ዝም ይባላል እንዴ ?

ዛሬም ቪዲዮው በግልጽ ተከፍቶ ያጠነጥናል፡፡ እየተላለፈ ያለው ስርጭት የሚሄደው በዩቲብ ነው። መቼም ይህ ማህበራዊ ሚዲየ ይሉት ከመጣ ወዲህ ቴክኖሎጂው በየሰዉ እጅ መመላለሱ ብርቅ አልሆነም ፡፡ እንዲህ መሆኑ ባልከፋ ነበር፡፡ ማንም እንደትኩስ ሻይ የሚደርሰውን መረጃ ሳይቀዘቅዝ ፉት ቢል አይጠላም፡፡

አንዳንዴ ግን ለማየትም ለማመንም የሚከበዱ መረጃዎች ይደርሳሉ፡፡ የሌላውን ዓለም ተወት አድርገን የኛውን ሀገር እውነት እንቃኝ ብንል እስከዛሬ ብዙ ሰምተን፣ አይተናል፡፡ የሚታመነው የትኛው ይሁን አይሁን ሳናውቀው የፈሰሰልንን ሁሉ ፊታችንን ሳናዞር አይተን ተደንቀናል፣ አዳንቀናል፡፡

አንዳንዴ ጆሮ መርጦ አይሰማ ፣ ሆኖብን ለውስጣችን የሚደርሰውን ሁሉ መቀበላችን ተጽዕኖው የጎላ ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ልብ የሚለው ያለ አይመስልም፡፡ አብዛኛው በተቀደደለት የአመኔታ ቦይ መፍሰሱን ይቀጥላል፡፡ ባየው እየተደነቀ ፣ በሰማው እየተገረመ መኖር ምርጫው ነው፡፡ ከሰሞኑ በዚሁ የማህበራዊ ሚዲያ የሚመላለሰውን መረጃ በርካታው ተመልካች ቃኝቶታል ፡፡

መረጃው በጽሁፍ ከመድረስ አልፎ ቪዲዮ ተሰርቶለት መታየቱ የመታመኑን ስፋት አልቆታል፡፡ ይህን ተከትሎም ጉዳዩ ለበርካቶች ፌዝና ጨዋታ ሰፊ በር መክፈቱ አልቀረም፡፡ የሃሳቡን ጫፍ የያዙ አንዳንዶች ከቁም ነገር በዘለለ ቀልዳቸው አሁን ድረስ ነገሩን እያቀለሉት ይገኛል፡፡

ለጊዜው ጥርስ ያስፈግግ የሚመስለው ታሪክ የብዙሃኑን ቤት ማንኳኳቱና ከስጋት መጣሉ አይቀሬ ሆኗል፡፡ ዛሬ በዚህ ጉዳይ የማይሳቀቅ የማይጠራጠር የለምና። ወዳጆቼ ስለምን እያወራሁ እንደሆነ ልንገራችሁ፡፡ አንኳር ርዕሰ ጉዳዬ ስለ አህያው ስጋ ሽያጭና ስለ ጥቂት ሉካንዳ ቤቶች ሚስጥር ነው፡፡

እውነት ለመናገር ይህን ቃል ደፍሬ ለመጻፍ ውስጤ ክፉኛ ተሸማቋል፡፡ እንዲህ አይነቱ ስሜት ከእኔ አልፎ ለበርካቶች እንደሚጋባም እገምታለሁ፡፡ ከጥቂት ጊዜያት ጀምሮ ርዕሰ ጉዳዩ በየቤታችን ገብቷል፡፡ ምንም እንኳን ጆሯችን ብዙ ወሬዎችን እየተላመደ ነው ቢባልም ለስጋ ወዳዱ ህብረተሰብ ይህ ዜና ከክፉም በላይ አስነዋሪና አሳፋሪው ይሆናል፡፡

አሁንም በዚሁ የማህበራዊ ሚዲያ ቅኝት ላይ ነኝ፡፡ ትኩረቴን በቅርቡ በተለቀቀው አንድ ገራሚ ቪዲዮ ላይ አድርጌያለሁ ፡፡ ከዩቲዩቡ ገጸ ታሪክ መረዳት እንደሚቻለው የስጋውን ሽያጭ ‹‹የአህያውን›› ጉዳይ ማለቴ ነው፡፡ ደርሰንበታል ባሉና ድርጊቱን ፈጽሟል በተባለ ግለሰብ መሀል አንድ ውዝግብ ተነስቷል፡፡

