ኩባንያዎችን መሳቢያው ቴክኖሎጂና እውቀት ማሸጋገሪያው – የማዕድን ኤክስፖ

ኢትዮጵያ በሀገር በቀል ኢኮኖሚው ማሻሻያው የምጣኔ ሀብቱ ምሰሶ አድርጋ ከያዘቻቸው አምስት ዘርፎች መካከል የማእድን ዘርፍ አንዱ ነው። ይህን ታሳቢ በማድረግ በዘርፉ እንደ ሀገርም በክልሎችም በስፋት እየተሰራ ይገኛል። ዘርፉን ለማልማት ማእድናት በጥናት የመለየት ስራዎች፣ ልማቱ ከባህላዊው መንገድ በዘመናዊ መንገድ እንዲካሄድ ለማድረግና ሀገሪቱ ከዘርፉ የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ የሚያስችሉ ጥረቶች እየተደረጉ ናቸው።

ማእድን ሚኒስቴር ልማቱ እንዲዘምን፣ ከልማቱ የሚገኘው ገቢም እያደገ እንዲመጣ ከሚያከናውናቸው ተግባሮች አንዱ ኢግዚቢሽኖችን ማካሄድ ይገኝበታል። ባለፈው አመት በርካታ የዘርፉ ተዋንያን የተሳተፉበት ኤክስፖ ማዘጋጀቱ ይታወሳል፤ ዘንድሮም በአይነቱ ከአለፈው አመት የተለየ ዓለማቀፍ የማዕድን ኤክስፖ አዘጋጅቷል። ኤክስፖው ነገ በሚሌኒየም አዳራሽ በይፋ የሚከፈት ሲሆን፣ ለአምስት ቀናት የሚካሄድም ይሆናል። ሶስት ሲምፖዚየሞች ይካሄዱበታል።

ባለፈው አመት ከተካሄደው ኤክስፖ ለማእድን ልማቱ የሚውሉ ብዙ ግብአቶች የተገኙበት ነበር። ከዘንድሮው ኤክስፖም ብዙ ይጠበቃል። ኢትዮጵያን ከማእድን ዘርፉ በርካታ ኩባንያዎች ጋር ያስተዋውቃታል፤ ለዜጎች የሥራ እድልና የገበያ ትስስር የሚፈጠርበትን ሁኔታ እንደሚያመቻችም ታምኖበታል።

አሰራሮችን ለማሻሻልና ቴክኖሎጂን ለማላመድም ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑ እየተገለጸ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ በመድረኩ የሚገኙ የዘርፉ ዓለም ተቋማት ተሞክሯቸውን ሊያጋሩ፣ ፋይናንሳቸውን ሥራ ላይ ለመዋል ስምምነት ሊፈጽሙ ይችላሉና የዘርፉ ከፍተኛ ፈተና እየሆነ ለሚገኘው የፋይናንስ እጥረት መፍትሄ ያመላክታል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል።

ኤክስፖውን አስመልክተን ከማዕድን ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሚሊዮን ማቲዮስ ጋር ቃለ ምልልስ ባደረግንበት ወቅት እንዳሉት፤ በሀገሪቱ የማዕድን ልማት በርካታ አመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም፣ አመራረቱ አሁንም ድረስ ከባህላዊው መንገድ አልወጣም። ስለ ማዕድን ልማት ስናስብ ስለ ሀገር ኢንዱስትራላይዜሽን እናስባለን፤ ኢንዱስትሪያላይዜሽን ደግሞ ለእኛ አዲስ ነገር ነው የሚሉት አቶ ሚሊዮን፤ ይሁንና ከወርቅ፣ ከሲሚንቶና ተያያዥ ኢንዱስትሪዎች ጋር በተያያዘ በማዕድኑ ዘርፍ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት በተወሰነና በመለስተኛ ደረጃ ሰርተናል ሲሉም ይጠቅሳሉ።

ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ስኩዬር ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት አላት፤ በዚህ መሬት ላይም በርካታ ማዕድናት የሚገኙባት ሀገር እንደመሆኗ መጠን ምንም አልሰራንም ተብሎ ይወሰዳል። ምክንያቱም በአንድ አለት አይነት ሳይሆን ሦስቱንም የአለት አይነቶች አቅፋ የያዘች በመሆኗ ሀብቶቿ ተዝቀው፤ የሚያልቁ አይደሉም። በመቶ ዓመታት ቆይታ ብቻ የሚፈጠሩ በርካታ የከበሩ ማዕድናት መገኛ ነች። እናም ሀገሪቱ እነርሱን ብቻ በኢንዱስትሪው ብታለማ ማንም የማይደርስባት ትሆናለች።

