የሆቴሎች የአለባበስ ሥርዓት ረቂቅ ደንብ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፡- በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች የሚደርስባቸውን አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጫናን ያስቀራል የተባለለት ረቂቅ ደንብ ይፋ ተደረገ፡፡

አዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የገፅታና የውበት አጠባበቅ እንዲሁም የጌጣጌጥ አጠቃቀም ሥነ-ሥርዓት ያወጣውን የደንብ ረቂቅ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።

በቢሮው የቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኃፍታይ ገ/እግዚአብሔር በወቅቱ እንደገለጹት፤ በባለሙያዎች የሚደርስን ጥቃት የሚያስቀር የአለባበስ ሥርዓት ረቂቅ ደንብ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ የደንብ ረቂቁ ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮዎችም የተካተቱበት ነው፡፡

በሂደቱም የቢሮው የቱሪዝም ባለሙያዎች፣ የኢትዮጵያ መስተንግዶ ማህበር፣ የአዲስ አበባ ሆቴሎችና ቱሪዝም ባለሙያዎች ማህበር፣ የቱሪዝም ማሰልጠኛ ተቋም እና የአዲስ አበባ ሆቴሎች ሥራ አስኪያጅ ማህበር እንደተሳተፉበት ገልጸዋል።

እንደ አቶ ሃፍታይ ገለጻ፤ ደንቡ በአዲስ አበባ ያሉ ሆቴሎችና መሰል ተቋማት ወጥ የሆነ ሥርዓት እንዲኖራቸው ከማገዙም በላይ ባህልና ወጉን ያልጠበቀ የአለባበስ ሥነ-ሥርዓትን በመቆጣጠር ኢትዮጵያዊ አለባበስና መስተንግዶ ሥርዓትን ለማስከበር ይረዳል፡፡

በዋናነትም ረቂቅ ደንቡ ባለሙያዎች የሚደርስባቸውን አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጫናን ለማስቀረት ያለመ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

የወጣው ረቂቅ በአዲስ አበባ ፍትህ ቢሮ ታይቶ በካቢኔ ከፀደቀ በኋላ ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል ያሉት ኃላፊው፤ በወጣው ረቂቅ መሰረት በተዋረድ ከማዕከል እስከ ክፍለ ከተማና ወረዳ ድረስ በባለሙያዎች ክትትልና ቁጥጥር መመሪያው የሚፈጸም ይሆናል ብለዋል።

የቁጥጥርና ክትትል ሥራው ባለሙያዎች የመንግሥት የሥራ ሰዓትን መሰረት በማድረግ የሚያረጋግጡ ሲሆን፤ የተለየ ጥቆማ ከደረሰ ግን ቢሮው ባልተጠበቀ ሰዓት በመፈተሽ እርምጃ መውሰድ እንደሚችል በውይይቱ ውስጥ ተጠቅሷል፡፡

በክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት መሰረት ጥሶ የተገኘ አካል በሕጉ መሰረት 50 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት የሚጠብቀው መሆኑን አስገንዝበው፤ ቅጣቱን በተሰጠው ጊዜ ያልከፈለ አካልም ተቋሙን እስከማሸግ የሚደርስ እርምጃ ይሚወሰድ ይሆናል ተብሏል፡፡

ደንቡ ሆቴሎችን ጨምሮ 28 የተለያዩ ተቋማት ላይ ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን፤ መመሪያውን ያልተገበሩ ተቋማት በሦስት ደረጃ የተከፈለ ቅጣት ይጠብቃቸዋል ሲሉ ገልጸዋል።

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You