በየአራት ዓመቱ የዓለም ሀገራትን በአንድ ጣሪያ ስር አሰባስቦ በስፖርቱ መድረክ የሚያፎካክረው ታላቁ ኦሊምፒክ ትልቅ ትኩረት ይሰጠዋል፡፡ በዚህ ታላቅ የስፖርት ድግስ ውጤታማ ለመሆን ሀገራት ብዙ ይለፋሉ። በሜዳሊያ ሰንጠረዥ ቀዳሚ ሆነው ለማጠናቀቅም በብዙ የስፖርት ዓይነቶች ላይ ትኩረት አድርገው ይዘጋጃሉ፡፡ ውጤታማ በሚያደርጋቸው የስፖርት ዓይነቶች ላይ ዝግጅት የሚያደርጉትም ኦሊምፒክ ሲቃረብ ብቻ አይደለም፡፡ ለሁሉም የስፖርት ዓይነቶች እኩል ትኩረት በመስጠት ዘወትር ይሠራሉ፡፡ በኦሊምፒክ በርካታ ሜዳሊያዎችን የሚያፍሱ ሀገራት ምስጢር ይሄው ነው፡፡
ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መድረክ በመሳተፍ ታሪካዊ የሆኑ ገድሎችን መጻፍ ከቻሉ አገራት መካከል ትጠቀሳለች። ስኬቶች ሁሉ የተመዘገቡት ግን በአንድ የአትሌቲክስ ስፖርት ያውም በረጅም ርቀት ውድድሮች ውጤት ላይ ብቻ ተንጠልጥለው ነው፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ተሳትፎዋ ከአትሌቲክስ ባሻገር የብስክሌትና የቦክስ ስፖርቶች በውጤት ባይታጀቡም ታሪክ አላቸው፡፡ ካለፈው የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ጀምሮም የወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ተሳትፎዋ አዲስ ምዕራፍ ከፍታለች፡፡
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ለሁሉም ስፖርቶች እኩል ትኩረት ሰጥታ መሥራት ከቻለም በበርካታ የስፖርት አይነቶች ኦሊምፒክ ላይ መሳተፍ የሚያስችል አቅም እንዳላት ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ የቀድሞ ቦክሰኛና የአሁኑ የማረሚያ ቤቶች ቦክስ ስፖርት ክለብ ቡድን መሪ ኮማንደር ፀጋሥላሴ አረጋይ ለሁሉም የኦሊምፒክ ስፖርቶች የሚሰጠው ትኩረት እኩል እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡
ኮማንደር ፀጋሥላሴ እንደሚያስረዱት፣ ኢትዮጵያ የእግር ኳስ ስፖርትን ቀድመው ከተዋወቁ ሀገራት አንዷ ብትሆንም ከአንድ የአፍሪካ ዋንጫና የሴካፋ ውድድር በቀር ያሳካችው ድል የለም፡፡ በዓለም ዋንጫም መሳተፍ ተስኗት ትገኛለች።በታሪኳ በዓለም ዋንጫ መሳተፍ የቻለችውም በወጣቶች መድረክ አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ለእግር ኳሱ የሚደረገው ድጋፍና የሚመዘገበው ውጤት የተገላቢጦሽ ነው፡፡ በአንጻሩ ኢትዮጵያ ከአትሌቲክስ እየተሰጠ ያለው ትኩረትና ድጋፍ አነስተኛ ነው፡፡ ይህም ያለውን አቅም መጠቀም እንዳይቻል አድርጓል፡፡
ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መድረክ በአትሌቲክስ፣ ብስክሌት እና ቦክስ ለብዙ ጊዜ በመሳተፍ ትታወቃለች። በአትሌቲክሱ ከፈር ቀዳጁ አትሌት አበበ ቢቂላ ጀምሮ በርካታ ሜዳሊያዎችንና ክብረወሰኖችን በእጇ ማስገባቱን ቀጥላበታለች፡፡ ይሁን እንጂ ለአትሌቲክስም የሚደረገው ድጋፍ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ የስፖርት ክለቦችም ውጤት ለሚያመጡ ስፖርቶችና ውጤት ለሌላቸው የሚሰጡት ትኩረትና የሚመድቡት በጀት እጅጉን የተለያየ ነው፡፡ ለቦክስና ብስክሌት ስፖርትም የሚሰጡት ትኩረት ከአትሌቲክሱ የተለየ እንዳልሆነ ኮማንደር ፀጋሥላሴ ያብራራሉ፡፡
