ጓደኝነትንና አብሮ አደግነትን ለቁም ነገር የማዋል አርዓያነት

ድህነትና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ችፍሮች ለተንሰራፋባቸው ማኅበረሰቦች፣ የበጎ አድራጎት ተግባራት የማኅበራዊ ፈውስ ሁነኛ መገለጫዎችና መሳሪያዎች ሆነው ያገለግላሉ፡፡ የበጎ አድራጎት ተግባራት ገንዘብን፣ ፍቅርን፣ ጊዜንና ሌሎች ሀብቶችን ከራስ ቀንሶ ለሌሎች በማካፈል የሌሎችን ችግር ለማቃለል፤ ፍቅርን፣ መተሳሰብንና አንድነትን ለማጠንከር እንዲሁም መተሳሰብና መከባበር የሰፈነበትን ማኅበረሰብ ለመፍጠር የማይተካ አወንታዊ ሚና አላቸው፡፡

መረዳዳትና በአንድነት መቆም የኢትዮጵያውያን አንዱ ባህል ነው። አብሮ መብላት ብቻ ሳይሆን “በደቦ” አብሮ መስራት፤ በደስታ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በሃዘንም ማፅናናት የማህበረሰቡ መገለጫና መልክ ነው። ይህ ቀድሞውንም በኢትዮጵያውያን ዘንድ የነበረ መልካም እሴት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በልዩ ልዩ መልኩ ተጠናክሮ ቀጥሏል። የመኖሪያ ቤታቸው በላያቸው ላይ የፈረሰባቸውን፣ ያዘነበለባቸውን፣የተጎሳቆለባቸውን ዜጎች ቤት በማደስ፣ በአዲስ መልክ በዘመናዊ መንገድ በመገንባት ፣ ማእድ በማጋራት፣ የምገባ መርሃ ግብር በማካሄድ፣ ደም በመለገስና በመሳሰሉት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

“መረዳዳት የኢትዮጵያውያን መገለጫ ነው” ስንል የእርስ በእርስ ማኅበራዊ መስተጋብራቸውን አጠንክሮ የኖረ የጀርባ አጥንት ስለመሆኑ እየተናገርን ነው፡ ፡ መረዳዳት ባይኖር ኖሮ አሁናዊ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አሁን ከሚታየው የተለየ ይሆን ነበር፡፡ ይህ የመረዳዳትና የመተጋገዝ በብዙ መንገዶች ይከወናል፡ ፡ በተናጠልና በጥቂት ግለሰቦች ስብስብ ከሚከናወኑ የመረዳዳት ተግባራት በተጨማሪ፣ መደበኛና ሕጋዊ አሰራሮችን ተከትሎ የበጎ አድራጎት ተቋማትን የማቋቋምና የመስራት ተግባርም በስፋት የሚታወቅ አሰራር ነው፡፡ ተቋማዊ በሆነ መልኩ በተደራጀ አግባብ ምግባረ ሰናይ ድርጅቶችን በማቋቋም የመረዳዳቱ ሥራ የቀጠለበት ሁኔታም ይታያል፡፡

እነዚህ ተቋማት የተቸገሩ ወገኖች የተለያዩ ድጋፎችን እንዲያገኙ በማድረግ ድጋፍ የተደረገላቸው ዜጎች የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው በማስቻል ሞራልና ማኅበራዊ ፍትሕ የሰፈነበት ማኅበሰረብና ሀገር ለመገንባት ቀላል የማይባል ሚና ይጫወታሉ፡፡ ከ13 ዓመታት በፊት የተመሰረተው ‹‹ባይሽ ኮልፌ›› የበጎ አድራጎት ማኅበር የዚህ ጥረት አንዱ ማሳያ ተደርጎ መጠቀስ የሚችል ምግባረ ሰናይ ተቋም ነው፡ ፡ ከማኅበሩ መስራቾች መካከል አንዱ የሆነው ኄኖክ ፍቃዱ፣ የማኅበሩ ምክትል ሰብሳቢና የኮሚዩኒኬሽን ክፍል ኃላፊ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡ ኄኖክ ስለማኅበሩ ምስረታና የሥራ አጀማመር እንዲህ በማለት ያስታውሳል…

