኋላ በማጠብ የማቃጠል ኃይሉ ከፍተኛ የሆነ የድንጋይ ከሰል ማግኘት እንደሚቻል አመልክተው፣ ወደ ድንጋይ ከሰል ማጠብ ሥራው የተገባውም ለእዚህ መሆኑን ገልጸዋል።
‹‹ፋብሪካው የታጠበ የድንጋይ ከሰል አምርቶ ለፋብሪካዎች ማቅረብ መቻሉ ድርጅቱ በቀጣይ ኢንቨስት አደርግበታለሁ ብሎ ወደያዘው ብረት የማምረት ትልቅ ኢንቨስትመንት ለመግባት የሚያስችለውን ሥራ ከወዲሁ እንደጀመረ የሚያሳይ ነው›› ብለዋል፤ አሁን የታጠበ የድንጋይ ከሰል ምርቱን በዋነኝነት ተጠቃሚ ለሆኑት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች እያቀረበ እንደሆነም ተናግረዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ፋብሪካው በተገነባበት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከማሼ አካባቢ በርካታ የድንጋይ ከሰል ክምችት መኖሩ ተረጋግጧል፤ ከዚህ ክልል አዋሳኝ በሆነው የኦሮሚያ ክልል በወለጋ አካባቢም እንዲሁ ብዙ ክምችት አለ። በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተደረገ አሰሳ 50 ሚሊዮን ቶን የሚሆን የድንጋይ ከሰል ክምችት እንዳለ ለማወቅ ተችሏል።
ከማዕድን ሚኒስቴር የተገኘን መረጃ ዋቢ አድርገው አቶ ቴዎድሮስ እንደተናገሩት፤ የድንጋይ ከሰል ከውጭ ለማስገባት ከ200 እስከ 300 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ ከፍተኛ ወጪ ነው። ፋብሪካው ኢትዮጵያ ከሚያስፈልጋት የታጠበ የድንጋይ ከሰል 50 በመቶ ያህሉን ለማሟላት እየሰራ ይገኛል። ሀገር ሰላም ከሆነች ይህንን ብቻ ሳይሆን፣ በርካታ እቅዶችን ማሳካት ይቻላል ብለዋል።
ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ዓይነት የድንጋይ ከሰል አለ፤ በኢትዮጵያ ‹‹ሰብ ቢትመስ›› እና ‹‹ቢትመስ›› የሚባሉት የድንጋይ ከሰሎች በብዛት ይገኛሉ። ‹‹ቢትመስ›› የተሰኘው የድንጋይ ከሰል ዓይነት የማቃጠል አቅም 5ሺ ካሎሪ ወይም ቢበዛ ደግሞ ከ6ሺ ካሎሪ አይበልጥም። ከውጭ የሚገባው ‹‹አንትራሳይት›› የሚባለው የድንጋይ ከሰል ዓይነት የማቃጠል አቅሙ ከፍተኛው ከ7ሺ ካሎሪ በላይ የሆነ ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ከ5ሺ ካሎሪ በላይ የማቃጠል አቅም ያለው የድንጋይ ከሰል የሚጠቀም ኢንዱስትሪ እንደሌለም ጠቅሰው፣ 7ሺና ከዚያ በላይ ካሎሪ የማቃጠል አቅም ያለው የድንጋይ ከሰል የሚጠቀመው ኢንዱስትሪ በጣም ግዙፍ ኢንዱስትሪ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህም ደረጃ ኢትዮጵያ ውስጥ የተዋቀረ ኢንዱስትሪ የለም ይላሉ።
አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ኃይል የሚፈልጉት ሴራሚክና ሲሚንቶ አምራች ፋብሪካዎች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ እነርሱም ከ5ሺ በላይ ካሎሪ የማቃጠል አቅም ያለው የድንጋይ ከሰል እንደማይፈልጉም ተናግረዋል። ፋብሪካውም ይህንን ኃይል በሀገር ውስጥ በማምረት ለፋብሪካዎች እያቀረበ ይገኛል ብለዋል።
ፋብሪካው የታጠበ የድንጋይ ከሰል ምርቶች እያመረተ ለገበያ እያቀረበ ቢሆንም የገበያ ትስስሩ ከጸጥታ ጋር የተያያዙ ችግሮች እያጋጠሙት መሆናቸውንም አቶ ቴዎድሮስ ጠቁመዋል፤ ድርጅቱ ምርቶቹን ለፋብሪካዎች ለማድረስ ባሉት የትራንስፖርት አማራጮች በመጠቀም ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሌላ ተጨማሪ የጭነት አገልግሎት የሚሰጡ ትራንስፖርት አገልግሎቶች እንደሚያስፈልጉም ገልጸዋል።
ይህንን የጭነት አገልግሎት የሚሰጡ የትራንስፖርት አቅራቢዎች ፋብሪካው ባለበት አካባቢ ለመድረስ የጸጥታ ጉዳይ ስጋት ሆኖባቸው መቆየቱን አቶ ቴዎድሮስ ጠቅሰዋል። እንዲያም ሆኖ ችግሩን በመጋፈጥ ለመሥራት የሚፈለጉትም ከገበያ ዋጋ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የትራንስፖርት ታሪፍ እንደሚጠይቁ አመልክተዋል። ይህ ችግር ምርቱ በሚፈለገው ጊዜና በወቅቱ ለደንበኞች ለማቅረብ እንቅፋት መሆኑን ጠቅሰው፤ እስካሁን ድርጅቱ ብዙ ችግሮችን ችሎ ገበያውን ለማርካት ብቻ እየሰራ እንደሆነም ይናገራሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ ከተወሰኑ ፋብሪካዎች ጋር ባለው የውል ስምምነት መሠረትም ምርቶቹን እያቀረበ ነው። ፋብሪካው ባለፈው ዓመት ደንበኞቹ ሀገር ውስጥ በሚመረተው የታጠበ የድንጋይ ከሰል ምርት ያላቸው እርካታ ምን ያህል እንደሆነ ለማረጋገጥ ይሰራል። አሁን እየተገነቡ ካሉ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ጋርም ኮንትራት በመግባት ምርቶቹን ለማቅረብ እየሰራ ነው።
