
አዲስ አበባ፡- የኢትዮ- ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት የጭነት አቅም በየዓመቱ ከ35 እስከ 40 በመቶ ዕድገት እያሳየ መሆኑን የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር አስታወቀ፡፡
የአክሲዮን ማኅበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አብዲ ዘነበ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የባቡር ትራንስፖርቱ የጭነት አቅም እንዲሁም የትራንስፖርት አገልግሎት በየዓመቱ እስከ 40 በመቶ እድገት እያሳየ ነው፡፡
በባቡር አገልግሎቱ ሁለት ሚሊዮን ቶን በላይ ጭነት የማጓጓዝ አቅም መፈጠሩን አመላክተው፤ አሁን ያሉትን 20 የባቡር ጣቢያዎች ለማሳደግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ዶክተር አብዲ አመላክተዋል።
የኢትዮ- ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ሥራ ከጀመረ አምስተኛ ዓመቱ እንደሆነው አስታውሰው፤ የባቡር ትራንስፖርቱ የተለያዩ የጭነት መስተጓጉሎችንና ለጭነት የሚወጣው የውጭ ምንዛሬ ወጪ መቀነስ አስችሏል ብለዋል።
የባቡር ትራንስፖርቱ ቀጣናዊ ትስስሩን ይበልጥ ለማጠናከርና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማረጋጋት ጉልህ አስተዋጽጾ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸው፤ የባቡር ትራንስፖርቱን አቅም ለማሳደግ ከቻይና ሁለት ተቋራጮች ጋር ሲከናወኑ የቆዩ የአቅም ግንባታ ሥራዎች ወደ መገባደድ መድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡
በሚቀጥሉት ጊዜያትም አሁን ላይ በባቡር አገልግሎቱ ማጓጓዝ ከሚቻለው ሁለት ሚሊዮን ቶን አቅሙን ወደ አራት ሚሊዮን ቶን ከፍ ለማድረግ ዕቅድ ተያዞ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በባቡር ትራንስፖርቱ ላይ የነበረው የኃይል መቆራረጥ ችግር ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በቅንጅት በመሥራት ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ችግሩ ተቀርፎ ተገቢውን አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡
ከስርቆትና ከውድመት ጋር ተያይዞ የነበረውን ችግር ለመቅረፍ ደግሞ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተገቢው ሥራ በመከናወኑ ስርቆቱን ከ85 በመቶ በላይ መቀነስ መቻሉን አስረድተዋል።
ከውጭ የሚገቡ የባቡርት ትራንስፖርት መቀያየሪያ ዕቃዎችን ለመግዛት የውጭ ምንዛሬ እጥረት ከፍተኛ ችግር ሆኖ ቆይቷል ያሉት ዶክተር አብዲ፤ አሁን ላይ ችግሩን ለመቅረፍ ከብሔራዊ ባንክ ጋራ በጋራ በመሥራት መፍትሄ ለማግኘት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በተያያዘ ለባቡር ትራንስፖርት አቅም ማደግና የኢንዱስትሪና የቴክኖሎጂ ትራንስፎርሜሽንን ለማሳደግ የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ጠቀሜታው የጎላ ነው ያሉት ዶክተር አብዲ፤ የተለያዩ ዓይነት ግብዓቶች በብዛትና በፍጥነት ማቅረብ እንዲሁም በዘርፉ የዳበረ እውቀትና ልምድ ለማግኘት ኢትዮጵያ ከኢኒሼቱቩ ይበልጥ ተጠቃሚ መሆን እንደምትችል አመላክተዋክል።
ልጅዓለም ፍቅሬ
አዲስ ዘመን ኅዳር 25 ቀን 2016 ዓ.ም