የኢትዮጵያ የማምረቻ ዘርፍ በርካታ ችግሮች እንዲቃለሉና የመዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግር እቅዱ እንዲሳካ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ:: እነዚህ ጥረቶች ሀገሪቱ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ካላት እምቅ አቅምና ከዘርፉ ችግሮች ስፋት አንፃር ሲመዘኑ በቂ ባይሆኑም አበረታች ውጤቶችን አስገኝተዋል::
በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመትም፣ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በዕቅድ በተያዙ ዋና ዋና ግቦች አበረታች ውጤት መመዝገባቸው ተጠቁሟል:: ለኢንዱስትሪ የሚሆኑ ግብዓቶችን በማቅረብ፣ ገቢ ምርቶችን በመተካት፣ ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብና አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ የተሻለ አፈፃፀም ተመዝግቧል:: ከአምራች ኢንዱስትሪው 38 ነጥብ ሰባት ሺህ ቶን ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከ72 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢም ተገኝቷል::
የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱና ሥራ የጀመሩ አዳዲስ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች እና የገበያ ትስስር የተፈጠረላቸው ኢንዱስትሪዎች ቁጥር ጨምሯል:: የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ተኪ ምርት መጠን ለማሳደግ በተደረገው ድጋፍና ክትትል 366 ሚሊዮን ዶላር በማዳን የእቅዱን 82 በመቶ ማሳካት ተችሏል::
በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ዓባይ እንደሚገልፁት፣ በሩብ ዓመቱ በከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች 16ሺ400 የሥራ እድሎች የተፈጠሩ ሲሆን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ደግሞ ለ33ሺ 328 ዜጎች የሥራ እድል ፈጥረዋል:: 527 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች (475 አነስተኛና 52 መካከለኛ) ተቋቁመዋል፤ ይህም ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው አፈፃፀም (419) ጋር ሲነፃፀር የ26 በመቶ እድገት አሳይቷል::
ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የፋይናንስ አቅርቦትን ለማሻሻል የተከናወኑ ሥራዎችን በተመለከተ፤ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ለሥራ ማስኬጃና ለሊዝ ፋይናንስ አንድ ቢሊዮን 175 ሚሊዮን ብር ለማቅረብ ታቅዶ፣ ከአንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ማቅረብ ተችሏል:: ለከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ደግሞ 12 ቢሊዮን ብር ብድር ለማቅረብ ታቅዶ፣ ከ10 ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ቀርቧል::
በውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ረገድ ደግሞ፣ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች የግብዓት ማሟያ 25 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ለከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ደግሞ 161 ሚሊዮን ዶላር እንዲቀርብ ተደርጓል:: በሩብ ዓመቱ በአምራች ዘርፉ ወደ ውጭ ከተላከው ምርት የአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ድርሻ 7364 ነጥብ ስምንት ቶን (19 በመቶ) ሲሆን፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ድርሻቸው ደግሞ 10 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ዶላር (14 በመቶ) ነው:: የፀጥታ አካላት ዩኒፎርምን በሀገር ውስጥ ማምረት በመቻሉ በተኪ ምርት ረገድ የነበረው የጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ አፈፃፀም አበረታችና ከታቀደው በላይ ሆኖ ተመዝግቧል::