የማእድን ዘርፉን የበለጠ ለማልማት እየገባን ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በዚህም በተሰሩት ሥራዎች ለውጦች እየተመዘገቡ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ። ከለውጦቹም አንዱ በመለስተኛ ደረጃም ቢሆን ኢንዱስትሪያላይዜሽን ላይ መገባቱ እንደሆነ ይጠቁማሉ። የማዕድን ዘርፉን በኢንዱስትሪ እናልማ ሲባል እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በርካታ የማዕድን ሀብት ባለቤቶች በቀላሉ ሊፈጸም የሚችል እንዳልሆነም ጠቅሰው፣ በቅድሚያ የማእድን ሀብቶቹ ተለይተው መታወቅ እንዳለባቸው ይናገራሉ። ከዚያም ቅድሚያ የሚሰጣቸውም እንዲሁ መለየት እንደሚኖርባቸው ያመለክታሉ።

እሳቸው እንዳሉት፤ ይህን ለማድረግ ደግሞ ከፍተኛ ፋይናንስና እውቀት ያስፈልጋል። እኛ ካለንበት የእድገት ደረጃ አኳያ ደግሞ ይህ ጉዳይ በቀላሉ የሚሞከር አይደለም። ስለሆነም አጋር አካላትን መፈለግ የግድ ይለናል። ለሀገር ውስጥም ለውጪውም አቅም ላለው ባለሀብት ወይም ኩባንያ እድሉን መስጠትም ይገባል። የኤክስፖው ዋና አላማም ይህ ነው።

እሳቸው እንዳሉት፤ ኤክስፖው በመንግሥት የፖሊሲ መሪነት እየተካሄደ እነዚህ ነገሮች እንዲገኙ ለማድረግ ያስችላል። አለማቀፍ ኢንቨስተሮችን በመሳብም በኩል የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ኢትዮጵያ ያላትን ሀብት በውል አስገንዝቦ ፋይናንስ ፈሰስ እንዲደረግ ከማስቻል አኳያም የማይተካ ሚና ይኖረዋል።

ኤክስፖው አልሚዎች በአንድ መድረክ እንዲሰባሰቡና እንዲቀራረቡ እድል ይፈጥራል። ፖሊሲ አውጪዎች የተለያዩ ጉዳዮችን እንዲያዩና ቀጣይ እንደ መንግሥት የሚሰራበትን ሁኔታም ያመላክታል። ዘርፉ ቴክኖሎጂ የሚፈልግ በመሆኑም ቴክኖሎጂ አቅራቢዎች ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ምንድነው የሚለውን እንዲለዩ ያስችላቸዋል። አልሚዎች ቴክኖሎጂውን አውቀው እንዲጠቀሙትና ምርታማ እንዲሆኑ ያግዛቸዋል።

በሌላ በኩል ዘርፉን ለማልማት ከፍተኛ የሆነ ፋይናንስ ያስፈልጋልና ፋይናንስ ለማቅረብ የሚያስቡ አካላት እድሉን እንዲያውቁ ያደርጋቸዋል ያሉት አቶ ሚሊዮን፤ ለአልሚዎች ደግሞ በሀገር ውስጥ ያለውን የልማት እድል እንዲያዩ እድል ይፈጥርላቸዋል። በምርምር ላይ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎችም እውቀትን የሚሸምቱበት ይሆናል ሲሉ አመልክተዋል።

ማዕድናትን ለማልማት ከፍተኛ ፋይናንስ ይጠይቃል። ስለዚህም ተሞክሮው ካላቸው ሀገራት ጋር በጋራ መስራት፤ ልምዶችን መቅሰምና ቴክኖሎጂያቸውን መጠቀም እንዲሁም እነርሱም ኢንቨስት እንዲያደርጉ በማበረታታት ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ይህም ሌላኛው የኤክስፖው አስፈላጊነት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ሀገሪቱ ከዚህ በፊት ያካሄደቻቸው ኤክስፖዎች ድክመቶች ቢታዩባቸውም፣ ብዙ መልካም እድሎችን እንዳመጡ የሚገልጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ለእዚህም ከተለያዩ ሀገሮች የመጡ በርካታ ኩባንያዎች በሀገሪቱ ለመሰማራት ፍላጎት እያሳዩ ያሉበትን ሁኔታም በአብነት ይጠቅሳሉ። ይህም እንደ ሀገር በብዙ መንገድ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅሰው፣ ያለንን ሀብት በቀላሉ አውጥተን እንድንጠቀምና ፤ ለዜጎች የሥራ እድል ፈጠራ አስተዋጽኦ እንዳለው ያስረዳሉ።

ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት፤ የዘንድሮው ‹‹ ማይን ቴክስ›› ኤክስፖ፤ ዋና ዓላማው ኢትዮጵያ ያላትን የማዕድን ሀብት በአግባቡ አልምቶ ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ የማእድን ሀብቱን ማስተዋወቅ ነው። የማዕድን ዘርፉን የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማሳየት ባለሀብቶችን መሳብና የሀገር ውስ ጥ አምራቾችን ማበረታታት ነው።

