የካሳሁን እናት
አዲስ አበባ ጳውሎስ ሆስፒታል ጀርባ የተወለደው ብላቴና ኑሮና ሕይወቱ ምቹ አልነበረም፡፡ በብቸኝነት የሚያሳድጉት እናቱ ስለእሱ ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። እናት በቂ መተዳዳሪያ የላቸውም፡፡ ለእሳቸውና ለትንሹ ልጅ ጉሮሮ ሁሌም ሮጠው ያድራሉ፡፡
ወይዘሮዋ ገጠር ብቸና ሳሉ ልጆቻቸውን ትተው ወጥተዋል፡፡ አዲስ አበባ ከመጡ የወለዱት ካሳሁንን ነው፡፡ የካሳሁን ብቸኛ ተስፋ አንድ እናቱ ናቸው። አብሯቸው በኖረበት ዓመታት ስለእሱ አልሆኑለት የለም፡፡ እንዳይራብ፣ እንዳይጠማ በጉልበታቸው አድረዋል፡፡ እንዳያዝን እንዳይከፋ በየቤቱ ሰርተዋል፡፡
የካሳሁን እናት ስለልጃቸው የሰነቁት ተስፋ ብሩህ ነው፡፡ እንደ እኩዮቹ ተምሮ እንዲለወጥ ይሻሉ፡፡ ነገን በተሻለ ዓለም እንዲኖር ምኞታቸው ነው፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ በየሰው ቤት እንጀራ እየጋገሩ፣ የተገኘውን እየሰሩ ያጎርሱታል፡፡
እንጀራ ጋጋሪዋ የካሳሁን እናት ውሎ ሲያድር ሕይወት ከበዳቸው፡፡ ብዙ የሚያስቡለት ልጅ ባክኖ እንዲቀር አልፈለጉም፡፡ ከዛሬ የተሻለ እንዲገጥመው በብዙ ታገሉ፡፡ አሳዳጊ ሆኖ የሚወስደውን፣ አስተምሮ ቁምነገር የሚያደርሰውን ድርጅት ጠያየቁ፡፡ ያሰቡትን አላጡም፡፡ ካሳሁንን ተረክቦ እያኖረ የሚያሳድግ አንድ ‹‹ተራድኦ›› ለምኞታቸው ደረሰ፡፡
ሕይወት በአዲሱ ቤት…
እናትና ልጅ ተለያይተው ሊኖሩ ጊዜው ደረሰ። ካሳሁንን የመካነ እየሱስ አዳሪ ትምህርት ቤት ሙሉ ለሙሉ ተረከበው፡፡ አሁን የእናቱ ተስፋ ለመለመ፡፡ ዘወትር የሚያስቡለት ልጃቸው ጥግ ሲይዝ ውስጣቸው በእፎይታ ፈጣሪን አመሰገነ፡፡
ካሳሁን ከእናቱ ተለይቶ ትምህርቱን በብርታት ቀጠለ፡፡ አንደኛ ደረጃን ጨርሶ ከሁለተኛው ተሻገረ። ይህ ጊዜ የማንነቱን መሰረት የሚጥልበት፣ የወደፊት ሕይወቱን የሚሰራበት ነበር፡፡ እሱ ስንፍናን ሳያውቅ አጥብቆ ተማረ፡፡ ሁሌም እናቱን ሲያስታውስ የነገውን ዓለም ያስባል፡፡ በዚህች ምድር ያሉት ብቸኛ ሐብት እናቱ ናቸው፡፡ ድካም ውለታቸውን መክፈል፣ ሀሳብ ውጥናቸውን ዳር ማድረስ ዕቅዱ ነው፡፡
