“የባሕላዊ ሕክምና” ሀገር በቀል የሆነና በልምድ የዳበረ እንዲሁም በሕብረተሰቡ ተቀባይነት ያገኘ ዕውቀት ሆኖ የእጽዋትንና የእንስሳትን ተዋጽኦ ወይም ማዕድናትንና የእጅ ጥበብን በመጠቀም የሚሰጥ የሕክምና አገልግሎት እንደሆነ ይነገራል። በኢትዮጵያ የባሕል ሕክምና ከጥንት ጀምሮ የነበረና ዘመናዊ ሕክምና ወደሀገሪቱ ከመግባቱ በፊት ሕዝቡ በስፋት ሲገለገልበት የቆየ ነው፡፡ ዘመናዊ ሕክምና በኢትዮጵያ ከተስፋፋም በኋላ ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነው የማሕበረሰብ ክፍል የዚሁ የባሕል ሕክምና ተጠቃሚ መሆኑን ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡
ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የባሕል ሕክምና ሙያ ያላቸው አዋቂዎች በተናጠልና በተበታተነ ሁኔታ አገልግሎቱን ለሕብረተሰቡ ሲሰጡ ቆይተዋል። ሕብረተሰቡም ከዘመናዊው ሕክምና ባልተናነሰ መልኩ የዚሁ ባሕላዊ ሕክምና አገልግሎት ተጠቃሚ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በተለይ የአዲስ አበባ የባሕል ሕክምና አዋቂዎች ማሕበር ተበታትነው እየሰሩ ያሉ በርካታ የባሕል ሕክምና ባለሙያዎችን በማሰባሰብና የማሕበሩ አባል እንዲሆኑ በማድረግ ከሚመለከተው አካል ፍቃድ አግኝተው ለሕብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ እየሰራ ይገኛል፡፡
በዚሁ መነሻነት ማሕበሩ የባሕላዊ መድኃኒት አገልግሎት ለመስጠት ያልተመዘገቡ አገልግሎት ሰጪዎች ካሉ እንዲመዘገቡና ሕጋዊ ሆነው እንዲሰሩ እያበረታታና ክትትል እያደረገ ይገኛል። የባሕል ሕክምና አገልግሎት በሚሰጡ እና ጉዳዩን በሚከታተለው በባለስልጣን መስሪያ ቤት መካከል ሆኖ በቅርበት ይሰራል፡፡ በባሕል ሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ስለሚከናወኑ የተለያዩ ተግባራት እቅድ ያወጣል፤ ተፈፃሚነቱንም ይከታተላል፤ ብሎም ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር የተለያዩ የመግባቢያ ሰነዶችን ይፈራረማል፡፡
በተጨማሪም በባሕላዊ መድኃኒት አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ጉዳዩ ለሚመለከተው ባለስልጣን መስሪያ ቤት የተለያዩ የአሰራር አቅጣጫዎችና ሃሳቦች ያቀርባል፡፡ አባላቱ ጥራት ያለው የባሕል ሕክምና አገልግሎት እንዲሰጡ የራሱን ሕገ-ደንብ አውጥቶ ይንቀሳቀሳል፡፡ ከሰሞኑም ማሕበሩ አራተኛ ዓመት የምስረታ በአሉንና ጉባኤውን በአዲስ አበባ ከልዩ ልዩ ባለድርሻ አካላትና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ጋር በመሆን አካሂዷል፡፡ በአሁኑ ግዜም 105 ዓባላትን ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
በዚሁ ጉባኤ ወቅት ማሕበሩ እያጋጠሙት ያሉትን ተግዳሮቶች የዘረዘረ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ስለ ባሕል ሕክምና አገልግሎት አሰጣጥና ሙያ የተሳሳተ ግንዛቤ በስፋት መኖር፣ በሚፈለገው ደረጃ በሕብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ የመፍጠር ችግር፣ እንደ ሀገር ጠንካራ የሆነ የባሕል ሕክምና ማሕበር ያለመሆን፣ ህገ ወጥ የባሕል ሕክምና ባለሙያ መሰሎች መበራከት እና ሙያውን የማይመጥኑ የተሳሳቱ ቅስቀሳዎች መብዛት ዋና ዋናዎቹ መሆኑን ጠቅሷል፡፡
