በመዲናዋ ከ140 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ ነው

  • በሩብ ዓመቱ ከ33 ቢሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል
  • ያለደረሰኝ ግብይት የፈጸሙ 339 ተጠርጣሪዎች ምርመራ እየተደረገባቸው ነው

አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ በ2016 በጀት ዓመት ከ140 ቢሊዮን በላይ ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን የአዲስ አበባ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ። በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ33 ቢሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል።

የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ የበጀት ዓመቱን የሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም አስመልክቶ ትናንት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ሲመክር የቢሮ ኃላፊው አደም ኑሪ እንደገለጹት፤ ተቋሙ በበጀት ዓመቱ ሊሰበስብ ያቀደውን ገቢ ለማሳካት ከተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት ጋር እየሠራ ይገኛል። የኅብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፍላጎት ለሟሟላት በከተማ ደረጃ ከ140 ቢሊዮን 291 ሚሊዮን በላይ ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ ነው።

በከተማዋ ውስጥ ከገቢ እንቅስቃሴው ጋር 32 የሚሆኑ ሴክተር ተቋማትና 11 ክፍለ ከተሞች ጋር በጋራ በመሆን ሥራው እንደሚከናወን ኃላፊው ተናግረዋል።

በገቢ አሰባሰብ ሂደቱ ከገቢዎች ቢሮ 100 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር፣ ከሴክተር ተቋማት 26 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ከክፍለ ከተሞች ሦስት ቢሊዮን ብር እንደሚጠበቅ ገልጸው፤ ብድርና ዕርዳታን ጨምሮ በድምሩ ከ140 ቢሊዮን ብር በላይ ይሰበሰባል ነው ያሉት።

የገቢ አሰባሰቡን ለማሳካት የሕግ ማስከበር ሥራዎችን ማጠናከር፣ ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥን ማሳለጥና ተቋማዊ አቅምን መፍጠር ቁልፍ ተግባራት እንደሆኑም ኃላፊው ተናግረዋል።

ቢሮው የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ ከገቢዎች ሚኒስቴር፣ ጉምሩክ ኮሚሽን፣ ከኦሮሚያ ገቢዎች ቢሮ፣ ከባንኮችና ትምህርት ቢሮዎች፣ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ስምምነት ፈጥሮ በቅንጅት እየሠራ እንዳለም ነው የጠቀሱት።

ከባለ ድርሻ አካላት ጋር የተደረጉ ስምምነቶች ገቢ ከማሳካት ባሻገር አገልግሎትን ለማቀላጠፍና ለማዘመን፣ እንዲሁም የቴክሎጂ አጠቃቀምን ለማሳደግ ጉልህ አስተዋፅዖ እንዳላቸው አመልክተዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ በዲጂታል የአከፋፈል ሥርዓት ማለትም፤ በሲቢኢ ብር፣ በሞባይል ባንኪንግና ቴሌ ብር አማካኝነት ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ ተችሏል።

ግብር ከፋዩ የታክስ ሕጎችን ማክበር እንዳለበት በመጥቀስ፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ ያለ ደረሰኝ ግብይት የፈጸሙ 339 ተጠርጣሪዎች እጅ ከፍንጅ ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው እንዳለም ነው የገለጹት።

በቢሮው የለውጥና የታክስ ሪፎርም አማካሪ አቶ ግርማ ዓለሙ ባቀረቡት ሪፖርት፣ በሩብ ዓመቱ በከተማ ደረጃ 35 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ 33 ነጥብ 59 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ እንደተቻለ ገልጸዋል።

ከዚህ ውስጥ 25 ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር የተሰበሰበው በገቢዎች ቢሮ አማካኝነት እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ሕገወጥ ንግድን ከመከላከል አንጻር አበረታች ሥራ እየተከናወነ እንዳለ ጠቁመው፤ በዚህም በቅንጅት በተሠራ የቁጥጥር ሥራ ሦስት ሺህ ስምንት ሕገወጥ ነጋዴዎችን ወደ ሕጋዊ የንግድ ሥርዓት ማስገባት እንደተቻለ አስታውቀዋል።

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን ኅዳር 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You