አስራ ሁለተኛ ክፍልን አጠናቆ ብሔራዊ ፈተና እንደወሰደ ውጤቱን ጠበቀ፡፡ ወጣቱ ተማሪ የድካሙን አላጣም፡፡ ካሳሁን ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባውን ውጤት ማግኘቱን አረጋገጠ፡፡ ይህ እውነት ለእሱ ትልቅ ትርጉም ነበረው፡፡ ከፈጣሪ በታች ‹‹አሉኝ›› ለሚላቸው እናቱ ታላቅ ደስታን ያቀብላል፡፡ ለእሱ የወደፊት ሕይወት ብሩህ ተስፋን ይሰንቃል፡፡
ካሳሁን በዓመታት የዩኒቨርሲቲ ቆይታው የፋርማሲ ዘርፍ ትምህርቱን በርትቶ ቀጠለ፡፡ ይህ ጊዜ ለእሱ የማንነቱ ማሳያ፣ የችግር ጊዜው ማምለጫ ነው። ከዚህ ልፋት በኋላ በድህነት ላሳደጉት ምስኪን እናቱ ይደርሳል፡፡ ለራሱ ሕይወት መልካም ዓለም ያልማል፡፡
«ያሰብኩት ተሳካ – ያለምኩት…
ካሳሁንና የዓመታት ትምህርቱ በእሱ ድል አድራጊነት ተለያዩ፡፡ የልፋት ድካሙን ውጤት ከምርቃት ልብሱ፣ ከክብር መነሳንሱ ባረጋገጠ ጊዜ የሕይወቱን ግማሽ መንገድ እንደጀመረው ተረዳ፡፡ ከዚህ በኋላ ከእሱ የሚጠበቀው የእናቱን ውለታ መመለስ፣ የድካሙን ውጤት ማፈስ ነው፡፡
ከምርቃቱ ማግስት የደረሰው የሥራ ቦታ ካለበት የሚያርቅ፣ ከውድ እናቱ የሚያለያይ ሆነ፡፡ በወቅቱ የጤና ባለሙያዎችን የሚመድበው መንግስት በመሆኑ የተባለውን ከማድረግ ሌላ ምርጫ አላገኘም፡፡ በእጁ የገባው ዕጣ ‹‹ጋምቤላ›› የሚል ጥቅል አቀበለው። ስፍራው ቢርቅም፣ ‹‹ይቅርብኝ›› አላለም፡፡ ጓዙን ሸክፎ፣ እናቱን ተሰ ናብቶ ወደ ም ድብ ቦታው ተጓዘ፡፡
የጋምቤላ አየር ከመሀል አገር ለመጣ እንግዳ ይከብዳል፡፡ አካባቢውን ለመልመድ ጥቂት ቢቸግርም ካሳሁን በማማረር አልተቀበለውም፡፡ በተመደበበት ሆስፒታል የፋርማሲ ሙያውን በብቃት ተወጥቶ ሥራውን አስመሰከረ፡፡ አምስት ዓመታትን በጋምቤላ የቆየው ወጣት ውሎ አድሮ ውስጡ ለለውጥ ተነሳ፡፡ ራሱን መለወጥ ማሻሻል ፈለገ፡፡
ካሳሁን አዲስ አበባ መመለስ በፈለገ ጊዜ ዋንኛ ሀሳቡ ትምህርቱን ማሳደግ ነበር፡፡ ዕቅዱ አልተደናቀፈም፡፡ ሀሳቡ ተቀባይነት አግኝቶ ቀድሞ በተማረበት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመልሶ ገባ፡፡ በተለየ ጥናት የሚማርበት የ‹‹ፋርማኮሎጂ›› ትምህርት ከፍላጎቱ ተጣመረ፡፡ የ‹‹ቶክሲኮሎጂ›› ዘርፍም የፍላጎቱ መሪ ሆነ፡፡
«ትምህርት እንደገና »
