በስፔኗ የባህር ዳርቻ ከተማ ቫሌንሲያ ታላቁ የቫሌንሲያ ትሪኒዳድ አልፎንሶ ማራቶን ትናንት ሲካሄድ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታ የበላይነት ይዘው ፈፅመዋል። የዓለማችን ከዋክብት አትሌቶች በተፋለሙበት በዚህ ውድድር ብዙም የአሸናፊነት ግምት ያልተሰጠው አትሌት ሲሳይ ለማ የቦታውን ክብረወሰን በመስበር አሸናፊ ሆኗል። በሴቶች አትሌት ወርቅነሽ ደገፋ አሸንፋለች።
የ2021 ለንደን ማራቶን አሸናፊው ሲሳይ ርቀቱን ለማጠናቀቅ 2:01:48 የወሰደበት ሲሆን፤ ይህም የቦታውን ክብረወሰን ከመሆን ባሻገር የራሱን ምርጥ ሰዓት ያሻሻለበት ሆኗል። በተጨማሪም ከጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በመቀጠል ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ የማራቶን ፈጣን ሰዓት ባለቤት አድርጎታል።
ሲሳይ ለማ ገና ከጅምሩ ጠንከር ያለ ፍጥነት በመሮጥ ከሌላኛው ኢትዮጵያዊ ዳዊት ወልዴ እና ኬንያዊው ኪቢወት ካንዲ ጋር መሪነቱን ቢቀላቀልም ከ35ኛው ኪሎ ሜትር በመምጣት ውድድሩን በ 2፡01 48.በሆነ ድንቅ ሰአት የፍጻሜውን መስመር በማለፍ ባለፈው ዓመት በኬንያዊው ኬልቪን ኪፕተም (2:01:52) የተያዘውን የቦታውን ክብረወሰን ሰብሯል። በዚህ ውድድር ትኩረት ያልተሰጠው ኬንያዊው አትሌት አሌክሳንደር ሙቲሶ ሲሳይን ተከትሎ በመግባት በ2:03:10 ሁለተኛ ሆኖ አጠናቋል። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ዳዊት ወልዴ 2:03.48 በመግባት ሦስተኛ ደረጃ ይዞ ሲያጠናቅቅ፣ በርቀቱ ከፍተኛ የአሸናፊነት ግምት ተሰጥቶት የነበረው ቀነኒሳ በቀለ 2:04.19 አራተኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል።
የዓለማችን ሦስተኛው ፈጣን የማራቶን ሰአትን በ2፡01.41 በበርሊን 2019 ማራቶን የጨበጠው ቀነኒሳ በቀጣዩ የፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ ለአራተኛ ጊዜ ሀገሩን ለመወከል ትልቅ ጉጉት የነበረው ሲሆን፤ እዚያ የሚያደርሰውን ቲኬት ለመቁረጥ የሚያስችለውን ሚኒማ ለማሟላት ያለው ብቸኛ አማራጭ ይህ የቫሌንሲያ ማራቶን ነበረ። ለዚህም ጥሩ ዝግጅት በማድረግ ከፍተኛ አሸናፊነት ግምት አግኝቶ ነው ወደ ውድድር የገባው።
ጀግናው አትሌት ከውድድሩ ቀደም ብሎ “ከዚህ ቀደም በትራክ እና በሀገር አቋራጭ ውድድሮች ላይ የተቀዳጃቸውን ታላላቅ ድሎች በጎዳና ላይ ውድድሮች መድገም አልቻልኩኝም። በማራቶንም የአቅሜን ያህል ስኬታማ ነኝ ብዬ አላስብም። ለረጅም ጊዜያት ከጉዳት ጋር ስታገል ቆይቻለሁ። ጠንካራ ልምምዶችን ስሰራ ቆይቻለሁ፤ ነገር ግን ልምምዶቼን በጥሩ መንገድ ጨርሼ አላውቅም። አዕምሮዬ የሚነግረኝ አሁንም