የአየር ኃይሉ አሁናዊ ቁመና የመከላከያ ሪፎርም ስኬት ማሳያ ነው!

 ሀገራችን ዘመናዊ የጦር ኃይል መገንባት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ በዋነኛነት ከሚጠቀሱት የጦሩ ክፍሎች አንዱ የኢፌዴሪ አየር ኃይል ነው። አየር ኃይሉ ከተመሠረተበት ከኅዳር 20 ቀን 1928 ዓ.ም. ጀምሮ የሀገርን የአየር ድንበር ከመጠበቅ አንስቶ በተለያዩ የውጊያ ዓውዶች ከፍተኛ ጀብዱዎችን በመፈጸም ለሀገርና ለሕዝብ የኩራት ምንጭ የሆነ ተቋም ነው።

ከምሥረታው እስከ 1942 ዓ.ም በንጉሡ ቀጥታ አመራር በስውዲናዊዎቹ ጄኔራል ሐርድና ካውንት ቮን ሮዛን (ኮሎኔል) አማካሪነት ሥራውን የጀመረው አየር ኃይሉ፤ ከምስረታው ማግስት ጀምሮ በሙያው አንቱታ ባተረፉ እንደ ሜ/ጄ አሰፋ አያና፣ ሜ/ጄ አበራ ወ/ማርያም፣ ሜ/ጄ ፋንታ በላይ እና ሜ/ጄ አምሐ ደስታ የተመ ራ ባለብዙ ገድል ተቋም ነው።

የአየር ኃይሉ ከሀገር ውስጥ ግዳጅ ባለፈ በዓለም አቀፍ የሠላም ማስከበር ሥራዎች ላይ በመሳተፍ አንቱታን ያተረፈ ነው ። ለዚህም በ1960 ዓ.ም በአራት ኤፍ 86 አውሮፕላኖች በፍላይት ደረጃ ኮንጎ ዛየር በተደረገው የሠላም ማስከበር ሥራ ላይ በቀዳሚነት ተሳትፏል። 2000 ዓ.ም ዳርፉር ሱዳን (UNAMID በአቭዬሽን የሠላም ማስከበር ዩኒት በአምስት ሚ-35 ተዋጊ ሄሊኮፕተሮች ከተሟላ የጥገና አቅምና የድጋፍ መሣሪያዎች ጋር ተሰማርቷል። በአብየና ሩዋንዳ የሎጅስቲክና ጦር ማዘዋወር ግዳጆችን በብቃት መወጣቱን መጥቀስ ይቻላል ።

የቀድሞው የሶማሊያ አምባገነናዊ መሪ ዚያድ ባሬ በምሥራቁ የሀገራችን ክፍል የከፈተውን የመስፋፋት ጦርነት በብቃት በታላቅ ተጋድሎ ለመከላከል በተደረገው ጦርነት አየር ኃይሉ ከፍ ባለ ብቃት የፈጸማቸው ጀብዱዎች የሀገሪቱን ሉዓላዊነት በማስጠበቅ ሂደት የጎላ ስፍራ ከመያዝ ባለፈ፣ ተቋሙና ባለሙያዎቹ የብዙ ጀብዱ ትርክቶች ባለቤት እንዲሆኑ አድርጓቸዋል ።

የአየር ኃይሉ እንደ ሌሎች ሀገራዊ ተቋማት ላለፉት ስድስት አስርተ ዓመታት በተለያዩ ውጣ ውረዶች ውስጥ ለማለፍ የተገደደባቸው አጋጣሚዎች ተፈጥረዋል፤ እንደ አጀማመሩ መቀጠል የሚያስችለውን እድል ማግኘት ሳይችል በመቅረቱም ፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሀገሪቱን እና ሕዝቦቿን የሚመጥን ቁመና ሳይላበስ ቀርቷል ።

ይህንን የተቋሙን ገጽታ ለመቀየር የለውጥ ኃይሉ ወደ ሥልጣን ከመጣ ማግሥት ጀምሮ ሰፊ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። በሀገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት ላይ ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት ታስቦ የሚተገበረው የመከላከያ ሪፎርም አካል የሆነው፤ የመንግሥት ጥረት በርግጥም በተቋሙ ላይ ለውጥ እያመጣ ስለመሆኑ በየዕለቱ በተጨባጭ መታዘብ እየቻልን ነው።

የአንድ ሀገር ሉዓላዊ የአየር ክልል መጠበቅ ውስብስብ እየሆነ በመጣበት በዚህ ዘመን፤ መንግሥት አየር ኃይሉን በሁሉም መስክ ብቁ በማድረግ ለሀገርና ለሕዝብ የኩራት ምንጭ እንዲሆን ከፍያለ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀሱ፣ የተቋሙ አመራሮችም አጋጣሚውን በአግባቡ በመጠቀም ተቋሙ ዘመኑን የሚመጥን/የሚዋጅ ለማድረግ በተነቃቃ መንፈስ እየሄዱበት ያለው መንገድ፤ ሀገርን እንደሀገር የማጽናት ተልዕኮ አካል ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

በአሁን ወቅት አየር ኃይሉን በትጥቅ ከማዘመን አንስቶ ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች እንዲደራጅ የተደረገው ጥረትና በተጨባጭ እየተገኘ ያለው ስኬት፤ የሀገርን ሉዓላዊነትና የሕዝባችንን ሰላም በተሻለ መልኩ ለማስጠበቅ የሚያስችል አስተማማኝ አቅም መፍጠር ያስቻለ ነው፤ ቀደም ሲል ሕዝባችን ስለተቋሙ ባለጀብዱ ባለሙያዎች የነበረውን ከበሬታ መመለስ የሚያስችል ነው ።

ከዚህም ባለፈ በልማት ድህነትን ለማሸነፍ ለጀመርነው መነቃቃት ስኬት፤ እንደ ሀገር መፍጠር የሚገባንን በራስ መተማመን እውን ለማድረግ፤ ለወዳጆቻችንም ሆነ ለጠላቶቻችን በኛ እና በእኛ ጉዳይ የሚኖራቸው እይታ የተስተካከለ እንዲሆን ትልቅ መልእክት ማስተላለፍ የሚያስችል የዛሬ ስኬታችን አንዱ ገጽታ ነው!

አዲስ ዘመን   ኅዳር 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You