አምራችና ሸማችን በዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂ

የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን ከተቋቋሙ ተቋማት መካከል አንዱ ነው፡፡ ተቋሙ በግብርናው ዘርፍ ለረዥም ጊዜ የቆዩና ትላልቅ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን በመለየት ለተለዩት ችግሮችም እንዲሁ የመፍትሔ ሃሳቦችን በማመንጨት ምርትና ምርታማነት እንዲያድግና አምራችና ሸማቹ ተጠቃሚ እንዲሆን እንዲሁም ከዘርፉ በሚገኘው ውጤት የሀገር ኢኮኖሚ እንዲያድግ የሚሠራ ተቋም ነው፡፡

ተቋሙ ለምርትና ምርታማነት ዕድገት እንዲሁም የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከሚያከናውናቸው ተግባሮች መካከል በዲጅታል ቴክኖሎጂ ለአርሶ አደሩ የሚሰጠው የምክር አገልግሎት አንዱ ነው፡፡ ተቋሙ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለአርሶ አደሩ የሚሰጠውን የምክር አገልግሎት ቀልጣፋ፣ ቀላልና ምቹ ማድረግ የሚያስችለውን 8028 የተባለ ፕላት ፎርም አልምቶ ተግባራዊ አድርጓል፡፡ ገበሬዎቹም በእጅ ስልካቸው ወደ 8028 እየደወሉ በግብርና ሥራቸው ሁሉ ለሚገጥማቸው ማንኛውም ችግር መፍትሔ እያገኙ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጪምዶ ዋንጫላ ገልጸዋል ፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ በዚህ ሥርዓት በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሆነ የምክር አገልግሎት ለአርሶ አደሩ ይሰጣል፡፡ አርሶ አደሩ በ8028 ነጻ ጥሪ ደውሎ ያጋጠመውን ችግር በአጭሩ በመግለጽ ፈጣን ምላሽና የምክር አገልግሎት እያገኘ ነው፡፡

እስካሁን በዚህ ሥርዓት ውስጥ የምክር አገልግሎት እየተሰጠ የነበረው በሰብል ምርቶች ብቻ እንደነበር ያስታወሱት ዶክተር ጪምዶ፤ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የገበያ መረጃን ለማካተትና ለአርሶና አርብቶ አደሩ ተደራሽ ማድረግ የሚያስችለውን ሲስተም ለማልማት ዝግጅቱ ተጠናቅቋል፡፡ ለዚህም ተቋሙ ከሜርሲ ኮርፕስ እና ከዩኤስአይድ ፊድ ዘ ፊውቸር ትራንስፎርሚንግ አግሪካልቸር/ MERCY CORPS Ethiopia እና ከUSAID Feed The Future Transforming Agriculture/ ከተሰኙት ድርጅቶች ጋር ለመሥራት መስማማቱን አስታውቀዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ በሰብል ምርቶች ብቻ የነበረውን የምክር አገልግሎትና የገበያ መረጃ ተደራሽነት በእንስሳት ሀብትም ማስፋት አስፈልጓል። በተለይም በአፋርና በሶማሌ ክልሎች የሚሰጠው የግብርና ምክር አገልግሎት በእንስሳት ሀብት ላይ የሚያተኩር ይሆናል፡፡ በእንስሳት ሀብት የሚሳተፉ የአፋርና የሶማሌ ክልል አርሶ አደሮች ወይም አርብቶ አደሮች ይህን መረጃ አግኝተው በሚገባ የሚጠቀሙበትን ዕድል መፍጠር የሚያስችል ይሆናል፡፡

በእስካሁኑ ሂደትም በእነዚህ ክልሎች 130 ሺ የሚደርሱ አርብቶ አደሮች በዚህ መረጃ እየተጠቀሙ ሲሆን፤ ይህም ከፍተኛ ፍላጎት መኖሩን ያመለክታል። በእነዚህ ክልሎች ሲስተሙን አስፍቶ መጠቀም እንዲቻልም ተቋሙ ከሁለቱ አጋር ድርጅቶች ጋር ስምምነት አድርጓል፡፡