ብርቱው ካሳሁን አሁን ከሚወዳቸው እናቱ ተጠግቷል፡፡ እሳቸው ሊያዩት በናፈቁ፣ እሱም ሊያገኛቸው በወደደ ጊዜ ይገናኛሉ፡፡ ‹‹በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ›› የሆነለት ተማሪ በደስታ ትምህርቱን ቀጠለ፡፡
አሁን ካሳሁን ካሰበው ዓላማ ተገናኝቷል። የጀመረው ትምህርት ሲጠናቀቅ ገና ብዙ ዕቅድ አለው። ለእሱና ለእናቱ የተሻለ ሕይወት የትምህርቱ ለውጥና ስኬት ያግዘዋል፡፡ እናም ሌት ተቀን ያለ እረፍት ይዋትታል፡፡ የመመረቂያ ስራውን ለማጠናቀቅ ይሮጣል፣ ይደክማል፡፡
ካሳሁን በዚህ ሩጫ መሀል ድንገት የሚሰማውን ሕመም አዳምጦታል፡፡ ይህን ስሜት ለይቶ ግን ከትምህርቱ አላስቀደመም፡፡ ቅድሚያውን ለዓላማው ሰጥቶ ቀለሙ ላይ አተኮረ፡፡ ውሎ አድሮ ሕመሙ ይብስ፣ ያስጨንቅ ያዘ፡፡
በግራ ጎኑና እጁ በኩል የሚሰማው ስቃይ ፋታ አልሰጠውም፡፡ ቀስ እያለ ከፈጣን ሩጫው አደናቀፈው። ለመመረቅ ጥቂት ጊዚያት የቀሩት ካሳሁን ከራሱ እየታገለ ጅምሩን ሊጨርስ ታተረ፡፡ አልቻለም። ሳያስበው ጎኑና እጁ ተሸማቀቀ፡፡
ካሳሁን ትምህርቱን ተወት አድርጎ ወደ ሕክምና ቀረበ። እንደታሰበው አልተሳካም። ትምህርቱን ትቶ እንደልጅነቱ ከእናቱ እጅ ወደቀ፡፡ እናት ልጃቸውን ይዘው ወደ ፀበል አመሩ፡፡ በስፍራው ቤት ተከራይተው ያለመታከት በወጉ አስታመሙት፡፡
የእናት ትከሻ …
የእናትና ልጅ እግር ካንዱ ወደ አንዱ መንከራተቱን ቀጠለ፡፡ የካሳሁን እናት ልጃቸው አልከበዳቸውም። ዕድሜና ድካም በጎዳው አካላቸው እየደገፉ፣ እየተሸከሙ ከጤናው ሊያገናኙት ሮጡ፡፡ ውስጡ በእጅጉ ተጎድቷልና እንዳሰቡት አልዳነላቸውም፡፡
ትናንት ብዙዎችን የደገፈ የካሳሁን እጅ በሕመም ታሰረ፡፡ ብዙ ዕቅድና ውጥን የሰነቀው ማንነቱ በድንገቴው ሕመም ተደናቀፈ፡፡ ካሳሁን ግራ ገባው፡፡ እንደዋዛ የጀመረው ሕመም አካሉን ገዝቶ፣ ዓይምሮውን እስረኛ ማድረጉ ያልተፈታ ዕንቆቅልሽ ሆነበት፡፡
እናት ልጃቸውን በማስታመም ብዛት ደከሙ፡፡ ሥራ ከጨረሰው ጉልበት የተረፈ ርጋፊ አቅም አልነበረም፡፡ ድካም ከዕድሜ መግፋት ተዳምሮ ለማስታመም፣ በርትቶ ለመጽናት አልበቃ አለ፡፡ እንዲያም ሆኖ ዝም አላሉም፡፡ በገፋ ዕድሜ፣ በደከመ አካላቸው ለልጃቸው ጤና አብዝተው ታገሉ።
ውሎ አድሮ የካሳሁን ጉዳይ ተስፋ አስቆረጠ፡፡ ትናንት ስለራእሱ፣ ተስፋ የጣለው ወጣት ዛሬ በህመም ተሸነፈ። በድህነት ደክመው ላስተማሩት እናቱ ውለታ ሳይመልስ እጁን ሰጠ፡፡ ሕክምናው፣ ጸበሉ፣ በታሰበው ልክ አልተሳካም። አሁንም ካሳሁን ጤና አላገኘም፡፡ እንደቀድሞው በሙሉነት አልተራመደም፡፡
