«በምግብ እራስን ለመቻል የእንሰት ምርት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው» ወጣት እሱባለው አለልኝ

ቴክኖሎጂና አዲስ የፈጠራ ሥራ የሰው ልጆችን ሕይወት በብዙ አሻሽሏል፡፡ ከትምህርት፣ ከጤና፣ ከግብርና እና ከሌሎች ዘርፎች አንፃርም የሚሰጠውን ጠቀሜታና የአጠቃቀም ሂደቱን ብንመለከት እንደ ዘርፎቹ ዓይነት ጥቅም ላይ የሚውልበት መንገድም ይለያያል። የሚጠቀምባቸው መሳሪያዎችም እንዲሁ እንደ አገልግሎቱ ዓይነትና ስፋት ይለያያሉ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ለሚገኙ ሀገራት ደግሞ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ሥራ ፋይዳው የላቀ ነው። በተለያዩ ዘርፎች ላይ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የማደግ ዕድል እንዳላት ሀገር፣ የማህበራዊ አገልግሎት አሰጣጥ ለመሻሻል፣ ለትምህርት ለግብርናና ለጤና አገልግሎት፣ በአጠቃላይ በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን በቴክኖሎጂና በአዲስ የፈጠራ ሥራ መታገዝ የግድ ነው።

በምግብ እራስን ችሎ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የማገዝ ጉዳይ ከልማዳዊ አሠራር ሥርዓት ማላቀቅ መቻል እንዳለበት ብዙዎች ይስማማሉ። በፍላጎትና በአቅርቦት መካከል ያለውን የሚዛን መዛባት ለማረም ኋላቀር አሠራሮችን በመፈተሽ ዘርፉን የማዘመን እስትራቴጂካዊ አሰራሮች ላይ ልዩ ትኩረት ያስፈልጋል፡፡ በግብርና ዘርፉ በተጨማሪነት ጥንቃቄ መደረግ ያለበት በንግድ ሰንሰለቱ ውስጥ ያሉ ተዋንያንን የሚያውኩ ሕገ ወጥ ድርጊቶች ምንጫቸው መፈተሽ ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም የገበያ ሥርዓቱ የሚያውኩና ከአርሶ አደሩ ማሳ እስከ ገበያ ድረስ ባለው መካከል ያለው በቀላል ቁጥር የማይገለጽ ሕገ ወጥ ደላላ አደብ እንዲገዛ ሥርዓት መበጀት ይኖርበታል። ሰፊ ለም መሬት፣ ከፍተኛ መጠን ያለው የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር ውኃ፣ ተስማሚ የአየር ፀባዮች፣ እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ ወጣት የሰው ኃይል ባለበት ሀገር ውስጥ በምግብ ዕጦት መቸገር መብቃት ያለበት ጉዳይ እንደሆነ እሙን ነው።

በእንስሳት ሀብትም ቢሆን ከአፍሪካ አንደኛ ደረጃን ይዘን ሥጋ፣ ዶሮ፣ ቅቤ፣ ወተት፣ ዕንቁላል እና ሌሎቹ የእንስሳት ተዋጽኦ የቅንጦት ምግብ መሆን እንቆቅልሽ ያደረገው የአሰራር ሥርዓት በየደረጃው ተፈትሾ መስተካከል ያለበት ነው፡፡ የትኛውም አደጉ፣ በለጸጉ የምንላቸው ሀብታም ሀገራት የመጀመሪያው መሸጋገሪያ ድልድያቸው የግብርና ዘርፉን በሚያስፈልገው ሁሉ በማዘመን ነውና እንደ ሀገር በዘርፉ መከወን ያለባቸውና እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ከንግግር ባለፈ የሀገራችንን ኢኮኖሚ አቅምን በሚያረጋግጥ እና በሚያረጋጋ ሁኔታ መሥራት ከሁሉም የሚጠበቅ ስለመሆኑ አያጠራጥርም።

ወጣት እሱባለው አለልኝ ይባላል ውልደቱ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በወላይታ ሶዶ ሊጋባ ትምህርት ቤት ነው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በዛው ከተማ በሚገኝ የወላይታ ሶዶ መሰናዶ ትምህርት ቤት ተከታትሏል። ከዛ በመቀጠል በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ጥሩ ውጤት በመምጣት የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቱን ለመከታተል ወደ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ማቅናት ችሏል።

