በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተከሰቱ የሰላም እጦቶች፤ ድርቅና ጎርፍ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ለችግር ተጋልጠዋል። ይህንንም ተከትሎ መንግሥት በራሱ አቅም ለተጎጂ ወገኖቻችን ድጋፍ በማቅረብ፤ ችግሩ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል በኃላፊነት መንፈስ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ሰሞኑን እንዳስታወቀው፤ በሀገሪቱ በጎርፍ፣ በግጭትና በድርቅ ለተጎዱ 7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች ከሁለት ሳምንት በፊት በሁለት ዙር 7 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ወጪ በማድረግ የርዳታ አቅርቦቶችን አከፋፍሏል፡፡
ርዳታው የቅድሚያ ቅድሚያ ለሚያስፈልጋቸው ፤ በሰሜን ጎንደር፣ በዋግኽምራና በትግራይ ክልል ለሚገኙ ሦስት ዞኖች ተከፋፍሏል፤ ርዳታው ለ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ለሚሆኑት ተጎጂዎች በገንዘብ ፤ለተቀሩት ደግሞ በምግብ ነክ ድጋፎች ተሰራጭቷል፡፡
በሶማሊያ ክልል ሰሞኑን የተከሰተውን ጎርፍ ተከትሎም፤ ለአደጋው ተጎጂዎች አንድ ሺህ 821 ኩንታል የስንዴ ዱቄትና ሩዝ፤ 9 ሺህ 200 ኪት ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች በመንግሥት በኩል ድጋፍ ተደርጓል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ ባጋጠመ የጎርፍ አደጋ ለተፈናቀሉ 16 ሺህ 648 አባ ወራዎችና እማ ወራዎች 3 ሺህ 140 ልዩ ልዩ ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች በመንግሥት ወደ አካባቢው ተልከዋል፡፡
ከመከላከያ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ሄሊኮፕተር በመታገዝ የሰዎችን ሕይወት የማዳን፣ የምግብ ቁሳቁሶችን፣ መድኃኒት፣ አጎበርና የውሃ ማጣሪያ ኬሚካል የማሰራጨት ሥራዎችም እየተሠሩ ነው፡፡
መንግሥት ካለበት፤በየትኛውም ሁኔታ ሊከሰቱ ከሚችሉ አደጋዎች የዜጎች ህይወት የመታደግ ኃላፊነት አንጻር በሰላም እጦት፤ በድርቅና በጎርፍ አደጋዎች ችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎቻችንን ሕይወት ለመታደግ እያደረገ ያለው ጥረት እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ነው።
ችግሩን በወቅቱ ከማሳወቅ ጀምሮ፤ ባለው አቅም በችግሮቹ ምክንያት አንድም ዜጋ መሞት አይገባውም በሚል ያለውን ሀገራዊ አቅም በማቀናጀት፤ ዜጎችን ለመታደግ እየሄደበት ያለው ርቀት ለዜጎች ህይወት ያለውን ከበሬታ በተጨባጭ የሚያመላክት ነው።
ዓለም አቀፍ የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ለችግሩ ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጡ ከማድረግ ጀምሮ፤የተገኙ የእርዳታ አቅርቦቶች የችግሮቹን አሳሳቢነት ታሳቢ ባደረገ መንገድ ለተጎጂዎች እንዲከፋፈል እያደረገ ያለውም ጥረት የሚበረታታ ነው።
በተለይም የመከላከያ ኃይሉ ያለውን ሙያዊ አቅም ጨምሮ፤ የእርዳታ አቅርቦቶች እና አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ለተጎጂ ወገኖቻችን በወቅቱ እንዲደርስ ማድረጉ፤ሀገራዊ አቅሞችን በማቀናጀት ችግር ውስጥ ላሉ ዜጎቻችን ፈጥኖ ለመድረስ ያስቻለ ነው። የመከላከያ ሠራዊቱን ሕዝባዊነትም በተጨባጭ ያመላከተ ነው።
ይህም ሆኖ ግን፤ ከችግሮቹ ስፋትና፤ አሁን ላይ እንደሀገር ካሉብን መልከ ብዙ ተግዳሮቶች አንጻር፤ በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎቻችንን የመታደግ ኃላፊነት ለመንግሥት ብቻ የሚተው ሳይሆን፤ የእያንዳንዱን ዜጋ ድጋፍ የሚሻ፤ ሀገራዊ ንቅናቄ መፍጠርን የሚጠይቅ ነው።
ለዚህ ደግሞ ከሁሉም በላይ ባለሀብቶቻችን በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን ህይወት በመታደግ ሂደት ኃላፊነት እንደሚሰማው ዜጋ የሚቻላቸውን ሁሉ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ፤ችግሩ በዜጎች ላይ የከፋ ጉዳት ከማስከተሉ በፊት ፈጥነው በመንቀሳቀስ በአደጋ ውስጥ ለሚገኙ ዜጎቻችን ያላቸውን አጋርነት በተግባር ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል።
ጉዳዩ ከሰብአዊነት ጋር የተቆራኘ በመሆኑ፤ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ችግሩን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የራሳቸውን አስተዋጽኦ በማበርከት፤ ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው ያላቸውን ፍቅር፤ እንዲሁም ለሰብአዊነት ያላቸውን ከበሬታ በተጨባጭ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል! ለዚህም ከዚህ ቀደም ወገኖች በችግር ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ ዜጎች በራሳቸው ተነሳሽነት ያደርጉ የነበረውን ዓይነት ድጋፍ አሁንም ለመደግም ዝግጁ መሆን ይገባቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ኅዳር 25 ቀን 2016 ዓ.ም