መልካም ዓይኖች…
እናትና ልጅ ተመልሰው ከችግር ላይ ወደቁ። በመጦሪያ ጊዚያቸው የልጅ አስታማሚ መሆናቸው ብዙዎችን አሳዘነ፡፡ እሳቸው ግን ‹‹ለላም ቀንዷ አይከብዳት›› ሆኖ በውጣውረድ ስለ ልጃቸው ፍቅር አብዝተው ታገሉ፡፡ አቅማቸው አስኪሟጠጥ ቀን ከሌት ደከሙ፡፡ ካሳሁን የእሳቸውን ልፋት ሲያስተውል እጅግ ይሰማዋል፡፡ እናቱን መጦር፣ ማገልገል ሲገባው ሕመም ባደረሰበት ፈተና ከልብ ይተክዛል፡፡
የእናትና ልጅ ፍቅር ዛሬም አልደበዘዘም፡፡ ልጅ በምድር ላይ ያሉት ብቸኛ ሀብትና ወገን እሳቸው ብቻ መሆናቸውን ያውቃል፡፡ ካሳሁን ከእሱ በፊት በገጠር የተወለዱ ሁለት እህትና ወንድም ስለመኖራቸው ሰምቷል። በአካል አለመተዋወቅና አለመግባባታቸው ግን አገናኝቶ አላቀራረባቸውም፡፡
ከቀናት በአንዱ ካሳሁን ራሱን ‹‹የወደቁት አንሱ የነዳያንና በጎ አድራጎት ማህበር›› ውስጥ አገኘው፡፡ ወደዚህ ተቋም ያደረሱት የእሱን አሳዛኝ ታሪክና ሕይወት ውጣውድ የተረዱ ሰዎች ነበሩ፡፡ ከእነዚህ መሀል አብረውት የሰሩና የተማሩ ባልንጀሮቹ ይገኙበታል፡፡
ካሳሁን በበጎ አድራጎት ድርጅቱ ገብቶ መታገዝ ጀመረ፡፡ ልበ ቀናው ወጣት ማንነቱ አልተደበቀም፡፡ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ከእሱ የባሱትን ለማገዝ ውስጡ ይፈቅዳል፡፡ ከእናቱ የራቀ ሕይወትን ቢኖርም እሳቸውን ከድካም ማሳረፉ አስደስቶታል፡፡ እሱ እናቱን ሲጠራ ‹‹እመዬ›› ይላቸዋል፡፡ እመዬ እውነተኛውን እናትነት ያሳዩታል፡፡ ባገኙት ቁጥር ፍቅር ይመግቡታል፡፡
ዘመነ- ኮቪድ …
ካሳሁን በበጎ አድራጎቱ ማረፊያ ከገባ ጊዚያትን ቆጥሯል፡፡ እናቱ ‹‹እመዬ›› ዘወትር ዕሁድ እሱን ለማየት ከግቢው ደጃፍ ይደርሳሉ፡፡ ዕድሜያቸው ቢገፋም፣ ሕመም ቢጎዳቸውም ስለእሱ የሚሆን ጉልበት አላጡም፡፡ በመጡ ቁጥር የልጃቸውን ራስ እየዳሰሱ ያወጉታል፡፡ እሳቸው ለእሱ የዓይን ርሀቡ ናቸው፡፡ ተስፋውን አሻግሮ ያይባቸዋል፡፡ የመኖር ትርጉሙን ይፈታባቸዋል፡፡