ድርጅቶቹ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርጉ የጠቀሱት ዶክተር ጪምዶ፤ የ USAID Feed The Future Transforming Agriculture የ23 ሚሊዮን ብር እንዲሁም MERCY CORPS Ethiopia ደግሞ አምስት ሚሊዮን የሚደርስ ብር ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት በበኩሉ ስድስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ በማድረግ በጋራ ሲስተሙን በማልማት አርሶና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ እንዲሆን ይደረጋል ብለዋል፡፡ ዲጅታል ሲስተም ማለት ህጻን ልጅ እንደማሳደግ ነው ያሉት ዶክተር ጪምዶ፣ በየጊዜው አዳዲስ ነገሮችን በመጨመር አቅምን በማሳደግ ሲስተሙን ማልማት የግድ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ ይህ ሲስተም የአርሶና አርብቶ አደሩን አቅም ለማሳደግ ከፍተኛ ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን፤ በተለይም ለአርሶና ለአርብቶ አደሩ በሚያመች መንገድ ሲስተሙ የሚለማ ይሆናል፡፡ ይህ ሲስተም ከለማ በኋላ በክልል የሚገኙ አርሶ አደሮች በተለይም አርብቶ አደሮች እንዲሁም በክልሉ የሚገኙ የልማት ሠራተኞች ይህን መረጃ የሚያገኙ ይሆናል፡፡

መረጃው እጅግ በጣም ፈጣን ምላሽ የሚሰጥበት መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ጪምዶ፤ አርብቶ አደሮች ደውለው በ24 ሰዓት ውስጥ መልስ የሚያገኙበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ መልስ ካላገኙ መረጃው በቀጥታ ወደ ኢንስቲትዩቱ እንደሚመጣ ጠቅሰው፣ ኢንስቲትዩቱም ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ ይህም አርሶና አርብቶ አደሩ ስለግብርና ወቅታዊ መረጃዎችን በፍጥነት ማግኘት ያስችላል ብለዋል፡፡

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ በቴክኖሎጂው ከሚያገኛቸው የተለያዩ መረጃዎች መካከልም የአንበጣና ሌሎች ተባዮች መረጃዎች ይገኙበታል፤ እነዚህን ችግሮች በጥናት በመለየት አስቀድሞ ከሳተላይት በሚገኘው መረጃ መሠረት እየመጣ ያለውን አደጋ ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ በማድረግ አስፈላጊውን የቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ ያስችላል፤ መረጃውም አስፈላጊ ከሆኑ ምክሮች ጋር ተደራሽ እንዲሆን ይደረጋል፡፡ አርሶና አርብቶ አደሩም ይህንኑ የምክር አገልግሎት በመቀበል አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይችላል፡፡

ሲስተሙ ለአርሶ አደሩ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እጅግ የላቀና የጎላ ነው፡፡ በተለይም ምርትና ምርታማነትን እንዲጨምር እና የገበያ መረጃ ማግኘት እንዲችል ጉልህ አበርክቶ ይኖረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት አርብቶ አደሩ የገበያ መረጃ የለውም፤ ምን ያህል እና የት ቦታ ወስዶ እንደሚሸጥ ምንም አይነት መረጃ የሌለው በመሆኑ በመሀል ለደላሎች ተጋላጭ ይሆናል፡፡ ደላሎች በተለይም በግብርና ምርቶች ሰፊ ድርሻ ያላቸው በመሆኑ አምራቹም ሆነ ሸማቹ ተጎጂ ናቸው፡፡

በዚህ ሲስተም ውስጥ አምራቹንና ሸማቹን በማስገባት ሁለቱም አካላት መረጃው እንዲኖራቸው ይደረጋል ያሉት ዶክተር ጪምዶ፤ ሲስተሙ ደላላውን ከመሀል ለማስወጣት እጅግ ጠቃሚ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ ሲስተሙ በተለይም አምራቹንና ሸማቹን በማስተሳሰር ህጋዊ ያልሆነውን ደላላ ሙሉ ለሙሉ ማስወጣት እንደሚችልም አስታውቀዋል፡፡

በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት በግብርና ምርቶች ላይ ትልቅ ችግር እየፈጠሩ ያሉትና ሰፊ ድርሻ ያላቸው ሕገወጥ ደላሎች መሆናቸውን ገልጸው፤ እነዚህ ደላሎች ምርት እያለ ምርት የለም በማለት ዋጋ እንዲጨምር የሚያደርጉና ምርቱ ወደ ሸማቹ እንዳይደርስ ሰው ሰራሽ እጥረት የሚፈጥሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም በየወረዳው የገበያ መረጃ የሚሰበስቡ ባለሙያዎችን በመቅጠር ወደ ተግባር መግባት መቻሉን ጠቅሰው፣ በየሳምንቱ የገበያ መረጃ ተሰብስቦ ትክከለኛነቱ ሲረጋገጥ ወደ ሲስተሙ እንደሚገባና እንደ አስፈላጊነቱ አምራቹና ሸማቹ እንዲጠቀምበት እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩቱ እያደራጀ ያለው ብሔራዊ የገበያ ሥርዓት እንደሆነ የጠቀሱት ዶክተር ጪምዶ፤ ይህ የገበያ መረጃ ሁሉም ቦታ ላይ ተደራሽ ይሆናል ማለት እንዳልሆነም አስታውቀዋል፡፡ የኢንተርኔት ተደራሽነትን እንደሚጠይቅ ገልጸው፣ ሁሉም አርሶ አደር መረጃው እንዲኖረውና ስለ ሲስተሙ በቂ ግንዛቤ ይዞ ተጠቃሚ መሆን እንዲችል በሚዲያ የማስተዋወቅ ሥራ መሥራት ተገቢ እንደሆነም አመላክተዋል፡፡

