የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የቴሌኮሙኒኬሽንና የፋይናንስ አገልግሎቶች ተደራሽነት መስፋፋት

ኢትዮጵያ በቴሌኮም አገልግሎቶች ተደራሽነት ላይ በስፋት እየሰራች ትገኛለች፡፡ ኢትዮቴሌኮም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ይህን ስራ ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ በዚህም የቴሌኮም መሰረተ ልማቶችን በመላ ሀገሪቱ በመገንባት ሀገሪቱና ዜጎች ከዘርፉ ማግኘት ያለባቸውን አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ የዘርፉ አገልግሎት ዘመኑን የዋጀ እንዲሆን ለማድረግም የመሰረተ ልማት ማስፋፋት ስራውን አጠናክሮ በመቀጠል በሀገሪቱ የቴሌኮም አገልግሎቶች ተደራሽነት እንዲሰፋ የበኩሉን ሰርቷል፡፡

በዲጅታል ቴክኖሎጂ ተደራሽነት በኩልም በስፋት እየሰራ ይገኛል፡፡ ይህ ደግሞ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ የሚያስችላትን ‹‹ዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ›› እየተገበረች ለምትገኘው ኢትዮጵያ ፋይዳው ከፍተኛ ነው፡፡ መንግስት ይህን እውን ለማድረግ ለዲጂታል ቴክኖሎጂው መስፋፋት በትኩረት እየሰራ ነው፡፡ ይህን ተከትሎም ገንዘብ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ማስተላለፍ እየተለመደ መጥቷል፡፡

የዲጂታል ግብይትና የመሳሰሉት ተግባሮች በቴሌኮም ዘርፉ ላይ ሰፊ ኢንቨስትመንት እንዲመጣ የሚጠይቁ ናቸው፡፡ መንግስት የቴሌኮም ዘርፉ ለሀገሪቱና ለሕዝቧ ያለውን ፋይዳ በሚገባ በመገንዘብ ለዘመናት በመንግስት ብቻ ተይዞ የቆየውን የቴሌኮም አገልግሎት በግሉም ዘርፍ የሚከናወንበትን ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ ይህን ተከትሎም ነው ሁለተኛ የቴሌኮም ኩባንያ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በኢትዮጵያ ኢንቨስት በማድረግ መስራት የጀመረው፡፡

ይህ በአፍሪካ ታዋቂ ኩባንያ በኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፍ የመጀመሪያ የግል ቴሌኮም ድርጅት በመሆን ተደራሽነቱን ለማስፋት በርካታ ተግባራት ሲያከናውን ቆይቶ አገልግሎት ወደ መስጠት ከተሸጋገረ ጥቂት ዓመታት ሆነውታል፡፡

ኢትዮጵያ ደጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት ስትራቴጂ ነድፋ እየሰራች ባለችበት ወሳኝ ወቅት የሀገሪቱን የቴሌኮም ዘርፍ የተቀላቀለው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ፣ አበረታች ለውጦች እያስመዘገበ መሆኑን በቅርቡ አስታውቋል፡፡ ኩባንያው በአገሪቱ በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ለመሆን እየሰራ መሆኑን ነው የገለጸው፡፡

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በቅርቡ በሰጠው መግለጫ ባለፉት ስድስት ወራት የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን በመገንባት የቴሌኮም አገልግሎትን በማስፋፋት ተደራሽነቱን እያሳደገ መሆኑን አስታውቋል። በሀገሪቱ ዲጂታል ኢትዮጵያን ለማድረግ እየተከናወነ ላለው ተግባር ከፍተኛ ሚና በሚጫወተው የዲጂታል ፋይናንስ ተደራሽነት ላይ በቅርቡ በመሰማራት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሷል፡፡

