በአንድ ትልቅ የኪነጥበብ ምሽት ላይ ነው። ብዙ ወጣት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ በምሽቱ የተገኙ የጥበብ ወዳጆችና በእንድግነት የተጋበዙ አንጋፋ ባለሙያዎች በቦታው አሉ። በመድረኩ ስራቸውን እንዲያቀርቡ አንድ እንግዳ ተጋበዙ። በእድሜ ገፋ ያሉ፣ አንገታቸው ላይ ስካርፍና ክብ ባርኔጣ ያደረጉ ሰው ወደ መድረኩ ቀረቡ።
ሰውዬው ወግ አዋቂ ናቸው። ካሳለፉት ሕይወት የሚሉት አላቸው። ወጋቸው በቁም ነገር የተከበበ ነው። ልክ ልጅ ለአባቱ የሚሰጠው ትህትናና ቅንነት የሚታይበት ምክር አይነት። በጨዋታ እያዋዙ ጥሩ ይናገራሉ። ታዳሚው በንግግራቸው መሀል በሳቅና በጭብጨባ ይከተላቸዋል።
ምክሮቻቸው በገጠመኞች የተዋዙ ናቸው። የዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች ስነ-ምግባር በጎደላቸው መመህራን ስለሚገጥማቸው የጾታ ትንኮሳ አንስተው እነዚህ መምህራን ከዚህ ተግባራቸው እንዲታቀቡ በቀልድ አዋዝተው ገሰጽ አደረጉ።
ቀጠል አደረጉ እና ይህ ችግር እሳቸው ዩኒቨርሲቲ በሚማሩ ጊዜ የነበረ እና አሁንም ያለ ስለመሆኑ አስታውሰው ችግሩ መቼም የማይፈታና የማይለቅ በሽታ ነው አሉ። በታዳሚዎቹ መሀል አሁንም ሳቅ ሆነ። ጨዋታ አዋቂው ሰው ቀጥለው ለወንዶች ተማሪዎች እንዲህ አሉ ‹‹ አስተማሪ አይኑን ከጣለባት ተማሪ 50 ሜትር ራቅ በሉ ወይንም በፍጹም እንዳታስቡት ›› ወጥወድ ውስጥ ናችሁ አይነት ማስጠንቀቂያ ጣል አደረጉ።
ንግግሮቻቸው በሙሉ ሳቅን ያዘሉ በመሆናቸው አለመሳቅ አይቻልም። እኔ ግን በዚህ ጨዋታ እንኳን ለመሳቅ ጥርሴ አልፈገገም። የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበርኩበት ወቅት በዚህ መንገድ የተፈተኑ ሴት ተማሪዎች መኖራቸውን ስለ ማውቅ ይሁን ሴት ስለሆንኩ አላውቅም ከሳቅ ይልቅ ወደ አዕምሮዬ የመጣው ጥያቄ ሆነ።
ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ ለግቢው ማሕበረሰብ አዲስ ስለሆኑ፣ የተለያየ ሀሳብ እና ልምድ ካላቸው ተማሪዎች ጋር ስለሚተዋወቁና በአፍላ ዕድሜያቸው ላይ ስለሚገኙ ቦታው ስብዕናቸውን የሚገነቡበት ይሆናል።
ይህ አካባቢ አዲስ ቦታ፣ አዲስ የመማሪያ ስፍራ፣ አዲስ ጓደኛ፣ አዲስ የመማር ማስተማር ሂደት በእኩል የሚገናኙበት ነው። ተማሪዎቹ በነዚህ ሁሉ አዳዲስ ነገሮች ይፈተናሉ። ወግ አዋቂው እንደተናገሩትም ለወጣት ወንድ ተማሪዎች ሁነኛ መፍትሄው ከጉዳዩ መራቅ ነው።
ለሴት ተማሪዎች ግን መፍትሄው ምን እንደሆነ አልጠቀሱም። አንድ ሰው ራሱን በስነ ምግባር ከማረቅ በዘለለ ምን ማድረግ እንደሚሻል ጠቅሰውም ይህ ነው አላሉም። ምናልባት የመፍትሄ አካል ናቸው የሚባሉት የነገሩ ተባባሪ ሆነው ይሆናል።
ለኔም ጥያቄ የሆነብኝ ነገር ለምን የማይፈታ ነገር ችግር ሆነ የሚለው ነው። ወግ አዋቂው በንግግራቸው መሀል ባነሱት ገጠመኝ አንዲት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ወደ እርሳቸው ጠጋ ብላ በትምህርት ቤት ውስጥ በሁለት ምክንያት መቸገሯን ታጫውታቸዋለች። ጉዳዩ በሁለት ስነ ምግባራቸውን ባልጠበቁ ‹‹ወደድኩሽ›› ባዮች መካከል ያለ እውነታ ነው።
አንደኛው ‹‹ወደድኩሽ›› ባይ ተማሪ ‹‹የፍቅር ጥያቄዬን ተቀበይኝ አለዚያ ግን ጉልበት አለኝ›› የሚላት ሲሆን ሌላኛው ጠያቂ ደግሞ በጊዜው አገላለጽ ‹‹እሺ በይኝ ካልሆነ ውጤት አለኝ ብለሽ እንዳታስቢ›› የሚል የመምህርነትን ካባ የለበሰ ነው።
