
የዋጋ ንረትንና የምርት አቅርቦት እጥረትን ለመቅረፍ የገበያ ማዕከላትን የማስፋፋት ሥራ ልዩ ትኩረት የሚሻው ጉዳይ መሆኑን በርካቶች ይስማሙበታል። የገበያ ማዕከላትን ማስፋፋቱ በተለይም አምራቹን ከሸማቹ ማህበረሰብ በቀጥታ በማገናኘት ጥራት ያለው ምርት ከማቅረብ ባሻገር የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት እንደሚያስችል በዘርፉ የተሰማሩ ምሁራን ይናገራሉ።
በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህሩ ፍሬዘር ጥላሁን ፤ በመዲናዋ የተገነቡትና በመገንባት ላይ የሚገኙት የግብርና ምርት መሸጫ ማዕከላት ለገበሬውና ለተጠቃሚው ማህበረሰብ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ የማዕከላቱ መገንባት ሻጭ ገበሬውንና ገዢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ይገልጻሉ።
ማዕከሉ ገዥና ሻጭን የሚያገናኝ፣ በወቅቱ ዋጋ ላይ በተመሠረተ ሁኔታ ምርት በማቅረብ የንግድ ውድድርን ጤናማ የሚያደርግና የምርት ጥራትን ለማሳደግ የሚረዳ መሆኑን ይናገራሉ።
በግብይት ሂደት ውስጥ የሚኖረውን የደላሎችን እንቅስቃሴ የሚያስቀር ነው። በመሆኑም የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር የሚያስችል መንገዶችን እንደሚፈጥር ያስረዳሉ።
ሻጭ ከገዢ ጋር በሚገናኝባቸው ሂደቶች ውስጥ ብዙ ውጣ ውረዶች ሲኖሩት የዋጋ መናርን እንደሚያስከትል የሚገልጹት መምህሩ የገበያ ማዕከላቱ መገንባት ጤናማ የገበያ ሁኔታዎችን በመፍጠር የሚኖረውን አላግባብ ተሳትፎና ወጪዎችን በመቀነስ የዋጋ ውድነትን ለመቆጣጠር ይረዳል ሲሉ ይናገራሉ።
የመሸጫ ማዕከላትን መገንባት ገበሬው ማግኘት የሚገባውን ትርፍ እንዲያገኝ ይረጋዋል። በሌላ በኩል በአነስተኛ ዋጋ ለሸማች ማድረስ የሚቻልበትን ሁኔታ መፍጠር እንደሚያስችል አብራርተዋል።
የገበያ ማዕከላቱ መገንባትና ወደ ሥራ መግባት ለአምራች ገበሬው የገበያ ትስስርን በመፍጠር ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖራቸው የተናገሩት የምጣኔ ሀብት መምህሩ የገበያ ትስስሩ ጥቅማቸውን የሚያስቀርባቸውን ደላሎች ሥርዓቱን ለማደናቀፍ የሚያደርጉትን ጥረት በሕግ አግባብ መቆጣጠር እንደሚያስፈልግ ነው ያመላከቱት።
በአንድ አካባቢ ተመሳሳይ ምርቶችን የሚያመርቱ ገበሬዎች በጋራ ወደ ምርት ገበያው የሚያመጡበት ሁኔታን መፍጠር ተገቢ መሆኑን አስረድተው፤ ገበሬዎች በህብረት ሥራ ማህበራት ተደራጅተው ምርቶቻቸውን ወደ ማዕከላቱ ማቅረብ የሚችሉበት መንገድ ማመቻቸት እንደሚያስፈል ይገልጻሉ።
በግብይ ሂደት ውስጥ የደላላውን እንቅስቃሴ መቀነስ፣ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነቱን ለማርገብ የገበያ ማዕከላቱ ሚና የጎላ ነው። በገበያው የዋጋ መጠንን ለመወሰን በሚደረገው ድርድር ላይ የገዢ የበላይነት እንዳይኖር ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ብለዋል።
ለገበሬውና ለማህበረሰቡ ማዕከላቱን ከማመቻቸት ባሻገር ሥርዓቱ የሚሄድበትን ሕግና ሥርዓትን መዘርጋት ተገቢ ነው። የግብይት ሥርዓቱ የሚመራበት ሕግ፣ ክትትል በማድረግ ማስፈጸም ያስፈልገዋል ሲሉ ነው የተናገሩት።
በተጨማሪም ገበሬው የምርት ውጤቱን የሚያቀርብባቸው የሰንበት ገበያዎች፣ ባዛርና መሰል የገበያ ማዕከላት ግንባታ ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል። በተለይም ገበሬው ወደ ምርት ገበያው ሲመጣ የመደራደር አቅም እንዲኖረው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ሊሰሩ ይገባል ይላሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህሩ አጥላው አለሙ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ የግብርና ምርቶች ተመርተው ወደ ገበያ ማዕከላቱ ለማስገባት፣ ገበሬው እንደልቡ እንዲሠራ፣ ኢንዱስትሪዎች ጥሬ እቃ አግኝተው አምርተው የውጭ ምንዛሬ እንዲያመጡ የሀገሪቱ የሰላም ሁኔታ ሊረጋገጥ ይገባል።
በገበያው ሂደት ላይ የሕገወጥ ደላሎችን እንቅስቃሴ ለመግታት ለአርሶአደሩ በቂ መረጃን መስጠት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ አምራቹ ተንቀሳቅሶ የሚሸጥበትን ሁኔታ መፍጠር ሲቻል የደላላውን እንቅስቃሴ መቆጣጠር ይቻላል ሲሉ ተናግረዋል።
አምራቹ የዋጋ ተመን፣ የመሸጫ ቦታና ሸማች የት እንደሚያገኝ በቀላሉ የሚያውቅበት ሁኔታ አለመኖርና የትራንስፖርት ችግሮች አስቻጋሪ ሁኔታዎችን መፍጠራቸውን ነው የገለጹት።
ለገበሬው የገበያ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችል የገበያ መረጃ መስጠትና ተገቢ መሆኑን የገለጹት ዶክተር አጥላው በተለይም መሸጫ ቦታ ማመቻቸት፣ የዋጋ መረጃ መስጠትን ጨምሮ ሰላምን ማስፈንና በቂ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚያስፈልጉ አመላክተዋል።
የኑሮ ውድነቱን ለማርገብ በመንግሥት በኩል የገንዘብ ፖሊሲን ማርገብ፣ ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ መሥራትና ሰላምን በማስፈን ውጥረቶችን ማቃለል እንደሚገባ ነው ያስረዱት።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አምራቹን ከሸማቹ ጋር በቀጥታ ለማገናኘት በኮልፌ፣ በአያትና ሰሚት በሚገኙ የመግቢያ በሮች የግብርና ምርት ማከማቻና መሸጫ ተገንብተው ወደ አገልግሎት በመግባት ላይ መሆናቸው ይታወሳል።
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ኅዳር 15 ቀን 2016 ዓ.ም