በመግለጫው ላይ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዊም ቫንሄሌፑት፤ ድርጅቱን የተቀላቀሉት በቅርቡ መሆኑን ጠቅሰው፣ በቆይታቸውም የተለያዩ ቦታዎች መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡ በጉብኝታቸውም የኢትዮጵያን መልካምድር ውበትና ብዝኃነትን መመልከታቸውን ጠቅሰው፣ ይህም ሀገሪቱን ለየት እንደሚያደርጋት አመልክተዋል፡፡ ይህ ደግሞ ስለኢትዮጵያ ብዙ ነገሮች እንዲያውቁ እንደረዳቸውም ይገልጻሉ፡፡

‹‹ከድርጅቱ ሠራተኞች፣ ከባለድርሻ አካላት፣ ከአጋሮችና ከተለያዩ አካላት ጋር ስብሰባዎችን አካሂጃለሁ፤ አሁን ከአየር ንብረቱም ሆነ ከሰው ጋር ቤተሰብ የሆንኩ ያህል ይሰማኛል›› ያሉት ዋና ስራ አስፈጸሚው፣ ‹‹እነዚህ ሁሉ ለድርጅቱ ሥራዎች ምቹ የሥራ ሁኔታና መልካም አጋጣሚዎች እንዳሉ እንድመለከት አስችለውኛል›› ብለዋል፡፡

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ 850 ሚሊዮን ዶላር የራሱን የኔትወርክ መሠረተ ልማት ለመገንባት በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረግ መጀመሩን አስታውሰው፤ ይህ ለአገሪቱም ከፍተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ነው ብለዋል። የኩባንያው ኢንቨስትመንት በመላ ኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎትን ለማስፋፋትና ሀገሪቱ ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት እየተከናወነች ለምትገኘው ተግባር ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ዘርፉ ከፍተኛ ቁጥር ላለው የሰው ኃይል የስራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በቴሌኮም ዘርፉ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ከፍተኛ ዕድል እንደፈጠረለትም ተናግረዋል፡፡ የቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፉን ከተቀላቀለ በኋላ ዲጅታል ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ረገድ በርካታ ሥራዎች እየሰራ መሆኑንም ዋና ስራ አስፈጻሚው ጠቅሰዋል፡፡

ይህ የድርጅቱ ጅምር ስራ ሁሉም ዜጋ በትንሽ ገንዘብ ጥራት ያለው የቴሌኮም አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ ‹‹እኛ እንደ ድርጅት የምንፈልገው በአገሪቱ ሁሉም ሰው ፈጣን እና ጥራት ያለው የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲያገኝ ነው፤ ለዚህ ደግሞ ኃላፊነት ወስደን እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚው እንዳሉት፤ ኩባንያው እየተከተለ ያለው የንግድ አሰራር የደንበኞቹን ፍላጎት በማወቅ መፈጸም ነው፤ በድምጽ በኩል አገልግሎቶችን በቅናሽ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል፡፡ አሁን የፋይናንስ አገልግሎትን ለማሳለጥ የሚችሉ አዳዲስ ሥራዎች አስተዋውቋል፡፡ በዚህም በዲጅታል ፋይናንስ ዘርፉ ብዙ ሥራዎች እየሰራ ነው፡፡

ኩባንያው ወደ ኢንቪስትመንት ከገባ ከስምንት ወራት በኋላ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ የኔትወርክ መሠረተ ልማቶች ሲሰራ የቆየ ሲሆን፣ የመሠረተ ልማት ግንባታውን በአዲስ አበባና በተወሰኑ የክልል ከተሞች አካሂዷል። ወደ ስራ የገባው 500 የቴሌኮም መሠረተ ልማቶች በመገንባት ነው፡፡ እነዚህ መሰረተ ልማቶች በአሁኑ ወቅት ሁለት ሺ ደርሰዋል፡፡ በእነዚህ መሰረተ ልማቶች የተለያዩ አገልግሎቱን ተደራሽ እያደረገ ይገኛል፡፡

