በሽርክና አቅምን በማጎልበት አምራችነትን የማሳደግ ጥረት

መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግርን እውን ለማድረግ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል ተብሎ ትኩረት ከተሰጣቸው ተግባራት መካከል የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት አንዱ ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሦስት ዋና ዋና መሰረታዊ ተልዕኮዎች አሏቸው። እነዚህ ተልዕኮዎቻቸውም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ፣ የሥራ እድል ፈጠራን ማስፋት እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማከናወን ናቸው።

ፓርኮቹ በሚገነቡባቸው አካባቢዎች ለሚኖረው ኅብረተሰብ ስራ በመፍጠርና ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የሆነ የሥራ ከባቢ እውን በማድረግ ለሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት ትልቅ አስተዋፅዖ ይኖራቸዋል፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ተመራጭ ከሚያደርጓቸው ነገሮች መካከል በርካታ አገልግሎቶችን አንድ ሥፍራ ላይ ሰብሰብ አድርገው የሚያቀርቡ መሆናቸው፣ ተገቢ መሰረተ ልማት የሚገነባላቸው እንዲሁም ከሌሎች አምራቾች ጋርም የሚያገናኙ መሆናቸው ይጠቀሳሉ ፡፡

ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያም ብዙ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማቋቋም እንዲሁም ርካሽ የሰውና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን፣ ማሽኖችን ከቀረጥ ነፃ ማስገባትን፣ የብድር አቅርቦትን፣ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን እና የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን እንደማበረታቻ በማቅረብ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ፋብሪካዎቻቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲከፍቱ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገሪቱ በመንግስት ብቻ የተገነቡ 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገኙ ሲሆን፣ በስራ እድል ፈጠራ፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ለሀገራዊ ምጣኔ ሀብት እድገት ቀላል የማይባል አስተዋፅዖ እያበረከቱ ይገኛሉ። ፓርኮቹ የተሻለ የመሰረተ ልማት አቅርቦትና የአገልግሎት አሰጣጥ ያላቸው ስለሆኑ፣ ሀብቶቻቸውን በማቀናጀት በሽርክና (Joint-Venture) ተጣምረው በእነዚህ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሰማሩ ኩባንያዎች ቁጥራቸው እያደገ ነው፡፡

‹‹ኢዜድኤም›› ንግድና ኢንቨስትመንት (EZM Trade and Investment) ሀገር በቀል የተባለ ድርጅት፣ የፕላስቲክ ቱቦዎችን በማምረት የ27 ዓመታት ልምድ ካለው የቻይናው ‹‹ሪፎ›› (RIFENG Enter­prise – FOSHAN) ኩባንያ ጋር በሽርክና (Joint- Venture) በመተባበር ከቻይና የሚገቡ የፕላስቲክ ቱቦዎችን በሀገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችለውን ፋብሪካ ሰሞኑን በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ስራ አስጀምሯል፡፡ የ‹‹ኢዜድኤም›› እና ‹‹ሪፎ›› ሽርክና ሁለቱ ኩባንያዎች የ‹‹ሪፎ››ን ምርቶች በሀገር ውስጥ በማምረት ለኢትዮጵያና ለዓለም አቀፍ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ በሦስት ሺ ካሬ ሜትር መሬት ላይ ተገንብቶ ስራ የጀመረው ፋብሪካ፣ በ14 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር የተገነባ ነው፤ ፋብሪካው ከውጭ የሚገባውን የፕላስቲክ ቱቦ ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካትና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እቅድ ይዞ እንደሚሰራም ተነግሯል፡፡ የኩባንያዎቹ ሽርክና በዘመናዊ መልኩ የተነደፉ፣ ከፍተኛ ጥራት ያላቸውና ለአካባቢ ሥነ-ምኅዳር ተስማሚ የሆኑ የመጠጥ ውሃና እና የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎችን ለማምረት ያስችላል፡፡

ፋብሪካው በዓመት እስከ ሁለት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ፒፒአር (PPR) ቱቦዎችን፣ አንድ ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ሺ የፒፒአር (PPR) መገጣጠሚያዎችን፣ አንድ ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የፒቪሲ (PVC) የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎችን፣ ዘጠኝ መቶ ሺ የፒቪሲ (PVC) መገጣጠሚያዎችን እንዲሁም ከሦስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሜትር በላይ የፒቪሲ (PVC) ኮንዲዩት ማስተላለፊያ ቱቦዎችን የማምረት አቅም አለው፡፡

የ‹‹ኢዜድኤም›› (EZM) ንግድና ኢንቨስትመንት ኩባንያ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ እስመለዓለም ዘውዴ፣ ኩባንያው በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ መግባቱን ጠቁመው፣ ከኢንዱስትሪ ፓርኩ ሼድ በተከራየ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ሰራተኞችን አሰልጥኖና ማሽኖችን ተክሎ የምርት ስራ መጀመሩን ይናገራሉ፡፡

