19ኛው የኢትዮጵያ ማራቶን ሪሌ ውድድር ነገ በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ይካሄዳል፡፡ ከዓመታት በኋላ በክልሉ በሚካሄደው በዚህ ትልቅ ሀገር አቀፍ ውድድር ላይ አምስት ክልሎችና ዘጠኝ ክለቦች አትሌቶቻቸውን እንደሚያሳትፉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከሚያካሂዳቸው ዓመታዊ ውድድሮች መካከል አንዱ የማራቶን ሪሌ ውድድር ነው፡፡ ውድድሩ በሁለት መንገድ የሚካሄድ ሲሆን አንዱ 42 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን ርቀት በተመሳሳይ ፆታ አትሌቶች በተለያዩ ርቀቶች ተከፋፍለው ዱላ እየተቀባበሉ የሚያደርጉት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ወንድና ሴት አትሌቶች በተለያዩ ኪሎ ሜትሮች ዱላ እየተቀባበሉ የሚሮጡት የድብልቅ ሪሌ ውድድር ነው፡፡ ውድድሩ ዘንድሮ ለ19ኛ ጊዜ ሲካሄድ መነሻ እና መድረሻውን በመቀሌ ከተማ የሰማዕታት ሃውልት ያደርጋል፡፡ ውድድሩ ማለዳ 1ሰዓት ላይ የሚጀምር መሆኑንም ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡
በጥንካሬያቸው ልቀው በዓለም አቀፍ ውድድሮች ሀገራቸውን ማስጠራት የቻሉ በርካታ አትሌቶችን በማፍራት የሚታወቀው የትግራይ ክልል ባለፉት ዓመታት በነበሩ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት ከውድድሮች ርቆ ቆይቷል፡፡ አሁን ግን በክልሉ በተፈጠረው የሰላም ሁኔታ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የማራቶን ሪሌ ውድድሩን እንዲሁም 27ኛውን የፌዴሬሽኑ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤው በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ነገ እና ከነገ በስቲያ ያደረጋል፡፡ በዚህ ውድድር ላይም የትግራይ ክልልን ጨምሮ አምስት ክልሎች እና ዘጠኝ ክለቦች በጥቅሉ አስራ አራት የአትሌቲክስ ተቋማት በአትሌቶቻቸው የሚወከሉ ይሆናል፡፡በሁለቱ ጾታዎችም ሰማንያ አራት አትሌቶች በሩጫው ላይ ተካፋይ እንደሚሆኑ ተረጋግጧል፡፡
እንደ መደበኛው የማራቶን ውድድር 42 ነጥብ 195 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የማራቶን ሪሌ ሩጫው ሁለቱም ጾታዎች በተለያየ ኪሎ ሜትር ስድስት አትሌቶች እየተቀባበሉ የሚሸፍኑት ይሆናል፡፡ በዚህም መሰረት የውድድሩን የመጀመሪያ 5 ኪሎ ሜትር ወንድ አትሌቶች የሚሮጡት ሲሆን፣ ቀጣዩን 5ኪሎ ሜትር ሴት፣ ቀጥሎ የሚኖረውን 10 ኪሎ ሜትር ወንድ፣ 5ቱን ኪሎ ሜትር ሴት፣ 10 ኪሎ ሜትር ወንድ የመጨረሻውን 7ነጥብ195 ኪሎ ሜትር ደግሞ ሴት አትሌቶች በመሮጥ ለሜዳሊያ የሚፎካከሩበትም ይሆናል፡፡ በዚህ ውድድር አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶችም እንደየደረጃቸው ከሚበረከትላቸው ሜዳሊያ ባለፈ አንደኛ የሚሆነው የ40ሺ ብር፣ ሁለተኛ የሚሆነው የ20ሺ ብር እንዲሁም ሶስተኛው የ15ሺ ብር ሽልማት የሚያገኙም ይሆናል፡፡
የዚህ ውድድር ዓላማ በዋናነት ተተኪ አትሌቶችን ማፍራት ሲሆን፤ ክልሎችና ክለቦች የሚያሰለጥኗቸውን ወጣትና ታዳጊ አትሌቶች ይህንን በመሰሉ የሀገር ውስጥ ውድድሮች በማሳለፍ ለዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚበቁበት ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በውጤታማነት የምትታወቅባቸው በ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ርቀቶች ዓለም አቀፍ የመም ውድድሮች እየጠፉ ይገኛሉ፡፡
በቅርቡ ለመጀመሪያ ጊዜ ሪጋ ላይ የተደረገው የዓለም የጎዳና ላይ ቻምፒዮናን ጨምሮ ሌሎች ውድድሮች እነዚህ ርቀቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደ ጎዳና እየወጡ ስለመሆናቸው አመላካች ናቸው፡፡ በመሆኑም የማራቶን ሪሌ ውድድሩ አትሌቶችን በመሰል ውድድሮች ማሳተፍና ማበረታታትን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ካላት የአትሌቶች ከፍተኛ ቁጥር የተነሳ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ መሳተፍ ላልቻሉ አትሌቶች የውድድር እድል በሀገር ውስጥ ለማመቻቸት እንዲሁም በሽልማት ማበረታታትም ሌላኛው አላማው ነው፡፡ በተጨማሪም በትግራይ ያለውን የአትሌቲክስ ስፖርትና አትሌቶች ማነቃቃትም ሌላኛው የውድድሩ ዓላማ መሆኑ ተጠቁማል፡፡
18ኛው የኢትዮጵያ ማራቶን ሪሌ ውድድር ባለፈው ዓመት በሰመራ ሲካሄድ የኦሮሚያ ፖሊስ አትሌቲክስ ክለብ የወርቅ ሜዳሊያና የገንዘብ ተሸላሚ ሲሆን፣ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አትሌቲክስ ክለብ የብርና የሜዳሊያ ተሸላሚ እንዲሁም የኢትዮጽያ ንግድ ባንክ አትሌቲክስ ክለብ የነሀስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ነበሩ፡፡
በዚያ ውድድር ሦስቱ ትዕግስቶች መጨረሻ ላይ ያሳዩት አስደናቂ ፉክክር የሚታወስ ሲሆን የበርሊን ማራቶን የሁለት ጊዜ አሸናፊዋና ዘንድሮ የማራቶን የዓለም ክብረወሰን የጨበጠችው ትዕግስት አሰፋ በአስደናቂ አጨራረስ አሸንፋ ኦሮሚያ ፖሊስ ቀዳሚ ሆኖ እንዲያጠናቅቅ አድርጋለች፡፡ ትዕግስት ግርማ ከፌዴራል ማረሚያ እንዲሁም ትዕግስት አንባይቸው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለተኛና ሦስተኛ ሆነው ያጠናቀቁ አትሌቶች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ህዳር 14/2016