ኤክስፖው ‹‹የማዕድን ሀብታችን የነገ ተስፋችን›› በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄድ ሲሆን፤ ከባለፈው ዓመት በዝግጅትም ሆነ በአቀራራብ ይለያል። ከፍ ባለ ደረጃ ዝግጅት የተደረገበትም ነው። ከፍታው ከምን አንጻር ከተባለ ደግሞ አንዱ እያንዳንዱ ክልል የራሱን የማዕድን ሀብት የሚያስተዋውቅበት ቦታ የተሰጠው መሆኑ አንዱ ነው፤ ሌላው ደግሞ ትልልቅ አለም አቀፍ ኩባንያዎች ቴክኖሎጂያቸውን ጭምር ይዘው የሚቀርቡበት መሆኑም ሌላው ልዩ የሚያደርገው ምክንያት ነው። በተመሳሳይ በኤክስፖው ትልልቅ ጉዳዮችን የያዙ የፓናል ውይይቶች ይካሄዳሉ።

ኤክስፖው ሦስት አንኳር ጉዳዮችን የያዙ የፓናል ውይይቶችም ይደረጉበታል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ አንዱ የፓናል ውይይት በማዕድን ዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የሚቃኝበት መሆኑን ጠቁመዋል። ሌላኛው ዘርፉ ምን ላይ እንዳለ የሚታይበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ሦስተኛው አውደ ጥናት ደግሞ ምን አይነት ተግዳሮቶች፤ ተስፋዎች እንዳሉ የማዕድን ዘርፉን እንዴት ማልማት ይቻላል የሚሉት የሚዳስስ ይሆናል ብለዋል።

በአውደ ጥናቶቹም ሀሳቦቹ ቀርበው ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶች ይደረግባቸዋል። በምክክር መድረኩ የዘርፉ ምሁራን፣ ኩባንያዎች፣ የመንግሥት አካላትና በየደረጃው ያሉ የዘርፉ ተዋናዮች ይሳተፋሉ፤ ይህም ለዘርፉ ተዋናዮች ብዙ እድሎችን እንደሚያመጣ ታምኖበታል።

ከእድሎቹ መካከል አንዱ ችግሮችን ለይቶ የሚያሳይና ለመፍትሄ የሚያዘጋጅ መሆኑ ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ ኩባንያዎች በሀገር ውስጥ ሲሰማሩ የትኛው ላይ ቢሳተፉ የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የሚያመላክት ነው። በኤክስፖው ላይ የሚሳተፉት አካላት በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ ማዕድን የሚያመርቱ ኩባንያዎች፣ አነስተኛ አምራቾች እና ማንኛቸውንም ማዕድን በማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ናቸው። በተመሳሳይ በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ የገበያ ሰንሰለት የሚገቡበትን ዕድል ለመፍጠር፤ የምርት ጥራትን የሚያሳድጉ ግብዓቶችና ሙያተኞችን ለመተዋወቅ ኤክስፖው ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።

የማዕድን ምርቶችን በዘመናዊ መንገድ ጥራትና መጠናቸውን በማሻሻል ከሀገር ውስጥ አልፎ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ዕድል የሚሰጣቸው እንደሆነም ይናገራሉ። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ከማዕድን ዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማረጋገጥ አቅም ለመፍጠር እንደሚያስችል ጠቅሰው፤ በዘርፉ የተሰማሩ ተዋንያንን እንደሚያነቃቃም ተናግረዋል።

የገበያ እጥረት ያለባቸው አምራቾች ወደ ሌሎች ሀገራት ሄደው ምርታቸውን በቀላሉ እንዲያቀርቡ ትልቅ ዕድል እንደሚሰጥ እንደታመነበትም ጠቅሰው፣ ስለዚህም ኤክስፖውን እንደ ሌሎች ሀገራት ኤክስፖ ሁሉ በርዕሰ ብሔር አለያም በጠቅላይ ሚኒስትር አማካኝነት እውቅና ሰጥቶ እንደሚከናወን አስታውቀዋል። ይህ መሆኑ የውጪ ኩባንያዎች በሙሉ ልብ ወደ ሥራው እንዲገቡ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም አመልክተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው እንዳስታወቁት፤ በኤክስፖው ላይ ከአውስትራሊያ፣ ከካናዳና፣ ከኖርዌይ እና ከሌሎች ሀገራት የሚመጡ ከ100 በላይ አለም አቀፍ ድርጅቶችና ባለሀብቶች እንዲሁም ከአፍሪካም በማዕድን ዘርፉ የሚታወቁት እንደ ታንዛንያ፣ ጋና፣ ደቡብ አፍሪካን የመሳሰሉ ሀገራት ይሳተፋሉ። የሀገሮች በኤክስፖው መሳተፋቸው ለኢትዮጵያውያን አምራቾች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። እነርሱ ቋሚ የሆነ የማዕድን ኤክስፖ በየጊዜው ያዘጋጃሉ፤ ያንን ተከትሎም ማዕድኑን በማልማትና በመጠቀምም ዜጎቻቸውን ተጠቃሚ ያደደርጋሉ። የሀገሮቹ መሳተፍ ልምድና ተሞክሯቸውን ለመጋራት ያስችላል።

