የትምህርት ሚኒስቴር ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ የተለያዩ ተግባራዊ የትምህርት ጥራት ማሻሻያ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ከነዚህም ውስጥ አንዱ የፈተና አሰጣጥ ሥረዓቱን ማሻሻልና መቀየር ነው፡፡ በዘንድሮው በጀት ዓመትም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የፈተና አሰጣጥ ሥርዓቱን በማጠናከሩና ከኩረጃ ነፃ በማድረጉ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት በትምህርት ጥራት ረገድ ያለውን ክፍተት በተዘዋዋሪ ፍንትው አድርጎ አሳይቷል፡፡
ከአሁን ቀደም በትምህርት ተደራሽነት እንጂ በጥራት ላይ ጉልህ ትኩረት ተሰጥቶ ባመለሠራቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተፈተኑ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ውስጥ 3 ነጥብ 2 ከመቶ ያህሉ ብቻ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ ማግኝት ችለዋል፡፡ ይህም ጠንካራ የፈተና አሰጣጥ ሥርዓት በመኖሩ ከዚህ በፊት በኩረጃና በስርቆት ተግበስብሶ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በቀላሉ መግባት እንደማይቻል አመላክቷል፡፡
ፈተናው በዚህ መልኩ እንዲሰጥ የተፈለገው ከኩረጃ፣ ፈተናን ከመሰረቅና ከመሳሰሉ ችግሮች ነፃ ለማድረግ እንደሆነም የትምህርት ሚኒስቴር በተደጋጋሚ ገልጿል፡፡ ፈተናዎቹን በዚህ መልኩ የመስጠቱ ጥቅም ከትምህርት ጥራት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ባይኖረውም በተዘዋዋሪ ጥራት ያለውና ብቁ ተማሪ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም እንዲገባ በማድረግ በኩል ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ተናግሯል፡፡
በሌላ በኩል የፈተና አሰጣጡ ተማሪዎች በአቋራጭና በስርቆት ፈተና ማግኘት እንደ ማይችሉ ሲረዱ በሚገባ እንደሚያጠኑና መምህራንም ተማሪዎቻቸውን በሚገባ ማስተማር እንዳለባቸው በቂ ትምህርት ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም ከፈተና ስርቆት ጋር በተያያዘ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚያመጣውን የሞራል ችግርም እንደቀረፈ ተነግሯል፡፡
ይህ ሲባል ግን እንደሀገር በትምህርት ጥራት በኩል የገጠሙ ችግሮች የፈተና አሰጣጥን በማጠናከርና በመቀየር ብቻ መቅረፍ እደማይቻል የብዙዎች እምነት ነው፡፡ ትምህርት ሚኒስቴርም የፈተና አሰጣጡን በመቀየር ብቻ የትምህርት ጥራትን ማሻሻል እንደማይቻል በተደጋጋሚ አስታውቋል፡፡
ሁሉንም ሊያስማማ የሚችለው ጉዳይ ግን ፈተናው ሀገሪቷ ያለችበትን የትምህርት ጥራት ችግር በሚገባ ማሳየቱ ነው፡፡ የፈተናው ውጤት አሁን ያለውን የትምህርት ጥራት ችግር ለማሻሻል መወሰድ ያለባቸውን ርምጃዎችን በተጨበጡ ማስረጃዎች ላይ ተንተርሶ ጠቁሟል፡፡ ከዚህ በመነሳት የትምህርት ሚኒስቴር የፈተና አሰጣጥ ሥርዓቱን ከመቀየር ባሻገር በትምህርቱ ዘርፍ ያሉ ሌሎች የሪፎርም ሥራዎችን በማከናወን የትምህርት ጥራቱን ለማረጋገጥ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡
የትምህርት ሚኒትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንደሚናገሩት የፈተና አሰጣጥ ሥርዓቱን ከመቀየር ባሻገር የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የተለያዩ የትምህርት ሪፎርም ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ አንደኛውና ዋነኛው ሥርዓተ ትምህርቱን /ካሪኩለም/ ማሻሻልና አስፈላጊ የትምህርት ቁሳቁሶችን በተለይ ደግሞ መፃህፍት ማቅረብ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ሥርዓተ ትምህርት/ካሪኩለም/ ተከልሷል። የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ካሪኩለም ባለፈው ዓመት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተዘጋጅቶ የነበረ ቢሆንም ዘንድሮ ወደ አማርኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ሥራ ላይ ውሏል፡፡