በሩብ ዓመቱ የተከናወነው ሌላው ተግባር ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት መስጠት ነው:: በዚህ ዘርፍ የተመዘገበው አፈፃፀም ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተከናወነው ጋር ሲነፃፃፀር ቅናሽ አሳይቷል:: በሩብ ዓመቱ ለ421 አነስተኛና መካከለኛ አምራቾች የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት ተሰጥቷል፤ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ግን የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት ያገኙ አምራቾች አንድ ሺ 278 ነበሩ::
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል፣ የአምራች ዘርፉ በብዙ ችግሮች ውስጥ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ በሩብ ዓመቱ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ይገልፃሉ:: እሳቸው እንደሚሉት፣ እያሽቆለቆለ የነበረው የማምረት አቅም አጠቃቀም ተሻሽሏል:: የማምረት አቅም በአማካይ 55 ነጥብ ስምንት በመቶ ደርሷል:: የኃይል አቅርቦት ጥሩ መሻሻል አሳይቷል:: ባለድርሻ አካላት ለዘርፉ ያላቸው ግንዛቤ እያደገ ነው:: አዳዲስ ባለሀብቶችን በመሳብ ረገድ የተከናወነው ተግባር እንዲሁም አምራቾች በችግሮች ውስጥ ሆነውም ሥራቸውን ለማስፋፋት ያላቸው ተነሳሽነት የሚያበረታታ ነው::
እስካሁን ድረስ ሀገሪቱ ከምትሰጠው አጠቃላይ ብድር ውስጥ ለአምራች ዘርፉ ሲሰጥ የቆየው 12 በመቶ እንደነበር ያስታወሱት ሚኒስትሩ፣ በ2015 በጀት ዓመት 60 ቢሊዮን ብር ብድር ለአምራች ዘርፉ መሰጠቱን አስታውቀዋል:: የብድር መጠኑ ወደ 24 በመቶ ከፍ እንዲል መወሰኑን ይገልፃሉ::
የሀገር ውስጥ ምርቶች በመንግሥት ግዥ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው አቅጣጫ ስለመቀመጡ የሚናገሩት አቶ መላኩ፣ ለተኪ ምርት ልማት ትልቅ ትኩረት እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ:: ‹‹120 ሚሊዮን ሕዝብ ያለው ሀገር እንዴት ራሱ አምርቶ እንደሚጠቀም ማሰብ አለበት:: አሁን ባለው ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ገንዘብም ተይዞ ሸቀጥ የማይገኝበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው:: ስለሆነም ገቢ ምርትን የሚተካ፣ ከዚያም አልፎ ኤክስፖርት ሊያደርግ የሚችል ስትራቴጂ ሊኖረን ይገባል›› ሲሉ አስገንዝበዋል::
ለዚህ ችግር ድርሻ ካላቸው ምክንያቶች አንዱ የአቅም ውስንነት መሆኑን አቶ መላኩ ይጠቅሳሉ:: ‹‹ግብዓት ቀርቦ፣ መሠረተ ልማት ተሟልቶ፣ የፖሊሲ ማሻሻያ ተደርጎ፣ ሌሎች ሥራዎችም ተሰርተውም በመንግሥት ተቋማትም ሆነ በግሉ ዘርፍ የአቅም ውስንነት ችግሮች ይስተዋላሉ:: የግብዓት አቅርቦትንና የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅትን አቀናጅቶ ማንቀሳቀስ የሚችል የማስፈፀም አቅም ካልተፈጠረ የሚዘጋጁ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተጨባጭ ለውጦችን ሊያመጡ አይችሉም:: ስለሆነም አቅምን መፈተሽና ስትራቴጂካዊ ማስተካከያዎችን ማድረግ ያስፈልጋል›› ይላሉ::