‹‹ማኅበሩ የተመሰረተው ከ13 ዓመታት በፊት፣ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ አካባቢ ነው፡፡ የማኅበሩ መስራቾች 10 አብሮ አደግ ጓደኞች ናቸው፤ ‹ባይሽ› የሚለው የማኅበሩ ስያሜ የእንግሊዝኛ ፊደላትም (BAYSH) የመስራቾቹን ግለሰቦች ስሞች የመጀመሪያ ፊደላትን የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ በኋላም ቃሉ ‹ኮልፌ አምሮብሽ፣ አብበሽ፣ ተውበሽ ባይሽ…› ለሚለው ምኞታችንም ትርጉም የሚሰጥ ሆኖ ስላገኘነው ስያሜው በዚሁ ቀጠለ›› ሲል ሄኖክ ይገልጻል፡፡

‹‹የማኅበሩ መስራቾች አብሮ አደጎች በመሆናችን ሻይ/ቡና መጠጣትንና ወደ እምነት ተቋማት መሄድን ጨምሮ በብዙ አጋጣሚዎች የመገናኘት እድሎች አሉን፡፡ በጓደኝነታችን ቁም ነገር መስራት እንዳለብን በማሰብ በአቅራቢያችን ላሉ 20 ተማሪዎች ደብተር ገዝተን መስጠት ጀመርን፡፡ ይህን ስራችንን የሰሙና የተመለከቱ ሰዎች ደግሞ ብቻቸውን የሚኖሩ አንዲት እናት እንዳሉ ሲነግሩን ሄደን ጠየቅናቸው፤ንፅህናቸውን መጠበቅን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎችን አደረግንላቸው፡፡ ይህ ተግባርና ስሜት ትልቅ ዋጋ ነበረው፡፡ በመቀጠልም ሌሎች እናቶችንና አረጋውያንን መጠየቅና መንከባከብ ቀጠልን›› ሲል ያብራራል፡፡

የማኅበሩ አባላት በአሁኑ ወቅት ለ80 ዜጎች ቋሚ ወርሃዊ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ኄኖክ ይናገራል፡ ፡ ሄኖክ እንዳለው፤ እነሱ ከ200 በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች በቻሉት አቅም ልዩ ልዩ ድጋፎችን እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ‹‹በቤት ለቤት ድጋፍ ለ80ዎቹ ቤተሰቦች አስቤዛ (ሽንኩርት፣ ዘይት፣ በርበሬ፣ ከሰል…) እናሟላለን፡፡ ቤታቸውን እናድሳለን፡፡ በዓላት ሲመጡ እንጠይቃቸዋለን፡፡ በተለያዩ በዓላት ወቅት ሃይማኖት ሳንለይ በየቤቱ በመሄድ ከተረጂዎቹ ጋር አብረን እናሳልፋለን፡፡ ህክምና ሲያስፈልጋቸው በመንግሥትና በግል የጤና ተቋማት ህክምና የሚያገኙበትን እድል እናመቻቻለን፡፡ ታካሚዎችን ለመንከባከብ ሐኪም ቤት ማደር አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሐኪም ቤት እናድራለን፡፡›› ሲል ያብራራል፡፡