በዚህ ዓመት የግብረ-ገብነት ትምህርት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሆኗል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ትመህርትም እንደዚሁ ከዚህ በፊት ከነበረው ሁኔታ የተቀየረውና በጣም አስፈላጊው በፊት የነበሩት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሆኑ መደረጋቸው ነው፡፡ በዚህም ከሚሰጠው የአካዳሚያዊ ትምህርት በተጨማሪ ተማሪዎች ከአስረኛ ትምህርት በኋላ የቴክኒክና ሙያ ትምህርቶችን የሚያገኙበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ተማሪዎችም ሁለት አይነት ክህሎት እንዲያገኙና እንደየፍላጎታቸው የአካዳሚያዊንና የቴክኒክ ትምህርቱን እንዲመርጡ ያስችላቸዋል። በዚሁ መሠረት በአንድ የክፍል ደረጃ አስራ ሶስት መፃህፍት ተዘጋጅተዋል፡፡
ሁለተኛው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል እያከናወነው ያለው ተግባር የመምህራንን ብቃትና ችሎታ እንዲሁም የትምህርት ቤት አስተዳደር በተቻለ መጠን ከምንም አይነት የፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ አውጥቶ ከትምህርት ጋር ብቻ የተያያዘ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ በዚሁ መሠረት የትምህርት ቤቶች አስተዳዳሪዎች የሚመረጡበት መስፈርት በተቻለ መጠን በችሎታቸውና በብቃታቸው ብቻ መሆን አለበት በሚልና ይህንኑ ለማድረግ ካለፈው ዓመት መጀመሪያ አንስቶ አራት ሺህ የሚሆኑ ትምህርት ቤት አስተዳዳሪዎች አንድ ዓመት የፈጀ የተግባር ሥልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡ ይህ ደግሞ ለአንድ ዓመት ብቻ የሚሆን ሳይሆን ቀጣይነት ያለው ነው፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር የዘንድሮ ትልቁ ትኩረት የመምህራንን ሥልጠናን በሚመለከት ሲሆን ከዚህ ጋር በተያያዘ በተለይ የክረምት የመምህራን ሥልጠና እንደ ካሁን ቀደሙ ዲፕሎማ ወይም ዲግሪ ለማግኘት የሚደረግ ሳይሆን ከሚያስተምሩበት ትምህርትና ከትምህርት ማበልፀጊያ ጋር የተያያዘ ብቻ እንዲሆን ተደርጎ ይሰጣል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችም በዚህ ክረምት ሰኔ ሰላሳ መደበኛ የማስተማር ሥራቸውን ጨርሰው በሀምሌና ነሐሴ ወራት የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ መምህራን ማሠልጠኛ እንዲሆኑ መርሃ ግብር ተይዟል፤ የማስተማሪያ ሞጁሎችም ተዘጋጅተዋል። ስለዚህ በመምህራን ብቃትና ችሎታ እንዲሁም በትምህርት ቤቶች አስተዳዳሪዎች ላይ ሥራ ይሠራል ማለት ነው፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ እንደሚያብራሩት የትምህርት ጥራትን ከማሻሻል አንፃር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በሶስተኛ ደረጃ የሚያከናውነው ሥራ የትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማት ማሻሻል ሲሆን ይህም ሥራ በጥናት የተደገፈና የተማሪዎችን ትምህርት የመቀበል አቅም ባገናዘበ መልኩ እየተከናወነ የሚገኝ ነው፡፡ ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች ምቹና ሳቢ እንዲሆኑ፣ የመማሪያ ክፍሎች በጣም የተጣበቡ እንዳይሆኑ መሠረት ባደረገ መልኩና በአንድ ክፍል ውስጥ በአማካኝ ከ 40 እስከ 50 ተማሪዎች ብቻ ሊማሩበት የሚያስችል ከፍተኛ የሆነ የመማሪያ ክፍሎችን የማሻሻያ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