ተገቢው ትስስር ባለመፈጠሩ ምክንያት አቅርቦቱ ኖሮም ጭምር የሚፈጠር የግብዓት እጥረት እና የምርት ጥራት ችግሮች እንዳሉ የሚጠቆሙት አቶ መላኩ፣ በዘርፉ አመራሮች ላይ የሚታዩ የግንዛቤና ተዛማጅ ክፍተቶችን በማስተካከል ዘርፉን ማሻገር እንደሚያስፈልግ ይገልፃሉ::
ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ አበረታች ውጤቶች ቢመዘገቡም ኢንዱስትሪዎች በቂ ድጋፎችን እያገኙ አይደለም:: በቀላሉ መፈታት የሚችሉ ችግሮች ሁሉ ሳይፈቱ ይቆያሉ:: በታችኞቹ የአስተዳደር እርከኖች መፈታት የሚችሉ ግን ያልተፈቱ ብዙ ናቸው:: ድጋፍ ቢደረግ ኖሮ ይቃለሉ የነበሩ ችግሮች አልተፈቱም:: ድጋፎች መሬት መንካት አለባቸው:: የእያንዳንዱን ኢንዱስትሪ ችግር የለየ ምልከታና ድጋፍ ያስፈልጋል:: ‹‹የዘርፉ ችግሮች እንዲፈቱ ከተፈለገ፣ በግልጽ መነጋገር ያስፈልጋል:: የተገኙ ትንንሽ ውጤቶችን በማጉላት ብቻ የሚገኝ ጥቅም አይኖርም›› በማለት የዘርፉን ችግሮች ለማቃለል በእውቀት የታገዘ ቅንጅታዊ አሰራር እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባሉ::
በሩብ ዓመቱ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የአምራች ዘርፉን ውጤታማነት የሚያሳድጉ ስትራቴጂዎችና መመሪያዎች ዝግጅት ይጠቀሳል:: ከእነዚህ ስትራቴጂዎች መካከል በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሰው የአምራች ዘርፍ የአቅም ልማት ስትራቴጂ ነው:: የግብዓት (ጥሬ ዕቃ)፣ የሰው ኃይል፣ የቦታ፣ የኃይል፣ የፋይናንስና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግሮችን በአስተማማኝነት ለመፍታት የአምራች ዘርፉን አቅም የሚያሳድግ የአቅም ልማት ስትራቴጂ ማዘጋጀትና መተግበር አንዱ ወሳኝ የመፍትሔ ርምጃ ተደርጎ ስለተለየ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በመተባበር የዘርፉን ችግሮች በመለየት ወደ መፍትሔው የሚያደርሱ አሰራሮችን የሚመራ የአምራች ዘርፍ የአቅም ልማት ስትራቴጂ አዘጋጅቷል::
ስትራቴጂው የግሉ ዘርፍ በአምራች ኢንዱስትሪው እድገት ዋና ባለድርሻ እንዲሆን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተፅዕኖ ያላቸው አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ፣ መንግሥት ለባለሃብቶች በቂ ድጋፍና ክትትል እንዲያደርግ፣ ለባለሀብቱ የተፈቀዱ ማበረታቻዎች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲደረጉ እንዲሁም አምራች ኢንዱስትሪው በግል ባለሃብቶች ተመራጭ ዘርፍ እንዲሆን ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እንዲያግዝ ታስቦ የተዘጋጀ የአሰራር መመሪያ ነው::
የሚኒስቴሩ የስትራቴጂክ ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚው አቶ ጥላሁን እንደሚገልፁት፣ የአምራች ኢንዱስትሪ አቅም ግንባታ ስትራቴጂ ማዘጋጀት ያስፈለገው በመንግሥትና በግል ተቋማት ያለው ተቋማዊ አቅም (የሰው ሀብት፣ አደረጃጀት፣ የአሰራር ሥርዓት፣ መሠረተ ልማት) በርካታ ክፍተቶች ያሉበት በመሆኑ ነው:: ስትራቴጂው የአምራች ኢንዱስትሪ ባለድርሻ አካላት የዘርፉን ችግር በሚገባ ተረድተው የተሟላና ውጤታማ የሆነ ድጋፍ እንዲሰጡ እንዲሁም ዘርፉ ያለበትን አጠቃላይ ደረጃ ለመገምገም ያስችላል ተብሎ ይጠበቃል::
ከዚህ በተጨማሪም ስትራቴጂው ትልቅ አቅም ያላቸውን አምራቾችን ለመሳብ፣ ከሌሎች ሀገራት ጋር ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት፣ የዘርፉ ተቋማዊ አቅም ሙሉ ቁመና እንዲኖረው እንዲሁም ለውጦችን ቀጣይና ዘላቂ ለማድረግ እና በዘርፉ ያለውን የእውቀት፣ የአመለካከትና የክህሎት ክፍተት ለመሙላት ያግዛል:: በአጠቃላይ ስትራቴጂው የግሉ ዘርፍ በአምራች ኢንዱስትሪው የምጣኔ ሀብት ድርሻ ውስጥ ትልቁን ሚና እንዲወጣ የሚያስችል መደላድል ለመፍጠር እገዛ እንደሚያደርግና በ10 ዓመቱ የልማት እቅድ በማምረቻው ዘርፍ የተቀመጠውን መዋቅራዊ ሽግግርን የማሳካት እቅድን እውን ለማድረግ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው አቶ ጥላሁን ያስረዳሉ::