ሐኪም ቤት መገኘታችን ከእንክብካቤው በተጨማሪ ‹ወገን፣ ዘመድ፣ ሰው አለኝ› የሚል ስሜት እንደሚያሳደር ሄኖክ ይናገራል፡፡እነ ሄኖክ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩም እንደየእምነታቸው ስርዓት ስርዓተ ቀብራቸው እንዲፈፀም ያደርጋሉ፡፡ ሰዎቹ አቅም ቢኖራቸው ኖሮ፣ ሊያደርጉት የሚችሉትን፣ ልጆች ቢኖሯቸው ልጆቻቸው ሊያደርጉላቸው የሚችሉትን ነገር ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡ በአጠቃላይ ፍቅርና እንክብካቤ እንዲያገኙ እና ‹ሰው የለኝም› የሚል ስሜት እንዳይሰማቸው ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ማኅበሩ ጎዳና የወጡ ወገኖች ወደ ማዕከላት እንዲገቡና ድጋፍ እንዲያገኙ ያደርጋል፤ከተቻለም ቤት እንዲያገኙ ይጥራል፡ ፡ ‹‹ባይሽ ኮልፌ›› ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም በርካታ ተግባራትን ያከናውናል፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም አድራሻቸው የተጠፋፉ ሰዎችን ያገናኛል፡፡ የጤና እክል አጋጥሟቸው ወደ ውጭ ሄደው ህክምና እንዲያገኙ ብዙ ገንዘብ የተጠየቁ ሰዎች ሲኖሩ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ አማካኝነት ድጋፎችን በማሰባሰብ ህክምናውን እንዲያገኙ የገንዘብ ማሰባሰብ ዘመቻ ያደርጋል፡፡ እርቅ የኢትዮጵያዊነት መለያና የበጎ ተግባር መገለጫ በመሆኑ የማኅበሩ አባላት የተጣሉ ሰዎችን ያስታርቃሉ፡፡

ማኅበሩ ከ500 በላይ አባላት ያሉት ሲሆን ለበጎ አድራጎት ስራዎቹ የሚያስፈልገውን ገንዘብ የሚገኘው ከአባላትና በጎ አድራጊዎች መዋጮ ነው፡፡ በተለይ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ በጎ አድራጊዎች ‹‹ለአንድ ሰው ድጋፍ ላድርግ፣ ሁለት ሰው ላግዝ…›› እያሉ በየወሩ ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የማኅበሩ አባላት በዓላትን ምክንያት በማድረግ ጫማ በመጥረግና ሶፍት በመሸጥ የሚያስገኟቸው ገቢዎች ድጋፎችን ለመግዛት ይውላሉ፡፡

ማኅበሩ በ13 ዓመታት የስራ እንቅስቃሴው ሕክምና ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ብቻ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ከ600 በላይ አድራሻቸው የተጠፋፉ ሰዎችን ማገናኘት ችሏል፡፡ በርካቶች ከጎዳና ላይ ተነስተው ወደ ማዕከላት ገብተው በማዕከላት ውስጥ ሆነው ድጋፍ እንዲደረግላቸው እንዲሁም ሕክምናና መኖሪያ ቤት እንዲያገኙ አድርጓል፡፡

‹‹በማኅበራችን እገዛ ከጎዳና ሕይወት ወጥቶ፣ ስራ በመስራት የራሱን ቤት መስራት የቻለና ለሌሎችም የስራ እድል የፈጠረ ግለሰብ አለ፤ይህ ግለሰብ ለበርካቶች አርዓያ መሆን የቻለ ሰው ነው፡፡ በአስቸጋሪ የጤና ሁኔታ ውስጥ የነበሩና በማኅበሩ ድጋፍ የሕክምና እርዳታ አግኝተው እንደ እድሜ እኩዮቻቸው መጫወት፣ መማርና መኖር የቻሉ ሕፃናትም አሉ፡፡ ቤት አግኝተው ከጎዳና ሕይወት ተላቀው ቤት ውስጥ መኖር የጀመሩ ሴቶች የሕይወት ለውጦችም የማኅበሩ በጎ ተግባራት ውጤቶች ናቸው›› በማለት ከማኅበሩ በርካታ ስኬታማ ስራዎች መካከል ጥቂቶቹን ይጠቅሳል፡፡

