በሰባት ክለቦች መካከል ሲካሄድ ቆይቶ የደረጃና የፍጻሜ ጨዋታዎች በተለያዩ ምክንያቶች ሳይካሄዱ ከወር በላይ ያስቆጠረው 17ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ትላንት በአበበ ቢቂላ ስቴድየም ፍጻሜ አግኝቷል። በዚህም የውድድሩ ተጋባዥ ክለብ ሀዲያ ሆሳዕና በፍፃሜው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን በመለያ ምት በማሸነፍ ዋንጫውን ማንሳት ችሏል።
ዳዋ ሆጤሳ በ5ኛውና ተመስገን ብርሃኑ በ13ኛ ደቂቃ ባስቆጠሯቸው ግቦች ሁለት ለምንም ሲመራ የቆየው ሀዲያ ሆሳዕና 27ኛ ደቂቃ ላይ አንተነህ ተፈራ ለኢትዮጵያ ቡና አንድ ግብ አስቆጥሮ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል። በሁለተኛው 45 ሀዲያ ሆሳዕና ውጤቱን አስጠብቆ ለመውጣት ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ የከተማው ዋንጫ ከእጁ እንዳይወጣ ያደረጉት ፉክክር ዘጠና ደቂቃው ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃ እስኪቀረው ድረስ ግብ አላስተናገደም።
88ኛው ደቂቃ ላይ ግን መስፍን ታፈሰ ለኢትዮጵያ ቡና የአቻነቷን ወሳኝ ግብ በማስቆጠር ጨዋታው ይበልጥ አጓጊ ሆኗል። በመደበኛው የጨዋታ ሰዓት ሁለት አቻ የተለያዩት ሁለቱ የፍፃሜ ተፋላሚዎች ወደ መለያ ምት አምርተዋል። በዚህም ሀዲያ ሆሳዕና ለጥቂት ከእጁ የወጣውን ዋንጫ በመለያ ምት 5ለ4 አሸንፎ መልሶ ማግኘት ችሏል። ሁለት ጊዜ ዋንጫውን የማንሳት ታሪክ ያለው ኢትዮጵያ ቡና ለሦስተኛ ጊዜ አሸንፎ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር የሚስተካከልበትን እድል ሳይጠቀም ቀርቷል።
የፍፃሜ ጨዋታውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራን ጨምሮ የፌዴራል እና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች አስጀምረውታል። ሻምፒዮናው ሀድያ ሆሳዕና ዋንጫው እና የወርቅ ሜዳልያውን ከዕለቱ የክብር እንግዳ ከአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን እጅ ተቀብለዋል።
ቀን 7፡00 ሰዓት ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከኢትዮጵያ መድን ያገናኘው የደረጃ ጨዋታ በፈረሰኞቹ 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በአህጉር አቀፍ ውድድር ተሳታፊ በመሆናቸው በተስፋ ቡድን በከተማው ዋንጫ የተሳተፉት ፈረሰኞቹ በምድቡ የመጀመሪያ ጨዋታ በኢትዮጵያ መድን በሰፊ የግብ ልዩነት ቢሸነፉም አገግመው በግማሽ ፍጻሜ በኢትዮጵያ ቡና እስከ ተሸነፉበት ጨዋታ ድረስ ተፎካካሪ መሆን ችለዋል። በደረጃ ጨዋታውም ተፎካካሪ በመሆን ኢትዮጵያ መድንን በመርታት ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን ፈጽመዋል። የፈረሰኞቹን የማሸነፊያ ግቦች ሰለሞን ታደሰ እና ሄኖክ ዮሐንስ በ43ኛው እና በ68ኛው ደቂቃ ማስቆጠር ችለዋል። የጨዋታው ኮከብ ተጫዋችም የቅዱስ ጊዮርጊሱ የአብስራ ተስፋዬ ሆኖ የተመረጠ ሲሆን የክሪስታል ዋንጫ እና የ10ሺ ብር ተሸላሚ ሆኗል።
ከመስከረም 07/2016 ጀምሮ በተካሄደው 17ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ሰባት ክለቦች በሁለት ምድብ ተከፍለው የተፋለሙበት ሲሆን በምድብ ሀ ኢትዮጵያ ቡና፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ሀድያ ሆሳዕና እና ሻሸመኔ ከተማ፤ በምድብ ለ ያለፉት ሁለት ተከታታይ የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ አሸናፊው ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ተጋባዡ አዳማ ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን ተደልድለው እንደነበረ ይታወሳል።
የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ባለፉት ዓመታት በርካታ ክለቦችን እያፋለመ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን 4 የከተማዋ ክለቦችም ዋንጫውን ማንሳት ችለዋል። ዋንጫውን ስድስት ጊዜ በማንሳት ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚስተካከል ክለብ የለም። ከፈረሰኞች በመቀጠል ኢትዮ ኤሌክትሪክ (የቀድሞው መብራት ኃይል) ዋንጫውን ሦስት ጊዜ በማንሳት ይከተላል። እአአ በ2014 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋንጫውን በማንሳት የውድድሩ አዲስ ሻምፒዮን እንደነበር ይታወሳል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ህዳር 13/2016