የትግራይ ክልል አትሌቲክስን ወደ ነበረበት የመመለስ አበረታች ጅምር

ከማርሽ ቀያሪው ምሩጽ ይፍጠር አንስቶ የ5ሺ ሜትር የዓለም ክብረወንን እስከሰበረችው ጉዳፍ ጸጋዬ ድረስ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ኢትዮጵያን የወከሉ 33 ብርቅዬ አትሌቶችን አበርክቷል፤ የትግራይ ክልል። የዘንድሮ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አሸናፊ እንደሆነው ወጣቱ አትሌት ቢንያም መሃሪ ያሉ ተተኪ አትሌቶችንም በማፍራት ላይ ይገኛል። በተለያዩ ስፖርቶች ብሄራዊ ቡድንን መወከል የቻሉ በርካታ ስፖርተኞችን በማፍራት እንዲሁም በሀገር ውስጥ ውድድሮችም ጠንካራ ፉክክር በማድረግ ከሚጠቀሱ ክልሎች መካከል አንዱ ትግራይ ነው። ከ2012 ዓም አንስቶ እስካለፈው ዓመት ድረስ በክልሉ በነበረው ጦርነት ምክንያት ተጎጂ ከሆኑ ዘርፎች አንዱ ስፖርት ነው። ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ ክልሉን መልሶ ለማቋቋም እየተደረጉ ከሚገኙ ጥረቶች አንዱም የስፖርቱ ዘርፍ ነው።

የትግራይ ክልል በተለይም በአትሌቲክስ ስፖርት ውጤታማ ሲሆን፤ በተለይ እንደ ማይጨው ያሉ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት በርካታ አትሌቶችን በማፍራት ይታወቃል። ነገር ግን በክልሉ በነበረው ጦርነት ምክንያት በሚሊዮኖች የሚገመት ውድመት በአትሌቲክስ ስፖርት ብቻ ደርሷል። የትግራይ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኪዳነ ተክለሃይማኖት ጉዳቱን በተለያየ ዘርፍ ከፋፍለው ይመለከቱታል። የማዘውተሪያ ስፍራዎችን በሚመለከትም፤ ደረጃውን የጠበቀ መም ባለቤት የነበረው የመቀሌ ስታዲየም ከባድ ተሽከርካሪዎች ሲንቀሳቀሱበት በመቆየቱ ለብልሽት ተዳርጓል። ቀድሞ በኮረም ለመገንባት መሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት የአትሌቲክስ መንደር እንዲሁም በሂደት ላይ የነበረው የአጭርና ሜዳ ተግባራት ማዕከልም እንቅስቃሴያቸው ሳይጀመር ሊቋረጡ ችለዋል።

በአትሌቲክስ ስልጠና ዘርፍም፤ ክልሉ ቀድሞ የነበሩት 8 ማዕከላት(ከ30-50 አትሌቶችን ያሰለጥኑ የነበሩ) ወደ 6 ሊወርዱ ችለዋል። ምክንያቱ ደግሞ ማዕከላቱ ያስተናገዱት ጉዳት ሲሆን፤ የስልጠና ቁሳቁሶችም ተዘርፈዋል። ለአብነት ያህል ውጤታማው የማይጨው አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል በአጠቃላይ ሲተመን 30ሚሊዮን ብር የሚገመት ጉዳት ደርሶበታል። ክለቦችን ሳይጨምር በጠቅላላው የክልሉ አትሌቲክስ ስፖርት ያስተናገደው ጉዳትም ከ43 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑም በቀረበው ሰነድ ተመላክቷል። በስፖርቱ ላይ የደረሰው ውድመት የጦርነት አስከፊነት በሁሉም ዘርፍ አውዳሚ መሆኑን ያሳየ ሲሆን፤ ከንብረት ባለፈ በርካታ የስፖርቱ ባለሙያዎች ህይወትም ተቀጥፏል። ከእነዚህም ውስጥ ጥቂት የማይባሉት አትሌቶች ናቸው። ይህ የደረሰው አስከፊ ጉዳት ሲጠቃለልም ስፖርቱን ወደኋላ የመለሰ እንደነበረም ፕሬዚዳንቱ አስታውሰዋል።