ሌላው በግብርና ግብዓት አቅርቦት ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ያስችላል የተባለው ዲጅታል የክፍያ ሥርዓት ነው፤ ይህም ልማዳዊ አሠራርን የሚያስቀር እንደሆነ ነው ዶክተር ጪምዶ ተናግረዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ ግብርና የተለያዩ ግብዓቶችን የሚጠቀም ሲሆን፤ የሀገሪቱ አርሶ አደር በተለይም ማዳበሪያ፣ ምርጥና የተሻሻሉ ዝርያዎችን ይጠቀማል። እነዚህን የግብርና ግብዓቶች የሚጠቀመው አርሶ አደርም ግብዓቶቹን የሚያገኝበት ሥርዓት እጅግ ኋላቀር በመሆኑ የግብዓቶቹን ጥራትም ሆነ ዋጋ መቆጣጠር አይቻልም፡፡

እነዚህን መረጃዎች ለማወቅ የልማት ሠራተኛው የግድ አርሶ አደሩ ቤት ተገኝቶ መመዝገብ ይጠበቅበት እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ዘመናዊ በሆነ መንገድ በዲጅታል የክፍያ ሥርዓት መቆጣጠር እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡

ለአብነትም ማዳበሪያ ከጅቡቲ ተጓጉዞ ታች ቀበሌ ደርሶ ለአርሶ አደሩ እስከሚሰራጭ ድረስ መቆጣጠር የሚያስችለው የኤሌክትሮኒክ ክፍያ ሥርዓት የማዳበሪያ አሰጣጡንም ዘመናዊ የሚያደርግ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ አርሶ አደሩ የእጅ ስልኩን በመጠቀም የሚፈልገውን የግብርና ግብዓት ይጠይቃል፡፡ ክፍያውንም በኤሌክትሮኒክ የክፍያ መንገድ ይፈጽማል፡፡ ለዚህም ከሲስተሙ ጋር የተናበበ የመለያ ቁጥር የሚሰጠው ሲሆን፤ ይህም ግብዓቱን መችና የት ቦታ ላይ መውሰድ እንደሚችል መረጃ ይሰጠዋል፡፡ በመሆኑም በአካባቢው በሚገኙ የህብረት ሥራ ማህበራት ቀርቦ መውሰድ የሚያስችለው ይሆናል፡፡ አገልግሎቱ ለአጠቃቀም ቀላል፣ ምቹና ወጪ ቆጣቢ እንደሆነም ተነግሮለታል፡፡

አርሶ አደሩ በሲስተሙ ሲጠቀም በቤቱ ሆኖ የእጅ ስልኩን ብቻ በመጠቀም የሚፈልገውን የግብርና ግብዓትና መጠን መጠየቅ ይችላል፤ ጥያቄውም ወደ ሲስተሙ ይገባል፡፡ በዚህ መሠረት ግብዓቱ ዝግጁ ሲሆን፣ አርሶ አደሩ የሚደርሰውን መልዕክት ተከትሎ ግብዓቱን መውሰድ የሚችልበት ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡

ይህ ሥርዓት በሙከራ ደረጃ የተጀመረ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ጪምዶ፤ በ65 ወረዳዎች ሥርዓቱ በሙከራ ደረጃ መጀመሩንም አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ በኋላ በማዳበሪያ ዙሪያ የሚነሱ ማጨበርበሮች ይወገዳሉ፤ ስግብግብ ነጋዴዎችንም ጭምር ሲስተሙ ያስወግዳቸዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ‹‹በሌሎች ሀገራት የሚታየው ቴክኖሎጂ በእኛም ሀገር ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል›› ብለዋል፡፡

የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ አጠቃላይ በግብርናው ዘርፍ ውስጥ ያሉ መሠረታዊ ችግሮችን በጥናትና በምርምር የመለየት ሥራ እንደሚሠራ ጠቅሰው፣ ከለየ በኋላም ለተለዩት ችግሮች የመፍትሔ ሃሳቦችን እንደሚያቀርብ ገልጸዋል፡፡

