አረብ ኢምሬትስ ለአየር ንብረት መፍትሔዎች የ30 ቢሊዮን ዶላር ፈንድ አቋቋመች

የአረብ ኢምሬትስ ፕሬዚዳንት ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ ሀገራቸው ለአየር ንብረት ለውጥ መፍትሔዎች የ30 ቢሊዮን ዶላር ፈንድ ማቋቋሟን አስታወቁ።

ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ ይህንን ያሉት 28ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ28) በመሪዎች ደረጃ ሲከፈት ባደረጉት ንግግር ነው።

በዚሁ ወቅትም ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህንያን ለአየር ንብረት መፍትሔዎች ፈንድ የተቋቋመው የአየር ንብረት ፋይናንስ ክፍተቱን ለመሙላትና እና ገንዘቡ በተገቢው መልኩ ተደራሽነቱን ለማመቻቸት ነው ብለዋል። ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ አክለውም የገንዘብ እጥረት በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ርምጃዎች ላይ ትልቁ እንቅፋት መሆኑንም አብራርተዋል።

አረብ ኢምሬትስ በታዳሽ እና ንጹህ የኃይል ምንጭ መጠቅሟ ላይ ትኩረት እንደምታደርግም ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል። በዚሁ ወቅትም ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ አረብ ኢምሬትስ በቀጣይ 7 ዓመታት ውስጥ ለአየር ንብረት ለውጥ ርምጃ በታዳሽ እና ንጹህ የኃይል ምንጭ ዘርፍ ተጨማሪ 130 ቢሊየን ዶላር ኢንቨስት እንደምታደርግም አስታውቀዋል።

የተመድ ዋና ፀሐፊው በኮፕ28 ጉባኤ ባደረጉት ንግግር፥ የአየር ንብረት ለውጥ ከአንታርቲካ እስከ ኔፓል ጉልህ ተጽዕኖውን እያሳየ እንደሚገኝ ተናግረዋል። “ከፍተኛው የዓለም የሙቀት መጠን በዚህ ዓመት ተመዝግቧል፤ ወደ ከባቢ አየር የተለቀቀው ካርበንም ከፍተኛው ነው፤ ድርቅና ጎርፉም እየተባባሰ ሄዷል” ያሉት አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፥ በፓሪስ የተደረሰውን ስምምነት መፈጸም አለመቻሉ ፈተናውን እያከበደው መሄዱን አብራርተዋል።

በመሪዎች ደረጃ የሚካሄደው 28ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ዛሬ መካሄድ የጀመረ ሲሆን፤ እስከ ነገ ይቀጥላል። በዚሁ የመሪዎች ጉባዔ ላይ የ137 ሀገራት እና መንግሥታት መሪዎች ንግግር እንደሚያደርጉም የወጣው መርሃ ግብር ያመለክታል ሲል የዘገበው አል ዓይን ነው።

 በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘም ህዳር 22/2016

Recommended For You