ለሕፃናቱ እፎይታን፤ ለቤተሰብ ተስፋን የሰጠው ሰዋዊ ተግባር

ሕጻን የአብስራ ሳሙኤል፤ ለአምስት ዓመታት ወረፋ ጠብቆ ከሕመሙ ሊፈወስ የልብ ቀዶ ሕክምና አግኝቷል። የአብስራ ሳሙኤል እናት ወይዘሮ ወጋየሁ አለፈ ልጃቸው ገና የሁለት ዓመት እድሜ እያለ ጀምሮ ሌሊት ላይ በሚያጋጥመው ሕመም የመተንፈስ ችግር እየገጠመው በብዙ ሲቸገሩ እንደነበር ያስታውሳሉ። በዚህ ምክንያትም በተለያዩ ሃይማኖታዊ ቦታዎች በመሄድ ልጃቸው የአብስራ ፍጹም ጤናማ እንዲሆን አምላካቸውን ተለማምነዋል።

ይሁንና ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ግን ሕመሙ የልብ ችግር እንደሆነ በሕክምና ከተረጋገጠ በኋላ በልብ ህሙማን ማዕከል የሕክምና ክትትል ሲደረግለት ቆይቶ ደጋግ ልቦች ባደረጉት ድጋፍ ሕክምናውን ማግኘት ችሏል። ላለፉት አምስት ዓመታትም በየሶስት ወሩ እና በየስድስት ወሩ ክትትል ሲደረግለት ቆይቶ ዛሬ ላይ የልብ ቀዶ ሕክምና ማድረግ ችሏል።

በአሁን ወቅትም ሕጻን የአብሥራ ከአምስት የስቃይ ዓመታት በኋላ በተደረገለት የልብ ቀዶ ሕክምና በጥሩ ጤንነት ላይ መሆኑን ወላጅ እናቱ ወይዘሮ ወጋየሁ በደስታ ገልጸዋል። ‹‹አንድን ሕጻን ሕይወት መታደግ በምድርም በሰማይም ጽድቅ ነው›› የሚሉት ወይዘሮ ወጋየሁ፤ በተመሳሳይ ወረፋ እየተጠባበቁ የሚገኙ በርካታ ሕጻናት መኖራቸውን ጠቁመው ወላጆች በጽናት እንዲጠብቁና ልጆቻቸው ደህና እንደሚሆኑ መክረዋል። በኢትዮጵያ ልብ ሕሙማን መርጃ ማዕከል የሚሰሩ ሠራተኞችን ጨምሮ ለማህበሩ ድጋፍ ለሚያደርጉ ተቋማትና ግለሰቦች ጭምር የላቀ ምስጋናም አቅርበዋል።

ከአምስት ዓመታት ክትትል በኋላ ለልጃቸው የልብ ቀዶ ጥገና ለማድረግ እየተጠባበቁ ያገኘናቸው አቶ ኤፍሬም ተድላ ሌላኛው ተስፋ ያገኙ ወላጅ ናቸው። የአምስት ዓመቱ ሕጻን ዮናታን ኤፍሬም ወላጅ አባት አቶ ኤፍሬም ከድሬዳዋ የመጡ ሲሆን፤ ዮናታን የልብ ታማሚ መሆኑ የታወቀው በተወለደ ገና በአምስት ወሩ እንደነበር አስታውሰው፤ ከድሬዳዋ አዲስ አበባ በየሶስት ወሩ ለክትትል ሲመላለሱ መቆየታቸው ብዙ ዋጋ ያስከፈላቸው መሆኑን አንስተው፤ አሁን ግን ወረፋ ደርሷቸው ልጃቸው የልብ ቀዶ ሕክምና ሊያደርግ የሰዓታት ዕድሜ የቀረው በመሆኑ ልባቸው በተስፋ ተሞልቷል። ድካማቸው ቀሏል። ለዚህም የማዕከሉን ሠራተኞችና አጋር አካላትን በሙሉ በማመስገን ሌሎችም ሕጻናትም መልካም ዕድል እንዲገጥማቸው ተመኝተዋል።