አርሶ አደሩ ከግብርና ሥራው ጋር ተያይዞ ለሚገጥመው ችግር ኢኒስቲትዩቱ የምክር አገልግሎት እየሰጠ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም አርብቶ አደሩ እንስሳቱን ወቅታዊ በሆነ ዋጋ መሸጥ እንዲችል የገበያ ዋጋ መረጃ የሚያገኝበትን ዘመናዊ አሠራር ለመተግበር ከአጋር ድርጅቶች ጋር ለመሥራት መግባባት ላይ መድረሱን ገልጸዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ የእንስሳት ግብይቱን ጨምሮ በእንስሳት ጤና አጠባበቅና አረባብ ላይ ትኩረት ተደርጎ የሚሠራ ሲሆን፤ በየወረዳው ማለትም የእንስሳት ገበያዎች ባሉባቸው አካባቢዎች የኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎች ተገኝተው በየአካባቢው ያለውን የገበያ ሁኔታ በማጥናት መረጃው ተሰብስቦ መልሶ የሚሰራጭ ይሆናል፡፡ መረጃውም ለማንኛውም መረጃውን ለሚፈልግ ሰው ተደራሽ ይሆናል፡፡

መረጃው ተደራሽ የሚሆነው በ6077 በስልክ የድምጽ ጥሪና አጭር የጽሁፍ መልዕክት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ይህ የአርሶ አደሮችና የአርብቶ አደሮች የግብርና መረጃ መስጫ አገልግሎት እንዲሁም የሀገር አቀፍ የገበያ መረጃ ሥርዓት ዲጅታል አገልግሎት በተለያዩ ቋንቋዎች እንደሚቀርብም ዶክተር ማንደፍሮ አስታውቀዋል፡፡ መረጃው ተደራሽ የሚሆነው ለአርሶ አደር፣ ለአርብቶ አደርና ለከፊል አርብቶ አደር ብቻ ሳይሆን ለሸማቹና የቄራ አገልግሎት ለሚሰጡም ጭምር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

መረጃውም የት ቦታ፣ በምን ያህል ዋጋ፣ ምን አይነት እንስሳ እንደሚሸጥ እንደሚያሳይ ጠቁመው፣ ለሰብል ምርትም ተመሳሳይ አገልግሎት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡ ይህም አርሶ አደሩንና ሸማቹን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ምርቱን እና እንስሳውን ያለአግባብ እንዳይሸጥ እንደሚያደርግ አብራርተው፣ ሸማቹም ያለአግባብ ከዋጋ በላይ እንዳይገዛ የሚያስችለው አሠራር ነው ብለዋል፡፡ ይህ የመረጃ ሥርዓት ለአርሶ አደሩም ሆነ ለሸማቹ መፍትሔ የሚሰጥ የመረጃ ሥርዓት ሆኖ እንደሚያገለግልና የአርብቶ አደሩና የአርሶ አደሩን ምርታማነት ማሳደግና ገቢ መጨመርን ዓላማ አድርጎ እንደሚሠራ አመልክተዋል፡፡

ይህ የመረጃ ሥርዓት ከዓመት በፊት ተግባራዊ እንደሆነና አርሶና አርብቶ አደሩ የመረጃ ልውውጥ በማድረግ እየተጠቀመቡት መሆናቸውን ያስታወሱት ዶክተር ማንደፍሮ፣ በአሁኑ ወቅት ይህንኑ አሠራር ለማስፋትና ባልተዳረሰባቸው ክልሎች ጭምር ተደራሽ ለመሆን ስምምነት መደረሱን ገልጸዋል። አገልግሎቱ እየሰፋ መሆኑን መሆኑን ጠቅሰው፣ በአሁኑ ስምምነት የአፋርና ሱማሌ ክልልን መጨመር እንደተቻለ ገልጸዋል። ይህን ተከትሎም የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ከ157 ወረዳዎች ወደ 250 ወረዳዎች ከፍ ማለቱንና ተደራሽነቱ እየሰፋ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

ግብርናን ለማዘመን እየተጋ ያለው የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ይህን ሥራ የሚሠራው ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ሲሆን፤ ግብርና ሚኒስቴር በዚህ ሲስተም ውስጥ ገብቶ አቅሙ እንዲጎለብት ያደርጋል፡፡ ከዚሁ ሲስተም የተገኘውን ዕውቀትና ልምድ የግብርና ሚኒስቴር ቀምሮና በበቂ ሁኔታ አዘጋጅቶ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ሥራውን ሲያቆም በከፍተኛ ሁኔታ አስፋፍቶ የሚቀጥልበት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You