ከሰላም ስምምነቱ በኋላም ስፖርቱን ለማገዝ የሚያስችል የ2 ሚሊዮን ብር እና የትጥቅ ድጋፍ የተደረገለት ሲሆን፤ በዚህም አበረታች የሚባሉ ሥራዎች ተከናውነዋል። የስልጠና ማዕከላትን ወደ ሥራ ለመመለስ በተደረገ ጥረት 6 የሚሆኑት በተቻለ አቅም ስልጠናቸውን ጀምረዋል። የፕሮጀክቶች ውድድር በማዘጋጀትም ማዕከላቱ እንዲሁም ክለቦች የአትሌቶች ምልመላ ማድረግም ችለዋል። የመደበኛ ውድድሮች ተሳትፎን በሚመለከትም ባለፈው ዓመት በተካሄደው 52ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ላይም አትሌቶችን አሳትፏል። በሌላ በኩል ክልሉ ስፖርቱን በማነቃቃት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የቆየውን ህዝብ ለማንቀሳቀስ የተለያዩ ስራዎች እያከናወነ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል አንዱ ህዝባዊ የጎዳና ሩጫዎችን ለአራት ጊዜያት በተከታታይ(በመቀሌ እና አክሱም ከተሞች) ማዘጋጀት ነው።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ባለፈው ሳምንት በክልሉ ያካሄደውን ጠቅላላ ጉባኤ ተከትሎ የተደረገው የማራቶን ሪሌ ውድድርም ስፖርቱን በማነቃቃት ረገድ ከተከናወኑ ሥራዎች መካከል ተጠቃሽ ነው። ሀብት ለማሰባሰብ በዕቅድ ቢሰራም በስፖንሰሮች ተሳትፎ ማነስ ምክንያት ውጤታማ ሊሆን አልቻለም። በዚህና ክልሉ ከነበረበት ሁኔታ አንጻርም ስፖርትም ሆነ አትሌቲክስ በፋይናንስ ረገድ ያለው ሁኔታ አሁንም ከችግር ያልተላቀቀ መሆኑን ተከትሎም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን 150ሺ ብር ድጋፍ ሰጥቷል። ከጠቅላላ ጉባኤው በኋላም በስፖርቱ ባለሙያዎች አማካኝነት የስነልቦና እና የተሳትፎ ስልጠናም ተሰጥቷል። በተጨማሪም በክልሉ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የ2 ሚሊዮን ብር እገዛ በፌዴሬሽኑ ተደርጓል።

ይህንን ተከትሎም የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽነር ተክላይ ፈቃዱ፤ ፌዴሬሽኑን ጨምሮ የክልል ስፖርት ቤተሰቦች ላደረጉት ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ምንም እንኳን ክልሉ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ቢገኝም ነባራዊውን ሁኔታ መሰረት ባደረገ ሁኔታ የፌዴሬሽኑን ዕቅድ ወስዶ በተግባር ለማዋል የሚሰራ ይሆናል። ስፖርት የሰላምና የወዳጅነት መገለጫ እንደመሆኑ የሰላሙን ፍሬ ማሳያ ይሆናል፤ በሚቀጥለው ጊዜም ክልሉ አሁን ከነበረው ሁኔታ በተሻለ አቋም ላይ እንዲገኝ ጥረቱ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።

ስፖርቱን በበላይነት የሚመራው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ በበኩሏ፤ የገንዘብ ድጋፉ ክልሉ ባለፉት ሶስት ዓመታ ተሳትፎ ስላልነበረው በልዩ ሁኔታ የተበረከተ መሆኑን ገልጻለች። ከዚህ ባለፈ በክልሉ ያሉ የአትሌቲክስ ማዕከላትና ፕሮጀክቶች መሰረተ ልማት የተጎዳ በመሆኑ በምን መልኩ መጠገንና የስልጠና ቁሳቁሶችን መልሶ ወደ ሥራ መመለስ ይቻላል በሚለው ላይ በሥራ አስፈጻሚ ደረጃ ውይይት ተደርጓል።

በተጨማሪም የዳኝነት፣ የአሰልጣኝነትና ሌሎች ሙያዊ ስልጠናዎችም በፌዴሬሽኑ ባለሙያዎች ይሰጣል፤ ፌዴሬሽኑ ይህንን ሲወስንም በደስታ ነው። ከክልሉ የወጡ አትሌቶች ያለባቸውን ጫና ችለው በኦሊምፒክ፣ በሁለት የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናዎች፣ በወጣቶች ቻምፒዮና እንዲሁም በቤት ውስጥ ውድድሮች ኢትዮጵያ የተሻለ ውጤት እንድታገኝ አድርገዋል። በዚህም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከልብ ያመሰግናል፤ የጥንካሬ ተምሳሌቶች ናቸውም ብላለች።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘም ህዳር 22/2016

Recommended For You