‹‹በሀገራችን የማዕድን ዘርፍ ገና ያልተነካና ያልተጠቀምንበት፣ ብዙ ያልተሰራበት ነው›› የሚሉት አቶ ሚሊዮን፤ የማዕድን ኤክስፖው የማዕድን ኩባንያዎች፣ የጌጣጌጥ አምራቾችና ላኪዎች፣ የማዕድን ቴክኖሎጂ አምራቾችና አስመጪዎች እንዲሁም የፋይናንስ ተቋማት የሚሳተፉበት ይሆናል ብለዋል። ይህም አምራቾችን ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ገዢዎች ጋር እንዲሁም፤ አምራቾችና ላኪዎችን ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በቀጥታ ለማገናኘት እንደሚያስችል ጠቁመዋል። ከውጪ የሚመጡ የማዕድን ኩባንያዎች በኤክስፖው ላይ መሳተፋቸው በኢትዮጵያ ያለውን የማዕድን ኢንቨስትመንት አማራጭ እንዲመለከቱና በኢንቨስትመንቱ እንዲሳተፉ እድል እንደሚፈጥርም አስታውቀዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው እንዳብራሩት፤ በኤክስፖው የማዕድን ቴክኖሎጂ አምራቾች መሳተፋቸው ደግሞ ለኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ አዳዲስ የቴክኖሎጂ አማራጮችን የማስተዋወቅ እድል ከመፍጠሩም በላይ የኢትዮጵያ የማዕድን እምቅ ሀብት በቀላሉ ወጥቶ ጥቅም ላይ እንዲውል ያግዛል። ኤክስፖው አምራቾችን ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ገዢዎች ጋር በቀጥታ በማገናኘት የልምድ ልውውጥና ተሞክሮን በማካፈል በኩልም የማይተካ ሚና ይኖረዋል።

ክልሎች ከክልሎች የሚተዋወቁበትና ምርታቸውን በማስተዋወቅ የገበያ ትስስር የሚፈጥሩበት እንደሆነም ጠቅሰው፤ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች በዘርፉ ቢሰማሩ ራሳቸውን ጠቅመው የሀገሪቱን ኢኮኖሚ መደገፍ የሚችሉበትን ዕድል እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል።

ኤክስፖው የቱሪዝም ዘርፉን የበለጠ ለማነቃቃት በሚልም ሰፋፊ ሥራ ይሰራበታል ይላሉ። ማዕድን ማለት ቱሪዝምም ነው። ምክንያቱም አንድ ባለሀብት ኤክስፖው ላይ ለመሳተፍ ሲመጣ የውጭ ምንዛሪ ይዞ ይመጣል። ከዚያም ባሻገር ኤክስፖው የሚዘጋጅባትን ከተማ መጎብኘቱ ስለማይቀር ለቱሪዝም ዘርፉ ሌላ እድል ይፈጥራል። በተለይ የቱሪዝም ዘርፉ የአገልግሎት ሰጪ ዘርፎች በብዙ መልኩ እንዲደገፉ ያስችላቸዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው እንዳስታወቁት፤ በዓለም 150 በሚቆጠሩ ዓመታት ውስጥ ዘርፉ ከጊዜ ወደጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መጥቷል። አሁን ያለ ማዕድን ቴክኖሎጂ የሚታሰብ አልሆነም። በሰማይ በአየር የሚበሩ፤ በምድር የሚንቀሳቀሱ፤ በባህር ላይ የሚንሳፈፉ በሙሉ በማዕድን ውጤቶች ይሰራሉ። የህክምና መሳሪያዎችም ሆኑ መድኃኒቶችም መሳሪያቸው ማዕድናት ናቸው። ድምጽ ጭምር ከአንዱ ወደ አንዱ የሚተላለፈው በማዕድን ነው።

በአጠቃላይ የምንጠቀምባቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች በማዕድን የተሰሩ አለያም የሚንቀሳቀሱ ናቸው ያሉት አቶ ሚሊዮን፣ እንደ ሀገር ለማዕድን ሀብቱ ትኩረት መስጠት የተቋሙ ኃላፊነት ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም ብለዋል። ሁሉም ለዘርፉ የተቻለውን ማበርከት እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን  ህዳር 14/2016

Recommended For You