ፋብሪካው ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠሩንም ጠቅሰው፣ 250 ቋሚ ሠራተኞች እንዳሉትም ጠቁመዋል። በማህበር ተደራጅተው ከድርጅቱ ጋር ለሚሰሩ 700 ተጨማሪ ዜጎችም ጊዜያዊ የሥራ እድል መፈጠር ችሏል ብለዋል።
በዘርፉ ልማት በጣም የላቁ የሚባሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እንዳሉም ጠቅሰው፣ እነዚህን ቴክኖሎጂዎች ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት እጅግ በጣም ጥራቱን የጠበቀ የድንጋይ ከሰል በማምረት ለደንበኞች ለማቅረብ ድርጅቱ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አቶ ቴዎድሮስ ጠቁመዋል። አዲስ ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እንደሚጠይቅ ተናግረው፣ ይህን እቅዱን ለማሳካት ከመንግሥት ድጋፍ በመጠየቅ ከልማት ባንክ ብድር ለማግኘት በሚያስችል ሂደት ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል። ይህ እውን ከሆነ ኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፉ በተለይ በድንጋይ ከሰል ልማት በአጭር ጊዜ ውስጥ አሁን ካለችበት ደረጃ መላቀቅ እንደምትችልም ገልጸዋል።
አቶ ቴዎድሮስ እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ ያለው የድንጋይ ከሰል ክምችት በብዛቱ ብቻ ሳይሆን በአቀማመጡና ሂደቱ ከሌሎች ሀገራት ይለያል፤ በተለይ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚገኘው የድንጋይ ከሰል ውፍረቱ በራሱ ልዩ ነው።
አሁን በማዕድን ዘርፉ ከተሰማሩት አብዛኞቹ ባሕላዊ የማዕድን አማራቾች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የዘርፉ ልማት ከባህላዊ አሰራር ወጥቶ በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን ለማድረግ በማዕድን ልማት ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚጠበቅ አመላክተዋል። ይህንን በመቀየር ትኩረት ተሰጥቶ ከተሰራ በሀገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ እምርታ ማምጣት ይቻላል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ የድንጋይ ከሰል በማውጣት ሂደቱ ላይ ከፍተኛ የእውቀት ክፍተቶች እንዳሉም አቶ ቴዎድሮስ ጠቁመዋል፤ በመንግሥት በኩል በተለያዩ ዘዴዎች የእውቀት ክፍተቶችን ለመሙላት ጥረት መደረግ እንዳለበት ተናግረው፣ ይህ ካልሆነ የምርት ብክነት እንደሚከሰት፣ ትርፋማና ውጤታማ ሥራ ለመሥራት እንደማይቻልና አቅራቢዎችም እንዲዳከሙ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ነው ያመለከቱት። ችግሩ ዘርፉን ለማዘመን የሚደረገውን ሂደትም አዳጋች ያደርገዋል ነው ያሉት። የድንጋይ ከሰል ሥራ የድንጋይ ከሰል ፈቃድ ከመስጠት ጀምሮ ማዕድኑ እስከ ማውጣት ሂደት እና የመሳሰሉት እያንዳንዳቸው ሂደቶች በእውቀት መመራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
‹‹አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመን የሀገር ውስጥ የድንጋይ ከሰል ፍላጎትን አሟልተን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ትኩረት አድርገን መሥራት አለብን›› ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፣ የድንጋይ ከሰል አቅርቦትን በተመለከተ ያሉት የእውቀት ክፍተቶች ፣ ማዕድን የሚወጣበት መንገድ፣ በክልሎች በኩል ያለው የማዕድን ማውጫ መሬት አቅርቦት እና የጸጥታ ችግሮች ከተስተካከሉ የድንጋይ ከሰሉን በጥሩ ሁኔታ ማም ረት ይቻላል›› ብለዋል።
በአጠቃላይ በማዕድን ዘርፉ ላይ በመንግሥት በኩል የእውቀት ሽግግር ሥራዎች መሥራት እንዳለባቸው፣ ቴክኖሎጂን መጠቀም እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፣ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑንም አመልክተዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ኅዳር 28 ቀን 2016 ዓ.ም