በኢትዮጵያ ብዙ ሠዎች ድንገት ህመም ቢሰማቸው አልያም የህመም ስሜት ሲብስባቸው እንደመጀመሪያ መፍትሄ የሚወስዱት ባህላዊ መድኃኒቶችን መጠቀም ነው። ፌጦ፣ ዳማከሴ፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ዝንጅብል፣ ጤና አዳም፣ ሽፈራው (ሞሪንጋ)፣ተልባና የመሳሰሉ እፀዋቶችና አዝርእቶችን በተለያዩ መንገዶች በማዘጋጀት ከህመማቸው ለመፈወስ ይጠቀሙባቸዋል። ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካና በሌላው ዓለም የሚገኙና 80 በመቶ የሚጠጉ ህዝቦች የባህል መድኃኒት እንደሚጠቀሙ መረጃዎች ያመለክታሉ። ባህላዊ መድኃኒቶች በቀላሉ የሚገኙ መሆናቸው፣ ብዙ ሰዎች ‹‹ፈዋሽነት›› አላቸው የሚል እምነትና አስተሳሰብ መያዛቸው፣ በዋጋ ረገድም ተመጣጣኝ መሆናቸው በብዙዎች ዘንድ ተመራጭ ያደርጋቸዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም የባህላዊ መድኃኒቶች አወሳሰድና አጠቃቀም ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ መሆን እንዳለበት በጤና ባለሙያዎች ይመከራሉ። ይህ ሳይሆን ሲቀር ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን እንደሚችል ይነገራል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የባህል መድኃኒትን በስፋት የማስተዋወቁ ተግባር በተለይም በማህበራዊ ሚዲያ በስፋት የመሰራጨቱና የመካሪዎች ቁጥር እየተበራከተ መምጣት በተደጋጋሚ ይታያል። ኢትዮጵያ በአዝርእት እና በእጽዋት የታደለች ሀገር ናት። ይህም ብዙዎች ባህላዊ መድኃኒቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ ያደርጋቸዋል። ይሁን እንጂ ፍቱነቱ እና ደህንነቱ የተረጋገጠ የባህል መድኃኒት ጥናትና ምርምር ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ይታወቃል። የባህል መድኃኒቶቹን አብዝቶ ያለጥንቃቄ የመጠቀሙ ነገር ሲበዛ ጉዳቱ የከፋ ሊሆን እንደሚችል በሚገባ ማጤን ያስፈልጋል።
የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በባህላዊና ዘመናዊ መድኃኒቶች ላይ የተለያዩ ምርምሮችን ያደርጋል። በኢንስቲትዩቱ የባህልና ዘመናዊ መድኃኒት ልማት እና ምርምር ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬሕይወት ተካ እንደሚገልጹት፣ በባህላዊና ዘመናዊ መድኃኒቶች ዙሪያ የምርምር ሥራ ሁሌም እንደሚደረግ መታወቅ አለበት። ጥሩ ውጤት ከሚገኝባቸው የምርምር ውጤቶች ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል የሚሰሩ ስራዎች አሉ። በተለይም የባህል መድኃኒት ላይ የሚደረጉ የምርምር ሥራዎች ላይ ፈታኝ ነገሮች አይጠፉም። ‹‹ማኅበረሰቡ የባህል መድኃኒት ላይ ያለው መረዳት እና ምርምሩ ምንድ ነው?›› የሚለው እንደ አንድ ክፍተት ይጠቀሳል። ከዚህ አኳያም በፍጥነት አገልግሎት ላይ የሚውል የሚመስላቸውም ጥቂቶች አይደሉም።
