አሁን ያለንበት ወቅት 2016/17 የመኸር ምርት የሚሰበሰብበትና አርሶ አደሩ ለቀጣይ ሥራ የሚዘጋጅበት ነው። ‹‹አንድ ክረምት የነቀለውን አስር ክረምት አይመልሰውም›› እንደሚባለው አርሶ አደር የክረምት ወቅት በረከቱን ሰብስቦ ጎተራውን ይሞላል። ከዚያም የቀጣዩን ሥራ ለማስጀመር ደፋ ቀና ይላል። እንደሚታወቀው አሁን ላይ በኢትዮጵያ የምርት ጊዜያት በርከት እያሉ መጥተዋል። ለወትሮው በዓመት አንድ ጊዜ ክረምት ተጠብቆ የሚሠራው የግብርና ሥራ ዛሬ በተለያዩ አካባቢዎች የበጋ መስኖ ተለምዷል።
በመኸር የተዘራው ሰብል ተሰብስቦ ሲያበቃ የሚቀጥለው የመስኖ ሥራ ነው። ይህ የመስኖ ሥራ ታዲያ በርካታ ግብዓቶችን ይፈልጋል። ከእነዚህም መካከል አርሶ አደሩ በብዙ ሲፈተንበት የቆየው የአፈር ማዳበሪያ ጉዳይ ነው። የአርሶ አደሩን የማዳበሪያ ጥያቄ ለመመለስ መንግሥት የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ እንደቆየ ይታወቃል። ይሁንና በተለያዩ ምክንያቶች የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ፈተና ሆኖ ቆይቷል።
ሀገራዊ እድገት እና ምጣኔ ሀብታዊው መሠረቱ በግብርና ትከሻ ላይ ለተመሠረተባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት የአርሶ አደሩን ፍላጎት አለማሟላት ጎን ለጎን በርካታ ችግሮችን የሚያስከትል ነው። አርሶ አደሩ ዛሬን እንደምንም ቢወጣው ነገ ሕዝቡ ላይ የሚፈጥረው ጫና ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። በመሆኑም አርሶ አደሩ የሚያስፈልገውን የግብርና ግብዓቶች ለማሟላት ቀድሞ ማሰብ የግድ ይሆናል። ለዚህም ነው የአምናው ዘንድሮ እንዳይደገም በሚል ግብርና ሚኒስቴር ከወዲሁ የአፈር ማዳበሪያ ገዝቶ ወደ አርሶ አደሩ ለመድረስ ደፋ ቀና እያለ የሚገኘው።
ከሰሞኑ የግብርና ሚኒስቴር የአፈር ማዳበሪያን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል። ይህም በኢትዮጵያ አንገብጋቢ የሆነውን የአፈር ማዳበሪያ ቀድሞ መግዛትን ይመለከታል። ምን ያህል ተገዛ፤ ምን ያህሉ ሀገር ውስጥ ገባ፤ ምን ያህሉ ጅቡቲ ወደብ ደረሰ የሚሉና መሰል ጉዳዮችን የገለጹት የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶክተር) ናቸው።
እርሳቸው እንዳሉት፤ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ የሚፈጸመው በፌዴራል መንግሥት አማካኝነት ሲሆን፤ ሀገር ያላትን አቅም መነሻ በማድረግ ይከናወናል። በዚህም መሠረት ለ2016/17 የምርት ዘመን ከ23 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ በእቅድ የተያዘ ቢሆንም በዘንድሮ የምርት ዘመን ሀገሪቷ ያላት የመግዛት አቅም 19 ነጥብ አራት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ መሆኑ ታውቋል። ለዚህም 930 ሚሊዮን ዶላር ወጪን ጠይቋል። ከዚህ ውስጥም እስካሁን የ14 ነጥብ 79 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ተፈጽሟል።
