ዓለማችን በአየር ንብረት ለውጥ መታመስ ከጀመረች ውላ አድራለች። ጎርፍ፣ ድርቅ፣ ሰደድ እሳት፣ ከባድ አውሎ ነፋስና ሱናሜን የመሳሰሉ ክስተቶች ዕለት ከዕለት እየፈተኗት፤ የሰዎችን ኑሮም እያመሳቀሉ ቀን ከሌት እረፍት ነስተዋታል። እነዚህ ክስተቶች ደግሞ የሰው ልጆች የሥራ ውጤት እንደመሆናቸው የሰው ልጆችን የመፍትሔ አካልነት አብዝተው የሚሹ ናቸው።
በዚህ ረገድ ቀድመው ያደጉ እና ከባድ ኢንዱስትሪዎችን ተግብረው የኢኮኖሚያቸው ማዕከል ያደረጉ ሀገራት ቀዳሚውን ድርሻ ይይዛሉ። ምክንያቱም ባለ ግዙፍ የኢንዱስትሪ ሀገራት፤ ከኢንዱስትሪዎቻቸው በሚወጡ በካይ ጋዞች አማካኝነት በከባቢ አየር ላይ የሚፈጥሩት ጫና ለአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል።
የችግሩ ምንጮች እንዲህ አይነት ባለ ግዙፍ ኢንዱስትሪ ባለቤት የሆኑ ሀገራት ይሁኑ እንጂ፤ ችግሩ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ሰለባዎች ግን ለአየር ንብረት ለውጥ ችግር እዚህ ግባ የሚባል አበርክቶ የሌላቸው ድሃ ሀገራትም ጭምር ናቸው። ዛሬ ላይ በአፍሪካም፣ በአውሮፓም፣ በአሜሪካም ሆነ በሁሉም የዓለም አካባቢ ያለልዩነት የሚታይው ጭንቅና መከራም ለዚህ ጉዳይ ሁነኛ ማሳያ ነው።
ምንም እንኳን የችግሩ መከሰት ቀዳሚ ተብለው የሚጠቀሱ ሀገራት ቢኖሩም፤ እነዚህ ሀገራት ከችግሩ ለመውጣት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ግን የቀዳሚነታቸውን ያህል ቀድመው መገኘት አልቻሉም። ለምሳሌ፣ ዛሬ ላይ አንዳንድ የአደጉ ሀገራት በተደጋጋሚ በሱናሚ ቢመቱም፣ ለሱናሚው መከሰት ምክንያት መሆናቸውን አውቀው ለችግሩ መቃለል እያደረጉ ያሉት የመፍትሔ ጥረት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
እነዚህ ሀገራት ምናልባት ችግሩን ለመሻገር የሚያስችላቸው የኢኮኖሚም፣ የቴክኖሎጂም አቅም ገንብተው ሊሆን ይችላል። ሆኖም ይሄን ማድረግ የማይችሉ ሀገራት ግን ዜጎቻቸው ለተደጋጋሚ ችግር ሲጋለጡ፤ ሀገራቱም በብርቱ ሲፈተኑ ማየት የተለመደ ሆኗል።
ኢትዮጵያም የዚህ አንዷ ሰለባ ናት። ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ችግር መከሰት ያላት አበርክቶ እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም፤ ችግሩ ባሰከተለው የድርቅ፣ ጎርፍና መሰል አደጋዎች ግን ከዓመት ዓመት ዋጋ እየከፈለች፤ ዜጎቿም ለከፋ ችግርና እንግልት እየተዳረጉባት ያለች ሀገር ናት።
በመሆኑም እንደ ሀገር ከዚህ ችግር ለመውጣት ብቻ ሳይሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የራስን አበርክቶ ለማድረግ ሲባል ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ላይ አተኩራ እየሠራች ትገኛለች። በዚህም ችግኝ ከመትከል ጀምሮ፣ በግብርናው ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን የሚያስችሉ የተፋሰስ ልማት ሥራዎችን በስፋት ተግብራ ውጤት አምጥታለች።