በሚተላለፈው የቪዲዮ ምስል አናት ውርንጭላ ቢጤ ቂብ ብላለች፡፡ ከፎቶው ቀጥሎ ‹‹ገንዘብ ካገኘን የጀብም ሥጋ ቢሆን እንሸጣለን›› የሚል ርዕስ ደምቆ ተጽፏል ፡፡ ከሰውየው አስደንጋጭ ንግግሮች መሀል የተመረጠ ቃል መሆኑ ነው። ቪዲዮውን በአግርሞት ማየቴን ቀጥያለሁ፡፡ አንድ የፕሮግራሙ መሪ ፊቱን በማስክ ሸፍኖ ታሪኩን ማስረዳት፣ ማብራራት ቀጠለ፡፡ እንደዋዛ እየሰማነው ያለው እውነት የአህያ ሥጋንና የሽያጩን ጉዳይ ሆኗል፡፡

ይህ ጆሮን ጭው የሚደርግ ታሪክ እየሆነ ነው የተባለው በሌላ ቦታ አይደለም፡፡ በእኛው ሀገር ሰማይ ሥር እንጂ፡፡ ከሁኔታው ስረዳ ግለሰቡ ባለሆቴልና የሥጋ አቅራቢ ነጋዴ ነው፡፡ ይህ መረጃ ያላቸው አነፍናፊዎች በስልክ ቀጠሮ ይዘው እርሱ ይገኝበታል ወደተባለ ስፍራ ያመራሉ፡፡ ይህ ሁሉ እንቅስቃሴ በድብቁ የቪዲዮ ካሜራ ተቀርፆ ለተመልካቾች እየተላለፈ ነው፡፡

ግለሰቡ ራሱን የሚያስተዋውቀው በተለየ መተማመን መሆኑ ይስተዋላል፡፡ ‹‹ክቡር ደንበኞቼ›› ለሚላቸው አጋሮቹ ሥጋውን በተሻለ ጥራት እንደሚያቀርብ ሲናገር ያለአንዳች ፍርሀትና ያለምንም ሀፍረት ነው፡፡ የሁለቱ አይታመኔ የሚመስል ውይይት ቀጥሏል፡፡ የገዢውና የአህያ ሥጋ ሻጩ ንግግር በመተማመንና በመስማማት እየዘለቀ ነው፡፡ ሰውየው አፉን ሞልቶ የአህያ ሥጋ ለተጠቃሚው እንደሚያቀርብና ሥራውም የተፈቀደ ስለመሆኑ ማብራራት ይዟል፡፡ አሁንም ድብቅ ካሜራው ሥራውን አላቆመም፡፡ እያንዳንዷን እንቅስቃሴ ከነንግግሩ እየቀረጸ ነው፡፡

 ሰውየው ስለዋጋው፣ ስለጥራቱ፣ መናገሩን አላቆመም። ይባስ ብሎ ሰርቶ ስለመለወጥ በኩራት መዘርዘር ጀምሯል። ዘመናዊ ቤቱንና የመኪና ቁልፉን እያሳየም ኑሮው የተቀየረው በዚሁ ሥራ መሆኑን ከከመግለጽ አላፈረም፡፡

በሥራ አጋሮቹ መሀል ውይይቱ ቀጥሏል፡፡ ሰውየው ጥያቄዎችን እየመለሰ ስለ ግሉ የአህያ ቄራ ማብራራቱን ይዟል፡፡ ስለሚታከሙት አህዮችና ድንገቴ እርድ ስለሚፈጸምባቸው በግልጽ ሲናገር ያለማጋነን አንድ ለሀገር የሚሰራ ታዋቂ ባለሀብት ይመስላል፡፡

ሰውየው ስለአህዮቹ ጤንነትና የቄራው ደረጃ በኩራት እያብራራ ራሱን መካብ ቀጥሏል፡፡ የግል ተሞክሮውንና ሊኖር የሚችልን የሕግ ተጠያቂነት ጭምር በስፋት ይዘረዝራል፡፡ በዚህ ጽሁፍ ለመግለጽ የሚከብዱ ንግግሮች ፣ ለማሰብ የሚያዳግቱ ቃላቶች በሁለቱ ሰዎች መሀል እየተካሄደ ነው። ‹‹ጉድ›› እስኪባል ‹‹አጀብ›› የሚያሰኝ ድብቅ ጉዳይ ገሀድ መሆኑን አስተዋልን፡፡

አሁንም በዚሁ የማህበራዊ ሚዲያ ሌሎች የቪዲዮ ምስሎች ወደ ዓይናችን እየደረሱ ነው፡፡ ሁሉም ተመሳሳይ ታሪክና አንድ አይነት ፍላጎት አላቸው፡፡ የሚገርመው ሚስጥሩን ደረስንበት በሚሉትና ጉዳችን ገሀድ ወጣ ባሉት መካከል ያለው ፍፃሜ በጠብና ድብድብ መጠናቀቁ ነው፡፡ ባለሆቴሉ ፣ ባለ አህያ ቄራዎቹና ሌሎች ባለታሪኮች ጭምር ሚስጥራችን ታወቀ ባሉ ጊዜ ዱላ ይመዛሉ፣ ለጠብ ይጋበዛሉ፡፡