መጋቢ ጥበብ መርጌታ መንግስቱ ደስታ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባሕል ሕክምና አዋቂዎች ማሕበር ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት የባሕል ሕክምና አዋቂዎች መድሃኒት የሚያዘጋጁባቸው ከእፅዋቶች በመጥፋት ላይ የሚገኙ ከመሆናቸው አንፃር እፅዋቶቹን በአንድ ቦታ ላይ በማሰባሰብ፣ በማራባት፣ በማሳደግና በመንከባከብ ለሕክምና እንዲውሉ ለማድረግ ማሕበሩ ለሚመለከተው የመንግስት አካል ጥያቄ አቅርቧል፡፡
በዚህ ረገድ መንግስታዊም ሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ማሕበሩን በልዩ ልዩ መልኩ እንዲደግፉ ይበረታታሉ፡፡ የባሕል ሕክምናውም ከአጉል እምነትና ባሕል ተለይቶና ይበልጥ ታውቆ ከእፀዋት፣ እንስሳትና ማእድናት ተዘጋጅቶ በስፋት ለታካሚዎች ተደራሽ እንዲሆን ይሰራል፡፡ የባሕል ሕክምና ጥንትም የነበረና ወደፊትም ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር ስለመሆኑም የማሳወቅና ከአጉል እምነት ተለይቶ እንዲታይ የማድረግ ስራ ማሕበሩ እየሰራ ይገኛል፡፡ ከዚህ አንፃር ሕብረተሰቡም የባሕል ሕክምና ከአጉል እምነት ጋር የተሳሰረ እንዳልሆነ በመረዳት የተሻሉና ከኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ሕጋዊ ፍቃድ ያገኙ አዋቂዎችን በማግኘት ተገቢውን ባሕላዊ ሕክምና ማግኘት ይችላል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሌሎችም የባሕል ሕክምና አዋቂዎች ሕጋዊ ሆነውና በዚሁ የመንግስት አካል ተመዝግበው ሙያቸውን በማሻሻል ተገቢውን የባሕላዊ ሕክምና አገልግሎት ለሕብረተሰቡ መስጠት ይችላሉ፡፡
ፕሬዚዳንቱ እንደሚናገሩት፣ ማሕበሩ በአሁኑ ግዜ እጩ አባላትን ጨምሮ 105 አባላት አሉት። ሕጋዊ ያልሆኑ የባሕል ሕክምና አዋቂዎችም በአዲስ አበባ የባሕል ሕክምና አዋቂዎች ማሕበር ተመዝግበውና ሕጋዊ ሰውነት አግኝተው በምግብና መድሃኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ባወጣው መመሪያና ሕግ መሰረት ስራቸውን እንዲሰሩና የበለጠ እውቅና እንዲገኝ ብሎም በሕገ ወጥ መልኩ በባሕል ሕክምና ስም ከሚሰሩ አካላት እንዲለዩ የማድረግ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡
እስካሁን ባለው ሂደት የአንድ የባሕላዊ ሕክምና አዋቂ ችሎታ የሚመሰከረው በታካሚዎች ነው። ይሁንና አሁን ባለው ሁኔታ አንድ የባሕል ሕክምና ባለሙያ አንድ ቦታ ላይ ሶስት ዓመት ከኖረ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪነት መታወቂያ ካለው፣ በሕብረተሰቡ እውቅና ካለው ወይም ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ የባሕል ሕክምና አዋቂዎች ማሕበር የባሕል ሕክምና አዋቂ መሆኑን ካረጋገጠ፣ ከየት እንደተማረ፣ ምን እንደሚያውቅ ምን አይነት እፅዋት እንደሚችል በዝርዝር ካወቀ በኋላ ማሕበሩ በደብዳቤ ወደ አዲስ አበባ ምግብና መድሃኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ይልከዋል፡፡
በመቀጠል አዲስ አበባ ምግብና መድሃኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን በመመሪያውና በሕጉ መሰረት ሕጋዊ የምዝገባ ሰርተፍኬት ይሰጠዋል፡፡ የባሕል ሀኪሙ ይህንኑ ሰርተፊኬት ይዞ እንዲሰራ ይደረጋል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ማሕበሩ በስሩ ያሉ የባሕል ሕክምና አዋቂዎች የሚያዘጋጇቸው መድሃኒቶች በሳይንሳዊ መንገድ እንዲመረመሩ ለማድረግ ፍቃደኛ ነው። በቀጣይም የማሕበሩ ፍላጎት መድሃኒቱን በማስመርመርና በተገቢው የሳይንሳዊ ፍተሻ ሂደት አልፎ ጥቅም ላይ እንዲውል ነው፡፡ መንግስት የሚፈለገውን ሁኔታ ካመቻቸና በተለይ ደግሞ ለባሕላዊ ሕክምና የሚውሉ እፅዋት እየጠፉ ስለሆነ እነርሱን ለማቆየት የሚያስችል ቦታ ቢፈቅድና በእፅዋቶቹ ላይ ምርምር አድርጎ ጎጂነታቸውንና ጥቅማቸውን ካረጋገጠ ለሕብረተሰቡ የሕክምና ጠቀሜታ እንዲውሉ ማሕበሩ ይፈልጋል፤ ለዚህም የራሱን ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡
በሌላ በኩል እንደ አዲስ አበባ ከተማ ማሕበሩ ሕጋዊ ሆነውና ፍቃድ አውጥተው የሚሰሩትንና ሕጋዊ ሳይሆኑ የሚሰሩትን የባሕል ሕክምና አዋቂዊችን ለይቷል፡፡ ይህ በመሆኑም ከሚመከተው አካል ጋር በመነጋገር ወደማሕበሩ እየመጡ ሕጋዊ ሆነው ቁጥጥርና ክትትሉን የሚመለከታቸው አካላት እያደረገላቸው ስራውን እንዲሰሩ እየተደረገ ነው፡፡ ማሕበሩን የሚወክሉና በክፍለከተማው የሚገኙ ባለሞያዎች በሚያመጡት መረጃ መሰረት ሕጋዊ ፍቃድ ይዘው ወደ ማሕበሩ እንዲመጡ፤ ሕብረተሰቡም ሕጋዊ በሆኑ የባሕል ሕክምና አዋቂዎች እንዲታከም ማሕበሩ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡
ከባሕል ሕክምና ጋር በተያያዘ ሕብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ማሕበሩ በዚህም ዘርፍ ያሉ ምሁራንንና የጤና ባለሞያዎችን በማምጣትና የውይይት መድረኮችን በመፍጠር ብሎም ስልጠናዎችን በማዘጋጀት ሕብረተሰቡ እንዲረዳ የማድረግ ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ባለስልጣን የመድሃኒት ምዝገባና ፍቃድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሃብታሙ በየነ እንደሚናገሩት፣ ባልስልጣኑ ባሕላዊም ሆኑ ዘመናዊ መድሃኒቶች ተመዝግበው ገበያ ላይ እንዲውሉ ይቆጣጠራል፡፡ መድሃኒቶቹ ገበያ ላይ ከዋሉም በኋላ በተጠቃሚው ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ፤ መድሃኒቱን የሚያዙ ባለሙያዎችም መድሃኒቶቹን በትክክል አውቀው እንዲሰሩ ክትትል ያደርጋል፡፡
በዚህ ሂደት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በተለይ በባሕላዊ ሕክምና ላይ የተሰማሩ ሰዎች መድሃኒታቸው ተመዝግቦ ወደ ሕጋዊ ስርዓት ገብተው እንዲሰሩ በሩን ክፍት አድርጎ እየጠበቀ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታም በኢትዮጵያ ባሕላዊ መድሃኒት በምርምር ታግዞና ተመዝግቦ ወደ ገበያ የሚወጣበት ሁኔታ የለም፡፡ ይህ እንዲሆን ግን ከምርምር ተቋማት ጋር በመገናኘት ባሕላዊ መድሃኒቶቹ ጉዳት እንደማያመጡ፣ ፈዋሽነታቸው የተረጋገጠ እንዲሆን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከባሕላዊ ሕክምና አዋቂዎችና በዚህ ዘርፍ ምርምር ከሚያደርጉ ተቋማት ጋር እየተነጋገረ ይገኛል። ለዚህም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሚያስፈልጉ መመሪያዎችን፣ ደምቦችን፣ ሕጎችንና ፖሊሲዎችን እያረቀቀ ነው፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ያሉት ባሕላዊ መድሃኒቶችና የባሕል ሕክምና አዋቂዎች በምርምር ታግዘው መድሃኒቶቻቸው ለተቃሚዎች እንዲደርሱ በማድረግ ሂደት ፍጥነት ባለመኖሮ ቻይናና ሕንድን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ምርቶቻቸው እንዲመዘገቡላቸው ጥያቄዎችን ያቀርባሉ፡፡ ይሁንና ሀገር በቀል መድሃኒቶች እንዳይቀጭጩና እንዳይጠፉ ለማድረግ የውጪዎቹን በመጥተው ለነዚህ ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተጠበቀ ነው፡፡ አሁንም የምርም ተቋማትና የባሕላዊ ሕክምና አዋቂዎች ተገናኝተው ቢሰሩና ወደ ውጤት ቢመጡ መልካም ነው፡፡
