ትዳርን በመጠበቅ ትውልድን መታደግ

ትዳር የሚለውን ቃል፣ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል ባልና ሚስት የመሆን ፍቃደኝነት ላይ የሚመሠረትና ቤተሰብ የመገንባት ነፃ ፍላጎት ነው በሚል ፍቺ ልንሰጠው እንችላለን። ይህ ነፃ ፍላጎት በሁለቱ ጥንዶች መካከል የሚገኙ የቤተሰብ አባላትን በዝምድና የሚያስተሳስር፤ በማኅበረሰቡ መካከል ትስስር የሚፈጥር፤ ሕጋዊ፣ ማኅበራዊ እና ሃይማኖታዊ መስተጋብሮችን ያካተተ ነው።

እንደ አንድ ትልቅ ማኅበራዊ ተቋምም ትዳር የተከበረ እና የተቀደሰ፤ ከዚህ የተነሳም በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ከፍተኛ ማኅበራዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ሕጋዊ ጥበቃ የሚደረግለት ተቋም ነው። በኛም ሀገር የቀደሙት አባቶቻችንና እናቶቻችን የትዳርን ክቡርነት ተረድተው፤ ከፍ ያለ ጥበቃ ሲያደርጉለት ቆይታል።

ይህ ሀገራዊ እውነታ አሁን አሁን መልኩን እየቀየረ፤ የትዳር ጉዳይ ወቅታዊ አጀንዳ መሆን የሚችልበት ደረጃ ላይ እየደረሰ ስለመገኘቱ መረጃዎች ያመለክታሉ። ለዚህም በአዲስ አበባ ከተማ በ2015 ዓ.ም. በጀት ዓመት የተመዘገበው የፍቺ መጠን፣ ከ2014 ዓ.ም. ጋር ሲነጻጸር 60 በመቶ ብልጫ እንዳለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሲቪል ምዝገባና ነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ መግለጹ አንዱ ማሳያ ነው።

ይህ አኀዝ የኢትዮጵያ የቤተሰብ ሕግ የተከበረ ለሆነው ትዳር ተገቢ የሆነ ጥበቃ አያደርግም፤ በተለይ ፍቺ ለማድረግ ለሚፈልግ ባለትዳር ሕጉ በሩን ከፍቶ ነው የሚያስተናግደው የሚል መከራከሪያ ይዘው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ለሚሞግቱ ዜጎች የመከራከሪያ አቅም እየሆናቸው ይገኛል።

በአንድ ወቅት ለንባብ የበቃ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የሕንድ አየር ኃይል አባል የሆኑት የ89 ዓመቱ ኒርማል ሲንግ ከ40 ዓመታት በፊት ከተለዩዋቸው ሚስታቸው ፓራምጂት ካውር ፓኔሳር ጋር በይፋ በፍርድ ቤት ለመፋታት ለ27 ዓመታት ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል። ጥንዶቹ የተጋቡት በፈረንጆቹ 1963 ሲሆን፣ በጋብቻቸውም ሦስት ልጆችን አፍርተዋል። ጋብቻው ከተፈጸመ ከ21 ዓመታት በኋላ ባል፣ ከሚስታቸው ጋር በሥራ ምክንያት በመራራቃቸው ‹‹ሚስቴ እና ልጆቼ ወደኔ ቀረብ ብላችሁ ኑሩ›› በማለት ያቀረቡት ሀሳብ በሚስታቸው ውድቅ ተደረገባቸው።

በመምህርነት ተቀጥረው ሲሠሩ የነበሩት ሚስት ‹‹ሥራዬን ለቅቄ አልመጣም›› ማለታቸው ልዩነቱን አስፍቶት ተለያዩ። ልዩነቱ በፍርድ ቤት የፀና እንዲሆንም ኒርማል በፈረንጆቹ 1996 ወደ ወረዳ ፍርድ ቤት አቤት ይላሉ። ይሁን እንጂ ባለቤታቸው ፓራምጂት ትዳራቸውን ለማጽናት የሚችሉትን ሁሉ ማድረጋቸውን በመጥቀስ በመከራከራቸው ፍርድ ቤቱ የፍቺ ጥያቄውን ውድቅ አደረገው።

