
አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ይዞታ የማረጋገጥ ሥራ በቅርቡ እንደሚጀመር የከተማዋ የመሬት፣ ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ አስታወቀ። እስከ 2016 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ330 ሺህ በላይ ቁራሽ መሬቶችና የጋራ መኖሪያ ቤቶች በካዳስተር ሥርዓት እንደተመዘገቡም ተገልጿል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ግፋወሰን ዴሲሳ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ በከተማዋ በ80 ሺህ የመሬት ይዞታዎችን እና 80 ሺህ ባለመብቶችን የማረጋገጥ ሥራ በቅርቡ ይጀመራል።
የመሬት ይዞታ የማረጋገጥ ሥራው ከለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በስተቀር በሁሉም ክፍለ ከተሞች ተግባራዊ ይደረጋል ያሉት አቶ ግፋወሰን፤ ይህ የይዞታ ማረጋገጥ እወጃ ከተላለፈ ከአሥራ አምሥት ቀን በኋላ የይዞታ ይረጋገጥልኝ ጥያቄዎች ማቅረብ ይቻላል ብለዋል። የማረጋገጥ ሥራውም በ80 ቀታናዎችና በ320 ሰፈሮች እንደሚከናወን ጠቁመዋል።
በከተማዋ 444 ሺህ ቁራሽ መሬት እና 750 ሺህ ባለመብቶች አሉ ያሉት አቶ ግፋወሰን፤ ከዚህ ውስጥ በዘመናዊ የመሬት ይዞታ ምዝገባ ሥርዓት የተከናወነባቸው ቁራሽ መሬቶች 172 ሺህ ሲሆኑ 335 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ የግል ይዞታዎች በሊዝ እና በኪራይ የሕዝብ መጠቀሚያ ቦታ ያላቸው ባለመብቶች ናቸው ብለዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ ይዞታዎቹ የግል ይዞታዎች በነባርና በሊዝ ስሪት፤ አረንጓዴ መሠረተ ልማት፣ መንገድ፣ ክፍት ቦታ፣ የአስተዳደር ቦታዎች እና ሌሎችን ይጨምራል። በዘመናዊ የመሬት ይዞታ ምዝገባ ሥርዓት በዋናነት ሁለት ዓይነት ቴክኖሎጂ ተግባራዊ እየተደረገ ሲሆን አንደኛው የሪል እስቴት ካዳስተር ነው። ሁለተኛው ደግሞ መብት ክልከላና ኃላፊነትን የሚመዘግብ ሥርዓት ነው።
በዘንድሮ በጀት ዓመት ሥር ነቀል የሆነ የይዞታ ማረጋገጥ ሥራ ይሠራል ያሉት አቶ ግፋወሰን፤ በጀት ዓመቱ ሲጠናቀቅ ደግሞ በአምሥት ክፍለ ከተሞች የካዳስተር ሥርዓት ሙሉ ለሙሉ እውን ይሆናል። እነዚህም አራዳ፣ ቂርቆስ፣ ልደታ፣ ጉለሌና አዲስ ከተማ ናቸው ብለዋል።
በከተማዋ ካሉት 424 ሺህ በላይ የመሬት ይዞታዎች መካከል በዘመናዊ የመሬት ይዞታ ምዝገባ ሥርዓት የተከናወነባቸው ከ330 ሺህ በላይ ቁራሽ መሬቶችና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ናቸው። በዘንድሮ ሩብ ዓመት 53 ሺህ የመሬት ይዞታዎች ወደ ካዳስተር ሥርዓት መግባቱን ገልጸዋል።
በ2015 በጀት ዓመት ወደ ካዳስተር ሥርዓት የገባው 120 ሺህ የመሬት ይዞታዎች ሲሆኑ የ2016 በጀት ዓመት እቅዱ ደግሞ 120 ሺህ የመሬት ይዞታዎችን ወደ ዘመናዊ የካዳስተር ሥርዓት ለማስገባት እየተሠራ እንደሆነም ተናግረዋል።
በይዞታ ማረጋገጥ ሂደት ከሚያጋጥሙት ተግዳሮቶች ውስጥ የባለይዞታዎች ማመልከቻ አለመያዝ፣ አጎራባች አለመፈራረም፣ የባለይዞታዎች ግንዛቤ ማነስ ተጠቃሽ ናቸው ያሉት አቶ ግፋወሰን፤ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ሁሉም ክፍለ ከተማ የመረጃ ማሰባሰብና ማደራጀቱን ሥራ አጠናቀው ለይዞታ ማረጋገጥ እወጃ ዝግጁ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።
ኤጀንሲው በ7ኛው ዙር የይዞታ ማረጋገጥ እወጃ ከ160ሺ በላይ ቁራሽ መሬቶችንና የጋራ መኖሪያ ቤቶችን አረጋግጦ በካዳስተር ሥርዓት ለመመዝገብ የዝግጅት ምዕራፍ ሥራዎችን በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ኅዳር 25 ቀን 2016 ዓ.ም