ሰሞኑን በተለያዩ ገጾች የምናያቸው ምስሎች በሙሉ ተረተትና ፊልም አስኪመስሉን ለማመን ተቸግረንባቸዋል፡፡ አብዛኞቻችን ስጋ ቤት በሄድን ጊዜ ልማዳችን እንደቀድሞው አልሆነም፡፡ ‹‹ከሽንጡ፣ ከአጥንቱ›› ማለትን ትተተናል። የስጋውን መቅላት፣ መስባት፣ መብዛትና ማነስ እያጤን የአመጣጡን ሚስጥርና ምንነቱን መመራመር ልምዳችን ሆኗል፡፡ ይህ ጥርጣሬና ሃሳብ ደጋግሞ ቢከተለን አይፈረድም፡፡ የእስከዛሬው ባህልና እምነታችን ከአህያ ሥጋ አዛምዶን አያውቅምና ፡፡ እኛ ማለት ነውርን በነውርነቱ የምናርቅ በጎውን በጥሩነት አክብረን የምንይዝ ነን፡፡

በዚሁ የማህበራዊ ሚዲያ ላይ እየተለጠፉ ያሉ አንዳንድ ጉዳዮች ከማስደንገጥ አልፈው ሳይወዱ በግድ ያስፈግጋሉ፡፡ አንዳንዱ ‹‹አፋልጉን›› የሚል ማስታወቂያ አድምቆ ይጽፍና ‹‹አህያችን ቀን ሲሰራ ውሎ ከሰአት ሳር ሲግጥ እንደወጣ አልተመለሰም›› የሚል ተማጽኖ ይጨምርበታል፡፡ ይህ በሰውኛ አሽሙር የተላለፈ መልዕክት ትርጉም የሚያሻው አይደለም፡፡

አንዳንዴ ከየት መጡ የማይባሉ አስደንጋጭ ወሬዎች በሀገር ምድሩ መናፈሳቸው ያለ ነው፡፡ እነዚህ እጅን በአፍ የሚያስጭኑ ድንገቴ ወሬዎች የመነሻ ምንጫቸው አይታወቅም ፡፡ አጥብቆ የሚጠይቅ ቢኖር ደግሞ ‹‹አሉ›› ከማለት ውጭ አንዳች ማረጋገጫ አያገኝም፡፡

እንዲህ አይነቶቹ የወሬ ንፋሶች እንደዋዛ ተጀምረው፣ ተጨምረው ተጨማምረው ይቆያሉ፡፡ እንደአመጣጣቸው ብን ብለው ለመጥፋትና ለመረሳት ደግሞ አፍታ አይቆዩም። የሰሞኑ ጆሮ አግል ወሬ ግን ከተለመዱት ሽውታዎች ሁሉ የተለየ ነው፡፡ የመነሻ ምንጩ ከመታወቅ አልፎ በማስረጃ ተረጋግጧል፡፡

ምስልና ድምጹን የሚያስተላልፈው የዩቲብ ገጽ ማንነቱን አልደበቀም፡፡ ከዚሁ ተያይዞ መግለጫ ቢጤ ለመስጠት የደፈሩ አንዳንዶችም በገሀድ ወጥተው እየተናገሩ ነው፡፡ አሁን ላይ ብዙሃኑ በግልጽ እንደሚያወራው የአህያ ሥጋ ለውጭ ገበያ እንዲቀርብ ተፈቅዷል እየተባለ ነው፡፡

ይህ የአሉ ወሬ ግን ከሚመለከታቸው አካላት አንደበት አልተሰማም፡፡ ጉዳዩ እንዲህ በአደባባይ የባቄላ ወፍጮ ሆኖ እያለ ከሕግ አካላትና ከሃይማኖት አባቶች፣ ከባለሙያዎችና ከጤና ጥበቃ አካላት አንዲት ቃል ትንፍሽ አልተባለም፡፡ ዝምታውን እንደመስማማት የቆጠሩት አንዳንዶች ጭራሽ ብዙሃን የሚጠየፉትን የአህያ ሥጋ በየፌስቡክና ዩቲዩብ ገጻቸው እየለጠፉ ማሳቀቁን ቀጥለውበታል፡፡

እኔ ‹‹ውሸት ሲቆይ እውነት ይሆናል›› ይሉት አባባል ዕውን እንዳይሆን ስጋቱ አለኝ፡፡ ይህ ገደብ የለሽ ወሬ በወቅቱ ያለመቀጨቱና ከሚመለከተው አካላት አንዳች ያለመባሉ ጥያቄውን እያባሰው ነው፡፡ ወዳጆቼ! እናንተስ ምን ትላላችሁ? ፣ መሸፋፈን መደባበቁ እስከመቼ መቀጠል አለበት ? ኧረ ! ጎበዝ ዝም ይባላል እንዴ ?

 መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን   ኅዳር17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You