በልብ ሕሙማን ህጻናት መርጃ ማእከል ተገኝተው ጉብኝት ያደረጉት የልማት ባንክ የሥራ ኃላፊዎች የማዕከሉን መሠረታዊ ችግሮች በመረዳት የአቅማቸውን ለማገዝ ቃል የገቡት ልክ የዛሬ ዓመት ነበር። ‹‹ቃል ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ›› እንዲሉ አበው በገቡት ቃል መሠረት ለሕክምና ሥራው ያስፈልጋሉ የተባሉትን ድጋፎች ይዘው በማዕከሉ ተገኝተዋል።

ድጋፎቹም 31 ሚሊየን ብር ዋጋ ያላቸው ለቀዶ ሕክምና የሚያገለግሉ ቁሳቁስ ናቸው፤ እነዚህ ቁሳቁስ ቢያንስ ለ250 የልብ ሕሙማን ሕጻናት ቀዶ ሕክምና አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችሉ የማዕከሉ የሥራ ኃላፊዎች ይገልጻሉ። የዚህ ድጋፍ አድራጊ ተቋም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ነው።

የሕክምና ቁሳቁሱን ለማዕከሉ ኃላፊዎች ያስረከቡት የልማት ባንኩ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሐንስ አያሌው ባደረጉት ንግግር ባንኩ ከሥራዎቹ አንዱ የሰው ልማት መሆኑን አስታውቀዋል። የሀገራዊ ልማቶች ሁሉ መሠረት ሰዋዊ ልማት መሆኑን የተናገሩት አቶ ዮሐንስ፣ ልማት ባንክ ባደረገው በዚህ ድጋፍ ለምንወዳቸው ሕፃናት መድረስ በመቻሉ እርካታ ተሰምቶታል ሲሉም ገልጸዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ የኢትዮጵያን ልማት ማምጣት በሚችሉ ሕጻናት ላይ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል። ተምረው፣ የሚፈለገው ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ጤናቸው ሊጠበቅ ይገባል። በተለይም የልብ ሕክምና ውስብስብ እና የተለየ ስፔሻላይዜሽን እንደሚፈልግ ጠቅሰው፣ የልብ ሕክምና አገልግሎት በሀገራችን ባልነበረበት ወቅት እናቶች ልጆቻቸውን ለማሳከም አቅም በማጣታቸው ሳቢያ ብዙ ተፈትነዋል፤ ልጆቻቸው እጃቸው ላይ ይሞቱባቸውም ነበር በማለት አስታውሰዋል።

የልብ ሕሙማን ሕጻናት መርጃ ማዕከል መስራች የሆኑት ዶክተር በላይ አበጋዝ ይህ ማዕከል እንዲመሰረት ላደረጉት ጥረት ሊታሰቡ እንደሚገባም አስታውቀዋል። ዶክተር በላይ ይሄንን ተነሳሽነት ወስደው ሕክምናው ወደ ሀገሪቱ እንዲመጣ በማድረግ አንድ ሕፃን ወደ ውጭ ሀገር ወስዶ ለማሳከም በመቶ ሺዎች ብር ያስፈልግ የነበረውን አገልግሎት በሀገር ውሰጥ መሰጠት የሚያስችል ሥራ ሰርተዋል፤ ለዚህም የልማት ባንከ ማኔጅመንት እና ሠራተኞች ዶክተር በላይን በእጅጉ ያመስግናሉ ነው ያሉት።

‹‹ዶክተር በላይ ሁሌም ሊታሰቡ ይገባል፤ ፎቶግራፋቸም እዚህ መታየት ነበረበት›› ሲሉም አስገንዝበው፣ እንደነዚህ ዓይነት ሰዎችን ማግኘት የሚቻለው ለሰዎች የምንሰጠው ክብር ሲኖር ነው ብለዋል። እንደሳቸው ዓይነት ሰዎች ወደፊትም የኢትዮጵያን ችግር በመፍታት ፈር ቀዳጅ ሆነው ያግዛሉ። መሰል ሥራዎችን መሥራት እና ማስፋት ይገባል፤ ይህን ሥራ የጀመሩ ሰዎች ሁልጊዜም ስለልብ ሲነሳ የንግግራችን መነሻና መጨረሻ ሊሆኑ ይገባል በማለት አቶ ዮሐንስ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ይሄንን እገዛ ያደረገው የችግሩን ውስብስብነት፣ ትልቅነት የዛሬ ዓመት ባደረገው ጉብኝት ተገንዝቦ ነው። ይህን ያህል ገንዘብ ወጥቶባቸው አሁን ለማዕከሉ የቀረቡት ድጋፎች ለ250 ሕፃናት ሕክምና ብቻ ሊውሉ እንደሚችሉ እንደተነገራቸው አቶ ዮሐንስ አስታውቀዋል።