ኢትዮጵያን በኦሊምፒክ ከወከሉት ስፖርቶች አንዱ በሆነው የቦክስ ስፖርት በኦሊምፒክ መሳተፍ የቻሉት ኮማንደር ፀጋሥላሴ፣ የኦሊምፒክ ስፖርቶች ትኩረት ተሰጥቷቸው ተገቢው ሥራ ሊከናወን ይገባል ይላሉ፡፡ የሀገር ባለውለታ ክለቦች ለእግር ኳስ በብዙ ሚሊየን ብሮች ሲያፈሱ ለቦክስ፣ አትሌቲክስና ብስክሌት የሚያወጡት እጅጉን አናሳ እንደሆነም በማሳያነት ያስቀምጣሉ፡፡ ይህን በምሳሌ ሲያስረዱም ቦክስ በትንሽ በጀት በአፍሪካ እና በዓለም መድረክ ኢትዮጵያን መወከል ይቻላል ይላሉ፡፡ ‹‹ከተመሠረቱ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠሩ ክለቦች በየዓመቱ ብዙ ገንዘብ ለእግር ኳስ ቢያፈሱም ውጤት አልባና ሀብትን ማባከን ብቻ ሆኖ ቀርቷል›› የሚሉት ኮማንደር ፀጋሥላሴ፣ እነዚህ ክለቦች በአትሌቲክስ ውጤታማና ሀገርን ማስጠራት የሚችሉ ስፖርተኞችን ቢያፈሩም ለስፖርቱ የሚመድቡት ገንዘብ ከእግር ኳስ ጋር ሲነጻጸር የሰማይና የምድር ያህል መሆኑን ያስቀምጣሉ፡፡
አትሌቲክሱ ለቁጥር የሚታክቱ ታሪክ ሠሪ ስፖርተኞችን በየጊዜው እያፈራ የዓለም መድረክን መቆጣጠር ቢችልም የክለቦች ትኩረት እንደ እግር ኳሱ እንዳልሆነና ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም ያስረዳሉ፡፡ ለቦክስና ብስክሌትም የሚመጥናቸውን ድጋፍና ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ ያስቀምጣሉ፡፡ ‹‹እግር ኳስ ላይ በርካታ ሚሊዮን ብር እያወጡ የቦክስ ክለብ የሌላቸውና ፍቃደኛ ያልሆኑ ክለቦችም ቁጥራቸው ጥቂት የሚባል አይደለም፡፡ የሚያስገርመውና የሚያንገበግበው ደግሞ ድሮ በቦክስ ስፖርት ታዋቂና ሀገርን መወከል የቻሉ ስፖርተኞችን ያፈሩ ክለቦች የቦክስ ክለብን አለመያዛቸው ነው፡፡›› በማለትም ቁጭታቸውን ይገልፃሉ፡፡
በኦሊምፒክ መድረክ የሀገርን ክብርን አጉልቶ ለማሳየት ሁሉም ክለቦች የኦሊምፒክ ስፖርት የሆኑትን ቦክስ፣ ብስክሌትና ወርልድ ቴኳንዶን የመሳሰሉ ስፖርቶችን መያዝ አለባቸው የሚል አቋም ያላቸው ኮማንደር ፀጋሥላሴ፣ እንደ ማሳያም ድሬዳዋ ከነማ ቦክስ ስፖርትን በመያዝ ውጤታማ እንደሆነና ሀገርን መወከል የቻሉ ስፖርተኞችን ማፍራቱን ይጠቅሳሉ፡፡
ስፖርቶቹ ብዙ ገንዘብን የማይጠይቁና የሀገርን ስም በዓለም መድረክ ማስጠራት የሚችሉ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ የሚናገሩት ኮማንደር ፀጋሥላሴ፣ በተለይም የቦክስ ስፖርት ተወዳጅነት እንደመሆኑ በሁሉም ክለቦች ቢታቀፍ ደጋፊዎች ደስተኛ እንደሚሆኑ ይጠቁማል። በኦሊምፒክ ከመሳተፍም በላይ ወጣቱን ለመያዝና ጤናማ ኅብረተሰብን ለመፍጠር ቦክስ ትልቅ አቅም እንዳለውም አክለዋል፡፡ ‹‹ከመንግሥት ካዝና ለስፖርቱ የሚወጣው ገንዘብ በአግባቡ ለኦሊምፒክ ስፖርቶችና ውጤትን ማምጣት ለሚችሉ ስፖርቶች መዋል አለበት፡፡›› በማለትም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ህዳር 15/2016