በአንድ ዓመት ውስጥ በ26 ከተሞችና በ254 ትናንሽ ከተሞች አገልግሎቱን እየሰጠ ነው። ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የቴሌኮም የአገልግሎት መስጫ ቅርንጫፎቹን ሁለት ሺህ 57 ያደረሰ ሲሆን፤ ድርጅቱ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ቅርንጫፎቹን ወደ ሰባት ሺህ ለማሳደግ እየሰራ ይገኛል፡፡ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በኢትዮጵያ በቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ዘርፉ ጥራት፣ ተደራሽነትና ፈጠራ ላይ የተሻሻሉ ውጤቶችን ለማምጣት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ነው፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ ኩባንያው በኢትዮጵያ ባደረገው ኢንቨስትመንት አንድ ሺህ ቀጥተኛና 10ሺህ ቀጥተኛ ያልሆኑ የሥራ ዕድሎችን መፍጠሩንም አስታውቀዋል። በቀጣይ ሁለት ዓመታት ውስጥ ይህንን ቁጥር በእጥፍ ለማሳደግ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

እንደ ስራ አስፈፃሚው ዊም ቫንሄሌፑት ገለፃ፤ አሁን ላይ አራት ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ ቋሚ ደንበኞችን ማፍራቱን ገልጸው፤ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የደንበኞቹን ቁጥር አሁን ካለበት 35 በመቶ ወደ 85 በመቶ ለማድረስም አቅዷል።

ይሄ በአንድ ዓመት ውስጥ የተሰራ የመጀመሪያ ሥራ ነው ያሉት ስራ አስፈጻሚው፤ በሚቀጥሉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ከዚህም በላይ በጣም ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ የቴሌኮም መሰረተ ልማቶቹን ወደ ሰባት ሺ ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡ የኔትወርኩንም ተደራሽነት ለማሳደግ ተጨማሪ 600ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት እንደሚደረግ አመልክተዋል፡፡

በቀጣይ በሚገነቡት ሰባት ሺ የቴሌኮሙዩኒኬሽን መሠረተ ልማቶች ከ80 እስከ 85 በመቶ ያህሉን ሕዝብ ተደራሽ ማድረግ እንደሚቻል ጠቅሰው፣ መሠረተ ልማቱን ለማሳደጉ ስራም እስከ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ ኢንቨስትመንት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚው ኩባንያው በኢትዮጵያ ሁለት ዓላማዎችን ይዞ ነው የተቋቋመው ሲሉ ይገልጻሉ። እነዚህም የቴሌኮም አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግና የፋይናንስ አገልግሎት መስጠት መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዘርፍ ከተሰማራበት ጊዜ አንስቶ ፈጣን፣ ጥራት ያለው እና አስተማማኝ የኢንተርኔት እና የስልክ አገልግሎትን ለማስፋፋት እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ከቴሌኮም አገልግሎት ባለፈ በፋይናንስ አገልግሎትም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ግንቦት ፍቃድ የወሰደው የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎት ‹‹ኤምፔሳ (M-PESA)›› የተሰኘ የሞባይል መተግበሪያ ስራ ወደ ስራ መግባቱን አስታውቀዋል፡፡

እሳቸው እንዳብራሩት፤ የፋይናንስ አገልግሎቱ ከተጀመረ እስካሁን ድረስም አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ደንበኞች ማፍራት ችሏል፡፡ የፋይናንስ አገልግሎቱም የኩባንያውን ደንበኞችና አጋሮቹን የተሻለ ጥራት ያለውና ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኙ አስችሏቸዋል፡፡

በግማሽ ዓመት አፈጻጸሙ የዲጅታል የክፍያ ሥርዓቱ እንዲከናወንባቸው በትግበራ ላይ ከዋሉት በጂ.ኤስ.ኤም እና ኢምፔሳ የክፍያ መተግበሪያዎች አገልግሎቶች ጠንካራ የንግድ እንቅስቃሴን በማከናወን ትልቅ ምዕራፍ እያስመዘገበ መሆኑንም ዋና ስራ አስፈጸሚው ዊም ቫንሄሌፑት ጠቅሰዋል፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በሀገሪቱ በቴሌኮሙኒኬሽንም ሆነ በፋይናንስ አገልግሎት ዘርፉ የተለያዩ አዳዲስ አገልግሎቶች እያመጣ ተደራሽነቱን እያሰፋ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡ ለሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተደራሽነቱን ለማስፋት እንደሚሰራም አስታውቀዋል፡፡