ፍርዶስ አብዱልሀፊዝ በኢትዮጵያ የምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የመድኃኒት ምዝገባ ዳይሬክተር ክፍል ውስጥ ባለሙያ ሆነው ይሰራሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፣ ባለስልጣኑ ባህላዊውንም ሆነ ዘመናዊ መድኃኒት እየተቆጣጠረ ይገኛል። የሚቆጣጠርበት መንገድ ራሱን የቻለ ሂደቶች አሉት። ባለሙያዎች መጥተው የራሳቸውን መድኃኒት ይዘው ወደ ባለስልጣኑ በማቅናት መመዝገብ መቻል አለባቸው። ቁጥጥር የሚደረግባቸው መድኃኒቶችን በተመለከተም፤ በምን ሁኔታ ነው የተመረቱት? የሚሉትን እና የተለያዩ ሰነዶች እንዲሁም የሚደግፉ ጥናቶች ምንድን ናቸው? በትክክለኛው የአመራረት ሂደት ነው ወይ የተመረቱት? የማምረቻው ቦታ ምን ይመስላል? የሚጠቀሟቸው ግብአቶችስ? እንዲሁም ባሉሙያው ስለመድኃኒት ጥልቅ እውቀት አለው ወይ? የሚለውን አካቶ ፍቃድ በመስጠት ለብዙኃኑ እንዲመረት ይደረጋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች አማካኝነት ባለሙያ ሳይሆኑ እንደባለሙያ ሆነው ሰዎች ባህላዊ መድኃኒትን መጠቀም እንዳለባቸው የሚመክሩ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም። ይህንን በተመለከትም ፍርዶስ እንደሚያብራሩት፤ ዘመናዊም ሆነ ባህላዊ መድኃኒት በማህበራዊ ሚዲያም ይሁን በብዙኃን መገናኛ ማስተዋወቅ በኢትዮጵያ ምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን አዋጅ ቁጥር 1112 የተከለከለ ነው። ይህንን የሚያስተዋወቁ ህገ ወጥ ናቸው። ማኅበረሰቡን ሊያደናግር ይችላል በሚል እሳቤ ክልከላ ተደርጎበታል።
ምርምር በባህሪው ረዥም ጊዜ የሚወስድ እንዲሁም ለአንድ ተመራማሪ የትኛውም ውጤት ቢሆን ውጤት እንደሆነ የሚገልጹት ወይዘሮ ፍሬሕይወት፤ የውጤት ቅበላ ላይ ያለውን ክፍተት ያነሳሉ። ችግሩን ለማቅለል ከባህል መድኃኒት አዋቂዎች ጋር በጋራ በመሆን የምርምር ሥራዎች ይሠራሉ። ነገር ግን ምርምር ሲደረግ እነርሱ ብቻ የፈለጉት እንዲሆን የመፈለግ፤ በተጨማሪም ውጤቱን ለመቀበል ብሎም ጊዜ የሚወስዱ የምርምር ውጤቶችን ታግሶ ያለመቀበል አዝማሚያ በስፋት ይታያል።
ሌላው ፈታኙ ነገር ከእርዳታ ሰጪዎች መካከል አብዛኞቹ በሀገር በቀል የምርምር ሥራን የመደገፍ ፍላጎት የላቸውም። በዚህም መንግሥት በሚሰጠው ገንዘብ ለመሥራት አስገዳጅ ስለሚሆን፤ ጥናቱን በስፋት ለመሥራትም የበጀት እጥረት አለ። በአሁኑ ወቅት መሻሻሎች ያሉ ሲሆን፤ ጤና ሚኒስቴርም ድጋፍ እያደረገ ይገኛል። ከተሠሩ ሥራዎች መካከል እንደ ሀገር የባህል መድኃኒት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል። ከባህል መድኃኒት አዋቂዎች ጋር በመቀራረብና በመተማመን ቢሠራ ችግሩ ይፈታል። የባህል መድኃኒት አዋቂዎችም መንግሥትን ማመን ይኖርባቸዋል።
እንደ ባለሙያዋ ገለፃ፤ በተለያዩ ጊዜ በሚከሰቱ ወረርሽኞች እና የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቷቸው የሚሠሩ ጉዳዮች በመኖራቸው ሥራውን ወደ ጎን በማድረግ፣ ባለሙያዎችን በማሰልጠን እና ሀብቱንም ከመጠቀም አንጻር አመርቂ ሥራዎች አልተሠሩም። የባህላዊ ሀኪሞችም ከባለሙያዎች ጋር በቅንጅት መሥራት ቢችሉ ጥሩ ነበር። በነበር ቁጭት ውስጥ ብቻ ከመኖር ይልቅ ከምርምር አካላት ጋር በጋራ ቢሠሩ የተሻለ እገዛ እንዲያገኙ ይረዳቸዋል።
