በስፖርት ውድድሮች ውጤት ላይ ተመስርቶ መወራረድ(ቢቲንግ) መነሻው ከጥንታዊ ሮማውያን ጋር እንደሚያያዝ የታሪክ ሰነዶች ላይ ሰፍሮ ይገኛል። ጥንታዊ ሮማውያን በሠረገላ ውድድር እና በግላዲያተሮች መካከል በሚደረጉ ግጥሚያዎች ላይ ውርርድ በማድረግ እንደጀመሩትም ይታመናል። ይህም በጊዜ ሂደት እያደገ መጥቶ በ19ኛው ክፍለ ዘመን በአውሮፓ የነበረው የእግር ኳስ እድገት አሁን የምናየውን የእግር ኳስ ውርርድ ወልዷል።
ከጥቂት ዓመታት በፊት ቢቲንግ በኢትዮጵያ እምብዛም የተለመደ ነገር አልነበረም። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን እንደ አሸን እየፈሉ የሚገኙ የስፖርት አወራራጅ ድርጀቶች የብዙ ወጣቶችን ቀልብ መሳባቸውን ቀጥለዋል። አቋማሪ ድርጅቶች መጀመሪያ አካባቢ ወደ ኢትዮጵያ መግባት እንደጀመሩ ከሕግ ጋር የተያያዙ በርካታ ውዝግቦች ተነስተው ዛሬም ድረስ መቋጫ አላገኙም። ያም ሆኖ በተለያዩ ከተሞች ሱቆች ጭምር እየተዘጉ በአንድ አዳር የቢቲንግ መቆመሪያ መሆናቸውን ቀጥለዋል።
በአስገራሚ ፍጥነትም ቀደም ሲል የቢቲንግ ሰለባ የሆኑት ወጣቶች ቢሆኑም አሁን አሁን ያገኙትን ቋጥረው አቋማሪ ድርጅቶች በር ላይ አዛውንቶች ሳይቀሩ ሰልፍ ይዘው መታየታቸው ነው። ከተማሪ እስከ ፖሊስ ድረስም ችግሩ እንደዘለቀ እየተመለከትን ነው። ሰሞኑን የሃይማኖት አባት እንኳን ሰው አየኝ አላየኝ ሳይሉ የቁማሩን ትኬት ቆርጠው ከአንዱ አቋማሪ ድርጅት ሲወጡ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማህበራዊ ድረ ገፆች ተሰራጭቶ መነጋገሪያ መሆኑ ችግሩ ምን ያህል ስር እንደሰደደ ማሳያ እስከ መሆን ደርሷል።
በኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 789 መሠረት ሎተሪዎችንና ውርርዶችን የሚመለከቱ ሕጎችን መጣስ አስመልክቶ “ውርርድ ፈቃድ ኖራቸውም አልኖራቸውም ማድረግ የተከለከለ እንደሆነ ያስቀምጣል”። ለመሰብሰቢያ በተዘጋጀ ስፍራ የቁማር ጨዋታ ወይንም ውርርዶችን ወይንም በመንግሥት ክልከላ የተደረገባቸው ሌሎች የዕድል ጨዋታዎችን ከልክሏል። በዚህም ቢቲንግ ወይንም የስፖርት ውርርድ ማድረግ እንደማይቻል ሕጉ አስቀምጧል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ እየተስፋፋ የመጣው የስፖርት ውርርድ (ቢቲንግ) ወጣቱን ኪሳራ ውስጥ እየጣለው እንደሚገኝ እየታየ ዝምታው ቀጥሏል።
ብሔራዊ ሎተሪ የስፖርት ውርርድ እንጂ ቁማር ስላልሆነ ፈቃድ ሰጥቻለሁ፤ እንደውም ለበርካቶች የሥራ እድል ፈጥሯል ይላል። የሕግ ባለሙያዎች “ውርርድ” በሚል ሽፋን ስሙን ለውጦ የመጣው ‹‹ቁማር›› ነው፤ እየተሰጠ ያለው ፈቃድም የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉን የጣሰ ነው ሲሉ ይሞግታሉ። “በግምት ብቻ በአጭር ጊዜ በቀላሉ ሕይወትዎን የሚቀይሩበት ታላቁ ዘዴ” በሚል ማስታወቂያ ተስቦ ወደ ጨዋታው እየገባ የሚገኘውን ሕዝብ ቤቱ ይቁጠረው።