ከዚህ በተጓዳኝ በከባቢ ላይ ጉዳት ከሚያደርሱ ኃይል የማምረትና አጠቃቀም ተግባራት ተቆጥባ፤ በታዳሽ ኃይል ምርትና አጠቃቀም ላይ ትኩረቷን አደረገች። በዚህም በርካታ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦችን ገነባች፤ የንፋስ ኃይል ማመንጫዎችን ተከለች፤ የፀሐይ ኃይል ማምረቻዎችን አስፋፋች፤ የእንፋሎት ኃይል ማመንጫንም እንደ አማራጭ መተግበር ጀመረች።
መለስተኛ ከሆኑ ግድቦች ጀምራ እስከ ግዙፉ የዓባይ ግድብ ድረስ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎችን እውን አደረገች፤ በቀጣይም በርካታ ፕሮጀክቶችን ለመተግበር ትልም አስቀመጠች። በአዳማ እና አሸጎዳ የተጀመሩ የንፋስ ኃይል ማመንጫዎችና አሁን ላይ 300 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለውን ግዙፍ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በሶማሌ ክልል ለመትከል የሚያስችል ጉዞን አደረገች።
ታዳሽ ኃይልን የማምረት ብቻ ሳይሆን የመጠቀም ልምዷንም አዳበረች። በቤተሰብ፣ በተቋማትና በድርጅቶች ብሎም በፋብሪካዎች ጭምር ታዳሽ ኃይሎች ቀዳሚ የኃይል አማራጭ እንዲሆኑ ተደረገ። ከፍ ያለ የአየር ብክለት የማድረስ አቅም እንዳላቸው የሚነገርላቸው ተሽከርካሪዎች ጭምር በታዳሽ ኃይል ላይ የተመሠረተ አጠቃቀም እንዲኖራቸው በሕግ ታግዛ ወደ ተግባር ገባች።
በካይ ጋዝን ወደ ከባቢ የመልቀቅ ሂደትን የመቀነስ ብቻም ሳይሆን፤ ሌሎች በሚለቁት በካይ ጋዝ ዓለማችን የሚደርስባትን አደጋ ለመቀነስ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሯ ለዓለም ሳንባን የመፍጠር እንቅስቃሴ ውስጥ ገባች። ይሄ ደግሞ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው ነው።
ተግባሩ በአንድ በኩል የተመናመነውን ሀገራዊ የደን ሽፋን የመመለስ፤ በሌላ በኩል በምግብ ራስን የመቻልና የሥራ ዕድል የመፍጠር፤ ከዚህ አለፍ ሲልም በ50 ቢሊዮን ችግኞች አጋዥነት የዓለምን የአየር ንብረት ለውጥ ሚዛን ማስጠበቅን የመሳሰሉ ከፍ ያሉ አበርክቶዎች ያሉት ነው።
በዚህ መልኩ የሚከናወነው የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ሂደት፤ እንደ ሀገር ልማትን፣ እንደ ዓለምም እፎይታን የሚያስገኝ ከፍ ያለ ተግባር መሆኑ እሙን ነው። ይሄ ደግሞ ዛሬ ላይ ዓለማችን በገጠማት ችግር ምክንያት እንደ ሀገርም ከምንቸገርበት የአየር ንብረት ለውጥ መዘዝ የሚታደግ እንደመሆኑ፤ ተግባሩ ሊወደስም፣ ሊታገዝም የሚገባው ነው። በተለይም ለአየር ንብረት ለውጡ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው የበለጸጉ ሀገራት የኢትዮጵያን መፍትሔ አምጪ መንገድ በሁሉም መልኩ ሊያግዙ ይገባል። ምክንያቱ ደግሞ በታዳሽ ኃይል ላይ የተመሠረተው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ግንባታ ጉዞ፤ ከራስም በላይ ለዓለም ፈውስን ይዞ የቀረበ ነውና!
አዲስ ዘመን ኅዳር 26 ቀን 2016 ዓ.ም