በአስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ክብር ከሚሰጠው የሃይማኖታዊ በዓል አንዱና ትልቁ የረመዳን ፆም የሚከወንበት ወሳኝ ወር ነው፡፡
ረመዳን የፍቅር ወር ነው ። ሁሉም በፍቅር የሚተያይበት፣ የሚተሳሰብበት፣ ያለው ለሌለው የሚሰጥበትና አብሮ ተባብሮ ገበታ የሚቆረስበት ወር ነው ። ከአንደበትህ ክፉ ነገር አይውጣ፤ ሰዎች እንኳን ክፉ ተናግረው ቢያስቀይሙህ ክፉ አትመልስላቸው ተብሎ ትምህርት የሚሰጥበት እና የሚሰበክበት ወር ነው። የሃይማኖቱ ተከታዮች ሲያልፉ ሲያገድሙ ሰላም ሳይባባሉ አይተላለፉም፡፡
በተለይ በፆሙ ወቅት ለፈጣሪ ሰላምታ ” አውቀዋለሁ ፣ አላውቀውም” የሚባል ነገር አይሰራም፡፡ ፈገግ ብሎ በሰላምታ ከመጨባበጥ ባለፈ አብሮ እንዳደገ ወዳጅ ዘመድ ትከሻ ለትከሻ ሰላምታ መለዋወጥ የተለመደ የረመዳን ወር ልዩ ህብረ ቀለማዊ ውበት ነው። ወሩ የመረዳጃ፣ የመደጋገፊያና የመተባበሪያ ከሆኑት ጊዜያት አንዱና ልዩ የፍቅር ጊዜ ነው፡፡ ታዲያ እነዚህን ሁነቶች ከሚያደምቁት መካከል አንዱ “መንዙማ” ነው፡፡
‹‹መንዙማ ምስጋና (ማወደስ) ማለት ነው። መንዙማ በይዘቱ በዋነኛነት ከሃይማኖታዊ ዝማሬዎች ይመደብ እንጂ በውስጡ የተለያዩ ማኅበራዊና ፖለቲካ መልዕክቶችንም ያቀፈ ነው፡፡ ሃይማኖታዊ ይዘቱም አላህ የሚመሰገንበት፣ ነቢዩ መሐመድ የሚሞገሱበት፣ የእስልምና ትምህርት የሚሰጥበት፣ ታላላቅ ሰዎች ወይም አሊሞች እና መላዕክት የሚወደሱበት፣ ገድላቸውና ተአምራቸው የሚነገርበት፣ ችግር (ድርቅ፣ ረሃብና
በሽታ) የመሳሰሉት ሲያጋጥሙ የተማፅኖ ፀሎት የሚደረግበት ነው፤›› ይላል በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የተዘጋጀ አንድ የጥናት መድበል፡፡
አብዛኛውን የመንዙማ ግጥሞች የሚጀምሩት አላህና ነቢዩ መሐመድን በማወደስ ሲሆን፣ የሚጨርሱት ደግሞ አላህን ለማመስገንና ለነቢዩ መሐመድ ሰላምና እዝነትን አላህ እንዲሰጣቸው በመማፀን እንደሆነ ጋዜጠኛ ተሾመ ብርሀኑ በፃፈው አንድ አርቲክል ላይ አስነብቧል፡፡
የመንዙማው አቀንቃኝ በተሳታፊዎች ፊት ሲያቀነቅን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የአከዋወን ስልት በመከተል የተለያዩ አካላዊ እንቅስቃሴዎችን ያሳያል፡፡ ከግራ ወደ ቀኝ፤ ከቀኝ ወደ ግራ ሰውነቱን ያወዛውዛል። ታዳሚዎችም አስፈላጊውን አጸፋ በድምፅና በጭብጨባ ይገልፃሉ፡፡ የመንዙማ አጨፋፈር እንደ ዜማዎቹ ዓይነት ይለያያል፡፡ ዝግ ያለ የድቤ መምቻ ያላቸው መንዙማዎች የአጨፋፈር ስልት ምቱን
