
ሮቤ፡- ሀገሪቱ ያላትን ቱሪዝም ሀብት በተለይም የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ተጠበቆ ለዘላቂ ልማት እንዲውል ሰፊ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ። የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ለዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት በባሌ ዞን ሮቤ ከተማ ትናንት ዕውቅና ተሰጠ።
በዕውቅና መርሃ-ግብሩ የተገኘ የት የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ እንደገለጹት፤ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በአካባቢው ማህበረሰብ፣ ክልልና ፌዴራል መንግሥት መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ጥረት የዓለም ቅርስ ሆኖ በዩኔስኮ ማስመዝገብ ተችሏል።
ፓርኩን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሳይንስ፣ የትምህርትና ባህል ማዕከል (ዩኔስኮ) ማስመዝገብ ብቻውን በቂ አይደለም፤ የቱሪዝም ሀብቱ ተጠብቆ ወደ ዘላቂ ልማት ለመቀየር ሃላፊነት ወስዶ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት ብለዋል።
ኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ በበኩላቸው፤ የአካባቢው ማህበረሰብ ያልተቋረጠ ድጋፍ በማድረጉ ባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በቅርስነት መመዝገብ ችሏል።
የተፈጥሮ ሀብቱን በመንከባከብ ወደ ዘላቂ ልማት መቀየር የሁሉም አካላት ድጋፍ ይፈልጋል ያሉት አቶ ኩመራ፤ ፓርኩን በመንከባከብ ወደ ዘላቂ ልማት በመቀየር ወደ ትውልድ ለማሸጋገር ከሁሉም ይጠበቃል ሲሉ አመላክተዋል።
የሮቤ ከተማ ከንቲባ አቶ ንጋቱ ሞቱማ በበኩላቸው፤ ባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በ1923 ዓ.ም የተቋቋመ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ለዘመናት በዩኒስኮ ቅርስነት መመዝገብ እንዳልቻለ አስታውሰዋል።
አሁን ላይ በአካባቢው ህብረተሰብና በመንግሥት ጥረት በዓለም ቅርስ መዝገብ ውስጥ ማስመዝገብ ተችሏል። ስኬቱ ዞኑ የቱሪስት ማዕከል ከማድረጉም ባሻገር ለኤክስፖርት ግብዓት የሚሆኑ ግብርና ምርቶች የማምረት አቅሟ እንዲያድግ አድርጓል ብለዋል።
መንግሥት ፓርኩን ይጠልጥ ስኬታማ ለማድረግ መሠረተ ልማት ግንባታ ሥራዎችን ጨምሮ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ በጀት መድቦ እየሠራበት መሆኑን ገለጸው፤ ዞኑ ለፓርኩ በሚሰጠው ትኩረት አካባቢው የልማት ማዕከል መሆኑን አመላካች ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የባሌ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አብዱላኪም አሊይ፤ ባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከበርካታ ዓመታት በኋላ በዩኔስኮ ቅርስነት በመመዝገቡ አካባቢው ማህበረሰብ እንዲሁም የተለያዩ አካባቢ ዜጎችን ማስደሰቱን ገልጸዋል።
ፓርኩ የአካባቢውን ተፈጥሯዊ ሚዛን በመጠበቅም ትልቅ ዕገዛ እንዳለው ጠቁመው፤ ፓርኩ በሕብረተሰቡና በመንግሥት እስከ አሁን በተደረገው ጥረት ለ30 ሚሊዮን ዜጎች የሚበቃ የከባቢ አየር በጎ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን አመላክተዋል።
ፓርኩ የ80 አጥቢ እንስሳት፣ 310 የተለያዩ አዕዋፋት፣ ከአንድ ሺህ 600 በላይ የተለያዩ ዕጽዋቶችና የ40 ወንዞች መገኛ መሆኑን ገልጸው፤ ሁሉም አካላት ፓርኩን ለመንከባከብ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።
ከዕውቅና አሰጣጥ መርሀ-ግብሩ በተጓዳኝ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ባለሥልጣን ከቱሪዝም ሚኒስቴር እና ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጋር በመተባበር የቱሪዝም ኤግዚቢሽን፣ ባሕላዊ ትርዒትና ጉብኝት አካሂደዋል።
ፓርኩን ከእሳት ቃጠሎ አደጋ ለማዳን ሕይወቱን አሳልፎ ለሰጠው ለአቶ ቢንያም አድማሱ የዕድሜ ልክ ዕውቅና ተሰጥቷል።
ገመቹ ከድር
አዲስ ዘመን ኅዳር 26 ቀን 2016 ዓ.ም