ይህ አይነቱ የእናትና ልጅ ፍቅር ውሎ አድሮ ጋሬጣ አላጣውም፡፡ በዘመኑ በተነሳው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት እመዬን ጨምሮ በርካቶች ወደ ግቢው እንዳይገቡ ተከለከሉ፡፡ ይህ በአዋጅ የተደነገገ ውሳኔ ለሁለቱ ነፍሶች ጭንቀትን አቀበለ፡፡ እናት ከግቢው ውጭ ሆነው በናፍቆት ዋተቱ፡፡ ልጅ በአጥር ተከቦ የእናቱን ዓይን ሊያይ አንጋጠጠ፡፡
ይህ ክፉ አጋጣሚ ናፍቆታቸውን አብሶ ለመለያየት ሰበብ ሆነ፡፡ እንዲህ መሆኑ አገር ቤት የሚኖሩትን የእመዬን ልጆች ትኩረት ሳበ፡፡ እናት በዚህ ዕድሜያቸው ለብቻቸው መኖራቸው ተገቢ አልሆነም፡፡ ልጆቹ እናታቸውን እነሱ ዘንድ ለመውሰድ አልዘገዩም፡፡ አጋጣሚው ካሳሁን ከእናቱ እንዲለያይ ምክንያት ሆነ፡፡ ከዚህ በኋላ ‹‹ልጄ›› ሲል የሚጠይቀው፣ እንዴት ነህ ብሎ የሚያየው ሰው የለም፡፡
አሁን ካሳሁን ደጅ ቆመው ‹‹አስገቡኝ›› እያሉ ስለሚማጸኑት እናቱ አያስብም፡፡ ከዚህ በኋላ የዓይን ርሀብ የለውም፡፡ በምድር ያሉት አንዲት እናቱ፣ ውዱና ወዳጁ ከዓይኖቹ ርቀዋል፡፡ ይህ እውነት ዓይምሮን ይይዛል፣ ውስጥን ይረብሻል፡፡ ካሳሁን ግን እናቱን በሀሳብ ሸኝቶ ራሱን አሳምኖ አጽናና፡፡
በስልክ አነጋግሪኝ..
እናትና ልጅ ከተለያዩ በኋላ ግንኙነቱ በስልክ ብቻ ሆነ፡፡ እናት በናፈቁ ጊዜ ከጎናቸው ያሉ ልጆች ድምጹን ያሰሟቸዋል። ናፋቂዋ እናት የልጃቸውን ቃል ሲያደምጡ ፈጣሪን ያመሰግናሉ፡፡ እሱም ሲያገኛቸው ደስ ይለዋል። ጥቂት ቆይቶ ግን የቀጭኑ ሽቦ አንደበት ተቋረጠ፡፡ እናት የልጃቸውን ድምጽ በሰሙ ቁጥር ትካዜ ማብዛታቸው ግንኙነቱን ገደበ፡፡ የእናትና ልጅ ፍቅር በትዝታ ታጅቦ ዓመታትን አሳለፈ፡፡
የኮቪዱ ወጀብ አልፎ ሌላ ቀን በነጋ ጊዜ የካሳሁን እናት ወደነበሩበት አልተመለሱም፡፡ እርጅናው ከጤና እጦት ተዳምሮ ካሉበት ሊቀሩ ግድ ሆነ፡፡ ካሳሁን ስልክ ደውሎ በጠየቀ ጊዜ ስለእሳቸው ደህንነት ይነገረዋል። ሄዶ አለማየቱ፣ አግኝቶ አለማዋየቱ ቢያሳዝነውም በመኖራቸው ብቻ ይጽናናል፡፡
የማለዳው እንግዶች…
ካሳሁን ባረፈበት የወደቁትን አንሱ የበጎ አድራጎት ተቋም የራሱ አልጋ አለው፡፡ ስፍራው ደህንነቱ የተጠበቀና ንጽህናው ያማረ ነው፡፡ በዙሪያው እሱን መሰል ጊዜና ቀን የጣላቸው ወገኖች ዓመታትን አብረውት ዘልቀዋል፡፡ ሁሉም በተለያየ ሕመምና ችግር ውስጥ ናቸው፡፡