በንግድ ስትራቴጂውም ተመራጭ የአገልግሎት አሰጣጥ አማራጮችን በመጠቀም ፈጣን፣ ከፍተኛ ጥራት ያለው እና አስተማማኝ የኔትወርክ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ሥራዎች እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንንም የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች በደንብ እንደሚያውቁት ተናግረዋል፡፡

አሁንም ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ እየሰጠ ያለው የቴሌኮም አገልግሎት በጣም ርካሽ ነው የሚሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ ለዚህም ከሳፋሪኮም ወደ ሳፋሪኮም የሚደረገው የድምጽ ጥሪ ሳይቀር በነጻ የሚደረግ መሆኑን በአብነት ይጠቅሳሉ፡፡ ይህም ደንበኞች ከቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ከጓደኞቻቸው ጋር እንደልባቸው እንዲነጋገሩ ወይም መረጃ እንዲለዋወጡ የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል፡፡

‹‹ኤምፔሳ (M-PESA)›› የተሰኘው የሞባይል መተግበሪያ ከኤኖቬሽንና ከዲጅታል ፋይናንስ አገልግሎት አንጻር ሲታይ ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ ትልቅ እድል ይዞ መምጣቱን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ኤምፔሳ›› የተሰኘውን የሞባይል መተግበሪያ ተጠቅመው መግዛትና መሸጥ የሚፈልጉ ገንዘብ ልውውጥ ለማድረግ በእጅጉ ጠቃሚ መሆኑን ገልጸው፤ ከገንዘብ ንክኪ ነጻ የሆነ ማሕበረሰብ ለመፍጠር ትልቅ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኩባንያው ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ባለባት ኢትዮጵያ ሁለተኛው የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ሆኖ መግባቱን አስታውሰው፣ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ አስገራሚ ጉዞ እያደረገ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ዊም ቫንሄሌፑት አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ በኢትዮጵያ ለሳፋሪኮም እድገትም ሆነ በኢንዱስትሪው ውስጥ ለማደግ ሰፊ እድል አለ። አስተማማኝ የቴሌኮም መሰረተ ልማት በመገንባት አገልግሎት ለመስጠት ትክክለኛ ቦታ ላይ እንደሆንን እናምናለን ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ይሄ እንደ ባለሀብት የተለየ ከፍተኛ እድል መሆኑን አስታውቀው፣ በአገሪቱ በጣም ትልቅ ኢንቨስትመንት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹በቀጣይ ከዚህ የበለጠ ጥሩ እድል እንደሚገጥመን እናምናለን›› ሲሉ ዋና ስራ አስፈጻሚው ዊም ቫንሄሌፑት አስታውቀዋል፡፡

በቀጣይ ጊዜያት ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዲጅታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እየተከናወነ ባለው ተግባር ውስጥም ሆነ በቴሌኮም ዘርፍ አገልግሎቶች በመስጠት የራሱን ድርሻ እንደሚወጣም ዋና ስራ አስፈጻሚው አረጋግጠዋል፤ ድርጅቱ አሁን ባሉት ጠንካራ ሠራተኞች ጥረት አገልግሎቶችንና ተደራሽነቱን እያሰፋ ዲጅታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በፊት በቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዘርፍ ለመሰማራት ከ850 ሚሊዮን ዶላር ምዋለንዋይ ስራ ላይ ለማዋል ፍቃድ ወስዶ ኢትዮጵያ የገባ ሁለተኛው የቴሌኮም ኦፕሬተር እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን   ኅዳር 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You