እንደሳቸው ገለጻ፤ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከሉን የመደገፉ ተግባር ዘላቂ መፍትሔ ያስፈልገዋል። አሰራሩን መቀየር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከማዕከሉ ቦርድ ጋር ውይይት ተደርጓል፤ የማዕከሉ የቢዝነስ ሞዴል ዘላቂ በሚሆንበት እና ራሱን በሚያግዝበት ደረጃ ለማድረስ ማሰብ የሚገባ መሆኑን ባንኩ ከማዕከሉ ኃላፊዎች ተነጋግሯል። ለዚህም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እገዛ ለማድረግ ቃል ገብቷል።

ማዕከሉ በአንድ ዓመት እስከ ሁለት ሺህ ለሚደርሱ ሕፃናት አገልግሎት መስጠት እንደሚችል መስማታቸውን የገለጹት ዶክተር ዮሐንስ፣ እዚህ ደረጃ ለመድረስ ቁሳቁሱን ለማዕከሉ በቀላሉ ማቅረብ ይገባል፤ ለእዚህ ደግሞ ቁሳቁሱን በሀገር ውስጥ ማምረት መቻል አለብን ብለዋል። ይህን ለማድረግ ቴክኖሎጂው እንዳለና አዲስ ፈጠራ ውስጥ መግባት እንደማይጠይቅ ጠቅሰው፤ ይህን ፋብሪካ ከውጭ በማስመጣት መሥራት የሚቻልባት ሁኔታ እንዳለም አመላክተዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ለሕክምና አገልግሎት የሚውሉ የተለያዩ ቁሳቁስን በስፋት ማምረት የሚቻልባቸው ሁኔታዎች መመቻቸት ይኖርባቸዋል። የሕክምና ቁሳቁሱ አምራቾችም ወደዚህ ዘርፍ መምጣት ይጠበቅባቸዋል። የኢትዮጵያ ልማት ባንክም እነዚህን አምራቾች ለማገዝ ዝግጁ ነው። ባንኩ ለአጭር ጊዜ ድጋፎች በፍጥነት በመድረስ፤ በረጅም ጊዜ ደግሞ በኢንቨስትመንቱ እና እቅዱን በቴክኒከ በማገዙም ጭምር እገዛውን አጠናክሮ ይቀጥላል። የዚህ ዓይነት ድጋፎች ቀጣይነት ሊኖራቸው ይገባል።

በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ሆስፒታሉን በማሳደግ እንዲሁም የቢዝነስ ተቋም እንዲሆን በማድረግ በኩል አቅዱ ተዘጋጅቶ እንዲመጣ ከቦርድ ጋር ተነጋግረናል ሲሉም ዶክተር ዮሐንስ ገልጸዋል። በዚህ በኩል በእነሱ የሚሰራ ይኖራል ብለን እናስባለን፤ ያ እንዳለ ሆኖ ይሄ ጉዳይ እገዛ እንደሚያስፈልገው ይታወቃል ያሉት አቶ ዮሐንስ፤ ‹‹ እርግጠኛ ነኝ ዛሬ ወረፋ እየጠበቁ ያሉ ታማሚ ሕጻናት በርካታ ናቸው፤ ባንኩ አምና በገባው ቃል መሠረትም ለእዚህ ዓመትም ይህንኑ ለማድረግ ቃል ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የብራንድ አምባሳደር እና የኢትዮጵያ ልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከል የበጎ ፈቃድ አምባሳደር አርቲስት መሠረት መብራቴ በበኩሏ፣ በጎ አድራጊ ተቋማት እና ግለሰቦች የሕጻናትን ልብ በመጠገን እያደረጉ ለሚገኙት ተግባር አመስግናለች።

