ሕዳር 12 ታሪካዊ ቀን ነው፡፡ በዚህ ቀን ብዙ ኢትዮጵያውያን በፋሺስት ጣልያን መስዋዕትነት የከፈሉበት ቀን ነው፡፡ ከዚያ ባሻገር ግን ቀኑ በመላው ኢትዮጵያ ጽዳት የሚካሄድበት እለት ነው፡፡ በብዙ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከየቤቱ ቆሻሻ እየወጣ ይቃጠላል፡፡ አሁን እየደበዘዘ መጣ እንጂ በተለይ አዲስ አበባ በጭስ ተሸፍና ንጋት ላይ እስከተወሰነ ሰዓት ድረስ ሰው ከሰውም አይተያይም ነበር፡፡ ይህ ልምድ ታሪካዊም መንፈሳዊም ዳራ አለው፡፡
በታሪካዊ ጎኑ ሲታይ የሕዳር በሽታ ከሚባለው ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ፈረንጆቹ ‹‹ስፓኒሽ ፍሉ›› ይሉታል፡፡ ይህም በፈረንጆቹ 1911 የተከሰተ ወረርሽኝ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ከተከሰቱት ወረርሽኞች ሁሉ አስከፊውና ከሃምሳ ሚሊዮኖች በላይ ሰዎችን የጨረሰ ሲሆን እኛም ሀገር ገብቶ ቀላል የማይባል ሕዝብ ፈጅተል፡፡ የታሪክ ምሁሩ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ሰሞኑን በሸገር ሬድዮ ከጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ ጋር ባደረጉት ሰፊ ቃለምልልስ በሽታው በሕዳር ወር በመከሰቱ የሕዳር በሽታ ከመባሉ ባለፈ የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መንገድ ስራ በጀመረበት ወቅት በሽታው በመነሳቱ ምክንያት ባቡሩ ያመጣው በሽታ ነው በማለት “የባቡር በሽታ” ይባል እንደነበር ይናገራሉ።
በወረርሽኙ ምክንያት በአዲስ አበባ ብቻ በሕዳር ወር 1911 ዓ.ም ከ6 ሺ ሰው በላይ መግደሉን ተከትሎ መንግስት በጀርመን ሀኪሞች ምክር ‘የበሽታው መንስዔ ቆሻሻ እንደሆነ በመታመኑ’ ሕዝቡ ቆሻሻን ከቤቱ አውጥቶ እንዲያቃጥል፣ አካባቢውን እንዲያፀዳና በተጨማሪ በሽታው በአየር ይተላለፋል ተብሎ ስለታመነ ‘አየሩን በማጠን’ በሽታውም በወቅቱ ስለጠፋ ከጊዜ በኋላም ‘አየሩ ስለታጠነ ነው በሽታው የጠፋው::’ ተብሎ በየዓመቱ ቆሻሻን ማቃጠል ልማድ ሆኖ እስካሁንም ቆይቷል፡፡
ዘንድሮም እንደወትሮው ባይሆንም ሰው ማለዳ ተነስቶ ቆሻሻ ሲያቃጥል አስተውለናል፡፡ መቼም በየሰፈሩ ሕዳር ሲታጠን ከየቤቱ ሊቃጠል የሚወጣው የቆሻሻ አይነት በጣም አስቂኝ ነው። ከዛፍ ርጋፊ አንስቶ ጭራሽ እሳት ውስጥ ሊገባ የማይችል ነገር ሁሉ ከያለበት ይወጣል። አንዳንዱማ የሚያቃጥለውን ነገር ብዛት እና የሚፈጥረውን የጭስ መጠን ሲታይ ጭራሽ ቆሻሻን አቃጥላለሁ በሚል ሰበብ የኦዞን መሸንቆርን ለማስከተል ታጥቆ የተነሳ ነው የሚመስለው። እንደውም አንዳንዱ በአካባቢ በቅርቡ እየታየ ላለው ሙቀት ምክንያቱ ‹‹አምና ሕዳር ሲታጠን ያቃጠልነው ቆሻሻ ጭስ ኦዞንን በመቅደዱ ነው›› እያለ ይሳለቃል፡፡
የሆነ ሆኖ ቆሻሻን የማስወገድ ስራው በአግባቡ እየተካሄደ ባለበት ወቅት አንድ ጎረቤታችን ያለቀ ነው ያሉት የሽቶ ጠርሙስ እሳቱ ውስጥ ጨምረው የሽቶ እቃው በመፈንዳቱ ቀላል የማይባል ትርምስ ተፈጥሮ ነበር፡፡ እውነቱን ለመናገር አውጥቶ ማቃጠል ቢቻል ማቃጠል መጥፎና የደከመ አስተሳሰብን ነበር፡፡