በትምህርት አቀባበሉ በመካከለኛ ደረጃ ከሚመደቡ ተማሪዎች መካከል እንደነበር የሚናገረው ወጣት እሱባለው በ2008 ወደ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲን ሲቀላቀል ለመማር አቅዶ የነበረው የሕክምና ትምህርት ነበር። ቢሆንም ይህ ባለመሳካቱ በሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ቆይተው ለኬሚስትርና ባዮሎጂ ትምህርቶች ልዩ ፍቅር ስለነበረው ከነዚህ ትምህርቶች ጋር ይበልጥ ቁርኝት አለው ያለውን የኬሚካል ምህንድስና ትምህርት በመምረጥ መከታተል ችሏል።

በ2013ዓ.ም የኬሚካል ምህንድስና ትምህርቱን አጠናቆ የተመረቀው ወጣት እሱባለው በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስለነበረ ቆይታ ሲናገር፤ ከምህንድስና ትምህርቱ ባሻገር የቢዝነስ ማኔጅመንት ትምህርት በመከታተል በሁለት የትምህርት ዓይነት ስኬታማ መሆን ቻለ። በመሆኑ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የነበረው ቆይታ ያልበከናና መጨረሻውም በውጤት የተደመደመ እንደሆነ በደስታ ይናገራል።

ከልጅነቱ ጀምሮ ለአዳዲስ ነገሮች ግኝት፣ ለፈጠራ ቀልቡ ይሳብ እንደነበር የሚናገረው ወጣት እሱባለው፤ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በነበረው ቆይታ ከትምህርቱ ጎን ለጎን የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች ስለፈጠራና መሰል ጉዳዮች የሚሰጡትን ስልጠና ለመውሰድ ጥረት ያደርግ እንደነበር ያስታውሳል።

ተቀጥሮ በአንድ የመንግሥት ወይም የግል ድርጅት ውስጥ በመሥራት ውጤታማ እሆናለሁ የሚል እምነት ያልነበረው እሱባለው ተቀጥሮ መሥራት ምርጫው ባለመሆኑና አዲስ አሠራር መገንባት ከጠንካራ ሠራተኝነት hard work ባሻገር ጥበበኛ ሠራተኛ smart worker መሆን የሚፈልግ በመሆኑ በራሱ መንገድ ተጉዞ ውጤታማ ለመሆን ጥረት ስለማድረጉ ያስረዳል።

በአሁኑ ሰዓት Bright Enset starch manufacturing የሚል ስያሜ የተሰጠው ኩባንያ መስርቶ በተለይ በእንሰት ተክል ላይ የምርምር ሥራ በስፋት እያከናወነ የሚገኘው ወጣት እሱባለው እያከናወነ ስላለው አዲስ የፈጠራ ሥራ ሲናገር፤ ባደገበት አካባቢ የእንሰት ምርትና ብሎም የንጥረ ነገሩ ጠቃሚነት በአግባቡ የሚረዳው በመሆኑ ይህ ተክል በመላው የሀገሪቱ ክፍል ተስፋፍቶ ለምግብነት የማዋል ትልም ስላለው እንሰትን በተሻለ ጥረትና ምርት ዘርፈ ብዙ ጥቅም ሊሰጥ በሚችል መልኩ አምርቶ ለገበያ ለማቅረብ የምርምር ሥራውን ስለመጀመሩ ይናገራል።

የእንሰት ምርት በተፈጥሮ ድርቅን መቋቋም የሚችል ቢሆንም ኢትዮጵያ በተገቢው መልኩ እየተጠቀመችበት አይደለም የሚለው እሱባለው፤ ቴክኖሎጂ በመፍጠር ምርቱን ለማሳደግ አልተቻለም በደቡብ የሀገሪቱ ክፍል በስፋት የሚመረተውን የእንሰት ምርት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢ እንዲመረት ለማድረግ ባለመታደሉ ይህንን ችግር እንዴት መፍታት ይቻላል በሚል በዘርፉ ምርምር ለማድረግ እንደተነሳ ይናገራል።

እንሰት በመሐል እና በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ማህበረሰብ ዘንድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጥቂቱ እየታወቀ ቢመጣም አዘገጃጀቱ አድካሚ በመሆኑ እርሱ ይህንን በመቅረፍ በዘመናዊ መንገድ በቀላሉ አዘጋጅቶ ለገበያ እንደቀረበ በተጨማሪ የእንሰት ዱቄቱ በተለየ መልኩ ለሁሉም ዓይነት የምግብ ስልቶች የሚውል ምንም ዓይነት ሽታ የሌለው በመሆኑ ወደፊት ባሉት ጊዜያት በስፋት ተመርቶ ለገበያ ቀርቦ ተወዳጅነት የሚያተርፍ ስለመሆኑ የማያጠያይቅ እንደሆነ ይገልጻል።

