በምርት አሰባሰብ ሂደት፣ መዘናጋት እንዳይፈጠር!

 ግብርና የአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሕይወት መሠረት ነውና ስለግብርናው ዘርፍ ደግሞ ደጋግሞ ማውራት ተገቢም አስፈላጊም ነው:: በተለይም፣ በአብዛኞቹ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከፍተኛው ዓመታዊ የግብርና ምርት የሚገኝበት፣ የመኸር እርሻ ምርት ስብሰባ ሥራ በሚከናወንበት በአሁኑ ወቅት ስለግብርናው መጠየቅና መከታተል እጅግ አስፈላጊ ነው:: የግብርናው ዘርፍ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ መሠረት ስለሆነ የዚህ ወሳኝ ዘርፍ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ትኩረት ይፈልጋል::

የግብርና ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው መረጃ፣ ከ2015/16 የመኸር እርሻ 513 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል:: ታዲያ ይህን እቅድ ለማሳካት የምርት አሰባሰብ ሥራን በከፍተኛ ጥንቃቄና ትጋት ማከናወን ያስፈልጋል:: በምርት አሰባሰብ ወቅት የሚፈጠሩ ችግሮች ከፍተኛ የምርት ብክነት እንዲከሰት ያደርጋሉ:: የምርት ብክነት መከሰት ደግሞ በኅብረተሰቡና በሀገሪቱ ላይ ተራዛሚ ተፅዕኖዎችን የሚያስከትሉ ችግሮችን ይፈጥራል:: የምርት አሰባሰብ ሥራ ተገቢ ትኩረት ተሰጥቶት በሚገባ ካልተከናወነ፣ የምርት እጥረት እንዲፈጠርና የዋጋ ንረት እንዲከሰት ምክንያት መሆኑ አይቀርም::

ሀገሪቱ ከበቂ በላይ የምታመርታቸው ምርቶች ጭምር ዋጋቸው ሰማይ ነክቶ በተደጋጋሚ እንታዘባለን:: ለአብነት ያህል የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ከበቂ በላይ ተመርተው ከማሳ የሚያነሳቸው አጥተው ለብክነት እንደሚዳረጉ የምርቶቹ ባለቤቶች ሲናገሩ ደግመን ደጋግመን ሰምተናል:: በከተሞች ያለው የእነዚህ ምርቶች ዋጋ ግን ‹‹ጆሮ አይስማ›› የሚያሰኝ ነው::

የአትክልትና ፍራፍሬ ዋጋ ለማሳያነት ያህል ተጠቀሰ እንጂ በሌሎቹም ምርቶች ላይ ተመሳሳይ ችግር መከሰቱ አይቀርም:: የዚህ ችግር ስር ቢመዘዝ የምርት አሰባሰብ ድረስ እንደሚደርስ አያጠራጥርም:: አሁን ባለው ከፍተኛ የዋጋ ንረት ላይ ተጨማሪ የዋጋ ንረት ከተፈጠረ የኅብረተሰቡ የኑሮ ፈተና “ከድጡ ወደ ማጡ” ይሆናልና ለምርት አሰባሰብ ትኩረት በመስጠት ተጨማሪ ችግር እንዳይፈጠር መትጋት ይገባል::

የምርት ስብሰባ ሥራው ምርትን ሰብሰቦ በጥንቃቄ ለፍጆታም ይሁን ለገበያ የማቅረብ ተግባርን ያካተተ እንዲሆን ጥረት ማድረግ ይገባል:: ይህን በማድረግ እያደገ ለመጣው የምግብና የገበያ ፍላጎት በጊዜ እና በጥራት ተወዳዳሪ የሆነ ምላሽ መስጠት እንዲሁም ጥራቱን የጠበቀ በቂ የሰብል ምርት ማቅረብ እና ዋና ዋና የምግብ ሰብሎች ለዘላቂ የግብርና ልማት ያላቸውን ሚና ማሳደግ ይቻላል::

የምርት ብክነትን ከሚቀንሱ ዘዴዎች መካከል አንዱ፣ ምርትን በዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያ መሳሪያዎች መሰብሰብ ነው:: ይህ ግብርናውን በቴክኖሎጂ የማዘመን ተግባር የግብርናውን ዘርፍ በማሳደግ ሀገሪቱ የግብርና አቅሟን በመጠቀም ከድህነት እንድትላቀቅ ለማድረግ ከሚቀርቡ ምክረ ሃሳቦች መካከል አንዱ ነው::

በተለይ ትርፍ አምራች በሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች ዘመናዊ የማጨጃና የመውቂያ ማሽኖችን የሚያገኙባቸውን አሠራሮችን መዘርጋት እጅግ አስፈላጊ ነው:: ይህን አሰራር በመተግበር የምርት ጥራትን መጨመርና ብክነትን መቀነስ ይቻላል::

የምርት ብክነት እንዳይፈጠር ከሚደረገው ጥረት ባሻገር፣ የደረሱ ሰብሎች ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሹም መትጋት ያስፈልጋል:: የብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩትም በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊከሰት ስለሚችል አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን እንዲሰበስብ አሳስቧል::

