ኢትዮጵያን በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ወክለው ውጤታማ የሆኑ በርካታ አትሌቶችን በማፍራት ተጠቃሽ ከሆኑ ክልሎች መካከል ትግራይ አንዱ ነው። ክልሉ በነበረው ጦርነት ለዓመታት ከስፖርት እንቅስቃሴ ርቆ የቆየ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴዎች እየተመለሰ ይገኛል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም በክልሉ 19ኛውን የማራቶን ሪሌ ውድድርን ትናንት በመቀሌ ከተማ በማካሄድ ስፖርቱን የማነቃቃት ሥራ አከናውኗል።
አትሌቶች 42 ኪሎ ሜትሮችን ተከፋፍለው ዱላ በመቀባበል የሚያደርጉት የሪሌ ውድድርም መነሻና መድረሻውን በሰማዕታት ሐውልት በማድረግ ተካሂዷል። በውድድሩም ላይ የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት ጄነራል ጻድቃን ገብረትንሳይ፣ የክልሉ ስፖርት ኮሚሽነር ተክላይ ፈቃዱ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ጠንካራ ፉክክር በታየበት ውድድር ላይም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አትሌቲክስ ቡድን አሸናፊ በመሆን የወርቅ ሜዳሊያ፣ የዋንጫ እንዲሁም የገንዘብ ሽልማቱን ወስዷል። የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ክለብ ደግሞ ሁለተኛና ሦስተኛ በመሆን አጠናቀዋል። በውድድሩም ላይ አምስት ክልሎችና ዘጠኝ ክለቦች 84 አትሌቶችን አሳትፈዋል። በውድድሩ በርካታ ታዋቂ አትሌቶች የተሳታፉ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል አትሌት ሰለሞን ባረጋ፣ ሰንበሬ ተፈሪ፣ ጽጌ ገብረሰላማ እና ደራ ዲዳ ጥቂቶቹ ናቸው።
ውድድሩን በሚመለከት የአሸናፊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አትሌቲክስ ቡድን አባል የሆነችው አትሌት ካሳነሽ አየነው ስትናገር፣ ውድድሩ ፉክክር የታየበት ቢሆንም በጠንካራ የቡድን ሥራ አሸናፊ ሊሆኑ መቻላቸውን ገልጻለች። ከ5 ኪሎ ሜትር እስከ ግማሽ ማራቶን ባሉት ርቀቶች በበርካታ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የተሳተፈችው አትሌቷ መሰል ውድድሮች የአትሌቶችን አቅም ለማየት የሚያግዝ መሆኑን ተናግራለች። በተለይም በዓለም አቀፍ ደረጃ የመም ውድድሮች እየጠፉ በመሆናቸው እንዲሁም በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የመም ችግር ያለ በመሆኑ መሰል ውድድር ጠቀሜታው ከፍተኛ በመሆኑ ሊስፋፋ እንደሚገባ አመላክታለች።
በውድድሩ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቀውና ያገኘውን የገንዘብ ሽልማት በክልሉ ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ እንዲውል ያደረገው የኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ ሲሆን፣ ክለቡን በመወከል ከተወዳደሩት አትሌቶች መካከል አንዱ የሆነው ጸጋዬ ኪዳን፤ በሪጋ በተካሄደው የዓለም የጎዳና ላይ ቻምፒዮና 21ኪሎ ሜትር ውድድር ኢትዮጵያን ወክሏል። በዚህ ውድድር ላይም ጠንካራ ውድድር በማድረግ የብር ሜዳሊያ በማግኘታቸው መደሰቱን ገልጿል። የጎዳና ውድድሮች በየጊዜው በሀገር ውስጥ መደረጋቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚካፈሉባቸው ውድድሮች እንደሚጠቅሟቸውም ይጠቅሳል።
የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፤ ክልሉ በርካታ ስፖርተኞችን ለሀገር ያፈራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ወጣቱን ወደ ስፖርት ለመመለስ እንዲሁም ለመልሶ ግንባታ የሚወጣውን ሚና በተግባር እያሳየ መሆኑን ገልጸዋል። በስፖርት አማካኝነት አትሌቶች እንዲገናኙ ያደረገው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምስጋና ይገባዋል ሲሉም ተናግረዋል። ሌሎች የስፖርት ማኅበራትም በተመሳሳይ ለሰላም ግንባታው የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በውድድሩ ላይ በመገኘት ለአሸናፊዎች የዋንጫ ሽልማት ያበረከቱት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት ጄኔራል ጻድቃን በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ይህንን ውድድር በመቀሌ በማካሄዱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ፌዴሬሽኑ በጦርነቱ ወቅት የትግራይ ክልል አትሌቶችን በመደገፍ ውጤታማ እንዲሆኑ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም አስታውሰዋል። «ስፖርት የሰላምና የወዳጅነት መሣሪያ በመሆኑ ወጣቶችን ያንጻል። በመሆኑም ሌሎች የስፖርት ማኅበራትም ወደ ክልሉ በመምጣት ጉዳት የደረሰባቸውን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በመገንባትና የፈራረሱ የስፖርት አደረጃጀቶችን በማስተካከል ሊያግዙ ይገባል» ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
የክልሉ ስፖርት ኮሚሽነር አቶ ተክላይ ፈቃዱም ይህ ውድድር እንዲሁም የፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባኤ በመቀሌ እንዲደረግ ክልሉ ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት በማግኘቱ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን አመስግነዋል። በቀጣይም ሌሎች ጉባኤዎችን በማድረግ መነጋገርና መወያየት እንደሚያስፈልግና እንደክልል ወደነበረበት የስፖርት አቋም ለመመለስ እገዛ እንደሚሹም ጠቁመዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ህዳር 16/2016