በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው ዓለም አቀፍ የወጣቶች የሜዳ ቴኒስ ውድድር ኢትዮጵያውያን የቴኒስ ተወዳዳሪዎች ጥሩ እንቅስቃሴን እያደረጉ ነው። በውድድሩ ከ24 የዓለም ሀገራት የተወጣጡ ከ45 በላይ የሚሆኑ እድሜያቸው ከ13 እስከ 18 ዓመት የቴኒስ ተወዳዳሪዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በሁለት ዙሮች የሚጠናቀቅ ‹‹ኢንተርናሽናል ጁኒየር (J- 30) አዲስ አበባ›› የተሰኘ የወጣቶች የሜዳ ቴኒስ ውድድርን በማስተናገድ ላይ ትገኛለች። ተመሳሳይ ውድድር በኢትዮጵያ ሲዘጋጅ በአጠቃላይ ለሦስተኛ ጊዜ ሲሆን በወጣቶች መካከል ሲዘጋጅ ደግሞ ሁለተኛው ነው። የመጀመሪያው ዙር ውድድር ከኅዳር 15 ጀምሮ በአዲስ አበባ ቴኒስ ክለብ የተካሄደ ሲሆን ከቀናት በፊት ተጠናቋል። ሁለተኛው ዙር ውድድርም እየተካሄደ የሚገኝ ሲሆን ኅዳር 30-2016 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ለማወቅ ተችሏል። ውድድሩን የኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን ከዓለም አቀፉ ቴኒስ ፌዴሬሽን የተሰጠውን እድል ተጠቅሞ ከአዲስ አበባ ቴኒስ ክለብ ጋር በመተባበር ማዘጋጀቱም ተጠቁማል።
በዚህ ወድድርም ከ5 መቶ እስከ 1ሺ ዓለም አቀፍ የቴኒስ ደረጃ ያላቸው ወጣት ተወዳዳሪዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ። ከዚህ ደረጃ ዝቅ ያሉት ተወዳዳሪዎች ውድድሩን መካፈል የማይችሉ ሲሆን እንደዚህ አይነት ውድድሮችን ለመሳተፍ እያንዳንዷ ነጥብ ያላት ዋጋ ከፍተኛ ነው። በሁለቱም ፆታዎች እየተካሄደ በሚገኘው ውድድር ኢትዮጵያ በ5 ሴትና በ5 ወንድ በጥቅሉ በ10 ተወዳዳሪዎች ተወክላ ተስፋ ሰጪ የሆነ እቅስቃሴን በማድረግ ላይ እንደምትገኝ የኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። በውድድሩ ጠንካራ እንቅስቃሴ እየተደረገበት ሲሆን ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ከዚህ በፊት ከነበሩት ውድድሮች የተሻለ እንቅስቃሴና ጠንካራ ፉክክር ማሳየት ችለዋል።
ከ24 የዓለም ሀገራት የተወጣጡ ቁጥራቸው ከ45 በላይ የሆኑ ድንቅ ተሰጥዖ ያላቸው ከ13 እስከ 18 ዓመት የሆኑ ታዳጊዎች በሚፋለሙበት ውድድር ኢትዮጵያውያን ተወዳዳሪዎች ውጤት ባይቀናቸውም ጠንካራ ፉክክር ማድረግ ችለዋል። ከዚህ በፊት በነበሩት ውድድሮች ሁለት በሴት እና ሁለት በወንድ ተጫዋቾች በአጠቃላይ በአራት ኢትዮጵያውያን ተወዳዳሪዎች ዓለም አቀፍ ደረጃን ማግኘት ተችሏል። በተጠናቀቀው የመጀመሪያ ዙር ውድድር በሁለቱም ፆታ አራት ተወዳዳሪዎች ቀጣዩን ዙር በመቀላቀል ተፎካካሪ ቢሆኑም ከዚያ በላይ መጓዝ ግን አልቻሉም።
ዓለማቀፉ የቴኒስ ፌዴሬሽን ለውድድሩ የሚያደርገው የገንዘብ ድጋፍ እንደሌለ ፌዴሬሽኑ የገለፀ ሲሆን፤ የተጫዋቾች ምዝገባ እና የውድድሩን ጥራት የመቆጣጠር በርካታ ሥራዎችን ሠርቷል። ፌዴሬሽኑ ለውድድሩ በራሱ ወጪ የውድድር አማካሪ ከውጪ በማስመጣት ውድድሩን እያካሄደ እንደሚገኝም አስታውቋል። ውድድሩን ከስፖንሰር በሚገኝ ገንዘብ አማካኝነት እያካሄደ እንደሆነና ዓለም አቀፉ ተቋም ሙያዊ ድጋፎችን ብቻ እንደሚያደርግለትም ጠቁሟል።