አንዳንድ ክልሎችም ተማሪዎች በምርት ስብሰባ

 ሥራ ላይ እንዲሳተፉ የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ተግባራዊ አድርገዋል:: እንዲህ ዓይነቶቹ ተገቢ ውሳኔዎች የመኸር እርሻ ምርት በሚሰበሰብባቸው በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ሊተገበሩ ይገባል:: ሰብሎች ከታጨዱ በኋላም በፍጥነትና በጥንቃቄ ወደ አውድማ እንዲገቡ መደረግ አለበት::

በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል:: በመንግሥትና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ትብብር በተተገበሩት ተከታታይነት ያላቸው የግብርና ልማት እንቅስቃሴዎች የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብት ያሳደጉና የሕዝቡን፣ በተለይም የአርሶ አደሩን፣ ሕይወት ያሻሻሉ ውጤቶች ተመዝግበዋል::

ከግብርና የሚገኘው ምርት በየዓመቱ ጭማሬ አሳይቷል፤ ቁጥሩ ቀላል የማይባል የህብረተሰብ ክፍልም ከድህነት መላቀቅ ችሏል:: የግብርናና ገጠር ልማትን ለማሻሻል የተወሰዱ ርምጃዎች ብዙ ባለሀብት አርሶ አደሮችን መፍጠርም ችለዋል::

ይሁን እንጂ እነዚህ ተግባራት ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ካላት አቅም አንፃር ሲመዘኑ ለሀገሪቱ የምግብ ዋስትና፣ የሥራ እድል ፈጠራና የምጣኔ ሀብት እድገትም ሆነ ለዘርፉ ችግሮች አስተማማኝ መፍትሔ የሰጡ አይደሉም:: አሁንም ግብርናው በዘላቂነት ከኋላቀር አስተራረስና ከዝናብ ጥገኝነት አልተላቀቀም፤ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በብዛት ከመጠቀም የራቀ ሆኖ ይታያል::

ሚሊዮኖች ከድህነት ወለል በታች እየኖሩ ነው:: በአጠቃላይ የምጣኔ ሀብት መዋቅራዊ ለውጥን እስካሁን ድረስ እውን ማድረግ አልተቻለም:: የምርት አሰባሰብን ጨምሮ በሌሎች የግብርናው ዘርፍ ስኬት ግብዓቶች ላይ የሚስተዋለው የትኩረት እጥረት እስካሁን በዘርፉ የተገኙ ውጤቶችን ወደኋላ እንዳይመልሳቸው ያሰጋል::

ወቅቱ በአብዛኞቹ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመኸር እርሻ ምርት የሚሰበሰብበት ጊዜ በመሆኑ፣ ዋናው ሀገራዊ ትኩረት የምርት አሰባሰብ ሊሆን ይገባል:: የምርት አሰባሰቡ ዕለታዊ ክትትል ይፈልጋል፤ የጎደለውን መሙላት፤ የተበላሸውን ማስተካከል ያስፈልጋል::

ኢትዮጵያ ለብዙ ሰብሎች ተስማሚ ሥነ-ምህዳር ያላት ቢሆንም የሰብሎቹ ምርታማነት በሚፈለገው ደረጃ አለማደጉ፣ የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ፈታኝ አድርጎታል:: ይህን ችግር ለማቃለል ከሚያስችሉ የመፍትሔ አማራጮች መካከል አንዱ ለምርት አሰባሰብ ሥራ ተገቢው ትኩረት መስጠት ነው::

የመኸር እርሻ ምርት ስብሰባ ሥራ የሚከናወንበት በዚህ ወቅት አርሶ አደሩ፣ የልማት ጣቢያ ሠራተኛው እንዲሁም አመራሩ ሁሉ ወደ ማሳ ዘልቆ ደፋ ቀና ማለት አለበት:: አርሶ አደሩ ምርቱን ይሰብስብ፤ የልማት ጣቢያ ሠራተኞች ሙያዊ/ቴክኒካዊ ድጋፍ ያድርጉ፤ አመራሩ ደግሞ ከአርሶ አደሩና ከባለሙያዎች በሚቀርቡ ጥያቄዎች መሠረት የጎደለው እንዲሟላ ትዕዛዝ ይስጥ፤ ክትትል ያድርግ!።

ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ እስከ አጨዳና ድህረ ምርት አያያዝ ድረስ ለሰብሎች ሊደረግ ስለሚገባው ጥንቃቄ በግብርና ሚኒስቴር የብርዕና አገዳ ሰብሎች አመራረት ኤክስቴንሽን ማኑዋል ላይ በዝርዝር ተብራርቷል:: የልማት ጣቢያ ሠራተኞች ይህን የምርት አመራረት መመሪያ ከአርሶ አደሩ ልምድና ተሞክሮ ጋር በማቀናጀት እንዲተገበር በብርቱ መትጋት ይኖርባቸዋል::

የግብርናው ዘርፍ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ስለሆነ የዚህ ወሳኝ ዘርፍ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ትኩረት ይፈልጋል:: ይህ ዘርፍ ለአፍታም ቢሆን ትኩረት ሊነፈገው አይገባም:: ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ግብርና ዘንግተው መኖር አይችሉም:: ቢያንስ፣ ለዓመታት የተመኘነው ‹‹ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ›› እውን እስከሚሆን ድረስ ግብርናውን ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት አንችልም!

 ፒያንኪ ዘኢትዮጵያ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You