‹‹በባህል መድኃኒት ላይ ካደጉት ሀገራት መካከል ቻይናና ህንድ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። ከአፍሪካ ደግሞ ደቡብ አፍሪካና ጋና ተጠቃሾች ሲሆኑ ፤ጋና የባህል መድኃኒት ዩኒቨርሲቲ አላት። በኢትዮጵያም ከሚመለካታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ካልተሠራ ብዙ ርቀት ለመጓዝ አዳጋች ይሆናል። ›› የሚሉት ወይዘሮ ፍሬሕይወት፤ በመተባበርና በመቀራረብ ቢሠራ ግን እንደሌሎቹ ሀገራት ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል ያብራራሉ።
እንደ ባለሙያዋ ማብራሪያ፣ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ባህላዊ መድኃኒቶች እና ቁጥጥር የማይደረግባቸው ባህላዊ መድኃኒቶች ተብለው ተለይተዋል። ቁጥጥር ከማይደረግባቸው መካከልም ማንኛውም በቤት ውስጥ የሚወሰዱ ባህላዊ መድኃኒቶች ናቸው። ለአብነትም ጤና አዳም፣ዳማከሴ እና የመሳሰሉት ናቸው። ሁለተኛው ክፍል ደግሞ በባህላዊ ሀኪም የሚሠጥ ባህላዊ መድኃኒት ነው። ባህላዊ ሀኪሙ ራሱ ኃለፊነትን ወስዶ ፤ ራሱ ክትትል አድርጎ የሚሠጣቸው ሲሆን ፤በዚህም ባለሙያው ላይ ሳይሆን መድኃኒቶቹ ላይ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል።
ቁጥጥር የሚደረገው ዝቅተኛ እና ከፍተኛ የጎንዮሽ ጉዳት ያለው የባህላዊ መድኃኒትችን ላይ ነው። ለብዙዎች ተመርቶ የሚቀርብ እንዲሁም በባለስልጣኑ የተመዘገበ ከሆነ ቁጥጥር ይደረግበታል። በዚህ ወቅት የሚያስፈልገው ምንድ ነው? የተጠኑ ጥናቶች፣ የመድኃኒቱ የጎንዮሽ ጉዳቱ ምን ነበር? እስካሁን ሲጠቀሙ ውጤቱ ምንድ ነው? የሚለውን አያይዘው ሊቀርቡ ይገባል።
ባለሙያዋ አክለው እንዳብራሩት፤ የጎንዮሽ ጉዳቱ ስጋት ውስጥ የሚከት (ክሊኒካል) ለሚባሉ ህመሞች ወይም ለረዥም ዓመታት ከታማሚው ጋር የሚቆዩ በሽታ ሲኖር የሚሰጥ ባህላዊ መድኃኒት ነው። እርሱም ቢሆን ጥልቅ የሆነ ጥናታዊ ጽሁፍ የሚያስፈልገው ሲሆን፤ ሰዎችም ላይ ይሁን እንስሳት ላይ የተደረገ ጥናት ውጤት አያይዘው እንዲመጡ ይደረጋል።
የባህል መድኃኒት ተብሎ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሲዘዋወር በብዛት ይታያል። አንዳንዶች መንገድ ላይም ይሁን ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያስተዋውቃሉ። ይህም ህጋዊ አይደለም። ስለሆነም ከህግ ባለሙያዎች ጋር በጋራ በመሆን እየሰራን እንገኛለን። ከዚህ በኋላም ተቋሙ ወደ እርምጃ ይሄዳል። ባህላዊ መድኃኒት በሀገር ደረጃ እስካሁን ያልተጠቀምነበት ሀብት ነው። ቁጭት ውስጥ ሊከተን የሚገባም ጉዳይ ነው። ስለዚህም ከዘመናዊ መድኃኒት ጋር እኩል በእኩል መጠቀም የሚቻልበት ሁኔታዎች መፈጠር መቻል አለበት። ኅብረተሰቡም ያልተመዘገቡ ባህላዊ መድኃኒቶችን ከመጠቀም ቢቆጠብ የተሻለ ይሆናል።
እንደ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ከዚህ በኋላ ኅብረተሰቡ የተመዘገቡ ባህላዊ መድኃኒቶችን በቀላሉ እንዲያገኝ ይደረጋል። ከዚህ አንጻር ከኅብረተሰቡ ጋር አብሮ መሥራት ይገባል። ባህላዊ መድኃኒት ላይ ከፖሊሲ እና ከመመሪያ አንጻር ይሠሩ እንጂ ወደ መሬት አውርዶ ከመሥራት አንጻር ግን ገና ብዙ ጥረቶችን ይጠይቃል።