ኒርማል ከሕንድ አየር ኃይል በጡረታ ከወጡ በኋላም ከ40 ዓመት በፊት ከተለዩዋቸው ሚስታቸው ጋር በፍቺ እንዲለያዩ ላለፉት 27 ዓመታት ፍርድ ቤት ተመላልሰዋል። የ89 ዓመቱ አዛውንት ከዚህ በፊት ያቀረቡት ተደጋጋሚ ጥያቄ ምላሽ ባያገኝም የ27 ዓመት ድካማቸው እንደሚያበቃ ተስፋ አድርገው ለሕንድ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፍቺ ጥያቄያቸውን አቅርበው ነበር።

በ82 ዓመታቸው ፍርድ ቤት የቀረቡት ፓራምጂት ፍቺውን እንደሚቃወሙና የ89 ዓመት ባላቸውን(ቢለያዩም ፍቺው ስላልፀደቀ) ለመንከባከብ ዝግጁ መሆናቸውንና በዚህ እድሜያቸው ፍቺ እንደማይፈልጉ ተናግረዋል። ዳኞችም ትዳር የተቀደሰና የተከበረ ተቋም መሆኑን በመጥቀስ ‹‹ለፍቺ የሚያበቃ አሳማኝ ምክንያት አላገኘንም›› በሚል የፍቺ ጥያቄውን ባለመቀበል ውድቅ አድርገውታል።

በሕንድ ሀገር ፍቺ እንደጋብቻ ቀላል አይደለም። በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል ፍቺ እንደነውር ስለሚታይ ሕጉም ለትዳር ከፍተኛ ጥበቃ ያደርጋል። ባል ወይም ሚስት ፍቺ ቢፈልጉ እንኳን አሳማኝ የበደል ወይም የጥፋት ማስረጃ ማቅረብ ስለሚኖርባቸው በፍርድ ቤት ጥያቄያቸው እምብዛም ተቀባይነት አይኖረውም። ጥናቶች እንደሚያሳዩት በሕንድ ከ100 የትዳር ፍቺ ጥያቄ በፍቺ የሚጠናቀቀው አንዱ ብቻ ነው።

ቀደም ሲል ለማንሳት እንደሞከርኩት በመዲናችን አዲስ አበባ፤ በዓመት 60 በመቶ ጭማሪ ያሳየ የፍቺ ምዝገባ እንደተካሄደ ይገኛል። እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ በወደድኩህ ወደድኩሽ ትዳር ተመሥርቶ፤ “በደበረኝ” ሰበብ እንደው እንደዋዛ ለአቅመ ምዝገባ ሳይበቁ የተደረጉ ፍቺዎች ደግሞ በየቤቱ መኖራቸው እሙን ነው።

ለጊዜው በየቤቱ የሚከናወኑትን ፍችዎች ትተን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሲቪል ምዝገባና ነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ቀርበው ትዳራቸውን በፍቺ ያጠናቀቁትን ብቻ የአንድ ዓመት ልዩነቱን ስናይ፣ አስደንጋጭ ነው ። የቤተሰብ ሕጋችን ሊፈተሽና ማስተካከያ ሊደረግበት የሚገባ እንደሆነም አመላካች ነው።

በተለይ የጭማሪ መጠኑ በዚህ ልክ በመሆኑ አስደንግጦኝ መፍትሔ ይበጅለት አልኩኝ እንጂ፣ በየሰፈሩ እዚህ ግባ በማይባል ምክንያት ትዳር ፈርሶ የተለያዩ ከፍተኛ ማኅበራዊ ችግሮች ሲያስከትል ታዝባለሁ። በተለይ ከተፋቺዎቹ አብራክ የተገኙ ሕጻናት የፍቺው ቀጥተኛ ተጎጂ ሆነው ሲሰቃዩም አስተውያለሁ።

ትዳር የተቀደሰና ክቡር ነው። በሰከነ አዕምሮ አሰላስሎ የሚገቡበት እንጂ፣ እንጣጥ ብለው የሚገቡበት እንዲሁም እንጣጥ ብለው የሚወጡበት መሆን አይገባውም። በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ ትዳር ልክ እንደሕንድ ሁሉ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ነው። ታዲያ በሚያስደነግጥ ሁኔታ ፍቺ በኢትዮጵያ እየጨመረ መምጣቱ ምክንያቱ ምንድን ነው?