የዛሬ ዓመት አካባቢ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሐንስ አያሌው ከባልደረቦቻቸው ጋር በማዕከሉ ተገኝተው ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ከማዕከሉ የቦርድ አባላት እና አስተዳደር ጋር መወያየታቸውን አስታውሳለች።

የብራንድና የበጎ ፈቃድ አምባሳደሯ አርቲስት መሠረት እንዳለችው፤ ማዕከሉ ብቁ ባለሙያዎች እያሉት ከአቅም በታች እየሰራ ይገኛል፤ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የሕክምና ግብዓት እጥረት ነው። በግብዓት እጥረቱ ሳቢያ ብዙ ሕፃናት ለወረፋና ለእንግልት መዳረጋቸው ግንዛቤ ተወስዶበት በጉብኝቱ ወቅት ውይይት ተደርጓል።

የባንኩ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሐንስም ይሄንን መነሻ አድርገው ለስድስት ወራት የሚሆን ድጋፍ ለማዕከሉ ለማድረግ እና በቀጣይነትም ከማዕከሉ ጋር አብሮ ለመሥራት ቃል በገቡት መሠረት ቃላቸው በተግባር ውሎ ዛሬ ከ31 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ በመደረጉ በኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማህበር እና በራሷ ስም ምስጋና አቅርባለች።

እርዳታውም የ250 ሕፃናትን ተስፋ የሚያለመልም፣ የብዙ ወላጆችንም እንባ የሚያብስ ተብሏል። “እንደ ኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕጻናት መርጃ ማዕከል አንድ ሕፃንን ልብ መጠገን፣ ሀገርን ማዳንና መጠገን ነው ብለን እናምናለን” ያለችው አርቲስት መሠረት፣ ድጋፉ ትልቅ እፎይታን እንደሚሰጥም አስታውቃለች።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ኤልሲ በመክፈት ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተያያዘ ያሉትን የማህበሩን ችግሮች ከመቅረፍ አኳያ ሰፊ ድጋፍ አድርጓል። በዚህም ሳይወሰን ይህን ድጋፍ ይዞ ማዕከሉ ድረስ መጥቷል፤ በዚህ ብቻ ሳይሆን ማህበሩን በቀጣይነት ለመደገፍ እቅድ እንዳለውም አረጋግጧል ስትል ገልጻለች።

ሰውን መሠረት ካደረገ እና ሰውን ካስቀደመ ባንክ ጋር በአምባሳደርነት ማገልገሏ ትልቅ ክብር እንደሚሰማትም ጠቅሳ፣ የዚህ ዓይነት ድጋፍ፣ ኃላፊነት እና ቁርጠኝነት መሰል ተቋማትም ምሳሌነቱን እንዲወስዱ አመላክታለች።

እሷ እንዳለችው፤ ድጋፉ ጥቂት እፎይታ ይሰጣል፤ ችግሩ ሰፊ እና አሁንም ድረሰ ወረፋ የሚጠብቁ በርካታ የሚንገላቱ ሕፃናት ያሉበት ነው። ባለሙያዎች እያሉ ማዕከሉ እጅ አጥሮታል፤ ማገልገል መሥራት እንፈልጋለን የሚሉ በርካታ ባለሙያዎች አሉት።

ሁሉም ኢትዮጵያውያን ግለሰቦች እና ተቋማት ለደጋፊው ጥቂት፣ ለሚደገፈው ሰው ግን ትልቅ ዋጋ ያለውን ድጋፍ በማበርከት የነገ ሀገር ተረካቢ ሕፃናትን ተስፋ እንዲያለመልሙም አርቲስቷ ጥሪ አቅርባለች። ጉዳዩ ሁሉም ዘንድ መድረስ አለበት፤ የሕፃናትን ልብ መጠገን የጋራ ሥራችን ነው፤ አብረን ተጋግዘን የሕፃናቱን ታሪክ እንቀይር በማለት ሃሳቧን ቋጭታለች።

