ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ህይወት ውስጥ ትልቅ ስፍራ ያለው ፤ በሀገረ መንግሥት ምስረታ ሆነ ፣ ሀገረ መንግሥቱን በማጽናት የዘመናት ታሪክ ውስጥ ሰፊ ታሪክ የጻፈ ነው። ሃይማኖቱ ያጎናጸፉትን መንፈሳዊ እሴቶች ፤ ይዟቸው ከዘለቃቸው ባህላዊና ማኅበራዊ እሴቶች ጋር በማስተሳሰር ለራሱ ፣ ለማኅበረሰቡና ለሀገሩ የሚተርፉ ትውልድ በመፍጠር ፤ ሀገር እንደሀገር ዛሬ ላይ እንድትደርስም የነበረውና ዛሬም ያለው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ነው።
እንደ ሀገር ከመጣንበት ረጅም ዘመንና ዘመናቱ ከፈጠሯቸው የተለያዩ ትርክቶች አንጻር የራሱ ጥያቄዎች የነበሩት ፣ ለጥያቄዎቹ ምላሽ ለማግኘትም ሰላማዊ ትግሎችን በማካሄድ ፣ ለችግሮቹ መፍትሔ በማፈላለግም የሚጠቀስ ነው።
በሀገሪቱ ሕገመንግሥት የተደነገገው የሃይማኖት ነጻነት በመጠቀም፤ በግለሰብ ሆነ በማኅበረሰብ ማንነት ግንባታ ውስጥ ኃላፊነት የሚሰማው ትውልድ ለመቅረጽ ለሚደረገው ሀገራዊ ጥረት ሃይማኖቱ ፣ የሃይማኖት ተቋማቱ እና ምእመናኑ እያደረጉት ያለው ጥረት እውቅና የሚሰጠው ነው።
በተለይም በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ዘንድ ከለውጡ ቀደም ባለው ጊዜ የነበረውን ጭቆና እንደ ማኅበረሰብም ሆነ እንደ ሀገር ሲያስከፍለን የነበረውን ያልተገባ ዋጋ ለማስቀረት መንግሥት የጀመረውን የሰላም ጥረት ተቀብለው ያስመዘገቡት ስኬት የሚበረታታ ነው።
ፍቅር ፣ ሰላም እና አንድነት የየትኛውም ሃይማኖት አስተምሮ ዋንኛ ማጠንጠኛ እንደሆኑ ይታመናል። ከዚህ የተነሳም እነዚህን መንፈሳዊ እሴቶች ታሳቢ አድርገው ለሚዘረጉ እጆች አዎንታዊ ምላሽ መስጠት ለአስተምህሮው ተገዥና ብቁ ሆኖ የመገኘት አንዱ ማሳያ ነው።
ሙስሊሙ ማኅበረሰብም በተለያዩ ገፊ ምክንያቶች ገብቶበት ከነበረው መከፋፈል ወጥቶ አሁን ላይ ወደ አንድ የሚያመጣው መንገድ ላይ መቆሙም ሆነ ፤መንገዱን አማራጭ የሌለው አድርጎ መቀበሉ ለሃይማኖታዊ አስተምሮው ያለውን ተገዥነት ያመላከተ ነው።
ከሁሉም በላይ ችግሮችን /ልዩነቶችን ሃይማኖታዊ አስተምሮው በሚያዘው መንገድ በሰላማዊ መንገድ ቁጭ ብሎ በመነጋገር ለመፍታት የሄዱበት መንገድና የተገኘው አበረታች ውጤት እንደሀገር ለጀመርነው በንግግር ችግሮችን የመፍታት አዲስ ባህል ጥሩ መማሪያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
የትኛውም ችግር በየትኛውም መልኩ አቅም አግኝቶ የገዘፈ ቢመስልም፤ ከባለ ጉዳዩ /ባለቤቱ ሊበልጥ የሚችለው ፤ በሰከነ መንፈስና ፣ በተረጋጋ አእምሮ ቁጭ ብሎ ማየት የሚያስችል አቅም ሲታጣ ብቻ መሆኑን በተግባር ያሳየ ፤ ለሌሎች አሁነኛ ተመሳሳይ ችግሮች እንደ ማሳያም የሚወሰድ ነው።
መንግሥትም በሙስሊሙ ማኅበረሰባችን ዘንድ ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት በሰላማዊ መንገድ በራሳቸው አቅም እንዲፈቱ አስቻይ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ያደረገው ጥረት ከፍያለ ከበሬታ ሊሰጠው የሚገባ ነው። ለተገኘው ስኬትም ትልቅ አቅም ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
ሙስሊሙ ኅብረተሰብ በለውጡ የተገኘውን ችግሮች በሰላማዊ መንገድ በውይይት የመፍታት ዕድል እንዲጠቀም መድረኮችን ከማመቻቸት ጀምሮ፤ በመካከላቸው መተማመን እንዲፈጠር የተጓዘበትም ርቀት የለውጡ አንድ ትሩፋት ተደርጎ ሊወሰድ የሚ ገባው አዲስ ልምምድ ነው።
የእስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት ሕጋዊ ሰውነት እንዲያገኝ የሚያስችል አዋጅ መጽደቁ፤ የእስልምና እምነት መርህን የተከተለ የፋይናንስ ተቋም እንዲቋቋም መደረጉ ፤ የሃይማኖቱ ተከታዮች የማምለኪያ ስፍራዎች እንዲያገኙ በመንግሥት በኩል የተደረገው ጥረት መንግሥት ለሃይማኖት ተቋማት ዕድገትና ለሰላማዊ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ያለውን ቁርጠኝነት ያመላከተ ነው።
መንግሥት በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ውስጥ የተፈጠረውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ካደረገው ጥረት ጎን ለጎን በማኅበረሰቡ ለሚነሱ የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የሄደበት ርቀትና፤ ምላሾቹ በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ውስጥ የፈጠሩት መነቃቃት ፤ እንደ ሀገር ለጀመርነው አዲስ ተሻጋሪ ትርክት ግብአት ሆኖ ሊያገለግል የሚችል ተጨባጭ ተሞክሮ ነው።
ከዛም ባለፈ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ቀደም ባለው ጊዜ በሀገረ መንግሥቱ ግንባታም ሆነ ፤ ሀገረመንግሥቱን ለማጽናት ያደረጋቸውን ጥረቶች፤ በቀጣይ አጠናክሮ እንዲቀጥል ፤ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ለጀመርነው እልህ አስጨራሽ ትግል ስኬት ተጨማሪ አቅም የሚሆን ነው!
አዲስ ዘመን ኅዳር 27 ቀን 2016 ዓ.ም