በማራቶን የተሻለ ነገር መሥራት እንደምችል ነው። ብዙ ግቦች አሉኝ። ኦሊምፒክ ከፊታችን አለ። ምናልባትም ፓሪስ የመጨረሻው ኦሊምፒኬ ሊሆን ይችላል።” በማለት ተናግሮ ነበር። ይሁን እንጂ የቀድሞው የኦሊምፒክ የሦስት የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ እንዲሁም የ10ና 5ሺ ሜትር ባለክብረወሰን ቫሌንሲያ ላይ ሊሳካለት አልቻለም። ያስመዘገበው 2:04:19 ሰአት ግን የዓለም የአንጋፋዎችን የማራቶን ክብረወሰን የሰበረ ሆኗል።
ቀነኒሳ ከውድድሩ በኋላ በማኅበራዊ ትስስር ገፁ ባሰፈረው መልእክት በቫሌንሲያ ያስመዘገበው ውጤት ወደፊት የተሻለ ሰአት ለማስመዝገብ ተስፋ እንዳሳደረበት ገልጿል። በውድድሩ የነበረው ድጋፍ ከጠበቀው በላይ እንዳስደሰተውና ቫሌንሲያ ክብረወሰን ሊመዘገብበት የሚችል ጥሩ ውድድር እንደሆነ ጠቁሞ ምስጋናውን አቅርቧል።
የ5 እና የ10 ሺ ሜትር የዓለም ክብረወሰኑን ከቀነኒሳ የተረከበው የዓለምና የኦሊምፒክ ቻምፒዮኑ ዩጋንዳዊ አትሌት ጆሽዋ ቼፕቴጌይ የመጀመሪያ የማራቶን ውድድሩን ትናንት ቫሌንሲያ ላይ ማድረጉን ተከትሎ ከቀነኒሳ ጋር የሚያደርገው ፉክክር ከፍተኛ ግምት አግኝቶ ነበር። ይሁን እንጂ ቺፕቴጌ በውድድሩ የተጠበቀውን ብቃት ሳያሳይ አቋርጦ ወጥቷል።
በሴቶች መካከል በተካሄደው ውድድር ከወሊድ መልስ ውድድሯን ያደረገችው አትሌት ወርቅነሽ ደገፋ በድንቅ ብቃት ወርቁን አጥልቃለች። ወርቅነሽ በ2፡15.51 ሰአት የግል ምርጥ ሰአቷን በማሻሻል በታሪክ 7ኛዋ ፈጣን አትሌት ሆናለች። በዚሁ ውድድር የሪዮ ኦሊምፒክን በ10ሺ ሜትር የዓለም ክብረወሰን ታጅባ ያሸነፈችው አትሌት አልማዝ አያና የራሷን ፈጣን ሰዓት አስመዝግባ 2ኛ ሆና ስታጠናቅቅ፤ ህይወት ገብረኪዳን 3ኛ በመሆን ውድድሩ በኢትዮጵያውያን የበላይነት ሊጠናቀቅ ችሏል። የቀድሞዋ የ1500 ሜትር የዓለም ቻምፒዮን የክብረወሰን ባለቤት ገንዘቤ ዲባባ ውድድሩን ማጠናቀቅ አልቻለችም።
የቦስተን እና የዱባይ ማራቶን አሸናፊዋ አትሌት ወርቅነሽ በ33 ዓመቷ ወደ ቀድሞ ድንቅ ብቃቷ የተመለሰችበትን ውጤት በቫሌንሲያ አሳክታለች። ወርቅነሽ ያለፉትን ሁለት ዓመታት ሁለት ጊዜ በወሊድ ምክንያት ከውድድር ርቃ ቆይታለች። አትሌቷ ከሳምንታት በፊት ወደ ውድድር በተመለሰችበት መድረክ የግማሽ ማራቶን ርቀትን 1:07:48 በሆነ ሰአት አጠናቅቃ ወደ ቀድሞ ብቃቷ ለመመለስ ብዙ እንዳልራቀች አሳይታ ነበር።
ሁለተኛ በመሆን ያጠናቀቀችው የ32 ዓመቷ አትሌት አልማዝ አያና ፊቷን ወደ ማራቶን ካዞረች ጥቂት ጊዜ ቢሆናትም በመድረኩ ግን እያስመዘገበች ያለው ውጤት ብዙዎችን ያስደነቀ ሆኗል። አልማዝ ባለፈው በአምስተርዳም ማራቶን የመጀመሪያ ማራቶን ውድድሯን ማሸነፏ ይታወሳል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ኅዳር 24 ቀን 2016 ዓ.ም