የወግ አዋቂው ሀቅ የሁሉም ችግር መፍትሄው ራስን ማነጽ እና በስነ ምግባር መገንባት መሆኑ ግልጽ ነበር። ይሁን እንጂ ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች በብልሹ ስነ-ምግበር ውስጥ ወድቀው ይገኛሉ። ይህ የስነምግባር ግድፈት ደግሞ ሌሎች ሰላማዊ ሰዎችንም ሲያውክ ይታያል። የሕግ አስፈላጊነትም ለዚህ ይመስለኛል።
ሴት ተማሪዎች ታዲያ የዚህ ሰለባ ላለመሆን የሚጠቀሙበት አንዱ መንገድ ውጤታቸው በማያውቁት መንገድ ቢበላሽ በምንም አይነት ሁኔታ ወደ መምህሩ ቢሮ አለመሄድን ነው። ቆፍጠን ያሉ ጎበዝ ሴት ተማሪዎችም ቢሆኑ ትክክለኛ ውጤታቸውን ለመጠየቅ ቢፈልጉ መጀመሪያ የአስተማሪውን ጀርባ ማጥናታቸው አይቀሬ ይሆናል።
በዚህ ጉዳይ ብዙ ችግር የደረሰባቸው፣ ከሚመለከተው አካል መፍትሄ ማግኘት ያልቻሉ የሚገባቸውን ውጤት የተነፈጉና ግፋ ሲልም ትምህርታቸውን ያቋረጡ ተማሪዎች አሉ።
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ መግባት ለወላጆችም ሆነ ለተማሪዎች ትልቅ ቦታ አለው። ወላጆች ‹‹ልጄ ትማርልኛለች፣ ትልቅ ደረጃ ትደርስልኛለች›› ብለው ልጆቻቸውን ከጉያቸው ሲለዩ በቆይታዋ የሚገጥማትን ፈተና እንዴት እንደምታልፈው ነግረው፣ መክረው፣ እና አስጠንቅቀው ይልካሉ።
ይህን መሰሉን ከአንዳንድ አስተማሪዎች የሚደርስባትን ትንኮሳ ግን እንዴት ታልፈው ይሆን ሲሉ የሚያስቡት አይመስልም። እንዲያው ይህን መሰል መፍትሄ ያጣ ጉዳይ በዩኒቨርሲቲ ስለመኖሩ ቢያውቁ ምን ይሉ ይሆን ? ተማሪዋ ደግሞ ‹‹ይበጀኛል›› የምትለውን የትምህርት ዘርፍ መርጣ ‹‹እደርስበታለው›› ያለችውን አቅዳ ስትመጣ ይህ ጉዳይ ከገጠማት ህልሟን እውን ስለማድረጓ ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ስጋት ነው።
ይህ ጉዳይ በዩኒቨርሲቲ ሕይወት ተንሰራፍቶ እንደ ልማድ መቆጠሩ አዲስ አለመሆኑ በራሱ የሚያሳፍር ጉዳይ ነው። ችግሩን ለመፍታት ወግ አዋቂው እንዳሉት ‹‹ራስን በስነ ምግባር ማነጽ›› ትልቅ ነገር ቢሆንም ሁሉም አንድ አይነት አይሆንምና ችግሩ ከዩኒቨርሲቲው ሳይወጣ መፈታት የሚችልበት ብዙ መፍትሄ ይኖራል።
ከነዚህ መፍትሄዎች አንዱ የትምህርት ክፍሉ ኃላፊዎች ይህ መሰሉ ጥቆማ ሲደርሳቸው የሚወስዱት እርምጃ ነው። እንዲህ መደረጉ ነገሩን ከጅምር አስቀርቶ የመማር ማስተማር ሂደቱን ሰላማዊ ያደርጋል። ሌላው በግቢው ከሚቋቋሙት ዘርፎች አንዱ ሴት ተማሪዎችን የሚደግፈው የስርዓተ-ጾታ ጉዳዮች ክፍል ሚና ነው።
በእኔ እሳቤ ይህ ክፍል ስለዚህ ጉዳይ ‹‹ጆሮ ዳባ ልበስ›› ብሎ መቀመጥ አይገባውም። ተማሪዎችን ከወላጆቻቸው በአደራ ተቀብለው በዚህ ረገድ ግን ኃላፊነታቸውን መወጣት ያልቻሉ ኃላፊዎችም ሊጠየቁ ይገባል። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ እንደመሆናቸው ትንሿ ኢትዮጵያን ይወክላሉ።
ችግሩ በትምህርት ገበታ ላይ ብቻ ታይቶ የሚቋጭ አይደለም። በተመሳሳይ ይህ መሰሉ ፈተና በስራ ዓለም ጭምር የሚያጋጥም እውነታ ነው። በትንሿ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ እየታየ የቆየው ችግር ወደሌላኛው ትውልድ እንዳይቀጥል ያስፈልጋል።
ችግሩ መኖሩ ሲታወቅ የሚመለከታቸውና ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን መወጣት ቢችሉ ይህ ማሕበረሰባዊ ጠንቅ ዕድሜው ባጠረ ነበር። ወግ አዋቂው በቦታው ተገኝተው ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያስተላለፉት መልዕክት ግን ከዓመታት በኋላ ባለውለታ አድርጎ እንደሚያስቆጥራቸው ጥርጥር የለውም። አበቃሁ!
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ኅዳር 19 ቀን 2016 ዓ.ም