‹‹ለ13 ዓመታት አብረን እንድንቆይ ያደረገን ፍቅር ነው›› የሚለው ኄኖክ፣ በ13 ዓመታት የማኅበሩ ምግባረ ሰናይ ተግባራት ብዙ ስኬቶችን እንዳስመዘገቡና አሳዛኝ አጋጣሚዎችን እንዳሳለፉም ያስታውሳል፡ ፡ ‹‹ድጋፍ ለሚፈልጉ ግለሰቦች በብዙ ድካም ገንዘብ ከሰበሰብን በኋላ አንዳንድ ጊዜ ባልተጠበቀ ሁኔታ ሰዎቹ ያርፋሉ፤እነዚህ አጋጣሚዎች አስደንጋጭና አሳዛኝ ትውስታዎችን ይፈጥራሉ፡፡ ብዙ ገንዘብ ተሰብስቦ ‹ታክመው ሊድኑ ነው› ብለን ተስፋ አድርገን፣ ሞታቸውን መስማት ልብ ይሰብራል፡፡ ውጭ ሄደው ታክመው ድነው የተመለሱትን እንዲሁም በእኛ ድጋፍ ከጎዳና ላይ ተነስተው ሥራ ሰርተው ተለውጠው፣ ንብረት አፍርተው ለሌሎች ሰዎች ጭምር የሥራ እድል የፈጠሩ ሰዎችን ስናስብ በእጅጉ እንፅናናለን›› ሲል ይገልጻል፡፡

ሄኖክ የክፍለ ከተማና የወረዳ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በስራቸው እንዲበረቱ በሞራል እንደሚደግፏቸውና መንግሥት ቢሮ እንደሰጣቸውም ተናግሯል፡፡ ‹‹የክፍለ ከተማና የወረዳ የሥራ ኃላፊዎች ‹በርቱ› ይሉናል፡፡ ፕሮግራሞች ሲኖሩን ስንጠራቸው ይገኛሉ፡፡ ለስራችን ጥሩ አመለካከት አላቸው፡፡ ሥራ ስንሰራ አለመረበሽ በራሱ እንደ ትልቅ ድጋፍ ይቆጠራል›› በማለት የመንግሥት አካላት ለማኅበሩ በጎ ዕይታ እንዳላቸውና ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ያስረዳል፡፡

‹‹ባይሽ ኮልፌ›› የበጎ አድራጎት ስራውን የሚያከናውነው በቤት ለቤት ድጋፍ መርሃ ግብር ነው፡፡ የማኅበሩ አባላት ድጋፍ ወደሚያስፈልጋቸው ግለሰቦች ቤት በመሄድ ድጋፎችን ያደርጋሉ፡፡ ማኅበሩ አረጋውያን እርዳታ የሚያገኙበት ቋሚ ማዕከል እንዲኖር ጥረት ማድረግ ከጀመረ ቆይቷል፡፡ ኄኖክ እንደሚለው፣ ‹‹ባይሽ ኮልፌ››ን ለትውልዶች የሚተላለፍ ዘላቂ ተቋም ለማድረግ ቋሚ የመርጃ ማዕከል ማቋቋም ያስፈልጋል፡ ፡ ከማኅበሩ የወደፊት እቅዶች መካከል ዋናው ይህን ማዕከል እውን የማድረግ ተግባር ነው፡፡

‹‹አረጋውያኑ በቤት ውስጥ ብቻቸውን ሆነው ለረጅም ሰዓታት የሚቆዩ በመሆናቸው አብረው የሚሆኑበት ቦታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የተጠፋፉ ሰዎች የሚቆዩበት ቦታም ያስፈልጋል፡፡ ማዕከል እንዲኖረን የሁልጊዜም ምኞታችን ነው፡፡ ማቆያ ማቋቋምን ጨምሮ ሌሎች ማሳካት የምንፈልጋቸው ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ ጥሩ የዓይን ማረፊያ የሚሆንና ቤተ-መጻሕፍትን ያካተተ ማዕከል የማቋቋም እቅድ አለን፡፡ ማዕከል እንዲኖረን ለመንግሥት ተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርበናል፡፡ በዚህ ዓመት በትኩረት ከምናከናውናቸው ተግባራት መካከል አንዱ ይኸው ነው›› በማለት የማዕከሉ ጉዳይ የማኅበሩ ዋና ትኩረት መሆኑን ያስረዳል፡፡ በተጨማሪም ፍቅር እንዲኖርና አብሮነት እንዲጠነክር ማኅበሩ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ይገልፃል፡፡