በዚህም ከአርከቴክት ባለሙያዎች ማህበር ጋር በመሆን ዘመኑን የዋጁ አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችል ዲዛይን የልጆች ሥነ – ልቦና ባለሙያዎችና የትምህርት ቤተሰቦችን ጭምር በማሳተፍ እንዲዘጋጅ ተደርጓል። ያሉትንና የተበላሹትን በሀገር አቀፍ ደረጃ ወደ 50 ሺ የሚጠጉ ትምህርት ቤቶችን ደግሞ ለማስተካከል ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር ጀምሮ ‹‹ትምህርት ለትውልድ›› የተሰኘ ፕሮጀክት ተጀምሯል፡፡
በዚህ ‹‹ትምህርት ለትውልድ›› እንቅስቃሴ ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ በህብረተሰቡ ተሳትፎ 14 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የሚገመት የገንዘብ፣ የጉልበትና የቁሳቁስ ሀብት ተሰብስቧል፡፡ ወደ 3 ሺ 180 የሚሆኑ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ወደ 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በሚያወጣ ገንዘብ ተሠርተዋል፡፡ አንዳንዶቹ ተሻሽለዋል፤ ሌሎቹ ደግሞ በአዲስ መልክ ተሠርተዋል፡፡ ወደ 1 ሺ 366 የሚሆኑ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተጠግነዋል፡፡ 236 የሚሆኑ አዳዲስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል፡፡ ባጠቃላይ ወደ 10 ሺ 117 የሚሆኑ የትምህርት ቤት እድሳቶችና ማሻሻያዎች ተደርገዋል፡፡
ከዚህ ባለፈ ቀደም ሲል የነበሩትን ትምህርት ቤቶችን ከማሻሻል ባሻገር አዳዲስና በተለይ ደግሞ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት የፈረሱትን መልሶ የመገንባትና ትምህርት ቤት ያልተዳረሰባቸውን አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ ትምህርት ቤቶችን በአዲስ የመገንባት ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡ በዚህ ዓመት 50 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአፋርና በአማራ ክልል እየተገነቡ ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉ ተጠናቀዋል፡፡ የተቀሩት ግማሾቹ በቀጣዮቹ ሶስት ወራቶች ውስጥ ይጠናቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
እነዚህም ባለፉት አራት ወራት ውስጥ የተከናወኑ ናቸው፡፡ ይህ ክንውን በዚሁ ከቀጠለና ከትምህርት ቤቶች ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር መፍታት ከተቻለ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ለሚደረገው ጥረት ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም 50 ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመሥራት በተያዘው እቅድ መሠረት የአስራ ስድስቱ ግንባታ በዚህ ዓመት ተጀምሯል፡፡ በተቻለ መጠን ሀብቱ እንደተገኘ በሁሉም ክልሎች እነዚህን ትምህርት ቤቶች ለመገንባት ውጥን ተይዟል፡፡
ከሁሉም ክልል የተውጣጡና በጣም ጎበዝ የሆኑ ተማሪዎች የሚማሩባቸው በየክልሉ አንድ አንድ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ቃል በተገባው መሠረት በዚህ ዓመት ስድስት አዳሪ ትምህርት ቤቶች የማስተማር ሥራ ይጀምራሉ። ከነዚህ ውስጥ ሶስቱ ወይ አራቱ በ2017 ዓ.ም ተማሪ ይቀበላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ትምህርት ሚኒስትሩ እንደሚሉት በከፍተኛ ትምህርት ደረጃም የተለያዩ የትምህርት ጥራት ማሻሻያ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱ ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝና ከምንም አይነት የፖለቲካ ተፅእኖ ነፃ የማድረግ ብሎም ራሳቸውን ማስተዳደር የሚችሉና ዋና ሥራቸው የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ ሥራ ነው፡፡ ይህም ሥራ ዩኒቨርሲቲዎችን ከቀጥታ የመንግሥት አስተዳደር ማውጣትና ራሳቸው ተወዳድረው ጎበዝ ተማሪዎችን እየተቀበሉ ማስተማር የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠርን ያጠቃልላል፡፡
