ወደ አሰባሳቢ እና ተሻጋሪትርክቶች እናማትር!

 ሀገር የብዙ ትርክቶች ድምር ውጤት ነች ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ ባህላዊ ፣ መንፈሳዊ … ወዘተ ። የእነዚህ ትርክቶች ምንነትም ሆነ በትርክቶቹ ዙሪያ ያሉ ትርጓሜዎች የአንድን ሀገር ዛሬዎች እና ነገዎች ከሚወስኑ መሠረታዊ እውነታዎች ዋነኞቹ ናቸው ።

በተለይም የረጅም ዘመናት የሀገረ መንግሥት ታሪክ እና ኅብረ ብሄራዊነት /የብዙ የብሄር ፣ ብሄረሰብና እና ህዝቦች/ መገለጫቸው በሆኑ ሀገራት ማኅበረሰቦች ውስጥ ትርክቶች ሊፈጥሯቸው የሚችሏቸው አሉታዊም ሆኑ አዎንታዊ ተጽዕኖዎች ሀገርን እንደ ሀገር ማጽናትም ፤ ማፍረስም የሚያስችሉ ናቸው ።

ይህ እውነታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተካሄዱ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ጎልቶ የተስተዋለ ነው ፤ ከዚያም መለስ የተለያዩ ሀገራትን ሰላምና መረጋጋት አደጋ ውስጥ በመክተት የሀገራቱ ሕዝቦች ከፍያ ያለ እና ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍሉ አስገድዷቸዋል።

አዶልፍ ሂትለርን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስማቸው የገነኑ አምባገነን መሪዎች ፤ ለፍላጎታቸው ማስፈጸሚያ ይሆን ዘንድ ታሪካዊ እውነታዎችን የሚያጣምሙ ትርክቶችን ከመፍጠር ጀምሮ የትውልዶችን አስተሳሰብ ለጥፋት የሚያነሳሱ ትርክቶችን ፈጥረው ተንቀሳቅሰዋል። በዚህም ዓለምን እጅግ አሳዛኝና ብዙ ዋጋ አስከፍለዋል፡፡

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላም ቢሆን በመላው ዓለም የተካሄዱ ጦርነቶች ሆኑ የሰላም እጦቶች በአብዛኛውን በተዛቡ ትርክቶች የተፈጠሩ ናቸው። ለዚህም በቦሲኒያ እና በሩዋንዳ የተካሄዱ የርስ በርስ ግጭቶችና የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ተጠቃሽ ናቸው ።

በአፍሪካ አህጉር የሚስተዋሉ አብዛኞቹ የሰላም እጦቶችም ዋነኛ ምክንያታቸው በቅኝ ገዥዎች የተፈጠሩ የተዛቡ የጥፋት ትርክቶች ፤ በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚፈጥሯቸው መከፋፈልና አለመተማመን እንደሆነም የተለያዩ ጥናቶች ያመላክታሉ ።

ይህ ችግር በኛም ሀገር ማታየት ከጀመረ ከስድስት አስርት ዓመታት በላይ እያስቆጠረ ስለ መሆኑ ፤ በዚህም ሀገር እንደ ሀገር ብዙ ዋጋ እየከፈለች ስለመሆኑ ምሁራን በስፋት እየተጋገሩ ነው። ችግሩ ሀገርን እንደ ሀገር የህልውና አደጋ ውስጥ መክተቱም በተጨባጭ የተስተዋለ ነው።

በአንድ በኩል ሀገር እንደ ሀገር የተመሰረተቸባቸውን ትርክቶች በማዛባት ያልተገባ ትርጓሜ እንዲኖራቸው በማድረግ ፤ በሌላ በኩል አዳዲስ የተዛቡ /ትናንቶችን ከፋፋይ ትርክቶችን በመፍጠር ሕዝባችን የትርክት ግራ መጋባት ውስጥ እንዲወድቅ ተደርጎ ኖሯል።

ይህ የትርክት ግራ መጋባት በተለይም ሀገር እንደ ሀገር እንዳትቀጥል ለሚፈልጉ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ሆነ የእነርሱ ባንዳ ሆነው ለሚያገለግሉ የውስጥ ኃይሎች የፖለቲካ ስትራቴጂ ሆኖ የመገኘቱ እውነታ ፣ ጉዳዩ እንደ ሀገር ትልቅ አጀንዳ እንዲሆን እያስገደደ ነው።

የሺህ ዓመታት የሀገረ መንግሥት ታሪክ ባለቤት ፣ በተለያዩ ወቅቶች “ትላልቆቹን” ኃይማኖቶች በመቀበል ግንባር ቀደም በመሆን የምትታወቅ ፣ የብዙ ብሄር ፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች መኖሪያ በሆነችው ሀገራችን ትናንቶች ለሁሉም አንድ ዓይነት ቀለም ይኖራቸዋል ተብሎ የሚታሰብ አይደለም ።

እንኳን እኛ ዓለም ከመጣችባቸው የፖለቲካ ፣ የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ትርክቶች አኳያ ለሁሉም አንድ አይነት ቀለም ይኖራታል ተብሎ የሚታሰብ አይደለም ፣ የእያንዳንዱ ትርክት ቀለም የሚወሰነው በዘመኑና ዘመኑን በዋጀው አስተሳሰብ ነው። ተጨባጭ የሆነው የዓለም ታሪከውም የሚመሰክረው ይህንኑ ነው።

እኛም ከዚህ የተለየ የታሪክ እውነት የለንም ፣ ሊኖረን አይችልም ፣ ይኖረናል ብሎ ማሰብም አይቻልም። የትናንት ታሪኮቻችን በተለያዩ ቀለሞች የሚገለጹ ናቸው። እነዚህን ቀለሞች የፈጠራቸው የተፈጠሩበት ዘመን የነበረው አስተሳሰብ ነው።

ያንን አስተሳሰብ ዛሬ ላይ ሆነን መኮነን ሆነ አስተሳሰቡ የፈጠረውን የታሪክ ቀለም መፋቅ አይቻልም ፣ ከዚያ ውጪ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ ፣ ስለ ዛሬይቱ ኢትዮጵያ ዛሬዎችም ሆነ ነገዎች ማሰብ አይቻልም። ለማሰብ መነሳትም ጊዜና አቅምን በከንቱ ከማባከን ውጪ የሚያተርፈው ነገር አይኖርም ።

አሁን ላይ እንደ ሀገር ለጀመርነው ድህነትን ታሪክ የማድረግ እልህ አስጨራሽ ትግል ፣ ኢትዮጵያ እንደሀገር የተመሠረተችባቸውን ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ ባህላዊ፣ መንፈሳዊ … ወዘተ አሰባሳቢ ትርክቶች በአግባቡ ልንረዳቸው ይገባል።

እነዚህ ትርክቶች የተዋጁባቸውን በየዘመኑ የነበሩ አስተሳሰቦች ፣ አስተሳሰቦቹ የፈጠሯቸው ቀለሞች ተቀብለን ከእነርሱ በመማር ነው ትልቅ ሀገር መገንባት ወደሚያስችል የአስተሳሰብ ልእልና ልንሸጋገር የምንችለው። ይህን ማድረግ ስንችል ብቻ ነው ከትናንቶች ወጥተን የዛሬ አሰባሳቢና ተሻጋሪ ትርክቶች ወስጥ መግባት የምንችለው!

አዲስ ዘመን ኅዳር 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You