ለጨዋታው ህጋዊ ፈቃድ የሚሰጠው ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ፤ የስፖርት ውርርድ ቁማር ባለመሆኑ ፈቃድ መስጠቱን ደጋግሞ ተናግሯል። ይህ የስፖርት ውርርድ ሎተሪ በመሆኑ በብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ማቋቋሚያ አዋጅ 135/1999 በመመሪያ 83/2005 መሠረት የሚሰጥ የፈቃድ እንደሆነም ተከራክሮበታል። በመመሪያውም ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ውርርዱን ማድረግ እንደማይችሉ ስለፀደቀ ቤቶቹ ይህንን መሠረት አድርገው ይሠራሉ ነው የሚለው።
በአሁኑ ወቅት ይህ ጨዋታ እየተስፋፉና ገበያው እየሰፋ ሕብረተሰቡም እየተሳተፈበት በመሆኑም ከሰላሳ በላይ ድርጅቶች ፈቃድ ተሰጥቷል። በዚህም መንግሥት ከድርጅቶቹ በአማካይ በየወሩ እስከ ስድስት ሚሊየን ብር ገቢ እንደሚያገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ። አቋማሪ ድርጅቶቹ ካገኙት ትርፍ ላይ 20 በመቶ የሚሆነውን ሥራውን ሲጀምሩ ለተዋዋሉት በጎ አድራጎት ድርጅት ገቢ ለማድረግ መገደዳቸው እንደ አንድ ማምለጫ ተደርጎ ተቆጥሯል። ድርጅቶቹ ከአንድ ሺህ 200 ዜጎች በላይ የሥራ ዕድል እንደተፈጠሩና ከጉዳቱ ጠቀሜታው እንደሚያመዝን በመግለጽ ቅሬታ አቅራቢዎቹ የሚያነሱት ሃሳብ ውድቅ ይደረጋል።
ከዚህ በተጨማሪ የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ከድርጅቶቹ ገቢ 15 በመቶውን በኮሚሽን መልክ የሚወስድ ሲሆን ድርጅቶቹ ከደንበኞቻቸው ግብር ሰብስበውም ለመንግሥት ገቢ ያደርጋሉ። በተጨማሪ ዓመታዊ የግብር ግዴታቸውንም ይከፍላሉ።
የሕግ ባለሙያዎች ግን በተለምዶ ውርርድ በሚል ሽፋን ስሙን ለውጦ የመጣው ‹‹ቁማር›› ነው ይላሉ። ቁማር ማለት በአነስተኛ የገንዘብ ወጪ አንድን ያልተገባ ነገር ለማግኘት ማሰብ ነው የሚሉት ሞጋቾች፤ ውርርዱ የስፖርት ጨዋታዎችን በመገመት ግምቱ ትክክለኛ ከሆነ የሚገኝ ገንዘብ እንደመሆኑ ያልተገባ ክፍያ ለመውሰድ የሚደረግ ጥረት ውርርድ ወይንም ቁማር መሆኑን ያስረዳሉ።
“ውርርድ ፈቃድ ኖራቸውም አልኖራቸውም ማድረግ የተከለከለ እንደሆነ ያስቀምጣል”። ለመሰብሰቢያ በተዘጋጀ ስፍራ የቁማር ጨዋታ ወይንም ውርርዶችን ወይንም በመንግሥት ክልከላ የተደረገባቸው ሌሎች የዕድል ጨዋታዎችን ከልክሏል። በዚህም ቢቲንግ ወይንም የስፖርት ውርርድ ማድረግ እንደማይቻል ሕጉ አስቀምጧል።
በሕግ አተረጓጎምም አዋጅ ደንብ ቀጥሎም መመሪያ ነው ፤ የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ አዋጅ በመሆኑ ማንኛውም ይህንን የሚጣረስ መመሪያ ተገቢነትም ሆነ ተፈፃሚነት አይኖረውም። ስለሆነም ፈቃድ ሰጪው አካል በምን አግባብ እንደሰጠ መመርመር ይገባል የሚሉ የማህበረሰብ ተቆርቋሪዎች ዛሬም ድምፃቸው አልተሰማም።