አንድ ማለዳ ከዕንቅልፉ ሲነቃ የሰዎች አትኩሮት ሳበው።ጥቂት ሰዎች ወደ እሱ እየቀረቡ ነበር፡፡ የእነሱ መምጣት አዲስ ባይሆንም ሁኔታቸው አስደንግጦታል። የማለዳው እንግዶች መልካም ነገር አልያዙም፡፡ ዝግ ባለ አንደበታቸው የእናቱን ማረፍ አረዱት፡፡ የእናት ሞት ውስጥን የሚሰነጥቅ፣ ማንነትን የሚያርድ ስብራት፡፡ ቀን የሚያጨልም፣ ብርሀን የሚነጥቅ ሀያል ስሜት፡፡
ካሳሁን በችግር በድህነት ያሳደጉትን፣ በስቃይ እንክርት ያስተማሩትን የውድ እናቱን ሞት ተረዳ፡፡ በሕመሙ ጊዜ ብቸኛ ትከሻው፣ በችግሩ ሰዓት አንድዬ መከታ የሆኑት ‹‹ዕመዬ›› ከእንግዲህ የሉም፡፡ አሁን ‹‹አለኝ›› ብሎ የሚጠራው ‹‹የት ነህ ?›› ብሎ የሚፈልገው የለም፡፡ ለራሱ እውነታውን አሳምኖ ሀቁን ተቀበለ፡፡ እርሙን አወጣ፡፡
ካሳሁንን ሳገኘው የእናቱን ሞት ከሰማ ከቀናት በኋላ ነበር፡፡ በርትቷል፡፡ ራሱን አጽናንቶ ጠንክሯል፡፡ ጉብዝናውን አደነቅሁለት፡፡ በፊቱ ያስተዋልኩት ቀናነት ማንነቱን አይደብቅም፡፡ ውስጤ የተሻለ ነገን እያሳየ በብርታት እንደሚያሻግረው ሹክ አለኝ፡፡
ካሳሁን ‹‹እግዜአብሔር ሁሌም ትከክል ነው›› የሚል አቋም አለው፡፡ ይህ እውነት መሽቶ በነጋ ቁጥር ከአዲስ የብርታት ቀን ጋር ያገናኘዋል፡፡ እንደዋዛ የጀመረው ሕመም ዛሬም ግማሽ አካሉን ይዞ እንዳሻው ላይሆን ገድቦታል። እስካሁን በሕክምናው የሞከረው ሂደት ባይሳካም እሱ ግን ተስፋ አይቆርጥም፡፡
ዘወትር ከሚዲያው ሳይርቅ የዓለምን ውሎ አዳር ይከታተላል፡፡ በቻለው አቅም ሌሎችን ለማገዝ የፈጠነ ነው። ትናንት ስለነበረበት ዓለም እያሰበ አይጨነቅም። የባልንጀሮቹ ዕድገት፣ የእኩዮቹ መለወጥ አሳስቦት አያውቅም፡፡ ሁሌም የበታቾቹን እያየ ፈጣሪውን ያመሰግናል፡፡ የእሱ ዓለም አሁን ያለበት ቦታና ከጎኑ ያሉት ሰዎች ናቸው፡፡
ከአምስት ዓመታት በላይ ለቆየበት ‹‹የወደቁትን አንሱ›› የበጎ አድራጎት ድርጅት የተለየ ክብርና ምስጋና አለው። እሱ ነገ የተሻለ እንደሚሆን ያምናል፡፡ ትናንት ብዙሀንን ያገለግል የነበረ ባለሙያ እጁ ዛሬ ቢሰበሰብም ስለነገው ተስፋ አይቆርጥም፡፡
ይህ ሰው ሁሌም ስለሀገር ፍቅርና ሰላም ዕንቅልፍ የለውም። ወደ ፈጣሪው አጥብቆ ይጸልያል፡፡ እሱ ባለው አቅም የደከሙትን ለማገዝ ሁሌም በቂ መሆኑን ያውቃል። ኑሮን ተቀብሎ፣ ሕይወትን እንዲህ እየኖረ ነው፡፡ ትሁቱ፣ ልበ ቀናው ካሳሁን ቤዛ፡፡
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ህዳር 15/2016