ኢትዮጵያ በዓመት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማውጣት 20ሺህ ቶን ለምግብ ፍጆታ የሚውል starch ኢምፖርት ታደርጋለች ይህንን የሚያስቀር ዱቄት የእንሰት ቡላ በመጠቀም ለኬክ፣ ለኩኪስ፣ ለዳቦ መጋገሪያ መሆን የሚችል ዱቄት መምራት እንደቻለ የሚናገረው ወጣት እሱባለው፤ በተለምዶ ጥቅም ላይ ከሚውለው ዱቄት በተሻለ የከርቦሀይድሬት መጠን ስላለውና ካለምንም የኬሚካል ንኪኪ ነፃ ስለሆነም ጤናማ በመሆኑ ተመራጭነቱ የማያጠያይቅ እንደሆነ ይናገራል።

በአሁኑ ሰዓት ገበሬው እንሰት ከማሳው እየነቀለ ቡናና ባህር ዛፍ ነው እየተከለ ያለው የሚለው የፈጠራ ባለሙያው ወጣት እሱባለው፤ የዚህ ምክንያትም እንሰት ምንም ዓይነት ገቢ እያስገኘለት ባለመሆኑ ነው። እንሰት ድርቅ የመቋቋም አቅሙ ከፍተኛ ነው። በአዲሱ የምርምር ሥራም እንሰት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ተለምዶ ዘመናዊ በሆነ መንገድ ምርት እንዲሰጥ ለማድረግ በተለያዩ አካላት ትኩረት ተሰጥቶ ቢሰራ መልካም እንደሆነ ይናገራል።

ሀገሪቱ በብዙ መመዘኛ አንፃር ጥቅሙ ብዙ ለሆነው የእንሰት ልማት ከስንዴ ልማት ያልተናነሰ ትኩረት መስጠት አለበት የሚለው ወጣቱ፤ በተለይ በደቡብ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዘንድ ከምግብና ባለፈ ለብዙ ነገር ጥቅም ላይ የሚውለው የእንሰት ተክል ያለው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በአግባቡ ተውቆ ማህበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ምርታማነቱን በማስፋት የሚሰራው የምርምር ሥራ በመንግሥት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ እንደሆነ ያነሳል።

እርሱ በሚሰራው የምርምር ሥራ የቆጮ ምርቱ ላይ የሚኖረው ምንም ዓይነት ጉዳት እንደሌለው የሚናገረው እሱባለው፤ በእርሱ የፈጠራ ሥራ ቆጮው እንዳለ ሆኖ ዱቄቱን ለማምራት የሚጠቀሙ የቡላውን ምርት ብቻ በመጠቀም በመሆኑ የሚሰራው የምርት ብክነት በከፍተኛ ደረጃ የሚቀንስ እንደሆነ ይናገራል።

የምርምር ሥራው ውጤታማነት ጥያቄ የሚነሳበት እንዳልሆነ የሚናገረው ወጣቱ፤ 20 ኪሎ ግራም የሚሆን በኢትዮጵያ የተመረተ ዱቄት ከእንሰት በኤክስፖርት ደረጃ በማምራት ለናሙና ወደ ውጭ በመላክ መረጋገጥ እንደተቻለ አዋጭነቱም ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር የሚያጠራጥር አይደለም አርሶ አደሩም የቆጮ ምርቱን ለራሱ እየተጠቀመ ለእነርሱ የቡላ ምርት በሽያጭ እያቀረበ ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ ተጨማሪ ገቢ ማግኘት የሚችልበት ዕድል እንዳመጣለት ያስረዳል።

መንግሥት ለአረንጓዴ ልማት የሰጠውን ትኩረት በእንሰት ተክል ላይም መስጠት አለበት የሚለው ወጣት እሱባለው፤ የተጀመረው የፈጠራ ሥራ ተስፋፍቶ በመላው ኢትዮጵያ እንሰት ለምግብነት እንዲውል ለማድረግ በቴክኖሎጂና ምርምር የተደገፈ የግብርና እስትራቴጂ ነድፎ መንቀሳቀስ እንዳለበት ይናገራል።

በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት በተዘጋጀው የክረምት ወራት የቴክኖሎጂ ማበልጸጊያ ፕሮግራም ላይ ተሳትፎ የነበረው የፈጠራ ባለሙያው በዚያ ስለነበረው ቆይታ ሲናገር፤ ብዙ እውቀት ያገኘበት፣ ከተለያየ አካባቢ ከመጡ የፈጠራ ባለሙያዎች ጋር እርስ በእርስ በሚኖር ግንኙነት የተለያየ ልምድ የቀሰመበት፣ የፋይናንስ ድጋፍ መገኘት እንዲችል ከባንክ ጋር ትስስር መፍጠር የሚቻልበት መንገድ የተገኘበት በመሆን የክረምት ቆይታው የተዋጣለት እንደሆነ ይናገራል።

እንደ ሀገር በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ወጣቶች በአንድ ቦታ ተሰባስበው እርስ በእርስ በሚኖራቸው ግንኙነት በተናጥል ከመሆን በጋራ ትልቅ ነገር ማለም እንዲችሉ ለማድረግ የተሰራው ሥራ ይበል የሚያሰኝ ነው። ጅምር የፈጠራ ሥራ ባለቤቶች ያለባቸው ችግር ምንድነው በማለት ወጣቶችን ከተለያየ አካባቢ ምግብ፣ ማደሪያ፣ ተችሎ ማሰልጠን ያልነበረ ነው። ይህንን ትልቅ ዕድል ላመቻቸው ተቋም ያለው ምስጋና ትልቅ እንደሆነ ወጣቱ ተናግሮ፤ የጎደለ ነገር ለማሟላት ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ የተደረገው ጥረት መበረታታት የሚገባው እንደሆነና ለብዙዎች ተስፋ ሰጪ ጅምር በመሆን ቀጣይናት ባለው መልኩ መሠራት ያለበት እንደሆነ ያስረዳል።

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የተለያዩ ድርጅቶች የምርምር ሥራውን በሚሰራበት ወቅት ድጋፍ እንዳደረጉለት የሚናገረው እሱባለው፤ መንግሥት በየአካባቢው እንደ እርሱ ዓይነት የፈጠራ ዝንባሌ ያላቸው ወጣቶች ሥራቸውን ማጎልበትና ማሳደግ የሚችሉባቸውን የፈጠራና የቴክኖሎጂ ማዕከላት ቢስፋፉ የተሻለ ሥራ መሥራት እንደሚቻል እና የቴክኖሎጂና የፈጠራ ሥራ በይበልጥ ድጋፍና ክትትል የሚያገኝበት መንገድ ቢኖር መልካም ነው ይላል፡፡

የፈጠራ ሥራውን ለመሥራት ጥረት በሚያደርግበት ወቅት የተለያዩ ተግዳሮቶች እንደነበሩ የሚናገረው ወጣት እሱባለው ከግለሰቦች የሚሰጡ አሉታዊ አስተያየቶች ነበሩ ነገር ግን የታየውን ህልም የሚሉ ሰዎች ነበሩ እርሱ ግን ያንን ፋይዳ አልባ አስተያየት ለመስማት ጆሮ እንዳልሰጠ ይናገራል።

የወደፊት ህልሙ ምን እንደሆነ ወጣቱ ሲናገር፤ የእንሰት ምርትን ለዓለም ለማስተዋወቅ ሲሆን በቡና፣ በአበባ ምርት በመላው ዓለም የምትታወቀው ኢትዮጵያን በእንሰት ማስተዋወቅ ይፈልጋል። እንሰት ደግሞ የኢትዮጵያ ሀገር በቀል ምርት እንደመሆኑ ይህንን ለዓለም በማስተዋወቅ ምግብነቱ ዕውቅና እንዲኖረው የማድረግ ግብ እንዳለው ተናግሯል። እንሰት ከኢትዮጵያ ባለፈ በድርቅና በምግብ ዕጥረት ለሚሰቃዩ የአፍሪካ ሀገራት ሕዝቦች ለምግብነት እንዲውል የማድረግ ህልም እንዳለው ተናግሯል።

ወጣት እሱባለው ለወጣቶች ባስተላለፈው መልዕክት አንድ ነገር ለማድረግ ሲታሰብ ሁልጊዜ ዋጋ መክፈል ይኖረዋል፤ ፀንቶና ተግቶ በመሥራት የማይሳካ ነገር ግን እንደሌለ ተናግሯል። የኢትዮጵያን ነገ የለመለመ የማድረግ ኃላፊነትና ግዴታ ያለባቸው የዛሬው ትውልድ ወጣቶች በመሆናቸው ለዓላማቸው መሳካት መክፈል ያለባቸውን መስዋዕትነት ሁሉ መክፈል አለባቸው። የነገው ራዕያቸውን ከግብ ለማድረስ ቀን ሌሊት ሳይሉ እና ተስፋ ሳይቆርጡ መትጋት እንደሚገባቸው አስረድቷል።

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን ህዳር 21/2016

Recommended For You