ተከትለው እየዘለሉና እጅን ከአናት በላይ እያሳለፉ ማጨብጨብ ሲሆን፣ ፈጣን የድቤ ምት ያላቸው መንዙማዎች ደግሞ እያጨበጨቡ ከወገብ በላይ አካላቸውን ወደ ግራና ወደ ቀኝ ማወዛወዝ ነው፡፡
ከዜማ ቅብብሎሹ/ከዝማሬው ለአብነት የሚከተለውን መጥቀስ ይቻላል፡፡
‹‹አሏሁም መሶሌ አላሙ ሀመዴ (2x)
ሙሐመድ፣ ሙሐመድ የዓለሙ ዘውድ፣
ተቆጥሮ የማያልቀው የሱማ ገለታ፣
ለሙሐመድ ኡመት ያደረገን ጌታ፣
መሻሪያ ሰጥቶናል ከወንጀል በሽታ፣
ሰላምና ሶላት ይጉረፉ ጠዋት ማታ፣
በአህመድ በኛ ጌታ በአዘሉውድ፣
ሙሐመድ፣ ሙሐመድ የዓለሙ ዘውድ›› በማለት በቅብብሎሽ ያዜማሉ፡፡
የፎክሎር ባለሙያው መሐመድ ዓሊ (ዶ/ር) በታዛ መጽሔተ ጥበብ እንደጻፉት፣ መውሊድን ለሚያከብሩ ሰዎች ነቢዩ ሙሐመድ ለተወለዱበት ወር የተለየ ክብር አላቸው ይላል። ይህ ወር ‹‹ረቢእ›› ተብሎ ይጠራል። ወሩ የዓለሙ መሪ ነቢዩ የተወለዱበት፣ ከፈጣሪ ወህይ መቀበል የጀመሩበት፣ ተልዕኳቸውን አድርሰው፣ ለሕዝባቸው አደራ ሰጥተው ያለፉበት ነው። እናም በመንዙማ ወሩን የነቢዩ ሙሐመድ ማወደሻ፣ ማስታወሻ አድርገው እንደሚከተለው ይገልፁበታል፡-
‹‹ረቢእ ተብለህ የምትጠራ፤
የወራት ጓል ንጉሥ አውራ፣
ነቢ ባለ ሙሉ ሰብእና፣
እውድጥህ ፈለቁና፣
ሀሴት አዝለህ አስደሰትከን ተስፋ ወልደህ
አደመከን፣
ቃል አደራህ ለኛ ከብዷል ውለታህ ክፋይን
ገዷል።
እንደ ዶ/ር መሐመድ አሊ ማብራሪያ፣ በመውሊድ መንዙማ የነቢዩ ሙሐመድ አካላዊ ገጽታ እየተነሳ ይታወሱበታል። ለምሳሌ ቀጥሎ በቀረበው የመንዙማ ግጥም የነቢዩ ሙሐመድን ዓይን፣ ፊት፣ ፀጉር ይገልፃል። ዓይናቸው በኑር (በብርሃን) እንደተኳለ፣ ፊታቸው የጨረቃ ብርሃንን እንደሚያስንቅ፣ ፀጉራቸው የሀርጉንጉን እንደሚመስል ሥዕላዊ በሆነ ጥበብ ስሎ ይታያል፡፡
‹‹የመድናውን ባየነው ዓይኑን
በኑር አረንጓዴ የተኳለውን
ፊቱ ከጨረቃ የሚያበራውን
ፀጉሩ የሚመስለው የሀር ጉንጉን
ብሎ ያወደሰው ጦሀው ያስኔ።››
መንዙማ ከሚተገበርባቸው በዓላት አንዱ የነቢዩ መሐመድ ልደት በዓል መውሊድ ነው። መውሊድ በኢስላማዊው የሒጅራ አቆጣጠር በረቢ አል አወል ወር 12ኛ ቀን ይከበራል፡፡ መውሊድ በልዩ ሥነ በዓል ከሚከበርባቸው ቦታዎች አንዱ የጡርሲና መስጊድ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 18/2011
አብርሃም ተወልደ