‹‹ባይሽ ኮልፌ›› ባለፉት 13 ዓመታት ላከናወናቸው የበጎ አድራጎት ተግባራት የተለያዩ ሽልማቶችንና እውቅናዎችን አግኝቷል፡፡ በ2014 የበጎ ሰው ሽልማት የመጨረሻ ሶስት እጩዎች መካከል አንዱ በመሆን የምስክር ወረቀት እንደተበረከተለትም ጠቅሷል። ‹‹መልካም ሥራ ሽልማት አያሻውም፤ከሁሉም የበለጠው ሽልማት ፍቅርና መረዳዳት ነው፡፡ እገዛ የሚስፈልጋቸው ሰዎች እገዛ አግኝተው ተደስተው ማየት ትልቅ ደስታና ሽልማት ነው›› የሚለው ኄኖክ፣ ማኅበሩ ለምግባረ ሰናይ ተግባራቱ በተለያዩ ጊዜያት፣ ከተለያዩ አካላት የዋንጫና የምስክር ወረቀቶች እንደተበረከቱለት ይገልፃል፡፡

እንደ መውጫ

“በጎነት መልካም መዋል ነው” ሲባል በአፍ የሚነገር ሳይሆን በተጨባጭ የማህበረሰቡን ህይወት የሚቀይር መሬት የነካ ስራ እንደሆነ ልንገነዘብ ይገባል። እንደ “ባይሽ ኮልፌ” አይነት የወጣቶች ስብስብ ቀደምት አያቶቻችን ያወረሱንን በክፉ ግዜ ለወገን፣ ለወዳጅ የመድረስ ባህል የሚያስቀጥሉ ስብስቦች ሊበዙ ይገባል። “ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ” እንደሚባለው ብሂል በተናጠል ያልቻልነውን በጋራ ሰብሰብ ብለን መተጋገዝና ለወገኖቻችን መድረስ ይገባናል።

ከቅርብ ግዜያት ወዲህ በበጎ ምግባር ላይ የተሰማሩ አደረጃጀቶችን በስፋት እየተመለከትን ነው። የዝግጅት ክፍላችን እነዚህ አደረጃጀቶች መብዛት ብቻ ሳይሆን መጠንከርም፣ መደርጀትም ይገባቸዋል ብሎ ያምናል። ይህ ሲሆን ለተቸገረ ቀለብ መቁረጥ ብቻ ሳይሆን ሳይቸገር ዘንበል እንዳለ ቀና ማድረግ የሚቻልበትን አጋጣሚ የሚፈጥር ነው። በመሆኑም ሁሉም ዜጋ ለእነዚህ ማህበራት፣ የበጎ ምግባር አደረጃጀቶች መጎልበት አንድ ጡብ መጣል ይኖርበታል ብለን እናምናለን።

ሁላችንም የምንስማማበት አንድ ሀቅ አለ “መረዳዳትና በአንድነት መቆም የኢትዮጵያውያን አንዱ ባህል ነው” አብሮ መብላት ብቻ ሳይሆን “በደቦ” አብሮ መስራት፤ በደስታ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በሃዘንም ማፅናናት የማህበረሰቡ መገለጫና መልክ ነው። ይህ ድርጊት ቀድሞውንም የነበረ አሁንም በልዩ ልዩ መልክ የቀጠለ ነው። በመሆኑም ይበልጥ እንዲደረጅና እሴቱ ተጠብቆ እንዲቆይ በጋራ እንስራ የሚለው መልእክታችን ነው።

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን  ህዳር 14/2016

Recommended For You