እኛ ቤት ብዙ የሚቃጠል ነገር ባለመኖሩ እናቴ ለቃጠሎ ያወጣችው ጥርሱ ያለቀውን መጥረጊያ ነበር፡፡ እሱንም ቢሆን እየከፋት ነበር ያቃጠለችው፡፡ ሌላ መጥረጊያ እንደሚገዛላት አሳምነናት እና ይሄኛው ዘመኑ እንዳለፈበት ብዙ ሰብከናት ነው እሺ ያለችው፡፡ እንደ እናቴ እምነት ከቤት ውስጥ ቆሻሻ ተብሎ ሊቃጠል የሚገባው ምንም አይነት እቃ የለንም፡፡ እንኳን እሳት ውስጥ ሊገባ ከእጃችን እንኳ ሲወድቅ የምትናደደው ንዴት በዚህ ዘመን አንድ ሰው ፕሮማክስ ስልኩ ሲጠፋበት ከሚናደደው ንዴት ያልተናነሰ ነው፡፡
በእናቴና በጊቢያችን ውስጥ ባለ ማንኛውም እቃ መሀከል ያለ ግንኙነት ጥብቅ ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ በቀላሉ መልቀቅ አትፈልግም፡፡ መጥረጊያው ራሱ ወደ እሳት ሲገባ እንዲሁ በከንቱ አልነበረም፡፡ አብረውት የተቃጠሉ የግቢውን ሌሎች ቆሻሾችን ጠርጎ ሲጨርስ ምን ያህል ጥሩ መጥረጊያ እንደነበር እና ሲገዛ ዋጋው ምን ያህል እንደነበር እንዲሁም ሲያጸዳ ምን ያህል ጥሩ እንደሆነ አጭር የስንብት ንግግር አድርጋ ነው ወደ እሳቱ እንዲሰናበት የተደረገው፡፡
የእኛ ሰፈር የቆሻሻ ማቃጠል ስርዓት አስቂኝ ክፍል አለው፡፡ ሁሉም ሰው ቆሻሻውን ሊያቃጥል በጠዋት ተነስቶ ሲጠራርግ እስከ ዛሬ ያልተነኩ ቆሻሻዎችን ሁሉ መዝዞ ያወጣል፡፡ ይህን ያህል እምቅ ቆሻሻ በሰፈራችን እንዳለ የምናውቀው ራሱ የዚያን ቀን ነው፡፡ ከዚያ ይህ ቆሻሻ ሰብሰብ ይልና ለቃጠሎ ሲዘጋጅ እድሉ ከሚያልፍ ተብሎ ሌሎች እስካሁን ቆሻሻ ናቸው ተብለው በይፋ ስያሜ ያልተሰጣቸው እንደ የእኛ ቤት መጥረጊያ ያሉትም ይጨመራሉ፡፡ ቆሻሻው ይከመራል፡፡ በሽታውን ሁሉ ውሰድልን፤ ጤና ስጠን፤ ሀገራችንን ሰላም አድርግልን ተብሎ ይለኮሳል፡፡ ከዚያ ቆሻሻው ተቃጥሎ እስከሚያልቅ ጊዜ ስለሚፈጅ ሁሉም ወደየጉዳዩ ይሄዳል፡፡ ከዚያ ያለ የተቃጠለ ቆሻሻ አመድ እዚያው ንፋስ ሲያበነው እና እግረኛ ሲያምሰው ውሎ ሌላ አዲስ ቆሻሻ ሆኖ ይከሰታል፡፡
ስናጠቃልለው ሕዳር ሲታጠን ጥሩ ባሕል ነው፡፡ ቆሻሻን ማስወገድ አስፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን ቆሻሻ ሲወገድ ሂደት አለው፡፡ የመጀመሪያው ሂደት ቆሻሻ የሆነውን እና ያልሆነውን መለየት ነው፡፡ ብዙዎቻችን የያዝነውን ቆሻሻ፤ ቆሻሻ መሆኑን እንኳ አንረዳውም፡፡ ቆሻሻ ባይሆን እንኳ አንደማያስፈልገን እና ቦታ እየያዘብን እንደሆነ አናምንም፡፡ አብሮን ብዙ ስለኖረ ከማይጠቅመን ነገር ጋር ፍቅር ይዞናል፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ ቆሻሻ እና አላስፈላጊ የሆነውን ነገር መለየት ያስፈልገናል። ከዚያም የትኛው ቆሻሻ እንዴት ይወገዳል የሚለውን መገንዘብ አለብን። አንዳንድ ቆሻሾች ይቃጠላሉ፡፡ ሌሎች በሌላ መንገድ ይወገዳሉ።
ሁሉንም ላቃጥል ማለት ሌላ ችግር ይወልዳል፡፡ አንዳንድ ቆሻሾች የሚቃጠሉ ቢሆን እንኳ የሚቃጠሉት ራቅ ባለ ቦታ እንጂ ግቢ ውስጥ አይደለም፡፡ በሕይወታችንም ውስጥ ሁሉን ችግር በአንድ መንገድ ለመፍታት መሞከር ነው ችግር ውስጥ የሚከተንና ችግራችንን እንዴት እንደምናስወግድ መለየት አለብን፡፡
በመጨረሻም አይጠቅመንም ያልነውን ነገር ስናስወግድ በቅጡ እንዳይመለስ አድርገን ነው መሆን ያለበት፡፡ አልያም በእጃችን ያወጣነውን ቆሻሻ በእግራችን ይዘነው እንመለሳለን፡፡ በሕይወታችንም ላይ በተመሳሳይ የምንነካካቸው ነገር ግን በቅጡ የማናስወግዳቸው ችግሮቻችን ለጊዜው ከፊታችን ዘወር ቢሉም ኋላ ላይ ግን ዞረው ወደ ሕይወታችን መመለሳቸው አይቀርምና ስናስወግድ በአግባቡ መሆን አለበት፡፡
ቸር እንሰንብት !
ሚዛን
አዲስ ዘመን ህዳር 15/2016