በአትሌቲክስና ብስክሌት ስፖርቶች በኦሊምፒክ የኢትዮጵያን ስም ያስጠሩና መልካም ገጽታና የገነቡ በርካታ ስፖርተኞች ከትግራይ ክልል ተገኝተዋል:: በእግር ኳስና ሌሎች ስፖርቶችም በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኖችን የወከሉ ጠንካራ ስፖርተኞች ተፈጥረዋል:: ይህ ሁኔታ ላለፉት ጥቂት ዓመታት በነበረው ጦርነት ምክንያት ተቀዛቅዞ ቆይተል:: አሁን ግን የክልሉን ስፖርት ወደነበረበት ለመመለስ በክልሉ፣ በፌዴራል መንግሥት እንዲሁም በተለያዩ የስፖርት ተቋማት ጥረት እየተደረገ ይገኛል
ከዚህም ጋር ተያይዞ እስካሁን የተሠሩና ከዚህ በኋላም የታቀዱ ጉዳዮችን በተመለከተ የትግራይ ክልል ስፖርት ኮሚሽነር አቶ ተክላይ ፈቃዱ፤ የክልሉን ስፖርት እንዴት ወደነበረበት መደበኛ እንቅስቃሴ ይመለሳል በሚል የተለያዩ ሥራዎች መከናወናቸውን ይጠቅሳሉ:: በዚህ ረገድ በብሔራዊ ስፖርት ማኅበራት አዘጋጅነት በክልሉ የተደረጉ ጥቂት የስፖርት ውድድሮች ተስፋ ያሳዩ ሲሆን፤ ቀጣይነት እንዲኖረውም ስፖርቱን ከሚመሩት አካላት ጋር እየተሠራ ነው:: ክልሉ አሁንም ከፍተኛ የፋይናንስ እጥረት ላይ የሚገኝ ቢሆንም ባለው አቅም እንቅስቃሴ ከማድረግ ባለፈ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚከናወኑ ውድድሮች ላይ ተሳታፊ ለመሆን የተቻለው ሁሉ እየተደረገ ነው::
በጦርነቱ ሳቢያ የክልሉ የስፖርት መሠረተ ልማቶች ውድመት ደርሶባቸዋል፤ ነገር ግን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ወደነበሩበት ለመመለስ የሚያስችል ሥራ አልተከናወነም:: ይሁን እንጂ መሠረተ ልማቶቹን ወደ ነበሩበት ከፌደራል መንግሥት ጋር መግባባት ላይ የተደረሰ ሲሆን፤ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች በመኖራቸው ወደተግባር እንዳልተገባ ኮሚሽነሩ ያብራራሉ:: ‹‹በእርግጥ የማዘውተሪያ ስፍራዎቹ ወድመዋል በሚል ሥራዎች ሳከናወኑ አልቀሩም፣ ይልቁንም ባለው ሁኔታ የትግራይ ካፕ በመቀሌ ስታዲየም እንዲካሄድ እንዲሁም ታዋቂው የአትሌቶች ማሠልጠኛ ማዕከል ማይጨውም ሠልጣኞችን እንዲቀበል ተደርጓል:: ክለቦችም ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ ወደ ሥራ ገብተዋል::›› ይላሉ ኮሚሽነሩ::
የተፈጠረውን የፋይናንስ ችግር ለመቅረፍ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብሮች ተጀምረው ወደ እንቅስቃሴ የገቡ ቢሆንም አሁን ላይ የመቀዛቀዝ ሁኔታ ይታይባቸዋል:: ይህም መሆነው መርሐ ግብሩን ባዘጋጁ አካላት መካከል በተፈጠረ አለመግባባት መሆኑን ኮሚሽነሩ ይጠቁማሉ:: በተለይ በእግር ኳስ ስፖርት የሊጉን ተሳታፊ ክለቦች የመደገፍ ሂደት ላይ የሚገኘው የገቢ ማስገኛ መርሐ ግብርም በሂደት ላይ መሆኑንም ነው የሚያነሱት::
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት ጄኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይ፤ ጦርነቱ ከፈጠረው ጠባሳ ለማገገም ከሚደረጉ ተግባራት መካከል ስፖርት አንዱ እንደመሆኑ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ድጋፉን እንደሚያጠናክር ይናገራሉ:: በጦርነቱ በነበረው ሁኔታ የደረሰው ውድመት ስፖርቱንም የሚነካ ሲሆን፤ አደረጃጀቱ የመፍረስ፣ ወጣቶችም ወደተለያዩ ሥራዎች የመሰማራት ሁኔታ ታይቷል::
ይህም የፈጠረውን የስነልቦና መረበሽ ለማስተካከል ጥቂት ጊዜ ይፈልጋል፤ ነገር ግን የስፖርት ማኅበራትን በመደገፍ ረገድ ስፖርቱን የሚመሩ አካላትን በማደራጀት ክልሉም ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል:: ከዚህ ባለፈ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያደረገው አይነት ስፖርታዊ እንቅስቃሴ መነቃቃትን ይፈጥራል:: በመሆኑም የስፖርት ማኅበራት ይህንኑ አበርትተው እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል:: ጊዜያዊ መንግሥቱም ለዚህ የተመቻቸ ሁኔታ በመፍጠርና ሰላምንም በማረጋገጥ ረገድ ቁርጠኛ መሆኑንም አስረድተዋል::