በዚህ መሠረት ይህ ሥራ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጀምሯል፡፡ በዚህም በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በርካታ የለውጥ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ የራስ ገዝ አሠራር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በዚህ ዓመት የተጀመረ ቢሆንም በዓመቱ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የወሰዱትን ይቀበላል፡፡ ነገር ግን በሙከራ ደረጃ በምደባ ከተቀበለው ተማሪ በተጨማሪ በተመላላሽ ከፍሎ መማር የሚፈልግ ሊማር የሚችልበትን ሁኔታ ለመፍጠር ጥናት እየተደረገ ነው፡፡ ይህም ዘንድሮ ትምህርት ከመጀመሩ በፊት ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የወረቀት ሥራዎችም እየተከናወኑ ነው፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ በድሮው አሠራር መሠረት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ወደ 3 ሺ 200 ተማሪዎችን እንዲቀበል ተመድቦለታል። በተጨማሪም ተመላልሰው መማር የሚፈልጉ ካሉ ከፍለው ሊማሩ የሚችሉበት እድል ለመፍጠር እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው። ከራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ አሠራር ባሻገር ዩኒቨርሲቲዎች ሁሉም ሁሉንም የትምህርት አይነት የሚያስተምሩ ሳይሆኑ በተልእኮ እንዲለዩና በተወሰኑ የትምህርት አይነቶች ላይ ጠንካራ ሆነው እንዲፈጠሩ በተለይ ደግሞ ዩኒቨርሲቲዎቹ ካሉበት አካባቢ የሕዝብ ኑሮና የኢኖሚና ሁኔታ ጋር የሚቀራረቡ ሥራዎችን መሥራት የሚችሉ ጠንካራ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲኖሩ ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡
በዚህ ዓመት እንቅስቃሴው ሥራ ላይ እየዋለ ይገኛል። ስለዚህ ዩኒቨርሲቲዎች በተልዕኮ የሚለዩ ይሆናል፡፡ አንዳንዶቹ የጥናትና ምርምር ይሆናሉ። ሌሎቹ ደግሞ አጠቃላይ ትምህርት የሚሰጡ ይሆናሉ፡፡ በዚህ መሠረት ተማሪዎችን መቀበል እንዲጀምሩ ነው እየተሠራ ያለው፡፡ ለአብነትም የኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ሙሉ በሙሉ የትምህርት ዘርፍ ማስተማሪያ ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን ተደርጓል። በተመሳሳይ ሌሎቹም ዩኒቨርሲቲዎች በተወሰነ ደረጃ ተማሪዎች ወደፊት የት ዩኒቨርሲቲ ሄደው መማር እንዳለባቸው ሲያስቡ ሊማሩ ከሚፈልጉት ትምህርት ጋር የተጣጣሙ እንዲሆኑ የማድረግ እንቅስቃሴ ነው እየተደረገ ያለው፡፡
ይህ ሁሉ ባጠቃላይ እየተከናወነ ያለው ሥራ ትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ያለው የፈተና አሰጣጥ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ምንም አይነት ሚስጢር የለውም፡፡ እንደውም ፈተናው ከብዶ ሊሆን ይችላል እንዲህ አይነት ውጤት የተመዘገበው የሚለውን ብዥታ ለማጥራት በፈተናው ዙሪያ በገለልተኛ አካል ጥናት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስጠንቶ በቀጣዩ ሳምንት በሚካሄደው የትምህርት ጉባዔ ላይ የጥናቱ ውጤትና ሪፖርት የሚቅርብ ይሆናል፡፡
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ኅዳር 17 ቀን 2016 ዓ.ም