የወጣቶች ወድድር ላይ የገንዘብ ሽልማት የማይፈቀድ በመሆኑ በውድድሩ የሚያሸንፉ ተወዳዳሪዎች 30 ነጥብ የሚያገኙ ይሆናል። አሸናፊዎቹ ተወዳዳሪዎች የሚያገኙት ነጥብ ከዚህ በፊት ባላቸው ነጥብ ላይ የሚደመርላቸው ሲሆን በዓለም ላይ ያላቸውን ደረጃ ይጨምርላቸዋል። ተጫዋቾቹ ዓለም ላይ ያላቸው ደረጃም በየትኛውም ዓለም አቀፍ ውድድር ቅድሚያ የመወዳደር እድል ስለሚሰጣቸው ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ።
በመጠናቀቅ ላይ እስካለው የፈረንጆቹ ዓመት ድረስ ነጥብ ማግኘት የቻለ አንድም ኢትዮጵያዊ ተወዳዳሪ አለመኖሩ የተገለጸ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ይህን ውድድር በማስተናገዷ ግን ኢትዮጵያውያን ነጥብ ማግኘት ችለዋል። በዚህም በተገኘው ነጥብ ዓለም አቀፍ ደረጃ ውስጥ መግባት በመቻላቸው የኢትዮጵያ ስም በዓለም የቴኒስ ደረጃ ውስጥ ከሰፈሩ ሀገራት አንዷ እንድትሆን ማስቻሉ ተጠቅሷል። በዚህም ውድድር በመጀመሪያው ዙር ውጤት ባይቀናቸውም ያሳዩት እንቅስቃሴ በሁለተኛው ዙር እንዲጠበቁ አድርጓልም።
የኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ሚካኤል ንጉሤ፣ ኢትዮጵያ ውድድሩን በተደጋጋሚ ማዘጋጀቷ ለኢትዮጵያውያን ተወዳዳሪዎች የሚያወጡትን ከፍተኛ ወጪ እንደሚያስቀርላቸው አስረድቷል። ስፖርተኞቹ ጥሩ የሚባል የቴክኒክ ብቃት ያላቸው ቢሆንም ውድድር የማያገኙ በመሆኑ ያንን በመቅረፍ የራስ መተማመንን እንዲያጎለብቱ ሊረዳ እንደቻለም ገልጸዋል። ዓለም አቀፍ ውድድሮች በበዙ ቁጥር ለውድድሩ የሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶች እንዲሟሉም ይረዳል። ለስፖርቱ የሚመደበው በጀት ጥቂት በመሆኑ እና የሀገር ውስጥ ውድድሮች ባለመስፋፋታቸው እንደዚህ ዓይነት ዓለማቀፍ ውድድሮች መፈጠራቸው የሀገር አቀፍ ውድድሮችን ለማነቃቃትና ስፖርቱን ለማሳደግ ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል። በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን ወጣቶች እያደረጉ የሚገኙት እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ በመሆኑ በቀጣይ ባሉት ውድድሮች በጉጉት እንዲጠበቁ ማድረጉንም ተናግረዋል።
ውድድሩን በበላይነት የሚያስተዳድረው ዓለም አቀፉ የቴኒስ ፌዴሬሽን፤ የቴኒስ ስፖርትን ከሚያሳድግባቸው ዋንኞቹ ተግባራት ውስጥ የወጣቶች ውድድር አንዱ ነው። በዚህም የኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን ለመደገፍና ስፖርቱን ለማሳደግ እንዲህ ዓይነት ውድድሮችን የማዘጋጀት ፍቃድ ይሰጣል። ለአንድ ጀማሪ ሀገር በአንድ ዓመት የማዘጋጀት እድሉ ሁለት ጊዜ ብቻ ቢፈቀድም፤ ኢትዮጵያ በከዚህ ቀደሞቹ ውድድሮችን በጥሩ መንገድ ስላስተናገደች ለሦስተኛ ጊዜ የማዘጋጀት እድሉን ልታገኝ እንደቻለችም ተጠቁሟል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ህዳር 26/2016