በአርሶ አደሩ ዘንድ በጣም ተፈላጊ የሆኑ የማዳበሪያ ዓይነቶች ሁለቱ ናቸው። እነርሱም ኤን ፒ ኤስ እና ዩሪያ ሲሆኑ፤ እነዚህም አጠቃቀማቸው ግን ልዩነት አለው። ለአብነት እንደ ሀገር ባለው አጠቃቀም በዘር ወቅት የሚያገለግለውና የሚጠቀመው የአፈር ማዳበሪያ ኤን ፒ ኤስ / ኤን ፒ ኤስ ቦሮን/ ሲሆን፤ 60 በመቶውን ይይዛሉ። አርሶአደሩ ሰብሉ በቡቃያ ወቅት ሲደርስ የሚጠቀመው ዩሪያ ደግሞ 40 በመቶን የሚሸፍን ነው። ከ19 ነጥብ አራት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ ስምንት ነጥብ ሁለት ኩንታል የዩሪያ አፈር ማዳበሪያ ሲሆን ቀሪው 11 ነጥብ 19 ሚሊዮን ኩንታል ደግሞ ኤን ፒ ኤስ መሆኑን ያስረዳሉ።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለጻ፤ ባለፈው ዓመት ለትግራይ ክልል የተገዛውን የአፈር ማዳበሪያ ሳይጨመር 12 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ተገዝቷል። ከዚህ የዘንድሮው አንጻር ከፍተኛ ጭማሪ አለው። በዚህ ደግሞ የምርት ዘመኑን ኢትዮጵያ በታሪኳ ከፍተኛ የሆነ የማዳበሪያ ግዥ የፈጸመችበት ያደርገዋል። ከዚያም ባሻገር ይህ የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያውን ፈጥኖ በማስገባትም ጥሩ አፈጻጸም የታየበት ነው።
እሳቸው እንዳሉት፤ የመጀመሪያዋ መርከብ ታኅሣሥ 18 ቀን 2015 ዓ.ም የደረሰች ሲሆን፤ በዚህ ዓመት ደግሞ 51 ሺህ 420 ሜትሪክ ቶን ዩሪያ የጫነች የመጀመሪያዋ መርከብ በጥቅምት ወር ጅቡቲ ወደብ ላይ ደርሳለች።
ለ2016/17 የምርት ዘመን እስከ ኅዳር 19 ቀን 2016 ዓ.ም 207 ሺህ 295 ሜትሪክ ቶን የዩሪያ ማዳበሪያ ጅቡቲ ወደብ መድረሱንና ከዚህ ውስጥም 104 ሺህ 304 ሜትሪክ ቶን ዩሪያ ወደ ሀገር ውስጥ መጓጓዙን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ከኅዳር 21 እስከ ታኅሣሥ 4 ቀን 2016 ዓ.ም ደግሞ 174 ሺህ 500 ሜትሪክ ቶን ኤን.ፒ.ኤስ ቦሮን የጫኑ ሶስት መርከቦች ወደ ጅቡቲ የሚደርሱ እንደሆነ በወቅቱ አስረድተዋል።
በተደጋጋሚ እንደተገለጸው የአፈር ማዳበሪያ ጉዳይ ለከፊል አርብቶ አደሩና አርሶ አደሩ ቀድሞ እንዲደርስ ከማድረግ አንጻር በርካታ ማሻሻያዎችን ማድረግ እንደቻሉ ያስረዱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ለዚህ ስኬት ደግሞ የተለያዩ ምክንያቶች እንዳሉት ጠቅሰዋል። ከእነዚህ ምክንያቶች መካከልም ቀድሞ የነበረውን የግዢ መመሪያ መቀየር፤ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ቦርድ በአዲስ መልክ እንዲደራጅ ማድረግ እና የቴክኒክ ኮሚቴ እንዲቋቋም መሆኑ፣ የተለያዩ የግዢ አማራጮችን በመጠቀም ግዥ ማከናወንና የማዳበሪያ ዋጋ በሚቀንስበት ጊዜ ጠብቆ ግዢውን ማከናወን የሚሉት ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም እስካሁን ድረስ ሆኖ የማያውቀው 11 ኤልሲ መከፈቱ፤ ለመስኖ፤ ለበልግና ለመኸር አፈር ማዳበሪያ የሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች የትኞቹ ናቸው ተብሎ መለየቱና ግዢ መፈጸሙ ደግሞ ስኬቱ ቀጣይነት እንዲኖረውና ማረጋገጫ የሚሰጥ እንዲሆን የሚያስችል እንደሆነ ነው የተናገሩት። አሁን ባለው የግዢ መጠን ትንሽ የሚቀረው ለመኸር የሚሆን ነው። ለዚህም ሰሞኑን የተወሰነ ግዢ የተፈጸመ ሲሆን፤ ቀሪውን ደግሞ የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ የሚቀንስበት ወቅት እየታየ የሚገዛ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ሚኒስቴር ዴኤታዋ ማብራሪያ፤ ግብርና ሚኒስቴር የሚቆጣጠረው ከጅቡቲ ተነስቶ እስከ ማዕከላዊ መጋዘን ያለውን የመጓጓዝ ሁኔታ ነው። መረጃ የሚሰጠውም ይህንን መሠረት አድርጎ ሲሆን፤ አርሶ አደሩ ጋር ባለፉት ሁለት ዓመታት በደረሰው ዋጋ እንዲደርስ በማሰብና ከምርት በኋላ የገበያው ዋጋ እንዳይጨምር ለማድረግ በመንግሥት በኩል የዋጋ ተመኑ ይወጣል። ያንን ተከትሎ አንዳንድ የትራንስፖርትና ጫኝ አውራጅ እንዲሁም የመጋዘን ኪራይ የመሳሰሉት በክልሉ ከደረሰ በኋላ በመጨመር ለአርሶ አደሩ የሚደርስ ይሆናል። ስለዚህም ዘንድሮ እንደ አምናው አርሶ አደሩ የዋጋ ጉዳይ አያሳስበውም። በአምናና በካቻምና ዋጋ የሚገዛበት እድል ተመቻችቶለታል።
በዚህ የምርት ዘመን በማዳበሪያ ግዢ ዙሪያ ቁጠባን ጭምር ያየንበት ነው። ምክንያቱም የማዳበሪያ ፍላጎታችንን ከፍ በማድረግ የመንግሥትን የድጎማ ጫና ቀንሰናል የሚሉት ሚኒስቴር ዴኤታዋ፤ ባለፈው ዓመት አንድ ቢሊዮን ዶላር ተሰጥቶን የትግራዩን ሳይጨምር 12 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል መግዛት ተችሏል። በዘንድሮው ዓመት ግን 930 ሚሊዮን ዶላር ተፈቅዶልን እስከ 19 ነጥብ አራት ሚሊዮን ኩንታል ተገዝቷል። ለዚህ ደግሞ አዲስ የተቋቋመው የቴክኒክ ኮሚቴ ከአቅራቢዎች ጋር ከፍተኛ ድርድር አድርጎ ግዢው እንዲፈጸም አስችሏል። በሌላ በኩል የማዳበሪያ ዋጋ ከፍና ዝቅ የሚልበትን ጊዜ ጠብቆ መገዛቱ አዋጭ ሆኗል።
ሌላው ሚኒስቴር ዴኤታዋ ያነሱት ነገር ያልተገባ የማዳበሪያ ዝውውርና ልውውጥን ለማስቀረት የተሰራውን ሥራ ሲሆን፤ ይህም እንደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ክትትል የሚደረግበትና የአፈር ማዳበሪያው ከጅቡቲ እስከ አርሶ አደር ድረስ መድረሱን የሚያረጋግጥበት ሥርዓት ነው። ሥርዓቱ ሰርቋል አልሰረቀም የሚለውን ለማሳደድ ሳይሆን፤ ለአርሶ አደሩ ማዳበሪያው መድረሱን ዋስትና ለመስጠት መሆኑን ገልጸዋል። ለአብነት አምና የገጠመው ዋነኛ ችግር አማራ ክልል ላይ በሕገ ወጥ ሲዘዋወር የነበረው የአፈር ማዳበሪያ ሲያዝ ከኦሮሚያ ነኝ ይላል፤ ኦሮሚያ የተያዘውም አማራ ክልል ነኝ ይላል። ስለሆነም ተጠያቂ ለማድረግ አልተቻለም። አሁን ግን ከመነሻው ጀምሮ በኮድ ተይዞ የሚወጣ በመሆኑ ወጥቶ ቢሸጥ እንኳን የመያዝ እድል አለው ብለዋል። ሥርዓቱ ተጠያቂነትን ጭምር የሚያሰፍን በመሆኑ በዚህ ዓመት እውን ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዚሁ የምርት ዘመን ሌላም ተግባራዊ የሚደረግ ሥራ ስለመኖሩ የገለጹት ሚኒስቴር ዴኤታዋ፤ ይህም ከአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ጋር ተያይዞ የሚከወነው ተግባር አዳዲስ ክልሎች ወደ ሥርዓቱ ማስገባትን ያለመ ነው። በመሆኑም ከግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የአፈር ማዳበሪያን በግዢ የሚወስዱ ክልሎች ይኖራሉ። አንዱ ደግሞ አፋር ክልል ሲሆን፤ ከማዕከላዊ መጋዘን ግዢው በይፋ ይጀመርለታል። በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ የጋምቤላና የሱማሌ ክልልን ወደ ግዢ ሥርዓቱ የማስገባት ሥራ ይከናወናል። ይህ መሆኑ ደግሞ ከማዕከላዊ መጋዘናቸው በቀላሉ የአፈር ማዳበሪያውን እንዲገዙና እንዲጠቀሙ ያስችላቸዋል ብለዋል።