ልማት ባንከ ያደረገው እገዛ ዘረፈ ብዙ ፋይዳ አለው። የቁሳቁሱ መገኘት ከብዙ ዘርፍ አኳያ ትልቅ ድጋፍ ነው የሚሉት ማዕከሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ሜክሎን መንግስቱ ናቸው። ዶክተር ሜክሎን እንዳሉት እንደ አንደ የጤና ባለሙያና እንደ ማዕከሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ብዙ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው ሲሉ ገልጸው፣ ድጋፉን ላደረገው የኢትዮጵያ ልማት ባንክም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የዛሬ ዓመት አካባቢ በማዕከሉ ጉብኝት ሲደረግ የማዕከሉን ችግሮች፣ በልብ ሕመም የሚሰቃዩ ሕጻናት የሚደርስባቸውን እንግልት፣ የሚያሳልፉትን አሳዛኝ ሕይወት ስናስረዳ ከልብ ተረድተው በዛሬዋ ቀን በቦታው ላይ ተገኝተው መረዳታቸውን በተግባር ሲያሳዩን ለእኛ ትልቅ ተስፋ ሆኗል ሲሉም ነው የተሰማቸውን ደስታ የገለጹት።

እሳቸው እንዳሉት፤ ባንኩ ባደረገው ድጋፍ ለማዕከሉ የቀረቡት የሕክምና ቁሳቁስ ቢያንስ የ250 ሕጻናት ታካሚዎችን የልብ ቀዶ ሕክምና በዋናነት ለመሥራት ያስችላል። የልብ ቀዶ ሕክምና በሚሰራ ጊዜ ልብ ይቆማል፤ እቃዎቹ የዚህን የልብና የሰንባን ሥራ ተክተው የሚሰሩ ናቸው። ቁሳቁሱ ለልብ ቀዶ ሕክምናው አንኳርና የጀርባ አጥንት የሆኑ አላቂ እቃዎች ናቸው።

‹‹ብዙ መድኃኒቶች በሀገራችን ልናገኝ የምንችልባቸው ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ እነዚህ አላቂ የሕክምና እቃዎች ግን በሀገር ውስጥ የሚገኙ አይደለም።›› ያሉት ሜዲካል ዳይሬክተሩ፣ እቃዎቹን ለማግኘት ብዙ ችግሮች እንደሚገጥም ነው ያመለከቱት።

ይህ ድጋፍ እነዚህን ሁሉ እቃዎች ለማግኘት የሚፈጀውን ጊዜና ውጣ ውረድ አስቀርቷል፤ ወጪንም መቀነስ አስችሏል፤ ይህ ድጋፍ ትልቅ እፎይታ ሰጥቶናል በማለት፤ የማዕከሉ ታካሚዎች የነበሩ አሁን በማዕከሉ የሚሰሩ፣ ከማዕከሉ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላቸውና ለማዕከሉ ከልባቸው ቀን ተሌት የሚተጉ እንዳሉና ድጋፉ ከቁጥርም በላይ መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን መርጃ ማህበር የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ዶክተር ምህረተአብ ኤርሚያስ እንደገለጹት ተቋሙ 70 በመቶ ሕጻናት የልብ ታማሚዎች የሕክምና አገልግሎት ይሰጣል። አሁን ላይም በጠቅላላ ከ20 ሺህ በላይ ሕጻናት ክትትል የተደረገላቸው የሚገኝ ሲሆን ስምንት ሺህ ያህል ሕጻናት የልብ ቀዶ ጥገና ለማድረግ ወረፋ እየተጠባበቁ ይገኛሉ።

ማህበሩ አገልግሎቱን በክልሎች ከማስፋት በተጨማሪም ጅግጂጋ ሀዋሳ በመሳሰሉት በሆስፒታሎች የክትትል አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል። በማህበሩ በአንድ ጊዜ የልብ ቀዶ ሕክምና መስጠት የሚችሉ ሁለት ሐኪሞች ቢኖሩም ሁለቱንም በአንዴ የሚያሰራ የሕክምና ግብዓት የለም። አሁን ያለውን ባለሙያ በመጠቀም በዓመት 1500 ሕጻናት ቀዶ ጥገና ማድረግ ቢቻልም በግብዓት እጥረት በዓመት አንድ ሶስተኛ ያህሉ ብቻ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ማህበሩ ላለፉት 35 ዓመታት የልብ ሕሙማን ሕጻናት የክትትልና ቀዶ ጥገና ሕክምና እየሰጠ የሚገኝ መሆኑ ይታወቃል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ህዳር 21/2016

Recommended For You