‹‹የአፍሪካ ደስተኛ እግሮች በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ››

በዓለም አቀፍ ደረጃ ተነባቢ ከሆኑ ጋዜጦች መካከል አንዱ የሆነው ዘ ጋርዲያን በአንድ ወቅት ስለ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የዘገበበት አምድ አርእስት ‹‹የአፍሪካ ደስተኛ እግሮች በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ›› የሚል ነበር:: በሃተታውም በአፍሪካ ግዙፍ፣ አስደሳች፣ በቀለማት የተዋበና ደማቅ ሩጫ ሲሆን፤ አዲስ አበባን ለመመልከትም ከዚህ የተሻለ ጊዜ አይኖርም ሲል አስፍሯል:: በእርግጥም ይህ ሃሳብ የጋዜጣው ብቻ ሳይሆን የሩጫው አካል በመሆን ስሜቱን ያጣጣሙት ሁሉ የሚስማሙበት ሃቅ ነው::

ከባህር ጠለል በላይ ከ2ሺ300 ሜትር ከፍታ በሚበልጠው የአዲስ አበባ አቀማመጥ የሩጫ ውድድር ማድረግ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ከስፖርት ቤተሰቡ የተሸሸገ አይደለም:: ይሁንና ከሌሎች ዓለማት የሚሰባሰቡ ሯጮች ይህንን ምክንያት አድርገው የደማቁንና አጓጊውን ውድድር ተሳትፎ ሊሰርዙ አይችሉም፣ ሩጫው 10ኪሎ ሜትር ብቻ መሸፈኑም የራሱ ሚና አለውና:: ይልቁኑም አስቀድመው በመምጣትና ለቀናትና ሳምንታት ከአየሩ ጋር ራሳቸውን በማላመድ በሯጮቹ ምድር በዓለም ዝናን ካተረፉ አትሌቶች ጋር መሮጥን ይመርጣሉ::

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከ10 ኪሎ ሜትር ሩጫነቱ ባለፈ ያለው ፌስቲቫላዊ ይዘትና አዝናኝነት ደግሞ ደስታቸውን በእጥፍ አሳድጎ ስለውድድሩ ልዩነት ምስክርነት እንዲሰጡ ያስገድዳቸዋል:: እአአ በ2018 ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ላይ ተካፋይ የነበረችው ብራዚላዊቷ አድሪያና ‹‹በአፍሪካ ካሳለፍኳቸው የማይረሱ እና ሰዎችን እንዲሳተፉበት ከምመክራቸው ሩጫዎች መካከል አነዱ ነው›› ስትል ነበር የገለጸችው:: ሌላኛው በተመሳሳይ ዓመት በሩጫው የመሳተፍ እድል የነበረው እንግሊዛዊው ፊሊፕ ደግሞ ‹‹በእርግጥም አስደናቂ የልምምድና የውድድር ሳምንት ነበር፤ ከኢትዮጵያውያን ሯጮች በርካታ ነገር ተምሬያለሁ›› ነበር ያለው::

በዓለም ታሪክ ሊደገሙ የማይችሉ በርካታ የአትሌቲክስ ጅግኖችን ያበረከተችው ኢትዮጵያ፤ የአትሌቲክስ ቤተሰቡ በፎቶም ቢሆን ትዝታቸውን ለማስቀረት የሚያልማቸውን አትሌቶች አትረፍርፋለች:: ታዲያ እነዚህ ድንቅ አትሌቶች በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ተሳትፎ ያላቸው በመሆኑ አብሯቸው መሮጥና በአካል መገናኘት የሚሰጠው ስሜት እግጅ ከፍተኛ ስለመሆኑ አያጠራጥርም:: ይህንን ተከትከሎም በርካቶች ባህር አቋርጠው አዲስ አበባ ላይ ይከትማሉ:: ሩጫን ባህል ያደረጉ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንም በአዘቦቱ የሚኖራቸውን ልዩነት ሁሉ ጥለው በአስደሳች ሁኔታ ዕለቱን ያሳልፋሉ::

ከዓለም ጥቂት አዝናኝ ሩጫዎች መካከል አንዱ የሆነውና የአፍሪካ ግዙፉ የሩጫ ውድድር በፈረንጆቹ ሚሊኒየም ማግስት ነበር የተጀመረው:: የውድድሩ ጠንሳሽ ደግሞ በታሪክ የምንጊዜም ምርጥ አትሌት የሆነው ጀግናው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ነው:: በኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ታሪክ ወርቃማ ተሳትፎ ከተመዘገበበት የሲድኒ ኦሊምፒክ መልስ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን ከእንግሊዛውያን አማካሪዎቹ ጋር በመሆን ነበር ያስጀመረው:: በወቅቱ 10ሺ ሯጮች የተካፈሉበት ሲሆን፤ በሂደት ቁጥሩ እያደገ አሁን ላይ የአትሌቶች ተሳትፎ ብቻ ወደ 500 የሕዝባዊ ሩጫው ደግሞ 45ሺ ደርሷል::

በዚህ ውድድር ላይ ራሱ ኃይሌን ጨምሮ ገብረእግዚአብሄር ገብረማርያም፣ ስለሺ ስህን፣ ጸጋዬ ከበደ፣ ሃጎስ ገብረህይወት፣ ታምራት ቶላ፣ አቤ ጋሻሁን፣ እና በሪሁ አረጋዊን የመሳሰሉ አትሌቶች በወንዶች ተሳታፊ ሊሆኑ ችለዋል:: ክብረወሰኑም እአአ 2006 ላይ በአትሌት ድሪባ መርጋ የተመዘገበው 28:18.61 የሆነ ሰዓት ነው:: በሴቶች ደግሞ ብርሃኔ አደሬ፣ ወርቅነሽ ኪዳኔ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ነጻነት ጉደታ እና ያለምዘርፍ የኋላው የብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው:: ክብረወሰኑም በዚህ ውድድር የሁለት ጊዜ ተሳትፎ ባላት ጠንካራዋ አትሌት ያለምዘርፍ የኋላው ከሁለት ዓመት በፊት የተመዘገበው 31:17 የሆነ ሰዓት ነው::

ሩጫን የአኗኗር ዘይቤ ማድረግ ራዕዩ የሆነው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ፤ በየዓመቱ በህዳር ወር ከሚካሄደውና ግዙፍ ከሆነው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪሎ ሜትር ዓለም አቀፍ ሩጫ ባሻገር በዓመት ውስጥ ሌሎች ውድድሮችንም ያካሂዳል:: ከእነዚህም መካከል የሴቶች ቀንን (ማርች 8) ምክንያት በማድረግ የሚካሄደው የሴቶች ሩጫ፣ የሃዋሳ ግማሽ ማራቶን ሩጫ፣ በበቆጂ የሚካሄድ የቱሪዝም ሩጫ፣ በእንጦጦ የሚደረግ ሳምንታዊ ሩጫ፣ በኢንተርኔት መተግበሪያ አማካይነት በመላው ዓለም የሚደረግ ሩጫ እንዲሁም የተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮችን በማንሳት በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች የሚደረጉ የጎዳና ላይ ሩጫዎች ናቸው:: በሀገር ውስጥ ከሚያዘጋጃቸው ሩጫዎች በተጓዳኝም በጋና እና በደቡብ ሱዳን የሚደረጉ መሰል ውድድሮን በማማከርም በጋራ ይሠራል::

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ህዳር 23/2016

Recommended For You