የትግራይ ክልል በአትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ ብስክሌት፣ ባድሜንተንና ሌሎችም ስፖርቶች ውጤታማ ስፖርተኞችን በማፍራት ይታወቃል፡፡ ክልሉ ባለፉት ዓመታት በነበረው ጦርነት ምክንያት ከስፖርት ርቆ የቆየ ሲሆን፤ እንደክልል ከፍተኛ ውድመት ካስተናገዱ ዘርፎች መካከል አንዱ ስፖርት ነው፡፡
በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ዘርፈብዙ ጉዳት የደረሰበትን የትግራይ ክልል ስፖርት መልሶ ለመገንባት የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ሲሆን፣ እነዚህ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተጠቁሟል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን 27ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ትናንት እና ከትናንት በስቲያ በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ አከናውኗል። በጉባኤው ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ለክልሉ ስፖርት በሚደረገው የመልሶ ግንባታ የስፖርቱ ዘርፍ የተጠናከረ እገዛ ማድረግ እንደሚገባው ገልፀዋል፡፡
በክልሉ በነበረው ጦርነት ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ ጉዳት ከደረሰባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ ስፖርት መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፣ በክልሉ በሚደረገው መልሶ ግንባታ ላይ የስፖርቱ ዘርፍ የራሱን ምልከታ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል፡፡ በመሆኑም ጉባኤው እንዲሁም ጉባኤተኛው በሚኖረው ቆይታ ክልሉ በሚያደርገው የመልሶ ግንባታ የሚኖረውን ተሳትፎ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል፡፡
አቶ ጌታቸው አክለውም፣ በጦርነቱ ወቅት በነበረው ሁኔታ የትግራይ አትሌቶች ሥነልቦና እንዳይጎዳ እንዲሁም ከጦርነቱም በኋላ አትሌቶችን ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ በማድረግ ረገድ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ላደረገችው አስተዋጽኦ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ስም ያስጠሩ የትግራይ ተወላጅ አትሌቶች የመኖራቸውን ያህል በርካቶች ደግሞ ወደፊት ስመጥር አትሌት ሊሆኑ የሚችሉ በመኖራቸው ፌዴሬሽኑ እገዛ ሊያደርግላቸው ይገባል ሲሉም ተናግረዋል፡፡ የአትሌቲክስ መንደርን ለማነጽ ቀደም ብሎ የተጀመረውንም እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት ጥረት እንደሚደረግም ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል፡፡ ስፖርት ጤናማ ማኅበረሰብን ለማፍራት የሚኖረውን ሚና የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡
በጉባኤው የመክፈቻ ንግግር ያደረገችው የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፤ በጦርነቱ ምክንያት ከስፖርቱ ርቆ በቆየው የትግራይ ክልል በድጋሚ መገናኘት መቻል አስደሳች መሆኑን ገልፃለች፡፡
በጉባኤው የ2015ዓም የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን፤ የተለያዩ ሃሳቦች በጉባኤተኛው በኩል ተሰንዝረዋል፡፡ በተለይም የስፖርት ማዘውተሪያ ጉዳይ፣ የብሔራዊ ቡድን ምልመላ በተለይም የአትሌቶችና የአሰልጣኞች አመራረጥ፣ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ከተካሄዱ በኋላ የነበሩ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመገምገም ለቀጣይ እርማት አለመውሰድ፣ በፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚዎች መካከል አለመግባባት መኖሩ፣ የቴክኒክ ባለሙያዎችና የሥራ አስፈጻሚ ሥራ መደበላለቅ እንዲሁም ጣልቃ ገብነት መኖሩ ተጠቁሟል፡፡
በዓመቱ ኢትዮጵያ በተካፈለችባቸው ዓለም አቀፍ ውድድሮች የተመዘገቡት ውጤቶች አበረታች ከነበሩ የዓመቱ አፈጻጸም መካከል ዋናው ነው፡፡ በፋይናንስ በኩልም የተለያዩ ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን፤ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የተደረገው የስፖንሰር ስምምነትም ለዚህ ማሳያ መሆኑንም በፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ተገልጿል፡፡
ክልሎች ከፌዴሬሽኑ የሚያገኙት ድጋፍን በተመለከተ ችግሮች መኖራቸው እንዲሁም የስፖርት አበረታች ቅመሞችና የዕድሜ ተገቢነት ችግር አሁንም የስፖርቱ ዋነኛ ስጋት ሆኖ መቀጠሉንና ጠንካራ ውሳኔ የሚያስፈልገው መሆኑም ተመላክቷል፡፡ በአዲስ መልክ የተዋቀረው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ያቀረበውን የአባልነት ጥያቄም በጉባኤው ተቀባይነት አግኝቷል፡፡
በጉባኤው ላይም የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ተወካይ፣ የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት እንዲሁም የጠቅላ ጉባኤው አባላት ተገኝተዋል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን 27ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን እንዲሁም 19ኛውን የማራቶን ሪሌ ውድድር በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ የነበረውን የሁለት ቀናት ቆይታ ትናንት አጠናቋል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ኅዳር 17 ቀን 2016 ዓ.ም