አንድ ሀገር በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ብላ ከምትደምቅባቸው ጉዳዮች አንዱ በዲፕሎማሲ ዘርፍ የሚኖራት ተቀባይነትና ስኬት ነው። ይህ ተቀባይነት እንደ ሀገር ለመገንባት ለምትሻው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ሥርዓቶች ተቀባይነት የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነም ይታመናል።
በተለይም አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት በመገንባት፤ በሕዝቦቻቸው ነገዎች ላይ ብርሃን ለመፈንጠቅ ጥረት በማድረግ ላይ ለሚገኙ ሀገራት በዲፕሎማሲው ዘርፍ የሚገኙ ስኬቶች በቀላሉ የማይገኙ፣ በብዙ መንገድ ስትራቴጂክ ሆኖ መንቀሳቀስን የሚጠይቁ ናቸው።
ዓለም በብዙ ፍላጎቶች በተወጣጠረችበት፤ እነዚህ ፍላጎቶች በተለያዩ ጎራዎች ዳግም እየከፋፈሉ ባሉበት በዚህ ዘመን ፤ የሀገርና የሕዝብን ዘላቂ ተጠቃሚነት ማጽናት የሚያስችል አቋም ይዞ፤ በመካከለኛው መንገድ፤ በመርህ መጓዝ ከዛሬ ተሻግሮ ነገዎችን ማየት የሚያስችል የአመራር ብስለትን የሚጠይቅ ነው።
በተለይም ራሳቸውን ሆነው በራሳቸው መንገድ እጣ ፈንታቸውን ለመቅረጽ ሌት ተቀን ለሚተጉ በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት በዲፕሎማሲው መድረክ የሚያጋጥማቸው ተግዳሮት በቀላሉ የማይታይ፤ ነገዎቻቸውን ብቻ ሳይሆን ዛሬዎቻቸው ላይ ጭምር ዋጋ ሊያስከፍላቸው እንደሚችል ከትናንት ተሞክሮዎች መረዳት የሚከብድ አይደለም።
ሀገራችን ኢትዮጵያም ለዘመናት ካካበተቻቸው የዲፕሎማሲ ተሞክሮዎች በመነሳት፣ ለረጅም ዘመናት በዓለም ፖለቲካ ውስጥ ገለልተኛ አቋም በመያዝ፣ ሀገርና ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የዲፕሎማሲ መንገዶችን ስትከተል ቆይታለች። በዚህም በዲፕሎማሲው መድረክ ያላት እውቅና ዘመናት ያስቆጠረ ነው።
በተለይም የለውጡ መንግሥት ወደ ስልጣን ከመጣ ማግስት ጀምሮ እንደ ሀገር ድህነትን ታሪክ ለማድረግ የጀመረውን እልህ አስጨራሽ ትግል በስኬት ለማጠናቀቅ ለዲፕሎማሲው ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፤ እየተንቀሳቀሰም ይገኛል።
በችግርም ሆነ በሰላም ወቅት የማይለዋወጥ፤ ወጥነት ያለው፤ ሀገርና ሕዝብን በዘላቂነት ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል፤ ከሁሉም በላይ ለጀመርነው ድህነትን ታሪክ የማድረግ ትግል በሁለንተናዊ መልኩ አቅም መገንባት የሚያስችል የዲፕሎማሲ ስትራቴጂ ተነድፎ እየተሰራም ነው።
በዚህም ከለውጡ ማግስት ጀምሮ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶች፤ ሀገር በሕልውና ስጋት ውስጥ በነበረችበት ወቅት ሳይቀር በተጨባጭ የታየና ሀገርን ከብዙ ውስብስብ ሴራዎች፤ ከዚያም ባለፈ ጠንካራ ኢኮኖሚ በመገንባት ሀገርና ሕዝብን ከከፋ ችግር መታደግ ያስቻለ ነው።
ገና በጠዋቱ ከኤርትራ ጋር የነበረውን በጦርነት የመፈላለግ ያልተቋጨ ታሪካዊ ክስተት በውይይት ወደ ሰላማዊ የታሪክ ምዕራፍ በመቀየር የተጀመረው አዲሱ ሀገራዊ የዲፕሎማሲ ጉዞ፤ በሀገራቱ ሕዝቦች መካከል እፎይታ በመፍጠር የቀደመው የወንድማማችነት መንፈስ እንዲታደስ አድርጓል።
ይህንን ተከትሎ ባለፉት አምስት ዓመታት የተከተልናቸው ሰጥቶ በመቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ፤ ሀገርና ሕዝብን በየትኛውም መልኩ ተጠቃሚ የሚያደርግ የዲፕሎማሲ አቅጣጫ፤ በብዙ መልኩ ስኬታማ በመሆን በክፉ ቀናት ጭምር በጽናትና በእውነት ከአጠገባችን የሚቆሙ ወዳጆችን ማፍራት አስችሎናል።
በዚህም በግልጽም ይሁን በስውር እንደ ሀገር በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በሀገር ውስጥ ያጋጠሙንን፤ ሀገርን እንደሀገር የማፍረስ፤ የመበተን ሴራዎች መሻገር የሚያስችል ትልቅ ጉልበት እንድናገኝ ረድቶናል። ከዚያም ባለፈ ከተለያዩ ሀገራት ጋር የነበረንን ታሪካዊ ግንኙነቶች በማደስ፤ ሀገራቱ ጠንካራ የልማት አጋሮቻችን እንዲሆኑ ረድቶናል።
ሀገራቱ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ድህነትን ታሪክ እናደርጋለን በሚል፣ ቁጭት በፈጠረው መነቃቃት ለጀመርነው እልህ አስጨራሽ ትግል ስኬት የሚጨበጥ አቅም የሚሆኑበትን አስቻይ ሁኔታ በመፍጠር፤ የቀደሙ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ወደ ልማት አጋርነት የሚለወጡበትን ዕድል መፍጠር አስችሎናል።
በአጠቃላይ የለውጡ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ ማግስት ጀምሮ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአውሮፓ፣ በአሜሪካ፣ በኤሲያና በመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ያደረጓቸው ጉብኝቶች ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የዲፕሎማሲ ከፍታ እንድትቀዳጅ ትልቅ ጉልበት ሆነዋል።
እያንዳንዱን ጉብኝት ተከትሎ የሚደረጉ ትላልቅ የልማት ስምምነቶችም የዲፕሎማሲው ስኬቱ ትሩፋት በመሆን ፤ በተለያዩ መንገዶች ወደ ሀገር ውስጥ ከፍ ያለ ሀብት እንዲፈስ በማድረግ፤ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የተለያዩ ጫናዎችን ተቋቁሞ ተከታታይ ዕድገቶችን እንዲያስመዘግብ እየረዳ ነው።
ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ቼክ ሪፐብሊክን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት ያደረጓቸው ጉብኝቶችና ጉብኝቶቹን ተከትሎ የደረሱባቸው የተለያዩ የጋራ ስምምነቶች፤ የሀገራቱንና የዓለም አቀፍ ተቋማትን ግንኙነት ከማደስ ባለፈ፤ ለልማታችን አጋር በመሆን የተሻለ አስተዋጽኦ ማበርከት እንዲችሉ ሰፊ ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ የሚበረታታና ዕውቅና ሊሰጠው የሚገባ ነው፤ ከፈጠረው የዲፕሎማሲ ከፍታም በላይ የሆነ ድል ነው!
አዲስ ዘመን ኅዳር 24 ቀን 2016 ዓ.ም