‹‹አሁን ላይ ጥሩ ጅምሮች አሉ። ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም በጋራ እየተሠራ ሲሆን፤ በተለይም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመናበብ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው። አሁን ላይ መንግሥት ብዙ ድጋፍና ትኩረት የሰጠው ቢሆንም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት መሠራት ይኖርበታል። ከሌላው በተለየ መንግሥት የተለየ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ዘርፉን መደገፍም ብዙኃኑን የባህል መድኃኒት ተጠቃሚውን ማኅበረሰብ የጤና ጥያቄውን ለመመለስ እድል የሚሠጥ በመሆኑ መንግሥት በገንዘብ መደገፍ ይኖርበታል።
ዳይሬክተሯ እንደሚያስረዱት፣ ብዙዎች የባህል መድኃኒት ያድናል የሚል እምነቱ አላቸው። በዚህም ምክንያት መድኃኒቱን እንጠቀማለን ነገር ግን ደህንነቱ እና ፈዋሽነቱ የተረጋገጠ እንዲሁም በቂ መረጃ ያለውን የባህል መድኃኒት መጠቀም ይኖርበታል። አንዳንዴም በዘመናዊ መድኃኒት መፍትሄ ያልተገኘላቸው በሽታዎች ያሉ በመሆናቸው የባህል መድኃኒትን ለመጠቀም የሚገደዱ ሰዎች መኖራቸውን ከግንዛቤ በማስገባት የህክምና ባለሙያዎችን ማማከር ይገባል። በተጨማሪም የባህል መድኃኒት ላይ ምርምር ለመሥራት ፍላጎት ካላቸው ተመራማሪዎች ጋር በጋራ በመሥራት ለሀገር አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚቻል በማመን በጋራ መስራት ያስፈልጋል።
‹‹እኛ እስከዛሬ እየተጠቀምን ምንም አልሆንም›› የሚሉ አሉ። ከዚህ በተቃራኒም ተጠቅመው ጉዳት እንደደረሰባቸው የሚገልጹ ጥቂቶች እንዳልሆኑ ያነሱት ፍርዶስ፤ በማህበራዊ ሚዲያም ይሁን በበሌሎች መገናኛ አማራጮች ኅብረተሰቡን የሚያደናግሩ በግለሰብም ይሁን በድርጅት ደረጃ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማድረግ ይገባል። ከዚህ ጎን ለጎንም የምርምር ተቋማት፣ብዙኃን መገኛኛ እና ከሚመለከታቸው ጋር አብሮ ካልተሠራ አመርቂ ውጤት ማምጣት አይቻልም። ስለዚህ ማህበረሰቡም እስካሁን ተጠቅሜ ምንም አልሆንኩም ብሎ ችላ ማለት የለበትም።
የጤና ሚኒስቴርም ጉዳዩን አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ላይ እንዳሰፈረው፤በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በተለይም በቲክ ቶክ ሀሰተኛ የጤና መልእክቶች በብዛት በመሰራጨት ላይ ይገኛሉ። ይህ ድርጊት ኃላፊነት በጎደላቸው፣ የጤና ሙያ ሳይኖራቸው ‹‹የጤና ሙያዊ ምክር እንሰጣለን። ›› በማለት የኅብረተሰቡን ጤና ሊጎዳ በሚችል መልኩ ትክክለኛ ያልሆነ መልእክት እያሰራጩ ይገኛሉ። ‹‹የጤና መረጃዎችን ከትክክለኛ የመረጃ ምንጭና ከጤና ባለሙያ ብቻ ማግኘት እንደሚገባ አውቀው ፤ በማህበራዊ ሚዲያ ከሚሰራጩ ሃሰተኛ የጤና መረጃዎች እና ከሚያስከትሏቸው የጤና አደጋዎች ተጠበቁ›› ሲል ማሳሰቡ ይታወሳል።
በጥቅሉ ኢትዮጵያ የባህል መድኃኒትን በመጠቀም የካበተ ልምድ ያላት ሀገር መሆኗን ከግንዛቤ በማስገባት የባህል መድኃኒታቸውን አዘምነው ከራሳቸው አልፈው ለብዙዎች እንደተረፉት ቻይና፣ህንድ እና የሌሎች ሀገራት ልምድ በመቅሰም ኅብረተሰቡ ጤናውን ከመጠበቅ ባሻገር ለመድኃኒት ግዢ የሚወጣውን ወጪ መቀነስ እንደሚቻል ብዙዎች ይስማማሉ። የህክምና ባለሙያዎችም በባህል መድኃኒት አጠቃቀም ዙሪያ ሰፊ እና ወቅቱን የጠበቁ ሥራዎችን መሥራት እንዳለባቸው ይጠበቃል።
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘም ህዳር 22/2016