ብዙ ምክንያት መጥቀስ የሚቻል ቢሆንም፣ እንደእኔ ዕይታ በኢትዮጵያ ፍቺ እየጨመረ የመጣበት ዋና ምክንያት ወደ ትዳር ለመግባት መግቢያው በር ሰፊ መሆኑ ይመስለኛል። አንድ ሰው 18 ዓመት ከሞላው/ከሞላት/ ምንም አይነት አስገዳጅ መስፈርት ሳያስፈልግ ጋብቻ በማድረግ ትዳር ውስጥ መግባት ይችላል/ትችላለች። ተዋደናል በማለትም ጋብቻ ሳይፈጽሙ “ትዳር አከል” ኑሮ ማድረግም ይቻላል፤ ይህንንም “ጋብቻ ሳይፈጸም እንደባልና ሚስት አብሮ መኖር”(ትዳር) በሚል ሕጉ ፈቃድ ሰጥቶታል።(የቤተሰብ ሕጉን አንቀጽ 98 ይመልከቱ)።

ይህን የመሰለ ወደ ጋብቻ ለመግባት ያለው ሰፊ በር ትዳርን ሁሉም እንዲሞክረው ያደረገው ይመስለኛል። ትዳር የሚሞክሩት ሳይሆን የሚኖሩት ሕይወት ነው። በትዳር አብሮ ለመኖር ብዙ ነገር ይጠይቃል። በአብዛኛው የፍቺ መንስኤ ከዝግጅት ማነስ ጋር ሊያያዝ ስለሚችል÷ ስለጋብቻ፣ ቤተሰብ አስተዳደር እንዲሁም ከራስ ይልቅ ለሌላ ሰው መኖርን በንባብና በሌሎች ዘዴዎች ሰዎች ራሳቸውን ቢገነቡ(ቢያዘጋጁ) የፍቺ መጠንን ለመቀነስ እንደሚያግዝ የጋብቻና የቤተሰብ አማካሪዎች ያስረዳሉ።

ለፍቺ መብዛት ሌላው ምክንያት የሚመስለኝ አንድ ሰው ከትዳር መውጣት ሲፈልግ እንደመግቢያው ሁሉ በሩ ሰፊ መሆኑ ነው። ለመግቢያው እንኳን 18 ዓመት መሙላትን እና ሌሎች ነገሮችን እንደመስፈርት አስቀምጧል። ከትዳር ለመውጣት ግን ሕጉ ያስቀመጠው መስፈርት ለፍርድ ቤት የፍቺ ጥያቄ ማቅረብ ነው። የፍቺ ጥያቄ ሲቀርብ ለመፋታት የወሰኑበትን ምክንያት እንኳን ለመግለጽ አይገደዱም። (አንቀጽ 76 እና 77 ይመልከቱ)

በቤተሰብ ሕጉ ለፍርድ ቤት የተሠጠውን ሥልጣን ስንመለከት፣ የትዳር ፍቺ ጥያቄ ሲቀርብ ፍርድ ቤቱ ሀሳባቸውን እንዲለውጡ ይጠይቃል፤ ሀሳባቸውን የማይለውጡ ከሆነ እንደነገሩ ሁኔታ ከሦስት ወር የማይበልጥ የማሰላሰያ ጊዜ በመወሰን ሊያሰናብታቸው ይችላል። ለተጋቢዎቹ የተወሰነው የማሰላሰያ ጊዜ ካበቃበት ቀን ጀምሮ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የፍቺ ውሳኔ ይሰጣል የሚል ድንጋጌ እናገኛለን። (ከአንቀጽ 78 እስከ አንቀጽ 82 ይመልከቱ)

ከላይ እንደተመለከትነው ዳኛው የፍቺ ጥያቄው በቀረበለት በአጭር ጊዜ ውስጥ ውሳኔ እንዲሰጥ ይጠበቅበታል። ይህ አጭር ጊዜ ትዳር የማፍረስ ሩጫ ነው!!! ትዳርን የሚያክል የተቀደሰና የተከበረ ተቋም ለማፍረስ ሩጫው ለምን አስፈለገ?!

“የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ለመገንዘብ የሚረዱ አንዳንድ ነጥቦች” በሚል ርዕስ የሕግ ምሑሩ መሓሪ ረዳዒ በጻፉት መጽሐፍ፣ ሕጉ በዚህ መልኩ እንዴት እንደወጣ ረቂቁ ሲዘጋጅ አባል ስለነበሩ ምክንያቱን አብራርተዋል። በወቅቱ ሕጉ እንዲወጣ ያስፈለገበት ምክንያት ቢኖርም እንኳን አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ለትዳር እጅግ ከፍተኛ ጥበቃ የሚያስፈልግበት ወቅት በመሆኑ ሕጉ ዳግም ሊፈተሽ ይገባል ብለዋል።

የሕንድ የቤተሰብ ሕግ ለትዳር የሚሰጠውን ያህል ጥበቃ፣ የቤተሰብ ሕጋችን ለምን ጥበቃ አያደርግም?! ቀደም ሲል በነበረው የቤተሰብ ሕግ በቀላሉ ፍቺ መፈጸም አይቻልም ነበር፤ ረቂቁም ላይ ፍቺን በቀላሉ መፈጸም እንዳይቻል ተደርጎ እንደነበርም የሕግ ባለሙያው በመጽሐፋቸው አመልክተዋል።

እንደኔ እንደኔ ከሆነ ግን የትዳር ጥበቃው አንድም ወደ ትዳር ሲገባ፣ አንድም ከትዳር ሲወጣ ሊሆን እንደሚገባ ይሰማኛል ። ለምሳሌ ትዳር ሲመሠረት፣ ቤተሰብ ለማስተዳደር የሚያስችል የንቃተ-ሕሊና ማዳበሪያ ኮርስ በማዘጋጀት ኮርሱን ወስዶ ማጠናቀቅ ለሁለቱም ተጋቢዎች ግዴታ ቢሆን እላለሁ። ምክንያቱም በአብዛኛው የፍቺ መንስኤ ወደትዳር ለመግባት ከሚደረግ ዝግጅት ማነስ ጋር ሊያያዝ ስለሚችል ነው።

ጋብቻ ለማፍረስ የሚመጣ ባለትዳር ደግሞ ወደፍርድ ቤት ከመምጣቱ በፊት ጋብቻ ሲፈርስ ምን አይነት ጉዳቶች ለራስ፣ ለልጆች፣ ለቤተሰብ እና ለሀገር ሊያስከትል እንደሚችል የግንዛቤ ማዳበሪያ ኮርስ በመስጠት ኮርሱን ማጠናቀቅ እንደግዴታ ተወስዶ ቢተገበር መልካም ነው። የጋብቻ ፍቺ ጥያቄ ወደ ፍርድ ቤት ይዞ የሚመጣ ባለትዳር ጉዳዩን በቅድሚያ በሽምግልና እንዲያሳየው እንደአስገዳጅ መስፈርትነት ማስቀመጥን ጨምሮ ሌሎች በጣም አሳሪ ያልሆኑ፣ ነገር ግን ትዳርን ሊጠብቁ የሚችሉ መስፈርቶች በመመካከር በሕግ አግባብ ማበጀት ይቻላል።

ይህን አይነት መስፈርት ማስቀመጥ ማስፈለጉ ትዳር የተከበረ ተቋም ከመሆኑ አንጻር ጥበቃ ሊደረግለት ስለሚገባ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ የቤተሰብ ሕጋችን ወደ ትዳር የመግቢያውን ሆነ የመውጫው በር ሰፊ ማድረጉ እንደ ሀገር እያስከተለ ያለው ቀውስ አሳሳቢ እየሆነ ነው፣ ከወዲሁ መፍትሔ ካልፈለግንለት ችግሩ የከፋ እንደሚሆን መገመት አይከብድም።

ከዚህ የተነሳም ፍቺን በተመለከተ የተቀመጡ አንቀጾችን ትኩረት ሰጥቶ በመመልከት ሊሻሻሉ የሚገባቸውን አንቀፆች ፈጥኖ ማሻሻል ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ ካልቻልን ዛሬ ላይ በየዓመቱ እየተስተዋለ ያለው 60 በመቶ የፍቺ እድገት፣ የዛሬ አምስት ወይም 10 ዓመት የት ሊደርስ እንደሚችል መገመት አይከብድም።

የትዳር መፍረስ በቅድሚያ እየጎዳ ያለው ሀገር ተረካቢ የሆነውን ትውልድ ነው፤ ስለሆነም ትዳርን በአግባቡ በመጠበቅ ትውልዱን፣ ቤተሰብን እና ሀገርን እንጠብቅ፣ ይህ ደግሞ የዚህ ትውልድ ኃላፊነት ነው እላለሁ።

ስሜነህ ደስታ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You