የ2016/17 ምርት ዘመን የማዳበሪያ ሥርጭቱን በተመለከተ ከጸጥታ አኳያም ችግር እንዳይገጥምና ሥርጭቱ እንዳይስተጓጎል ከክልሎች ጋር በመነጋገር እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በእጀባ ጭምር ማዳበሪያ ወደ ክልሎች እየገባ እንደሆነ ገልጸዋል። የአፈር ማዳበሪያን በስፋት የሚወስዱ ክልሎችን በመጥቀስ ካለፈው ዓመት ጋር ያነጻጸሩት ሚኒስቴር ዴኤታዋ፤ ትግራይ ክልል ባለፈው ዓመት 800 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ የተገዛለት ሲሆን፤ በዘንድሮው ደግሞ 700 ሺህ የአፈር ማዳበሪያ ተገዝቶለታል። በተመሳሳይ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የአፈር ማዳበሪያ የሚጠቀሙት አማራና ኦሮሚያ ክልሎች ሲሆኑ፤ ኦሮሚያ ክልል ባለፈው ዓመት አምስት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል የቀረበለት ሲሆን፤ በዚህ ዓመት ስምንት ነጥብ 92 ሚሊዮን ኩንታል የሚወስድ ይሆናል። ባለፈው ዓመት አምስት ነጥብ ሁለት ያገኘው አማራ ክልል ደግሞ በዚህ የምርት ዘመን ስምንት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እንዲያገኝ ይደረጋል ነው ያሉት።
መንግሥት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የማዳበሪያ ዋጋ ጭማሪ ቢኖርም የአርሶና ከፊል አርብቶ አደሮችን አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት በየዓመቱ ያደረገውን ከፍተኛ ድጎማ ያነሱት ሚኒስቴር ዴኤታዋ፤ ባለፉት ሶስት ተከታታይ ዓመታት ያሉትን መረጃዎች ሲጠቅሱ መንግሥት የ52 ቢሊዮን ብር ድጎማ ማድረጉን ነው ያብራሩት። ይህም ማለት በ2014/ 15 የምርት ዘመን 15 ቢሊዮን ብር፤ በ2015/16 ምርት ዘመን 21 ቢሊዮን ብር እንዲሁም በ2016/17 ምርት ዘመን 16 ቢሊዮን ብር በድምሩ 52 ቢሊዮን ብር ድጎማ ተደርጓል። ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ ገበያውን ከማረጋጋት አኳያ የማይተካ ሚና እንዳለው በመታመኑ ነው ብለዋል።
እነዚህ ተግባራት መከናወናቸው በርካታ ችግሮችን እንደሚፈቱ ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ አንዱ እስከዛሬ እንደሆነው ሚያዝያና ሰኔ እንዲሁም ሌሎች ወቅቶች ላይ የሚዘራው አርሶ አደር እስከ ሰኔ እኩል ማዳበሪያ ፍለጋ እንዳይሰለፍ ያደርገዋል። ሌላኛው ደግሞ ከኮርፖሬሽኑ ማዳበሪያ በመውሰድ ችግሩ ወደ ገጠመበት ቦታ ለማድረስ መሯሯጥ አይኖርም። ከክልል ክልል ማዳበሪያ የማዘዋወር ሥራም አይከናወንም። በቀጥታ የሚያስፈልጋቸውን የአፈር ማዳበሪያ በጊዜው ከማከፋፈያ ማዕከላቸው እንዲያገኙ ይሆናሉ። ክልሎችም ሆኑ አርሶ አደሮች ይህንኑ አውቀው መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ኅዳር 24 ቀን 2016 ዓ.ም