በ2012 ዓ.ም የውድድር ዘመን በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተፎካካሪ ከነበሩ ክለቦች መካከል ሦስቱ የትግራይ ክልል ክለቦች መቀሌ ሰባ እንደርታ፣ ስሁል ሽረ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ዋነኞቹ ነበሩ፡፡ እነዚህ ክለቦች የሊጉ ድምቀት ከመሆን ባለፈ ጠንካራ የዋንጫ ተፎካካሪም እንደነበሩ ይታወሳል። ተሰጥኦ ያላቸውና ጠንካራ ተጫዋቾችን ለብሄራዊ ቡድን እንዲሁም በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ በማፍራትም የራሳቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት ችለዋል፡፡
ሦስቱ ክለቦች በትግራይ ክልል በነበረው ጦርነት ምክንያት ውድድራቸውን ለማቋረጥና ተጫዋቾቻቸውንም ለመበተን ተገደዋል፡፡ ባለፈው ዓመት የተደረሰበትን የሰላም ስምምነት ተከትሎም ክለቦቹን ወደ ውድድር ለመመለስ ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ የክለቦቹ ጥያቄ እስከተያዘው የውድድር ዓመት ተቀባይነት ባያገኝም ወደ ቀደመ አቋማቸው ለመመለስ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
በ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮን የነበረው መቀሌ ሰባ እንደርታ እግር ኳስ ክለብ አሁንም በብዙ ፈተናዎች ውስጥ እንደሚገኝ ሥራ አስኪያጁ አቶ ሽፈራው ተክለሃይማኖት ይናገራሉ፡፡
አቶ ሽፈራው እንደሚናገሩት፣ ዓለም አቀፉ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ተከትሎ የተነሳው የሰሜኑ ጦርነት ስፖርትን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች በርካታ ጥፋቶችን አድርሷል፡፡ በዚህም አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለቦች በመንግሥት ተደጓሚ እንደመሆናቸው በነዚህ ችግሮች በእጅጉ ተፈትነዋል፡፡ በተለይም የክልሉ ክለቦች ተጨማሪ ችግር መጋፈጣቸው የግድ ሆኗል። በአሁኑ ወቅትም በመቀሌ ከተማ አስተዳደር ይደጎም የነበረው የክለቡ ድጋፍ የተቋረጠ ሲሆን፤ ከስፖርት ንግድ ይገኝ የነበረውም ገቢም አሁን ላይ የለም፡፡ ይህ ሁኔታ ተደማምሮም ክለቦቹን ወደ መፍረስ አዝማሚያ እንዲቃረቡ አድርጓል፡፡ በርካታ ደጋፊዎች ያሉት መቀሌ ለ30 ወራት ደመወዝ መክፈል አልቻለም ነበር፡፡ በዚህ ዓመት የክለቦች ምዝገባ ቢኖርም ኖሮ ክለቡ አቅም አልነበረውም፡፡ አሁንም ዋናው ቡድን ቀርቶ ለታዳጊ ቡድኑ እንኳን ማሊያና ኳስ ለማቅረብ ያልተቻለበት ሁኔታ ላይ እንደሚገኝም ሥራ አስኪያጁ ያስረዳሉ፡፡
የክለቦቹን በዚህ ሁኔታ መገኘትና የቀድሞ ተጫዋቾችን መበተን ተከትሎም ስፖርቱን የመደገፍ እንቅስቃሴዎች በተለያዩ አካላት መጀመራቸው ይታወቃል፡፡ በተለይም የፕሪምየር ሊጉ ተሳታፊ የነበሩ ክለቦችን ከመፍረስ የመታደግ ዓላማ በማንገብ ‹‹ክለቦቻችንን እንታደግ›› በሚል ንቅናቄ የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን እና ሌሎች የገቢ ማስገኛ መንገዶችን በሀገር ውስጥ እና በውጪ በሚኖሩ አትዮጵያዊያንን ለማሳተፍ ታቅዶ ሰፊ እንቅስቃሴ ተጀምሮ ነበር፡፡
በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ ውድመት ያስተናገዱትን ክለቦች መልሶ ለማጠናከር በዚህ የሀብት ማሰባሰብ እንቅስቃሴ የተጓዙበትን ርቀት ሥራ አስኪያጁ ሲያብራሩ፤ ካለፈው ዓመት ግንቦት ወር አንስቶ እንቅስቃሴው እንደተጀመረ ይናገራሉ፡፡ መቀሌ ሰባ እንደርታ እግር ኳስ ክለብ ከአንድ ተቋም ጋር በመሆን የገቢ ማሰባሰብ ሥራውን ለማከናወን ውል ቢያስርም በተለያየ ምክንያት ሊዘገይ ችሏል። ነገር ግን የስፖርት ቤተሰቡ እንዲሁም ተቋማት በሚያደርጉት ርብርብ እቅዱ በቅርቡ ግቡን ሊመታ ይችላል የሚል ተስፋ አላቸው፡፡
ውድድርን በሚመለከትም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቀድሞ በሊጉ ተሳታፊ የነበሩ ክለቦች በህጉ መሰረት ከዓመታት በኋላ ‹‹ወደ ውድድር እንመለስ›› የሚለውን ጥያቄ ውድቅ ማድረጉ የሚታወስ ነው። በዚህ ውሳኔ ያልተስማሙት ክለቦችም፤ በፕሪቶሪያ የተደረሰው የሰላም ስምምነት ከሚያካትታቸው ጉዳዮች መካከል እንደዘርፍ ስፖርትንም ታሳቢ ሊያደርግ ይገባል የሚል አመለካከት በማራመድ ላይ ይገኛሉ፡፡ ክለቦቹ ወደ ከፍተኛ ሊግ እንዲወርዱ መደረጋቸው ‹‹ፍርደ ገምድልነት ነው›› የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያላደረገ ውሳኔ ነው ሲሉ ቅሬታ ያቀርባሉ፡፡ በመሆኑም ሊግ ካምፓኒውና ፌዴሬሽኑ ይህንን ከግንዛቤ በማስገባት የሰላም ስምምነቱ፤ ተቋማትን ወደነበሩበት መመለስ የሚል በመሆኑ ይኸው ሁኔታ ተቀባይነትን አግኝቶ በቀጣዩ ዓመት ወደ ሊጉ እንዲመለሱ ማድረግ እንደሚገባቸው ያስረዳሉ፡፡
ክለቦቹ በዚህ የውድድር ዓመት እንዳቀዱት ወደነበሩበት መመለስ ባይችሉም በ2017 ዓ.ም በሀብት ደረጃ በመላው ኢትዮጵያውያንና መንግሥት ድጋፍ በሁለት እግራቸው የሚቆሙበት ዓመት እንደሚሆንም ሥራ አስኪያጁ ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ዘንድሮ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ሲሆን፤ እንደ መቀሌ ሰባ እንደርታ ክለብ ደግሞ ወደ ደመቀበት መድረክ ይመለሳል የሚል እምነት አላቸው፡፡ መቀሌ ሰባ እንደርታ ጠንካራ ተፎካካሪና በርካታ ቁጥር ያለው ደጋፊ ባለቤት ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ዓመት ሀብት በማሰባሰብ፣ አሰልጣኝና ተጫዋቾች በመመልመልና በማደራጀት ላይ ትኩረቱን እንደሚያደርግም ጠቁመዋል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ኅዳር 25 ቀን 2016 ዓ.ም