በተለይ ደግሞ በባሕላዊ ሕክምና አዋቂው በኩልና በተመራማሪው በኩል የሚኖረውና ‹‹መድሃኒቱ የኔ ነው›› የሚለው ስጋት የአእምሮ ንብረት ባለቤትነት እውቅና ማግኘት ከቻለና በዚህ ላይ ከተሰራ በሃገር ውስጥ ያለውን ትልቅ የባሕል ሕክምና አቅም መጠቀም ይቻላል፡፡ በትክክለኛው ሂደት የባሕል መድሃኒቶች ገበያ ላይ እንዲውሉ የማድረግ ስራው ገና ቢሆንም ሂደቶች ግን አሉ፡፡
ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፣ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የባሕላዊ መድሃኒቶች ወደ ገበያ ወጥተው ጥቅም ላይ ከመዋላቸው በፊት ጥራታቸውን፣ ፈዋሽነታቸውንና ደህንነታቸውን ያረጋግጣል፤ ፍቃድ ይሰጣል፡፡ ለዚህም ነው ፍላጎት አሳይቶ የባሕላዊ መድሃኒቶች አዋቂዎች ወደተቋሙ መጥተው የመድሃኒታቸውን ጥራት፣ ፈዋሽነትና ደህንት እንዲያረጋግጡ እየተጠባበቀ የሚገኘው። ይህን ለማድረግ በባሕላዊ መድሃኒት አዋቂውና በተመራማሪዎች በኩል ያሉ ፍላጎቶች ናቸው የሚጠበቁት፡፡
በተለያዩ የማሕበራዊ ሚዲያዎች የሚተዋወቁ የባሕላዊ መድሃኒቶችና ሕክምና ሕጋዊ እውቅና ያላቸው አይደሉም፡፡ ለዛም የኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ሕብረተሰቡ ይህን አውቆ ራሱን እንዲጠብቅ የባሕላዊ መድሃኒቶች ጥራት፣ ፈዋሽነትና ደህንነት አረጋግጦ ሕጋዊ ፍቃድ የሚሰጠው፡፡ በርግጥ በኢትዮጵያ ባሕላዊ መድሃኒቶች በሳይንሳዊ መንገድ ታይተውና ተፈትሸው ብሎም በፋብሪካ ደረጃ ተመርተው ገበያ ላይ የዋሉ የሉም፡፡ ባስልጣን መስሪያ ቤቱም የሚሰራው የባሕላዊ ሕክምና አዋቂዎች መድሃኒት ሲያዘጋጁ በምን ያህል ደረጃ እንደቀመሙ ለማየትና የመድሃኒቶቹን ፈዋሽነትና ደህንነት ማረጋገጥ ነው።
ስለዚህ የባሕል ሕክምና አዋቂዎች መድሃኒቶቻቸውን ወደ ገበያ ከማውጣታቸው በፊት ወደ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መጥተው የመድሃኒታቸውን ጥራት፣ ደህንነትና ፈዋሽነት ማረጋገጥና ሕጋዊ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ማግኘት አለባቸው፡፡ የሕክምናው ቦታውና መድሃኒቱ የሚዘጋጅበት ሁኔታም በደምብ መታወቅ አለበት፡፡ ይህም የተለያዩ ደረጃዎች ያሉት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታም አብዛኛዎቹ የባሕል መድሃኒቶች የመጀመሪያው የአመራረት ሂደት ደረጃ ላይ ነው ያሉት፡፡ እነዚህም ማድረቅና መበጥበጥ ናቸው፡፡
ይሁንና በሶስተኛ የአመራረት ሂደት ደረጃ ማለትም ባሕላዊ መድሃኒቶቹ በእንክብልና በፈሳሽ መልክ ሲቀርቡ ብዙ መታየት ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡ ምርምር ሊደረግባቸውም ይገባል፡፡ ስለዚህ ይህ እንዲጎለብት ነው ስራዎች እየተሰሩ የሚገኙት። ከዚህ አኳያ ምርምር ተቋማትም በራቸውን በዚህ መልኩ ክፍት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡
እስካሁን ድረስ ባለው ሁኔታ በባሕላዊ መድሃኒቶች ላይ ምርምር ሲያደርግ የቆየው የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ነው፡፡ አሁን ግን ስራው ወደ አርማወር ሃንሰን ኢንስቲትዩት ዞሮ በአንድ እንዲጠቃለል ተደርጓል። በዚህም የምርምር ስራው በተሻለ ሁኔታ እየታየ ነው፡፡ ነገር ግን አብዛኛዎቹ ጥናቶች ሳይተገበሩ የሼልፍ ማሞቂያ ሆነዋል፡፡ ስለዚህ እነዚህን ጥናቶች ወደ ተግባር መለወጥና በኢትዮጵያ ያለውን እምቅ የባሕላዊ መድሃኒት አቅም በስፋት መጠቀም ያስፈልጋል፡፡
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ህዳር 15/2016