እንደ እሳቸው ማብራሪያ፣ የፋብሪካው ምርቶች ለኮንስትራክሽን ስራ በግብዓትነት የሚያገለግሉ ቱቦዎች ሲሆኑ፣ ከውጭ የሚገባውን የፕላስቲክ ቱቦ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የሚደረገውን ጥረት ከግብ ለማድረስ ያስችላሉ፡፡ ፋብሪካው አሁን ባለው አቅም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን የፕላስቲክ ቱቦ ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ይችላል። ፋብሪካው በዓመት 17 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን የሚያመርት ሲሆን፣ ከምርቱ 50 በመቶውን ለውጭ ገበያ ለማቅረብም አቅዷል፡፡

ፋብሪካው ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃዎችን ያሟሉ የፕላስቲክ ቱቦዎችን እንደሚያመርት የሚናገሩት ዋና ስራ አስፈፃሚው፣ በሀገር ውስጥ የሚመረቱት ምርቶች ቻይና ውስጥ ከሚመረቱትና ለውጭ ገበያ ከሚቀርቡት ምርቶች ጋር አንድ ዓይነት እንደሆኑና ተመሳሳይ የጥራት ማረጋጋጫ እንዳላቸው ይገልፃሉ፡፡ ኩባንያው ወደ አዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ገብቶ መስራቱ ብዙ ጥቅሞችን እንዳስገኘለትም አቶ እስመለዓለም ያስረዳሉ፡፡

‹‹ፋብሪካው በሦስት ፈረቃዎች ለ24 ሰዓታት የሚሰራ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ለ200 ሰዎች ቋሚ የስራ እድል ፈጥሯል፡፡ በንግድ ትስስርና በሌሎች አማራጮች ለ400 ዜጎች ተጨማሪ የሥራ ዕድሎችን አቅርቧል። ፋብሪካው የምርት አቅሙ ሲጨምር ተጨማሪ የሥራ እድሎችን እንደሚፈጥር ይጠበቃል፡፡ ድርጅቱ በአፍሪካ ውስጥ አስተማማኝና ቀዳሚ ተመራጭነት ያለው የፕላስቲክ ቱቦዎችና መገጣጠሚያዎች ማምረቻ ኩባንያ ለመሆን በሚያስችለው አቅም ላይ ይገኛል›› ይላሉ፡፡

የ‹‹ሪፎ›› ኢንተርናሽናል ስራ አስኪያጅ ጄሰን ቻን በበኩላቸው፣ ኩባንያው የፕላስቲክ ቱቦዎችን በማምረት የብዙ ዓመታት ልምድ እንዳለውና ስራውንም በበርካታ የዓለም አገራት እያስፋፋ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ በመቀጠል በአፍሪካ ሁለተኛዋ የኩባንያው መዳረሻ እንደሆነች ተናግረዋል። አገሪቱ ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ከሆኑ አገራት መካከል አንዷ በመሆኗ የኩባንያው ምርጫ መሆኗንም ጠቁመዋል፡፡ ኩባንያው ከ‹‹ኢዜድኤም›› ጋር በጀመረው ሽርክና ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ምርቶች ተመርተው ለገበያ እንደሚቀርቡ ይገልፃሉ፡፡

ፋብሪካው በአጭር ጊዜ ማሽኖችን ተክሎና ሰራተኞችን አሰልጥኖ ወደ ስራ የገባ ድርጅት እንደሆነ የሚናገሩት የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ስራ አስኪያጅ አቶ ጉልላት አበበ፣ የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ በመሆኑ የፋብሪካው ምርቶች ለዘርፉ እጅግ አስፈላጊ ግብዓቶች ናቸው ብለዋል፡፡

ባለፉት አራት ዓመታት በፓርኩ ውስጥ ተመርተው ለውጭ ገበያ ከቀረቡ ምርቶች ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንደተገኘም አቶ ጉልላት ይናገራሉ። ‹‹ለውጭ ገበያ ከቀረቡ ምርቶች የተገኘው ገቢ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ማዳን ከተቻለው እና ለሀገር ውስጥ ገበያ ከቀረበው ምርት ከተገኘው ገቢ ጋር ሲደመር ኢንዱስትሪ ፓርኩ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እያስገኘ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡›› ያሉት ስራ አስኪያጁ፣ የ50 ሚሊዮን ዶላሩን ገቢ ማሳካት የተቻለው በአምስት አምራቾች ብቻ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ ፓርኩ ከስምንት ሺ በላይ ለሆኑ ዜጎች የስራ እድል ፈጥሯል፡፡ አሁን በፓርኩ ውስጥ 13 አምራቾች አሉ፤ እነዚህ ሁሉ ማምረት ሲጀምሩ ከውጭ ምንዛሬና ከሀገር ውስጥ ግብይት የሚገኘው ገቢም ሆነ የሚፈጠረው ስራ እድል ይጨም ራል፡፡

በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ አምራች ኩባንያዎች በመደበኛነት ከሚያከናውኗቸው የምርት፣ የስራ እድል ፈጠራና የቴክኖሎጂ ሽግግር ተግባራት ባሻገር፣ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣት ረገድም የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ እንደሚገኙ ዋና ስራ አስኪያጁ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ኩባንያዎቹ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ትኩረት መስጠት የሚገባቸው በመሆኑ ላይ አስፈላጊው ግንዛቤ አላቸው›› የሚሉት አቶ ጉልላት፣ የአካባቢውን ኅብረተሰብ ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ባለሃብቶቹ ትምህርት ቤቶችን ማደሳቸውንና ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን ይገልፃሉ፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አክሊሉ ታደሰ ‹‹የ‹ኢዜድኤም› እና ‹ሪፎ› የጋራ ትብብር የውጭና የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች በሽርክና (Joint-Venture) የሚሰሩበት የቢዝነስ ሞዴል እድገት እያሳየ እንደሆነ ጠቋሚ ነው›› ይላሉ። ሀገር በቀል ኩባንያዎች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው በምርት ስራ ላይ ለመሰማራት የሚያሳዩት ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱ የኩባንያዎቹ የማምረት አቅም አድጎ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ተወዳዳሪ የመሆን አቅማቸው ውጤት እያስመዘገበ ስለመሆኑ እንደሚያመላክትም ይገልፃሉ፡፡

ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው የሚያመርቱ ኩባንያዎች ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ከሚያበረክቱት አስተዋፅዖ በተጨማሪ የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግርን እውን በማድረግ የሚኖራቸው ሚናም የላቀ እንደሚሆን ይናገራሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው የሚያለሙ ኩባንያዎች ለዜጎች የስራ እድል የመፍጠር ፋይዳቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖርና የምርት ተግባራት በቴክኖሎጂ የታገዙ እንዲሆኑ ያደርጋሉ፡፡ በዚህም የምርት ስራዎች ቀልጣፋና ውጤታማ እንዲሆኑ ያግዛሉ፡፡

እንደ ዋና ስራ አስፈፃሚው ገለፃ፣ ባለፉት አራት ዓመታት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ተመርተው ወደ ውጪ አገራት ከተላኩ ምርቶች ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ተገኝቷል። በተኪ ምርቶች አማካኝነት ደግሞ 550 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማዳን ተችሏል። በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ከተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የጨርቃ ጨርቅ፣ የግብርና፣ የፕላስቲክና ሌሎች ምርቶች ለውጭ ገበያ እየቀረቡ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም ‹‹የኢንቨስትመንት ዘርፍን ለማሳደግ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ጥራቱን የጠበቀና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ያለው አገልግሎት እየተሰጠ ነው›› የሚሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው እንዲያመርቱ ኮርፖሬሽኑ በትኩረት ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ ይናገራሉ፡፡ ባለሀብቶች በርካታ ጥቅሞችንና እድሎችን ወደያዙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ እንዲሰማሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ያላትን አቅም በመጠቀምና ከዚሁ ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የምታደርገውን መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግር ለማሳካት አምራች ዘርፉ አሁን ካለው አፈፃፀም በብዙ እጥፍ እንዲጨምርና እንዲሻሻል ማድረግ ያስፈልጋል። የአምራች ዘርፉ እድገት ሊሻሻል የሚችለው ከኢንቨስትመንት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ነው፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ደግሞ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ተግባራዊ በማድረግ ለኢንቨስትመንት መስፋፋት ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ ስለሆነም የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በመፍታትና አፈፃፀማቸውን በማሻሻል መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግሩን ማሳካት ይገባል።

በጦርነት ቀጣና ውስጥ የነበሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በሙሉ አቅማቸው ወደ ምርት ስራቸው እንዲመለሱ ለኢንቨስትመንት ዘርፉ መነቃቃትና ማንሰራራት ዋስትና ሊሆኑ የሚችሉ የድህረ ጦርነት የኢንቨስትመንት ማነቃቂያ ስትራቴጂዎችን ማዘጋጀትና በብቃት መተግበር ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ጥረት ውስጥ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶችና ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በሽርክና ለሚሰሩ ሀገር በቀል ድርጅቶች ልዩ ድጋፍ ማድረግም ሊዘነጋ አይገባም፡፡

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን   ኅዳር20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You