በስፖርታዊ ውድድሮች ገንዘባቸውን ለማስያዝ የሳምንቱ መጨረሻ ቀናትን በጉጉት የሚጠብቁ ጥቂት አይደሉም። የትምህርት ወጪያቸውን የተበሉ፣ ደመወዛቸውን አስረክበው በራሳቸውና በቤተሰባቸው ላይ ሌላ ጣጣ የመዘዙም እንዳሉ በተለያዩ አጋጣሚዎች ወሬው ተሰምቷል። እንደ ሀገር የጉዳዩን አሳሳቢነት ምን ደረጃ እንደደረሰ ጥናት የሚያደርግ ቢኖር ቢቲንግ እየፈጠረ የሚገኘው ማህበራዊ ቀውስ ከዚህም ልቆ ሊገኝ ይችላል።
በስፖርታዊ ውድድሮች መወራረድ ጋር አብሮ የሚነሳ አንድ ችግር አለ። እሱም እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎችና ተማሪዎች በዚሁ ተግባር ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን ሊያጠፉ መቻላቸው ነው። አብዛኛዎቹ አወራራጅ ድርጅቶች ለመወራረድ ከሚመጡት ሰዎች መካከል ምን ያህሉ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች መሆኑን እንደማይቆጣጠሩ ዞር ዞር ብሎ መቃኘት በቂ ነው። አንድ ተማሪ ዩኒፎርም እስካለበሰ ድረስ ለመቋመር ደጅ ቢጠና እድሜህ ስንት ነው የሚለው የለም።
”በስፖርት ውድድሮች ይሄኛው ቡድን ያሸንፋል ሌላኛው ይሸነፋል እያሉ መወራረድ የተለመደና ሁሌም የነበረ ነገር ነው” የሚሉ ግን አይጠፉም። እንዲህ ዓይነት ክርክሮችን የሚያነሱ ሰዎች የስፖርት ውርርድ ድርጅቶች ተገቢውን ቅድመ ሁኔታዎች እስካሟሉ ድረስ ማህበረሰቡ ላይ የሚያሳድሩት ጫና እንደሌለ ይናገራሉ። ስለዚህም ቢቲንግ ቁማር አይደለም የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። ቁማር ሲሆን አንዱ የሚጎዳበት አንዱ ብቻ ደግሞ የሚጠቀምበት ነው። የስፖርት ውርርድ ባህሪው የሎተሪ ነው። ማህበረሰቡ በተለይም ወጣቶች ጊዜያቸውን በሌሎች ነገሮች ላይ ከሚያሳልፉ እየተዝናኑ እድላቸውን የሚሞክሩበት ነው የሚለው በብሔራዊ ሎተሪ ጭምር ድጋፍ ያለው እሳቤ ወጣቱን በዘመን አመጣሹ አዲስ ሱስ ተዘፍቆ እንዲቀር ትልቁን ሚና እየተጫወተ ነው።
የስፖርታዊ ውድድሮች ላይ የሚደረግ ውርርድ ዙሪያ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎችን ድርጅቶቹ እንዳያጫውቱ የሚከለክል መመሪያ የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ባይኖረውም ውርርዱ ላይ ሕጻናት እንዳይሳተፉ ስምምነት አላቸው፣ ተግባራዊነቱን ግን ለመጠርጠር ከበቂ በላይ ምክንያት አለ።
ውርርድ ሱስ የማስያዝ ባህሪ ሊኖረው ስለሚችል ወደፊት የዘርፉን አካሄድ በመመልከትና ተያይዘው የሚመጡ ሌሎች ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ተገቢውን ርምጃ መውሰድ የግድ ነው። ከስፖርታዊ ውርርዶች ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የወጣቶች ሥራ አጥነት፣ ለስፖርታዊ ውድድሮች ያለ ከፍተኛ ፍቅር፣ የላላ የቁማር ሕግና ቀላል የተንቀሳቃሽ ስልክ ክፍያ መንገዶች መብዛት እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ ሀገራት ትልቅ ፈተና ሊደቅኑ እንደሚችሉ ግን ማስታወስ ተገቢ ይሆናል።
ሚዛን
አዲስ ዘም ህዳር 22/2016