አቶ መላኩ ስትራቴጂዎቹን በተመለከተ ሲናገሩ ‹‹ስትራቴጂዎቹና መመሪያዎቹ የአሰራር ማነቆዎችን ለመፍታት የተዘጋጁ የፖሊሲ ማስፈፀሚያ ማዕቀፎች ናቸው:: እያንዳንዱ ዘርፍ ምን ዓይነት መመሪያ እንደሚያስፈልገው የመለየት ሥራዎች ተሰርተዋል:: እነዚህ ስትራቴጂዎች ‹አሁን ያሉትን ችግሮች በጥናት ላይ ተመስርተን ካልፈታን፣ ዘርፉ ሙሉ በሙሉ መውደቁ አይቀርም› በሚል መነሻ የተዘጋጁ ናቸው:: ስትራቴጂዎቹን የመጠቀም/ያለመጠቀም ጉዳይ የአምራች ዘርፉን አፈፃፀም የማሻሻል/ያለማሻሻል ጉዳይ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል:: ስትራቴጂዎች ወደ መፍትሔ የሚወስዱ መንገዶች በመሆናቸው መፍትሔው ላይ ለመድረስ ስትራቴጂዎችን በሙሉ አቅም መተግበር ያስፈልጋል:: ችግሮችን ለመፍታት የችግሩን መነሻና መድረሻ መረዳት ያስፈልጋል:: መፍትሔ የሚገኘው በስትራቴጂዎች ትግበራ ነው:: ፍላጎትን በመግለፅ ብቻ የሚፈታ ችግር የለም፤ ኢንዱስትሪ እውቀት ይፈልጋል:: ስትራቴጂዎችን ማዘጋጀት ብቻ ግብ አይደለም:: የስትራቴጂው ዝግጅት ብዙ ገንዘብና የሰው ኃይል ተመድቦ የተከናወነ በመሆኑ ሰበብና ምክንያት መፍጠር ሳያስፈልግ ለትግበራው ቁርጠኛ ሆኖ መሥራት ያስፈልጋል›› ይላሉ::
መንግሥት የኢንዱስትሪው ዘርፍ ችግሮችን ለማቃለል እየተገበራቸው ከሚገኙ የመፍትሔ ርምጃዎች መካከል እየተተገበረ ያለው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሀገራዊ ንቅናቄ ተጠቃሽ ነው:: የንቅናቄው ዋና ዋና ዓላማዎች የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግሮች በጋራ በመፍታት ለዘርፉ ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ዘርፉ ለኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ ማስቻል እንዲሁም በዘርፉ ያለውን የሥራ ባህል ማሻሻልና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ጥራትና ተወዳዳሪነት በማሳደግ ገቢ ምርቶችን የመተካት ሽፋንን ማሳደግ ናቸው::
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሐሰን መሐመድ በ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ በመጨመር እና የተዘጉ ኢንዱስትሪዎች ሥራ እንዲጀምሩ በማድረግ ከ18 ሺህ 800 በላይ የሥራ ዕድል መፍጠር እንዲሁም 370 አምራች ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ መመለስ እንደተቻለ ይገልፃሉ:: በንቅናቄው ሥራ ያቆሙ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ ከመመለስ ባሻገር የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ከነበረበት 48 በመቶ ወደ 58 በመቶ ማደጉንም ይናገራሉ::
የማስፈፀም አቅምን መገንባት፣ የማምረት አቅም አጠቃቀምን ማሳደግ፣ የግብዓት አቅርቦት ችግሮችን መለየት፣ ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄን አጠናክሮ ማስቀጠል፣ ቀሪ የስትራቴጂ ዝግጅት ሥራዎችን ማጠናቀቅ፣ ለኢንዱስትሪ የሰው ኃይል አቅርቦት ክትትል ማድረግ፣ ክልሎችንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን መደገፍ፣ ኤክስፖርትን ማሳደግ እና የተቀናጁ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ውጤታማ ማድረግ የዘርፉ ቀጣይ ዋና ዋና ትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን ሚኒስትሩ አቶ መላኩ ገልጸዋል::
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ኅዳር 27 ቀን 2016 ዓ.ም