‹‹ስፖርት ሰላም እና የማኅበራዊ ግንኙነትን የሚያሳድግ መሣሪያ ነው›› የሚሉት ደግሞ የኢፌዴሪ ባሕልና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ናቸው:: በጦርነት ምክንያት ተራርቆ የቆየውን ሕዝብ አንድ የሚያደርገውን የስፖርት ዘርፍ በመልሶ ግንባታም አይነተኛ ሚናን የሚጫወት የሰላም ማጽኛ ቁልፍ መሣሪያ ነው ይላሉ:: እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለፃ፣ ስፖርት ወጣቶች ተስፋቸው እንዲለመልምና እንዲታደሱ በማድረግ ብቁ ዜጋ እንዲሆኑ ያደርጋል:: የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና ብስክሌት ፌዴሬሽን እንዳደረጉት የስፖርት ውድድሮችንና ሌሎች ጉባኤዎችን በክልሉ መደረጋቸው ከፍተኛ ጥቅም ይኖረዋል::
በመሆኑም ሚኒስትሩ በዚህ ረገድ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ሲሆን ከወራት በፊት በሚኒስትሩ የሚመራና የተለያዩ የስፖርት ማኅበራት አመራሮችን ያካተተ ልዑክ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ጉብኝት ተከናውኗል:: ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ጋር በመገናኘትም በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት ተደርጓል:: አቅም በፈቀደ ሁኔታም ድጋፎች መደረጋቸውን ሚኒስትር ዴኤታው ያብራራሉ::
ክልሉ በተለያዩ ስፖርቶች በርካታ ስፖርተኞችን ለብሔራዊ ቡድን በማፍራት የሚታወቅ ሲሆን እነዚህ ክለቦችና የስፖርት ተቋማት በሃገሪቷ በሚደረጉ ውድድሮች ተመልሰው ለስፖርቱ አቅም የሚሆኑበት ሁኔታም ሊፈጠር ይገባል:: ክልሉም በስፖርት ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚሆንበትና ተተኪ ስፖርተኞችም የሚፈሩበት ሁኔታ ለመፍጠርም ከተለያዩ የስፖርት ማኅበራት ጋር ምክክር እየተደረገም ይገኛል:: ለአብነት ያህል የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ድምቀት የነበሩት የክልሉ ክለቦች ወደ ውድድር እንዲመለሱ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ውይይት ሲደረግ መቆየቱንም ሚኒስትር ዴኤታው ያስታውሳሉ::
ሚኒስትሩ ይህንን የመሳሰሉ ሥራዎች በማከናወን ላይ ያለ ሲሆን፤ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ከክልሉ ፌዴሬሽኖች ጋር በጎንዮሽ በቁሳቁስ፣ በገንዘብ እና ሌሎች ድጋፎች ላይ እንዲሠሩ በማድረግ ረገድም የምክክርና ክትትል ሥራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናል::
የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን በሚመለከትም ዘመናዊው የመቀሌ ስታዲየም ጉዳት የደረሰበት በመሆኑ፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ወደ ነበረበት እንዲመለስ ምክረ ሃሳቦችን አቅርቧል:: በዚህም ጊዜያዊ አስተዳደሩ ጊዜያዊ መፍትሔ በመፍጠር በባለሃብቶች እገዛ እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ስታዲየሙ ወደ አገልግሎት እንዲመለስ የሚችልበት ሃሳብ ቀርቧል::
በማኅበረሰብ አቀፍ የስፖርት እንቅስቃሴም በክልሉ ዋና ከተማ እና የዞን ከተሞች ውስጥ ንቅናቄዎች እንዲደረጉና ተግባራዊ እንዲሆኑም ክትትልና ድጋፍ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ኅዳር 27 ቀን 2016 ዓ.ም